Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት የውጭ ኩባንያዎችን ጨምሮ 200 ተሳታፊዎች ይጠበቃሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው በዘንድሮው የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት፣ የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ እንደሚጨምርና ከአሥር አገሮች የሚመጡ ኩባንያዎችም በዓውደ ርዕዩ እንደታደሙ አስታወቀ፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከጥቅምት 16 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚካሄደው 10ኛው የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት 200 የሚደርሱ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ሲጠበቅ፣ እስካሁን ግን ለተሳትፏቸው ማረጋገጫ የሰጡት 150 ኩባንያዎች ብቻ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ የሞሮኮ ኩባንያዎች በተለየ መንገድ እንደሚሳተፉ፣ ከአሥር አገሮች የሚውጣጡ 75 የውጭ ኩባንያዎችን ጨምሮ ከ85 በላይ የአገር ውስጥ ድርጅቶችም በዓውደ ርዕዩ ከሚታደሙት መካከል የሚጠበቁ ናቸው፡፡ 

በንግድ ትርዒቱ በርካታ ኩባንያዎችን በማሳተፍ እንደምትታደም የምትጠበቀው ሞሮኮ ነች፡፡ ከሞሮኮ ብቻ በዚህ ንግድ ትርዒት ላይ ከ80 በላይ ኩባንያዎቿን የሚወክሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሏል፡፡  

ሞሮኮ በዚህ ደረጃ በኢትዮጵያ ንግድ ትርዒት ስትሳተፍና ይህን ያህል ብዛት ያለው የንግድ ልዑክ ስትልክ የመጀመርያዋ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ሞሮኮ እንዲህ ባለው የንግድ ትርዒት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ለመሳየቷ፣ በርካታ ኩባንያዎቿን ይዛ ለመቅረብ አወንታዊ ምላሽ የሰጠችበት ምክንያት ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን የንግድ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት ለማጠናከር ከቀረፀችው ፖሊሲ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚንት አቶ ሰሎሞን አፈወርቅ ገልጸዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒትና ኩነቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ባግናወርቅ ወልደ መድን በበኩላቸው፣ የሞሮኮ ንጉሥ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ብሎም የሞሮኮ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማስቻል፤ የሞሮኮ ኩባንያዎች በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቻቸው ተወክለው ይመጣሉ፡፡ እንደ ወ/ሮ ባግናወርቅ ገለጻ፣ ኦፒሲ አፍሪካ በተባለው የኬሚካል ማዳበሪያ ተቋም አስተባበሪነት የሚመጡት የሞሮኮ ኩባንያዎች፣ በተለያዩ የኢንቨስትመንቶች መስኮች የተሰማሩ ናቸው፡፡ በኦፒሲ አፍሪካ ሥር ከሚገኙ ኩባንያዎች ውስጥ በኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ለመሥራት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎችንም እንደሚካተቱበት ተገልጿል፡፡

80ዎቹ የሞሮኮ ኩባንያዎች በከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎቻቸው አማካይነት በንግድ ትርዒቱ ላይ ከመሳተፋቸው በተጓዳኝ፣ ዋና ተልዕኳቸው እንደሚሆን የሚጠበቀው በኢትዮጵያና በሞሮኮ ኩባንያዎች መካከል የንግድ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚያስችል የሚታመንበትን የሁለትዮሽ ምክክር ለማድረግ ብሎም ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ለመምከር ነው፡፡ 

ከዚህ በተጓዳኝ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የሞሮኮ የንግድ ልዑክ ከሚያካትታቸው ከፍተኛ የሞሮኮ ኩባንያዎች ሥራ አስፈጻሚዎች ባሻገር፣ አብረው 50 ያህል በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከኦፒሲ አፍሪካ ጋር እየሠሩ የሚማሩ ተማሪዎችን ያካተተ ነው፡፡ በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ እየሠሩ ጎን ለጎንም ትምህርታቸውን ይከታተላሉ የተባሉት ባለሙያዎች፣ በኢትዮጵያና በሞሮኮ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ጥናትና ምርምር እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል፡፡ በተለይም ኦፒሲ አፍሪካ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚኖረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መረጃዎችን ለማጠናቀር እንደሚመጡም ታውቋል፡፡

ኦሲፒ አፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ብሎም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተለያዩ የኬሚካል ማዳበሪያ ምርቶችን በማምረት ያቀርባል፡፡ ኢትዮጵያ የኩባንያው ከፍተኛ የምርት ተቀባይ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ የምትጠቀስ ሲሆን፣ ኩባንያው በድሬዳዋ ግዙፍ የማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የሰባት ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በመጪው ወር አጋማሽ በሚካሄደው የንግድ ትርዒት ለመሳተፍ ከሞሮኮ በተጨማሪ ከአሥር አገሮች የሚውጣጡ ኩባንያዎች ይጠበቃሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የግብፅ፣ የቡልጋሪያ፣ የፓኪስታን፣ የህንድ፣ የሱዳንና የኢራን ኩባንያዎች  ይገኙባቸዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ባለፈው ዓመት ባካሄደው የንግድ ትርዒት፣ አነስተኛ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ይህም የሆነው በወቅቱ በአገሪቱ በተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሳቢያ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ከመሳተፍ በመቆጠባቸው ነበር፡፡ በመሆኑም የአገር ውስጥ ኩንያዎችን አካቶ፣ አጠቃላይ የተሳታፊዎች ቁጥር ከ100 በታች እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዘንድሮ የተሻለ የተሳታፊዎች ቁጥር እንደሚመዘገብ ይጠበቃል፡፡ እስካሁን እንደሚሳተፉ ያረጋገጡ ኩባንያዎች ቁጥርም ከቀደሙት ዓመታት በላይ ሆኖ መገኘቱም የተሻለ ውጤት የሚታይበት ዓመት እንደሚያደርገው ንግድ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ ከንግድ ትርዒቱ ጎን ለጎን የውጭ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚመክሩበት መድረክ እንደተዘጋጀና ኢትዮጵያ ያሏትን የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያስተዋውቅ ፕሮግራም እንደተሰናዳም ከወ/ሮ ባግናወርቅ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህ ዝግጅት የውጭ ተሳታፊዎች እንደ ቦሌ ለሚ ያሉትን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጉብኝት እንደሚያጠቃልል ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት፣ ኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትን በየዓመቱ በቋሚነት የሚያካሂድ ሲሆን፣ የዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች