የሰው ልጅ እርስ በርሱ በሚያደርገው ግንኙነት በሰከነ መንገድ መነጋገር፣ መወያየትና ብሎም መደራደር ትልቅ ጥቅም ያስገኝለታል፡፡ ከዕለት ተዕለት የንግድ እንቅስቃሴ አንፃር ሲታይ እንኳ በሸማችና በነጋዴ መካከል ያለው ግንኙነት በድርድር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አገሮች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሲገናኙ የሚቀድመው ድርድር ነው፡፡ ድርድር ግልጽነትና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ የሚከተል ከሆነ ደግሞ ጥቅሙ ለሁለቱም ወገኖች ነው፡፡ መነጋገርና መደራደር መቻል የሰከነ አዕምሮ ውጤት ነው፡፡ በአገራችን ለዓመታት የዘለቀው የፖለቲከኞች የመነጋገርና የመደራደር ፈቃደኝነት መጥፋትና በቂምና በበቀል መፈላለግ፣ የአገሪቱን ፖለቲካ ምን ያህል እንዳሽመደመደው ግልጽ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በአጎራባች ክልሎች መካከል የተስተዋሉ ግጭቶች ለዜጎች ሕይወት መጥፋትና ከቀዬ መፈናቀል ሰበብ የሆኑት፣ በሰከነ መንገድ ለመነጋገርና ለመደራደር ቅድሚያ ባለመሰጠቱ ነው፡፡ እልህና ግትርነት ደግሞ ስሜትን ለማጎንና እሳት ለመቆስቆስ ቅርብ ናቸው፡፡ የሰከነ አዕምሮ በስሜት አይነዳም፡፡ ይልቁንም ጥፋትን በሩቅ ለመከላከል መላ ይዘይዳል፡፡
በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በተደጋጋሚ የተከሰቱ ግጭቶች ቀደም ሲል የማያዳግም መፍትሔ ማግኘት ነበረባቸው፡፡ በሕዝበ ውሳኔ አማካይነት የተደረሰባቸውን ስምምነቶች በመያዝ በጊዜ የወሰን ማካለልና የክትትልና የቁጥጥር ሥራው በጋራ ቢከናወን፣ ግጭት ሊያስነሱ የሚያስችሉ ድርጊቶች ቁጥጥር ቢደረግባቸውና በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ በቅርበት መነጋገር ቢቻል በወንድማማች ሕዝቦች መካከል ችግር አይፈጠርም ነበር፡፡ ካለፈው ስህተት በመማር ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አላስፈላጊ ቃላትን በመጠቀም ከመወጋገዝና ከመፈራረጅ መውጣትም የግድ ይላል፡፡ በተደጋጋሚ እንደምንለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ለዘመናት ደግና ክፉ ጊዜያትን አንድ ላይ አሳልፏል፡፡ በተለይ በርካታ የመከራ ጊዜያትን ያሳለፈውና የሚወዳት አገሩን በጋራ ሲጠብቅ የኖረው በመረረ ድህነት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ ነገር ግን በማስተዋልና በአርቆ አሳቢነቱ የጋራ እሴቶቹን ጠብቆ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ ይህንን ኩሩና የተከበረ ሕዝብ ሰላምና ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን አስጠብቆ ወደ ብልፅግና ማምራት የግድ ነው፡፡ ከግጭት የሚገኘው ዕልቂትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም፡፡
የአሁኗ ኢትዮጵያ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ብቻ ነው የሚያዋጣት፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ አገር ከሚመራው መንግሥት ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ ለአገር ህልውና ማሰብ ይገባል፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ከሕዝብ በላይ ምንም አይቀድም፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው መልክዓ ምድር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በአንድነት የጋራ አገራቸውን እንዲወዱና እንዲያሳድጓት መወያየትና መደራደር ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይገታቸው በጋራ አገራዊ ጉዳይ ላይ ተቀምጠው መነጋገር መቻል አለባቸው፡፡ አንድ ማኅበረሰብ የሠለጠነ ነው የሚባለው ልዩነቶቹን ማስተናገድ ሲችል ነው፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት ጊዜ አልፎበታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት ማግኘት የሚቻለው ለውይይትና ለድርድር ፈቃደኝነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ከቂምና ከጥላቻ የፀዳች አገር የምትኖረውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ክፋት፣ አሻጥር፣ ቁርሾና ጭካኔ ባሉበት ተያይዞ ከመጥፋት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ የሰከነ አዕምሮ ግን ከእነዚህ ደዌዎች የፀዳ ነው፡፡
ኢትዮጵያ 76 ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት የብዙኃን አገር ናት፡፡ በተለያዩ መስኮች የተለያዩ ፍላጎቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችና ድምፆች ይኖራሉ፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን የዘረጋው ሕገ መንግሥት በውስጡ በርካታ መሠረታዊ መብቶችን አጭቆ ይዟል፡፡ ራስን ከማስተዳደር፣ በራስ ከመዳኘት፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ከመማር፣ ቋንቋና ባህልን ከማሳደግ ጀምሮ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዋስትና አግኝተዋል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እያረመና ማስተካከያ እየተደረገበት መሄድ እንዳለበት ግንዛቤ በመያዝ፣ በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደርን የአገር ባህል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ዋስትና የሰጣቸው መብቶች ተግባራዊ ሆነው የመወያየትና የመደራደር ባህል ሲዳብር ድንጋይ ወርዋሪና ንብረት አውዳሚ ሳይሆን ሞጋች ትውልድ መፍጠር ይቻላል፡፡ ድንጋይ ውርወራና ውድመት ውስጥ የሚገባው ግን መብቶች ሲደፈጠጡ መሆኑን ማመን የግድ ነው፡፡ በቅርቡ የተከሰተው የበርካታ ወገኖቻችንን ሕይወት ያሳጣውና በርካቶችን ከቀዬአቸው ያፈናቀለው ግጭት ሙሉ በሙሉ ቆሞ፣ በሰከነ አዕምሮ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ለአገር ህልውናና ለሕዝብ ልዕልና ሲባል ውይይትና ድርድርን ማስቀደም ተገቢ ነው፡፡ ይህ በተግባር ይታይ ዘንድ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጣቸው መብቶች ይከበሩ፡፡ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት የሚፈጠረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡
የአገር ጉዳይ ሁሉንም ዜጎች ይመለከታል፡፡ የአገር አስተዳደር ሥርዓት ምን መምሰል አለበት ከሚለው መሠረታዊ ጥያቄ አንስቶ በበርካታ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የመወያየት ባህል መኖር አለበት፡፡ ጥያቄዎች ተነስተው የጦፉ ክርክሮች መኖራቸው የሚጠቅመው ለአገር ነው፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት ሲደመጡ የመዳኘት ሥልጣን ያለው ሕዝብ ነው፡፡ በሕዝብ የህሊና ዳኝነት ሥልጣን ላይ መውጣት እንደሚቻለው ሁሉ፣ ከሥልጣንም መውረድ እንዳለ በቀላሉ ለመቀበል ያስችላል፡፡ የሐሳብ ነፃነት ባለበት አሻጥርና መጠላለፍ የሞኝ ጨዋታ ይሆናሉ፡፡ በሰከነ አዕምሮ የሚነጋገርና የሚከራከር ማኅበረሰብ ከሸፍጥና ከአሉባልታ የፀዳ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ስለሚሆን አጥፊዎች አይፈነጩም፣ ሕገወጦች እንደልባቸው አይቦርቁም፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር ሥልጣን ልጓም ይኖረዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኝ የመንግሥት መዋቅር ተጠያቂነት ስላለበት ብልሹ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ በሙስና የሚገኝ ሀብት አይኖርም፡፡ ልፋትና ድካም በአደባባይ የሚታዩበት ከሌብነት የፀዳ ሥርዓት ሲኖር ደግሞ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ይኖራል፡፡ የአገር ህልውና አስተማማኝ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልገው በነፃት እየኖረ ከድህነት መላቀቅ፣ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት፣ ማኅበራዊ ፍትሕና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ተሟልቶ ይገኝ ዘንድ ደግሞ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ለሰከነ ውይይትና ድርድር ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ጠብና ግጭት እንዳይቀሰቀስ፣ መወያየትና መደራደር ባህል እንዲሆንና ለአዲሱ ትውልድ አርዓያ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ካሁን በኋላ በምንም ዓይነት የዜጎች ሕይወት እንዳይጠፋ፣ መፈናቀል እንዳይኖር፣ የንብረት ውድመት እንዳይደርስና በአጠቃላይ ሰላም እንዳይደፈርስ የሁሉም ዜጎች ተሳትፎ ይጨምር፡፡ አግላይና ጠቅላይ አስተሳሰቦች ተወግደው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶችና ድርድሮች እንዲያብቡ በጋራ መነሳት የግድ ይላል፡፡ አገር የጋራ ነውና፡፡ ይህም ተፈጻሚ ይሆን ዘንድ በሰከነ አዕምሮ ለችግሮቻችን መፍትሔ እንፈልግ መባል አለበት!