Monday, December 4, 2023

‹‹የሕዝብን ተሳትፎ ለማሳደግ ትልቅ ሚና ያላቸው አካላት የሚፈለገውን ያህል አቅማቸው አልተገነባም››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ወ/ሮ ውብአምላክ እሸቱ፣ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የአቅም ግንባታና  የመልካም አስተዳደር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ

ወ/ሮ ውብአምላክ እሸቱ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የአቅም ግንባታና የመልካም አስተዳደር ዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ዘርፍ አግኝተዋል፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ  ሌላ ዲግሪ አላቸው፡፡ እንግሊዝ ከሚገኘው የላንካስተር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በሂዩውማን ሪሶርስ ዴቨሎፕመንትና የአመራር አማካሪነት ትምህርት ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የተለያዩ ትምህርቶችን የወሰዱ ሲሆን፣ የድኅረ ምረቃ ፕሮፌሽናል ዴቨሎፕመንት አሜሪካ ከሚገኘሰው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን በሂዩማን ሪሶርስ ማኔጅመንት ዲፕሎማም አግኝተዋል፡፡ በርካታ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በማሠልጠን፣ በማማከርና በምርምር ሥራዎች ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ውስጥ ደግሞ የማኔጅመንት ዴቨሎፕመንት አሠልጣኝና አማካሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከዚያ ባለፈም በርካታ ጊዜያትን በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ውስጥ የብሔራዊ ኮሚቴ አባል ሆነው፣ በተለይ ከብቃት ማኔጅመንትና ተቋማትን ከመለወጥ ጋራ ተያይዞ በርካታ የማማከር ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ለአሥር ዓመታት ያህል የአመራር አሠልጣኝና አማካሪ ሆነው ከሠሩ በኋላ፣ ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ውስጥ የአቅም ግንባታና የመልካም አስተዳደር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የኢፌዴሪ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የመልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ዘርፍ ‹‹መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የሕዝብ ተሳትፎ ማነቆዎች፣ መንስዔዎችና የመፍትሔ ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ ጥናት ካካሄዱት አንዷ ሲሆኑ፣ መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በሳሮማሪያ ሆቴል የመንግሥት አመራር አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ወቅት ጥናቱን ካቀረቡት መካከል አንዷ ናቸው፡፡ ማዕከሉ ስለሠራው ጥናትና ሌሎች ተያያዝ ጉዳዮች በተመለከተ ዘመኑ ተናኘ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናቱን ለመሥራት ያነሳሳችሁ ጉዳይ ምንድነው?

ወ/ሮ ውብአምላክ፡ በ2007 ዓ.ም. የተጠናው የመልካም አስተዳደር ጥናት በርካታ ችግሮችን ነው የለየው፡፡ ከእነዚያ ጎላ ብለው ከወጡት ችግሮች መካከል አንዱ የሕዝብ ተሳትፎ በሚገባው ደረጃ አለመዳበሩን ይጠቁሟል፡፡ ይኼ የሕዝብ ተሳትፎ አለመዳበር ደግሞ በርካታ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይኼ ችግር በራሱ ችግር ከመሆን አልፎ፣ ለሌሎች ችግሮች መንስዔ ሊሆንም ይችላል፡፡ ይኼንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ይኼንን ጥናት ለመሥራት የተነሳሳነው፡፡  

ሪፖርተር፡– በዋናነት የዚህ ጥናት ዓላማ ምንድነው?

ወ/ሮ ውብአምላክ፡- በዋናነት የዚህ ጥናት ዓላማ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የሕዝብ ተሳትፎን የገቱ ችግሮች ምንድናቸው? የእነዚህ ችግሮች መንስዔዎች ምንድናቸው? መንስዔዎቹን ለመቅረፍ ሊወሰዱ የሚገባቸው የመፍትሔ ሐሳቦችስ ምንድናቸው? የሚለውን ለማውጣት ነው፡፡ ችግር እያስከተለ ያለውን ይህንን ችግር ለመፍታት ሊወሰድ የሚገባው ነገር ምንድነው? በተለይ ትኩረት አድርገን ደግሞ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር ምን ሊደረግ ይገባል? የሚል ነው ዓላማው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ግን የተዘረዘሩ ነገሮች አሉ፡፡ የሕዝብ ተሳትፎን ቁልፍ ጉዳያቸው አድርገው የሚሠሩ በርካታ ተቋማት አሉ፡፡ እነዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት የምንላቸው ማለት ነው፡፡ ከእነዚያ ውስጥ እኛ ትኩረት አድርገን ጥናቱን የሠራነው ሦስቱ አካላት ላይ ማለትም በሕዝብ ምክር ቤቶች፣ በብዙኃንና ሙያ ማኅበራትና ሚዲው ላይ ነው፡፡ እነዚህ የሕዝብ ሦስቱ አካላት የሕዝብ ተሳትፎን ቁልፍ ጉዳያቸው አድርገው ከመንቀሳቀስ አንፃር ያሉባቸው ማነቆዎች ምንድናቸው? ብለን ነው የሄድነውና ከሕዝብ ተሳትፎ አንፃር እነዚህ ላይ በትኩረት ሊሠራ የሚገባው ነገር ምንድነው? ብለን ለማየት ነው ሙከራ ያደረግነው፡፡

ሪፖርተር፡– በቅርቡ ጥናታችሁን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ሐሳብና አስተያየት እንዲሰጥበት እያደረጋችሁ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ምን ዓይነት ግብዓት አገኛችሁ?

ወ/ሮ ውብአምላክ፡- ጥናቱን እናካሂድ በተቻለ መጠን የሚፈለገው ግብዓት እንዲገኝ ሲባል ራሱ ጥናቱ ውስጥ የተለያዩ አካላት እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ የጥናት አባላት እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ የምክር ቤት ሰዎች የሚዲያ በተለይ ከተቆጣጣሪው የብሮድካስት ባለሥልጣንና የሲቪል ሰርቪስ ተወካዮች እንዲሁ ነበሩበት፡፡ ሐሳቡ የሁሉንም አካላት ሐሳብ ይዘን መንቀሳቀስ እንድንችል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ መጀመሪያ ያደረግነው ነገር ጥናቱ ከወጣ በኋላ፣ የእኛ የውስጥ ባለሙያዎች እንዲያዩት ተደርጓል፡፡ ለአመራር ከመቅረቡ በፊት ደግሞ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከጥናት ተቋማትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች ሐሳብ እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ በሒደቱ የተገኘው ነገር ደግሞ ያመጣናቸውን ጉዳዮች በትክክል አይተናቸዋል ወይ የሚለውን እንድናረጋግጥና ባለሙያዎችም ከራሳቸው ልምድ ተነስተው ያላቸውን ሐሳብ እንዲሰነዝሩ ተደርጎ፣ ያ ከዳበረ በኋላ ነው ዓውደ ጥናት የተዘጋጀው፡፡ ዓውደ ጥናቱ ትኩረት ያደረገው ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ማሳየት ላይ ነው፡፡ እነዚህ አካላት ችግሩንም የሚያዩት አካላት ናቸው፡፡ ራሳቸው የአመራር ናቸው፡፡ ስለዚህ የተጠራው አመራሩ ነው፡፡ ከተለያዩ ተቋማት ነው የተመረጡት፡፡ የምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች እንዲገኙ ተደርጓል፡፡  የሚዲያ አካላት እንዲገኙ ተደርጓል፡፡ ከብዙኃንና ከሙያ ማኅበራት የተውጣጡ አካላትም እንዲገኙ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ሰዎች የችግሮቹን መኖር እንደሚቀበሉ አረጋግጠውልናል፡፡ ሁለተኛው ነገር ደግሞ መፍትሔውን የጋራ ለማድረግ አስችሎናል፡፡ የዚህ ተቋም ዋና ሥራ ፖሊሲ ማውጣት ሳይሆን፣ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችን ለውሳኔ ማቅረብ ነው፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ወስደውና ለራሳቸው አድርገው ውጤት እንዲያመጡበት፣ ወይም ደግሞ ዕርምጃዎች እንዲወስዱበት ለማድረግ ነው የምንሠራው፣ ከዚህ አንፃር የተገኘው ግብዓት ጥሩ ነው፡፡ እያንዳንዱ የሚመለከተው አካል ችግሩ የራሴ ነው ብሎ ወስዶታል፡፡ በራሳቸው ደግሞ ሊወስዷቸው የሚችሏቸውን ዕርምጃዎች እንደሚወስዱ እዚያው ስብሰባው ላይ አንስተዋል፡፡ ስለዚህ ችግሩንና መፍትሔውንም የጋራ አድርጎ ከመሄድ አንፃር ትልቅ ግብዓት የተገኘበት ዓውደ ጥናት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ጊዜ ጥናቶች ከተሠሩና ለሕዝቡ ይፋ ከሆኑ በኋላ ወደ መደርደሪያ ይወረወራሉ፡፡ ይኼ ጥናት ተግባራዊ እንዲሆንና እንዲፈጸም ምን ያህል ክትትል ታደርጋላችሁ?

ወ/ሮ ውብአምልክ፡- በጣም ትክክል ነህ፡፡ ብዙ ጥናቶች ይጠኑና መደርደሪያ ላይ ዝም ብለው ይቀመጣሉ፡፡ ለሚፈለገው አካል ሳይደርሱ ይቀራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሀብት ብክነት ይሆናል፡፡ የእኛ ተቋም እነዚህ ጥናቶች ምን ውጤት አምጥተዋል? ያጠናናቸው ጥናቶችስ ምን ያህል መሬት ላይ ወርደዋል? የመንግሥት አካላት በትክክል ወስደዋቸዋል? ውጤታማ አድርገዋቸዋል? የሚያስፈልጉ መመርያዎች ወጥተዋል? የፖለሲ ማዕቀፍ ሊዘጋጅላቸው የሚገቡ ተዘጋጅቶላቸዋል ወይ? የሚሉትን እናረጋግጣለን፡፡ አንዳንዴም አለፍ ብለን ሐሳቦችን መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ እንዴት አድርገው ነው ተግባራዊ የሚያደርጉት የሚለው ላይ እየገፋን የማስፈጸሚያ ሥልቶችን ጭምር አብረን እየሰጠን ነው፡፡ የጥናት ማንዋል አለን፡፡ ማንዋላችን ትኩረት ከሚያደርግባቸው ነገሮች አንዱ የክትትል ሥርዓቱ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በማዕከላችሁ ይኼን የሚከታተል የተለየ ባለሙያና አደረጃጀት አለ?

ወ/ሮ ውብአምላክ፡ ከዚህ በፊት እኛው ነን የምንሠራው፡፡ የማስፈጸሚያ ሥልቶቹንም ሆነ መሥሪያ ቤቶችን አግዘን የምንሠራው እኛው ነን፡፡ ምናልባት ወደፊት የሚጠኑ ጥናቶች እየበዙ ሲሄዱ እንደዚህ ዓይነት ራሱን የቻለ ተፅዕኖ ላይ የሚሠራ አካል ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በጥናታችሁ የሕዝብን ተሳትፎ ሊገቱ የሚችሉ የጥናቱ ዋና ዋና ግኝቶች ተብለው የተለዩ ጉዳዮች ምንድናቸው?

ወ/ሮ ውብአምላክ፡- የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ሁሉንም ማዳረስ ስለማንችል ሦስቱን አካላት ነው የመረጥነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝብ ወክሎ፣ የሕዝብና የአካባቢውን ጉዳይ ለሚመለከተው አካል የሚያቀርቡና የሚወስዱ ግለሰቦች ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የውክልና ተሳትፎ የሕዝብ ተሳትፎ እንዴት እየሄደ ነው? እውነት የመረጣቸውን አካላት ያያሉ ወይ? ጉዳዩን ያስቀድማሉ ወይ? ያስወስናሉ ወይ? የሚለውን ለማየት ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር ልክ እንደ ምክር ቤቶች ሁሉ የብዙኃንና የሙያ ማኅበራት የምንላቸውም ከሥራቸው በርካታ አካላት አሏቸው፡፡ ብዙኃን ማኅበራት የምንላቸው ወጣቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከጀርባቸው ብዙ አካላት ይኖራሉ፡፡ የእነዚህን ሐሳብ ነው ይዘው የሚሄዱት፡፡ ይኼ ምን ይመስላል ብለን ነው ለማየት የሞከርነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የምናገኘው ደግሞ ሚዲያው ነው፡፡ በውክልናም ይምጣ በግልም ይምጣ ሕዝብን አሳትፎ፣ የሕዝብን ጉዳይ እንዲሁ ለሕዝብ ይዞ የሚቀርብ አካል ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን የመረጥነው ለዚህ ነው፡፡

በዚህ ጥናት አሥራ ሁለት ችግሮች ናቸው ነጥረው የወጡት፡፡ የመጀመሪያው ነጥሮ የወጣው ችግር ለሕዝብ ሊሰጥ የሚገባውን ያህል ትኩረት ያለመስጠት ነው፡፡ የሕዝብን ኃይል፣ የሕዝብን ጉልበት፣ የሕዝብን አቅም በሚገባው ደረጃ አለመረዳት ነው፡፡ ለዚህ ችግር መገለጫዎቹ ብለን ያስቀመጥናቸው ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የአመለካከትና የግንዛቤ ችግር ነው፡፡ የአመለካከትና የግንዛቤ ችግር ስንል በአንድ በኩል ራሱ ሕዝብን እንደ ሕዝብ፣ ሕዝብን እንደ ጉልበት፣ ሕዝብን እንደ ኃይል ቆጥሮ  ሊሳተፍ በሚገባው ነገር ላይ አለማሳተፍ ሲሆን፣ በአብዛኛው ይኼ ችግር የሚንፀባረቀው ደግሞ አስፈጻሚው ዘንድ ነው፡፡ አስፈጻሚው ስንል በሁሉም ደረጃ የሚገኘው ማለት ነው፡፡ በአስፈጻሚው ከላይ እስከ ታች ድረስ ባለው የሚያጋጥም ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ አስፈጻሚው አካል ምክር ቤት ያሉ ሰዎች ከተጠናከሩ እኮ ይሞግቱኛል፣ ይጠይቁኛል ብሎ በተሳሳተ መንገድ የመረዳት ችግር ይታያል፡፡ ምክር ቤቶችን አንዳንድ ጊዜ አሳንሶ የማየት ነገር እናያለን፡፡ የምክር ቤት አባላት ምን አይሠሩም፣ ዝም ብለው ነው የሚሄዱት ዓይነት ሐሳቦች ይንፀባረቃሉ፡፡ ይኼ ደግሞ የግንዛቤ ችግር ነው፡፡ ልክ እንደ ምክር ቤቶች ሁሉ ብዙኃንና ሙያ ማኅበራትም ጋ የምናየው ችግር አለ፡፡ ብዙኃንና ሙያ ማኅበራት ከጀርባቸው በርካታ አካላት ያሏቸው ናቸው ብሎ አለመገንዘብ፤ ጉልበታቸውን አለመረዳት፣ እነሱን ይዤ ብሠራ ውጤት አመጣለሁ፣ የእነሱን ሐሳብ ባስገባ ውጤታማ እሆናለሁ ብሎ ያለማሰብ ችግር አለ፡፡ ሊሆን በሚገባው ደረጃ አለመዳበር ችግር አለ፡፡ ሊሆን በሚገባው ደረጃ አልዳበሩም፡፡

በአስፈጻሚው በኩል ሚዲያ ላይ ያለው አመለካከት በሚፈለገው ደረጃ የዳበረ አይደለም፡፡ አሳንሶ ማየት፣ ተፅዕኖ ማሳደር፣ የሚባለውን ብቻ ነው መዘገብ ያለበት ብሎ ማመን በአስፈጻሚው በኩል ከሚታዩ ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስም የመገንባት ዓይነት እንጂ ሚዲያው የሕዝብና የመንግሥት ነው፣ ሕዝብንና መንግሥትን የሚያገናኝ ድልድይ ነው ብሎ ያለመውሰድ ነገር በብዙ አስፈጻሚዎች ዘንድ ይታያል፡፡ ይኼም በመሆኑ ዝም ብለህ የተሰጠህን ሥራ፣ ጥሩ ነገሬን ብቻ አቅርብልኝ የማለት ሁኔታ አለ፡፡ አልፎ ተርፎም ሚዲያውን የራሳቸው የሕዝብ ግንኙነት አድርገው መውሰድ፣ የተቋማቸውን ገጽታ መገንቢያ መሣሪያ አድርገው መውሰድ ችግሮች ይታያሉ፡፡ እነዚህ በጥናቱ ጎላ ብለው የወጡ ችግሮች ናቸው፡፡ የሕዝብን ተሳትፎ ለማሳደግ ትልቅ ሚና ያላቸው አካላት የሚፈለገውን ያህል አቅማቸው አልተገነባም፡፡ አንደኛ እነዚህ የምንላቸው ሦስቱ አካላት ላይ አስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል፡፡ ሁለተኛ ብቃታቸው ያልተገነባና መብታቸውን በማስከበር ሊሠሩ የሚገባቸውን ያህል ደፍረው እየሠሩ አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በስፋት የሚታዩ ናቸው፡፡ ሊሳተፍ የሚገባውን አካል ትተን ሌላውን የማሳተፍ ችግሮች አሉ፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የመጀመሪያው ነገር ሊሳተፉ የሚገባቸውን አካላት በትክክል መለየት ስንችል ነው፡፡ ራሱ ጉዳዩ ምንድነው ብሎ መለየት ይጠይቃል፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ወይ? ማን ነው የሚሳተፈው? ምን ዓይነት ሰው ነው የምጠራው? እነማን ናቸው የሚመጡት? ለሕዝብ ተሳትፎ የሚያመች መንገድ አለ ወይ? ብለን መጠየቅና መመለስ አለብን፡፡

ሌላው በጣም ትልቁና በሕዝብ ተሳትፎ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድረው ጉዳዩ የምሰጠው አስተያየት ይወሰድልኛል ብሎ ማመን አለበት፡፡ ይኼንን ጉዳይ የሚቀበል አስፈጻሚ አካል አለ ብሎ ማመን መቻል አለበት፡፡ ሌላው ጉዳይ በተፅዕኖ ሥር መውደቅ ነው፡፡ ምክር ቤቶች፣ የሙያና ብዙኃን ማኅበራትና ሚዲያው ጋ ይኼ ችግር አለ፡፡ ሰዎች ለመናገር የሚፈልጉትን አይገልጹም፡፡ ተደማጭ አለመሆን ሌላው ችግር ነው፡፡ በቃ የምናገረው ነገር ተሰሚነት ከሌለው ለምን እንናገራለን ብሎ የማሰብ ሁኔታ አለ፡፡ ተደማጭ እንዳልሆን ካወቅን ደግሞ ከመናገር እንገደባለን፡፡ ሐሳቤ ተቀባይነት የለውም ካልን አንዴ ትሞክራለህ፣ ሁለቴ ትሞክራለህ ከዚያ በኋላ ታቆማለህ፡፡ ባለፈው ስብሰባ ላይ የተነሳ ነገር አለ፡፡ ሕዝብም አስፈጻሚውም ችግሮች እንዳሉ ይስማማሉ፡፡ ልዩነቱ ያለው ይኼንን ችግር ወስዶ ምላሽ የመስጠትና ያለመስጠት ላይ ነው፡፡ የተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ችግር ደግሞ ሁሉም ጋ የሚታይ ነው፡፡ ከሕዝብ ምክር ቤትም ጋር ተያይዞ ሕዝብ የወከለኝ ነኝ፣ ከጀርባዬ ብዙ ሕዝብ አለ፣ ስለዚህ የእነሱን ሐሳብና ጥያቄ ይዤ መሄድ አለብኝ ብሎ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የማሳየት ችግር ይታያል፡፡ በተለይ ማኅበራት ጋ ችግሩ የጎላ ነው፡፡ ብዙዎቹ የሙያ ማኅበራት የምንላቸው የተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ችግር አለባቸው፡፡

ሚዲውም ላይ እንደዚሁ ይታያል፡፡ ጋዜጠኛው የሕዝብ ጉዳይ ጉዳዬ ነው ብሎ ያለመሥራት፣ እዚያ ውስጥ የወጣ ነገር አለ ብሎ በተነሳሽነትና በቁርጠኝነት የመሥራት ችግር አለ፡፡ የደመወዝ ማግኛ ብቻ አድርጎ የመውሰድ ነገር አለ፡፡ ይኼንን የሕዝብ ችግር በመሥራቴ ደስተኛ ያደርገኛል ብሎ ያለመንቀሳቀስ ነገር በጣም እናያለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የቁርጠኝነት የሥነ ምግባር ችግሮችም ይታያሉ፡፡ በሁሉም ደረጃ በሚባል ሁኔታ የአቅም ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ ከአሠራር ጋር የተያያዙ ክፍተቶች አሉ፡፡ ሌላው ከአደረጃጀቶች ጋር የሚያያዝ ችግር አለ፡፡ ይኼ ችግር በአብዛኛው የሚታየው ምክር ቤቶች ጋ ነው፡፡ የቋሚ ኮሚቴዎች ቋሚ ሆኖ አለመሥራት፣ በታችኛው ደረጃ ምክር ቤቶች አለመደራጀት፣ ወዘተ ዓይነት ችግሮች ይታያሉ፡፡ ከመረጃ ጋር የተያያዙ ችግሮችም አሉ፡፡ መረጃ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ አገር ቋሚ የመረጃ ቋት የለንም፡፡ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ መረጃዎችን የመያዝ ነገር ገና ያልዳበረ ነው፡፡ ከሚዲያዎች አካባቢ የሚነሳው ነገር ደግሞ መረጃ ለማግኘት ውጣ ውረድ የበዛበት ነው፡፡ አድሏዊነት መኖር፣ አንዳንድ ጊዜ ለተወሰኑ ሰዎች ይሰጣል፣ ለተወሰኑት ደግሞ የሚከለከልበት ነገር አለ፡፡ እነዚህ ከሞላ ጎደል በጥናቱ ነጥረው የወጡ ችግሮች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡– እነዚህ ነጥረው የወጡ ችግሮች ለሚመለከተው አካል ተደራሽ ሆነው የሕዝብን ተሳትፎ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ በአሁኑ ጊዜ ምን እየሠራችሁ ነው?

ወ/ሮ ውብአምላክ፡- በእርግጥ  ገና ከዚህ በኃላ ነው የሚሠራው፡፡ ጥናቱ የወጣው አሁን ነው፡፡ አሁን ጥናቱ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቧል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በሰፊው የሚሠራበት ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ችግሮች አሉ ብለን በለየናቸው ጉዳዮች ላይ ከአመራር አካላት ጋር መስማማት ተደርሷል፡፡ ስለዚህ ከአሁን በኃላ እያንዳንዱ አስፈጻሚ  የራሱ የሆነን ችግር ወስዶ እንዲሠራ የምናደርግበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ያው ማጠንጠኛው አስፈጻሚው ላይ ነው፡፡ አስፈጻሚው በእነዚህ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ለውጥ ስለሚኖር ነው፡፡ የሚቀጥለው ሥራችን የሚሆነው ችግሮቹን ችግሩ ያለባቸው አካላት ዘንድ መወሰድ ነው የሚሆነው፡፡ የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት አድርጎ ወደ ሥራ መግባት ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በስብሰባው ላይም ያረጋገጥነው በችግሮች ላይ ልዩነት የለም፡፡ ልዩነት ያለው እንዴት አድርገን እንፍታው በሚለው ላይ ነው፡፡ ችግርን ማወቅ አንዱ ትልቁ ደረጃ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያ በኋላ እንዴት እንሂድ በሚለው ላይ በደንብ ተነጋግሮና አቅጣጫ ይዞ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ደንብና ሥርዓት ባለው ሁኔታ አሠራር ዘርግቶ መሄድ ይጠይቃል፡፡ ይህ ጥናት በአሁኑ ጊዜ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ስለሆነ ወደፊት መሥራት ግን ይጠይቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ሰዎች የሚጠኑ ጥናቶችና በኋላ ላይም ፖሊሲ ሆነው የሚወጡ ጉዳዮች ተመልሰው የሚሻሩበት ሁኔታ አለ ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን አቶ ዓባይ ፀሐዬ የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ከአምስት ጊዜ በላይ እንደተሻረ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ የሚጠኑ ጥናቶች ተጨባጭ ሆነው የሕዝብን ችግር ከመፍታት ባሻገር፣ ሌላ ሁለተኛና ሦስተኛ ጥናት ሳያስፈልግ ፖሊሲ ሆነው የሚወጡበትን ሁኔታ ከመፍጠር አንፃር ምን ዓይነት ሥራዎችን እየሠራችሁ ነው?

ወ/ሮ ውብአምላክ፡- አንዱ በእኛ ጥናት ያወጣነው ነገር ይኼ ነው፡፡ ከጥናት በኃላ ፖሊሲዎች ይወጣሉ፡፡ ፖሊሲ የማውጣት ኃላፊነት ደግሞ የሁሉም አስፈጻሚ አካል ነው፡፡ ሁሉም አስፈጻሚ አካል የራሱን ፖሊሲ ነው የሚያወጣው፡፡ የሚወጡ ፖሊሲዎች ከመውጣታቸው በፊት ሐሳብ ሊሰጡ የሚገባቸው አካላት በሙሉ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል፡፡ ልዩነት ያለውና አሁንም እንዲመለስ የሚያደርገን ይኼ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት አዋጁ ሊወጣ ነው ሲባል ማንን ነው የሚመለከተው ብሎ መጠየቅና ከሚመለከተው አካል ጋር በቂ ውይይት መደረግና ግብዓት መሰብሰብ አለበት፡፡ አሁን ይኼ ፖሊሲ ወጥቶ ተግባራዊ የሚደረገው ኢንቨስተር ላይ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ሌላ አካል ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ እነሱ ዘንድ ሂዶ ምንድነው ሊያመጣ የሚችለው? ሐሳባችሁ ምንድነው? ትክክል ነው ወይ? ወደ መሬት ሊወርድ ይችላል ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ችግር መንስዔ የሚሆነው በበቂ ደረጃ ውይይት አለማድረግ ነው፡፡ እኛም ጋ ጥናት ስናደርግ ያየነው አንዱ ችግር ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ያመጣው የሚመለከታቸው አካላት በበቂ ሁኔታ እንዲሳተፉ ተደርጎ፣ ሐሳባቸው ተሰብስቦ መሥራት ባለመቻሉ ነው፡፡ ችግሩ ትክክል ነው፡፡ በእኛ ጥናትም በቂ የሆነ ውይይት ባለመደረጉ፣ በቂ የሆነ ተሳትፎ ባለመደረጉ ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባቸው የነበሩ ነገሮች እንደገና እንዲሻሻሉ የሚደረጉበት ሁኔታ እንዳለ አረጋግጠናል፡፡

ሪፖርተር፡– የጥናቱን ወሰን ስንመለከት በአራት ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ላይ የተገደበ ነው፡፡ ይኼ ጥናት በታዳጊ ክልሎች ቢሠራ ኖሮ የበለጠ የችግሩን ጥልቀት ያሳይ ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህንን ሐሳብ እንዴት ያዩታል?

ወ/ሮ ውብአምላክ፡- ጥናት ሲጠና እንደሚታወቀው ናሙና ተወስዶ ነው፡፡ በዋነኛነት ደግሞ እነዚህ ላይ ትኩረት ያደረግነው የመልካም አስተዳደሩ ተከታይ ናቸው ብለን ነው የወሰድነው፡፡ ይኼንን ነው ይዘን የሄድነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ጥናት ሲጠና እነዚህን አሁን ለተሳትፎ የተጠቀምናቸውን ነው የወስደነው፡፡ ከዚህ አንፃር ያንን ተከትለን ነው የሄድነው፡፡ ለዚህ ነው እነዚህን አራት ክልሎችና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች የመረጥነው፡፡ እንደ አገር ስናየው ችግሮቹ ተወራራሽነት አላቸው፡፡ መጠኑ ነው ሊሰፋና ሊጠብ የሚችለው፡፡ ከዚህ አንፃር የገነነ ልዩነት ይመጣል ብዬ አላምንም፡፡ አንዳንድ ነገሮችንም ለማየት ሞክረናል፡፡ በዚህ አገር የሕዝብ ተሳትፎ ምንድነው የሚመስለው ብለን ስናይ ያየናቸው ነገሮች አሉ፡፡ የተወሰነ የመግዘፍና ያለመግዘፍ ካልሆነ በስተቀር ችግሮቹ ተመሳሳይነትና ተወራራሽነት አላቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -