Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየባህረ ሰላጤውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሥጋት በቅርበት ለመከታተል ኢትዮጵያ በኦማን ኤምባሲ ልትከፍት ነው

የባህረ ሰላጤውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሥጋት በቅርበት ለመከታተል ኢትዮጵያ በኦማን ኤምባሲ ልትከፍት ነው

ቀን:

በየመን የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስታከው የባህረ ሰላጤው አገሮች የሚያካሂዱት ፖለቲካዊ ፍልሚያና ከቀጣናው ውጪ በሚታየው የመስፋፋት አዝማሚያ የተነሳ ሥጋት የገባት ኢትዮጵያ፣ ሁኔታውን በቅርበት ሆና ለመከታተል አዲስ ኤምባሲ በኦማን ልትከፍት መሆኑ ተሰማ፡፡

ኤምባሲውን በፍጥነት ለመክፈትም የባህረ ሰላጤው ቀጣና ውስጥ ከምትገኘው ኦማን የመንግሥት ባለሥልጣናት ይሁንታ መገኘቱን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የተደራጀ የሰው ኃይል መረጣ የተጠናቀቀ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥም ተልዕኮ ተቀብለው ወደ ኦማን ሊያቀኑ እንደሚችሉ ምንጮች አክለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ በየመን የተፈጠረው ቀውስና የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ በኢትዮጵያ ላይ ስለሚኖረው ፖለቲካዊ አንድምታ ተጠይቀው ነበር፡፡

በየመን በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስና የለየለት ጦርነት ሳቢያ ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከሰንዓ ለማስወጣት መገደዷን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ወቅታዊ መረጃ የማግኘት እክል እንደተፈጠረ አስረድተዋል፡፡  

‹‹ኤምባሲያችንን ከየመን ካስወጣን በኋላ በየመን አካባቢ ያለውን ሁኔታ በተለይ ደግሞ በገልፍ አገሮችና በኢራን መካከል እየተካሄደ ያለውን የእጅ አዙር (Proxy) ጦርነት ለመከታተልና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አኳያ ለመተንተን በቂ መረጃ በወቅቱ የማግኘት ችግር አጋጥሞናል፡፡ ይህንን ችግር በፍጥነት ለመፍታትና በቅርበት ለመከታተል አዲስ ኤምባሲ በኦማን ለመክፈት እየጣርን ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

የዓረብ አብዮት በየመን መቀጣጠሉን ተከትሎ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ የተገደዱት ፕሬዚዳንት ዓሊ አብዱላህ ሳላህን በመተካት ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሐዲን በመቃወም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ በአሁኑ ወቅት መልኩን ቀይሮ የአልቃይዳ፣ የአይኤስ፣ የሒዝቦላህና የሁቲ አማፂያን የጦር አውድማ ሆኗል፡፡

በየመን የተቀሰቀሰው ውስጣዊ ቀውስም የፖለቲካዊ ኢስላም ፍልሚያ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ፍልሚያውም በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራው በሱኒ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑት የባህረ ሰላጤው አገሮች ማለትም በሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት፣ ቤሩት፣ ኳታርና ኦማን ባንድ በኩልና የሺያ እስልምና ተከታይ በሆነችው ኢራን መካከል የሚደረግ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢራን በየመን የሚንቀሳቀሰውን የሁቲ አማፂያን በመሣሪያ እየደገፈች ሲሆን፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራው የዓረብ አገሮች ጥምረት አባል አገሮች ደግሞ የፕሬዚዳንት ሐዲ ደጋፊዎችን ለመርዳት የእግረኛ ጦራቸውን ወደ የመን ልከዋል፡፡ በተጨማሪም ከኤርትራ መንግሥት በኪራይ ባገኙት የአሰብ ወደብ የጦር ኃይላቸውን እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ለፓርላማው ያስረዱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በዚህ አካባቢ ያለው ጉዳይ በሒደት እኛን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካን እየሆነ ነው፡፡ የእነዚህ አገሮች ፍልሚያ ቀስ በቀስ ወደ ቀይ ባህርና ወደ ሶማሌላንድ እንዲሁም ወደ ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች እየተሳበ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢራንን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚል ምክንያት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት የባህር ኃይሉን በሶማሌላንድ ማስፈር የሚያስችለውን ስምምነት ከወራቶች በፊት ፈጽሟል፡፡ በሁለቱ መካከል የተደረገው ስምምነት እንደሚያስረዳው ሶማሌላንድ የበርበራ ወደብን ለሚቀጥሉት 25 ዓመታት ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አከራይታለች፡፡ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የሶማሌላንድ መንግሥት በሰሜን በርበራ የሚገኘውንና ለኤደን ባህረ ሰላጤ ቅርብ የሆነውን አካባቢ ከሊዝ ነፃ ለወታደራዊ አገልግሎት እንዲጠቀምበት ፈቅዷል፡፡

መረጃ በተጨማሪ እንደሚያመለክተው፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሶማሌላንድ የሚገነባውን ወታደራዊ የጦር ሠፈር ለሌላ ዒላማ መጠቀም አትችልም፡፡ በሶማሊያ ሞቃዲሾ ተመሳሳይ ወታደራዊ የጦር ሠፈር የመገንባት ጥረት በኳታር በኩል መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

‹‹በባህረ ሰላጤው አካባቢ የበላይነትን ለመያዝ በኢራንና በዓረብ አገሮች መካከል የተጀመረው ፍልሚያ ቀይ ባህርንና የአፍሪካ ቀንድን እንዳይመርዝ በኢትዮጵያ በኩል ሥጋት አለ፤›› የሚሉት አንድ የውጭ ጉዳይ ባለሙያ፣ በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሚገኘው የአሜሪካ ጦር ጥቃት የመሰንዘር ፈቃድ ሊሰጡ የቻሉት፣ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ እንቅስቃሴው በአሜሪካ ደኅንነት ላይም ሥጋት የሚፈጥር ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በየመንና በባህረ ሰላጤው የሚፋለሙት ሁለት ትልልቅ ኃይሎች ጉዳይ ከእኛ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ሲመዘን ምን ማለት ነው የሚለውን በቅርበት ሆነን መከታተል አለብን፤›› ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የኳታሩ አሚር ሼክ ታማም ቢን ሃማድ አል ታኒ ለይፋ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ዋነኛ የመወያያ አጀንዳቸው የአካባቢው ደኅንነት እንደነበር መንግሥት ገልጿል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...