በኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ ሪጅን ቢዝነስ ፓርትነር ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ፣ አራት በተለያየ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩ ሠራተኞችና ሁለት ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ፡፡
ተከሳሾቹ የምዕራብ ሪጅን ቢዝነስ ፓርትነር ሥራ አስኪያጅ አቶ ደቻሳ ነመራ፣ የትራንስፖርት ሱፐርቫይዘር አቶ ጉርሜሳ አብዲሳ፣ የትራንስፖርት ፍሊት ኢንስፔክተሮች አቶ ገመችስ ኃይሉና አቶ አሸናፊ ጌታሁን ናቸው፡፡ ከእነሱ ጋር ተመሳጥረዋል የተባሉት ግርማ አስፋው የከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች ጥገና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ አስፋውና የሒሳብ ሠራተኛው አቶ ጴጥሮስ ታረቀኝ ናቸው፡፡
በኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን የትራንስፖርት ፍሊት ኢንስፔክተር የነበሩት ሦስተኛና አራተኛ ተከሳሾች፣ ከግርማ አስፋው የከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች ጋራዥ ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር፣ የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ በተቋሙ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮምና ግርማ አስፋው የከባድና የቀላል ተሽከርካሪዎች ጥገና መካከል በተደረገው የተሽከርካሪዎች ሰርቪስና ጥገና ውል የገቡ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ ከውል ውጪ የክፍያ ሰነዶችን በማዘጋጀት ትክክለኛ ጥያቄ በማስመሰል ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ተከሳሾቹ በተለያዩ ጊዜያት በድምሩ 1,152,106 ብር ከውል ውጪ ለጥገና አገልግሎት በመክፈል በመንግሥት ላይ ጉዳት በመፈጸማቸው፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡