በሐሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ የቡና ላኪነት የንግድ ፈቃድ በማውጣትና ሐሰተኛ የውክልና ሰነዶችን በመጠቀም የብቃት ማረጋገጫ በመውሰድ፣ 223,846 ዶላር ወይም 4,702,506 ብር የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉ ሦስት ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ እንደሚያስረዳው ድርጊቱን በመመሳጠር የፈጸሙት አቶ አብዱልዋሀድ ሞሐመድ፣ ወ/ሮ ሉባባ ከሊልና አቶ ሸሪፍ ሱሌማን ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ በመመሳጠር ጉዳይ አስፈጻሚ ነው በተባለ ቴዎድሮስ ከበደ ስም ሐሰተኛ መታወቂያ በማውጣትና ሐሰተኛ የውክልና ሰነድ በማስያዝ፣ ከግብርና ሚኒስቴር የቡና ላኪነት ብቃት ማረጋገጫና ከንግድ ሚኒስቴር ንግድ ፈቃድ እንዲያወጣ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ለዚህ አገልግሎቱም 300 ሺሕ ብር እንደተከፈለው ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአብዱልዋሀድ ሞሐመድ ስም 200,000 ብር ገቢ በማድረግና ከግብርና ሚኒስቴር ገንዘብ በባንክ መኖሩን የሚገልጽ ደብዳቤ በማጻፍ፣ ቡናን ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችል በቂ አቅም እንዳላቸው በማስመሰል፣ የተሳሳተ ግምት እንዲያዝ ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
በአንደኛ ተከሳሽ አቶ አብዱልዋሀድ ስም በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደጋጋሚ ገንዘብ በማስገባት፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 694.7 ቶን ቡና ገዝተው ሳይልኩ መቅረታቸውንም አክሏል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ተከሳሾች ከባድ የማታለል ወንጀል በመፈጸማቸው ክስ እንደተመሠረተባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡