የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ጠቅልሎ የገዛው ዲያጆ፣ በዓለም ከሚታወቅባቸው ምርቶቹ አንዱ የሆነውን የጊነስ ስታውት ቢራ ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ እንደሚጀምር ይፋ አደረገ፡፡ ዓርብ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲሱን ቢራ ያስተዋወቀው ሜታ አቦ ቢራ ይኸው ምርቱ በቅርቡ ወደ ገበያ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት የኢትዮጵያን የቢራ ገበያ የተቀላቀለው ዲያጆ፣ ጥቁር መልኩን በጠበቀ አጠማመቅ ለኢትዮጵያ የሚያቀርበው ጊነስ ቢራ የአልኮል ይዘት 6.5 በመቶ እንደሚሆንና በርካታ ጌሾ እንዲሁም በእርጋታ የታመሰ ገብስ ተጨምሮበት እንደሚጠመቅ ስለቢራው በተሰጠ መግለጫ ተጠቅሷል፡፡
ቀደም ሲል የመንግሥት ይዞታ የነበረውና ሰበታ ከተማ ውስጥ በ1967 ዓ.ም. የተመሠረተውን ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን በ225 ዶላር የገዛው ዲያጆ፣ አዲሱን ጊነስ ቢራ በ15 ብር መሸጫ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡፡
የጊነስ ቢራ ብራንድ አምባሳደር የሆኑት አቶ ነብዩ ካሳ ስለቢራው ሲገልጹ፣ ጥሩ ጣዕም እንዲኖረው እያዳንዱ የገብስ ፍሬ በጥንቃቄ መታመሱን፣ ጊነስ ቢራ የሚለይበትን የበለጸገ የመራራ ጣዕም ምጣኔ፣ ይዘትና የዕርካታ ደረጃ እንዲኖረው ተደርጎ መቅረቡን አብራርተዋል፡፡ ምርቱን በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማ እንደሚያቀርብና የገበያውን ፍላጎት ካጠና በኋላ በክልሎችም ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉን፣ ከስድስት ሺሕ በላይ ገበሬዎችም ለምርቱ ግብዓት የሚሆነውን ገብስ በማቅረብ ከኩባንያው ጋር እንደሚሠሩ አቶ ነብዩ ተናግረዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ የቢራ ምርት መጠን በየዓመቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በፍጆታ ረገድም በነፍስ ወከፍ አምስት ሊትር የነበረው መጠን ወደ ስምንት ሊትር ከፍ በማለት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የቢራ ፋሪካዎች 12 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ቢራ በዓመት መመረት እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡ ዲያጆ ካስታዋወቃቸው የአልኮል ይዘት የሌላቸው መጠጦች መካከል ማልታ ጊነስ ከአራት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ማስገባቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ምርቱን በኢትዮጵያ ሲያቀርብ አገሪቱን ከአፍሪካ 50ኛዋ መዳረሻው አገር አድርጓታል፡፡
በ180 አገሮች ውስጥ ምርቱን የሚያሠራቸው ዲያጆ በአረቄ፣ በወይንና በቢራ መጠጦች አምራችነት የተሰማራ ሲሆን፣ ጆኒ ዎክር፣ ሲሚርኖፍ፣ ሲሮክ፣ ኬተል ዋን የመሳሰሉት ቮድካ መጠጦች ከሚታወቅባቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዲያጆ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም. ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ከገዛ በኋላ ለፋብሪካው ማስፋፊያ 119 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ሐረር ቢራ ፋብሪካ ጥቁር ሐኪም ስታውት ቢራ የተባለውን ቢራ በማምረት ቀዳሚው መሆኑ ይታወቃል፡፡