Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገር በቀል አማካሪዎች የተቆጣጠሩት የመንገድ ማማከር ሥራ በጨረታ አወጣጥ ቅሬታ ይቀርብበታል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በግንባታ ዘርፍ ግንባታዎችን ከሚያካሂዱ ተቋራጮች በተጓዳኝ የግንባታውን ዲዛይን፣ ግብዓትና ጥራት ደረጃና ሒደት በተቀመጠው መሥፈርት መካሄዱን የመቆጣጠር ኃላፊነት የሚጣልባቸው አማካሪ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

በግንባታው ባለቤት የሚሰየሙ፣ በተቋራጩና በግንባታው ባለቤት መካከል በመሆን አስገንቢውን ወክለው የሚሠሩት ሥራ እንዲያማክሩ በተረከቡት ፕሮጀክት ላይ ከፍተኛ ኃላፊነትና የውሳኔ ሥልጣን ይኖራቸዋል፡፡ አማካሪ ኩባንያዎች የሚረከቡት የቁጥጥር ሥራ አንድ ፕሮጀክት በጥራት ለመገንባትም ሆነ ላለመገንባቱ ትልቅ የኃላፊነት ድርሻ ይይዛል፡፡  

ተቋራጩ በሚያካሂደው ግንባታ ላይ ግድፈት ከተገኘበት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አማካሪ መሐንዲሱ ወይም ኩባንያው ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ በዚህ የአገልግሎት መስክ በተለይ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ከ80 በላይ ኩባንያዎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአገሪቱ የመንገድ ልማት ዘርፍ ፕሮግራም ከጀመረበት ከ1990 ዓ.ም. ቀደም ብሎ በመንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ አገር በቀል ኩባንያዎች ቁጥር በጣት የሚቆጠር ነበር፡፡ ከ1989 ዓ.ም. በፊት የአገር በቀል አማካሪዎች ቁጥር ከአምስት ያነሰ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንደ ተቋራጮች ሁሉ በጊዜው የነበሩ አገር በቀል አማካሪዎችም እጅግ ጥቂት ስለነበሩ፣ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን እንዲያማክሩ የሚሰየሙት በአብዛኛው የውጭ ኩባንያዎች እንደነበሩ መረጃው ያስረዳል፡፡

በዚህም በየዓመቱ ለሚገነቡት መንገዶች ለማማከር አገልግሎት ከሚወጣው ገንዘብ ውስጥ ከ90 በመቶውን የውጭ ኩባንያዎች ይወስዱት እንደነበር የሚያመላክተው የባለሥልጣኑ መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት አገር በቀል አማካሪዎች ድርሻቸው እያደገ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቀድሞ አምስት ብቻ የነበሩት አማካሪዎች አሁን ከ75 በላይ እንደደረሱ መረጃው ይገልጻል፡፡ ምንም እንኳ የመንገድ ዘርፍ አሁንም ድረስ ከውጭ አማካሪዎች እጅ ሙሉ ለሙሉ ባይወጣም፣ አብዛኛው የማማከር ሥራ ግን በአገር ውስጥ አማካሪዎች እየተሠራ ይገኛል፡፡

የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንደገለጹት፣ በ1990 ዓ.ም. በመንገድ ግንባታ አገር በቀል አማካሪ መሐንዲስ ይህን ያህል እንዳልነበር አስታውሰው፣ እስከ 2003 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የአገር ውስጥ አማካሪ ኩባንያዎች ቁጥር በ15 ብቻ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን 75 ያህል የተመዘገቡ አማካሪዎች በዘርፉ እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ይህም አገር በቀል አማካሪ መሐንዲሶች የሚያማክሯቸው ፕሮጀክቶች ቁጥር እየተበራከተ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ እስከ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ባለሥልጣኑ ወደ ግንባታ ካስገባቸው መንገዶች 74 በመቶውን የአገር ውስጥ አማካሪዎች ተቆጣጥረዋል፡፡

አማካሪዎች አገልግሎት ከሰጡባቸው 779 ፕሮጀክቶች ውስጥ 576 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች የአገር ውስጥ አማካሪ ኩባንያዎች ድርሻ ነው፡፡ ቀሪዎቹ 283 ወይም 38 በመቶው በውጭ ተቋራጮች የተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

 

 በ2008 ዓ.ም. ተጠናቀው ወደ አገልግሎት ከገቡና ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ከጠየቁ 20 መንገዶች ውስጥ በ14ቱ ላይ የአገር ውስጥ አማካሪዎች የቁጥጥርና የማማከር ሥራዎችን አከናውነውባቸዋል፡፡ አምስት ፕሮጀክቶች ደግሞ የአገር ውስጥና የውጭ አማካሪዎች በመጣመር የተሳተፉባቸው ሲሆን፣ የውጮቹ በተናጠል የተሳተፉባቸው ፕሮጀክቶች አራት ብቻ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

በ2008 ዓ.ምም ከተጠናቀቁት ውስጥ ኮር አማካሪዎች ኢንጂነሪንግ አራት ፕሮጀክቶችን አማክሯል፡፡ ቤዛ ኮንሰልታንት ለብቻው ከተረከበው አንድ ፕሮጀክት በተጨማሪ አምስቱን በጋራ አማክሯል፡፡

በመንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍ የአገሪቱን መሐንዲሶች ተሳትፎ በተመለከተ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ እንደገለጹት፣ ባለፉት 19 ዓመታት ከተከናወኑ ፕሮጀክቶች ውስጥ 62 በመቶውን እነዚሁ አማካሪዎች ተረክበዋል፡፡ በገንዘብ ሲተመንም ከ3.9 ቢሊዮን ብር ዋጋ እንዳለው አቶ አርዓያ ጠቅሰዋል፡፡

የአገር ውስጥ አማካሪዎችን አቅም ለማሳደግና ቁጥራቸውን ለማብዛት በሰባት የምሕንድስና ዘርፎች 7,000 ባለሙያዎች ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከ1,500 በላይ ባለሙያዎች ፕሮግራሙን አጠናቀው የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንደሠሩ የገለጹት አቶ አርዓያ፣ ከዚህ ባሻገር ከፍተኛ የክህሎት ክፍተት የሚየታይበትን የመካከለኛ ባለሙያዎችና የቴክኒሽያኖች ዘርፍንም ለማሻሻል ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ከ20,000 በላይ ባለሙያዎች እንደሠለጠኑ አስታውቀወዋል፡፡

የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞቹ ምርታማነትን ከማሳደግ፣ ብክነትን ከመቀነስ፣ ከጊዜው ጋር የሚሄዱ የግንባታ ዘዴዎችን፣ የአሠራር ሥርዓቶችን፣ ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከማስተዋወቅ አኳያም አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

በአንፃሩ የአገር በቀል አማካሪዎች መበራከት ተፅዕኖ አለው የሚሉም አሉ፡፡ የአገር ውስጥ አማካሪ ድርጀቶች ተሳትፎ መብዛትና በቁጥር ደረጃም እያየለ መምጣቱ በመልካምነቱ ቢጠቅስም፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ ከፍተኛ ውድድር የሚታይበት ዘርፍ ሆኗል እየተባለ ይገኛል፡፡

በዚህም ምክንያት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለማማከርና ለቁጥጥር ሥራ በሚወጡ ጨረታዎች ውስጥ የሚቀርቡት የመወዳደሪያ ዋጋዎች መጠን ከሌላው ጊዜ ይልቅ እየቀነሰ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ የመጫረቻ መሥፈርቶቹ ወጥ መሆንም ለዋጋው መቀነስ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገለጻል፡፡ ይህም በኢንዱስትሪው ውስጥ ብዙ ልምድ ያላቸው አማካሪ መሐንዲሶች በጨረታ አሸናፊ ሆነው ለመውጣት እየፈተናቸው እንደመጣ ሲታሰብ፣ አዳዲስ አማካሪዎች በሚያቀርቡት ዝቅተኛ ዋጋ ምክንያት ተመራጭ እየሆኑ መምጣታቸውም ይጠቅሳሉ፡፡

ከውጮዎቹ ይልቅ ሥራውን ለአገር ውስጥ አማካሪዎች መስጠቱ ተመራጭ መሆኑን የሚገልጹት አስተያት ሰጪዎች፣ የፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች የጥራት ደረጃው ላይ ግን ተፅዕኖ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡ በተለይ የመወዳደሪያ መስፈርቶቹ 15 እና 20 ዓመታት ልምድ ላካበቱትም ሆነ የአምስት ዓመት ልምድ ላላቸው ተመሳሳይ እንዲሆኑ መደረጋቸው ገበያው ውስጥ ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ የሚያምኑ አሉ፡፡ ይህም ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ሌሎች የሥራ መስኮችን፣ ምናልባትም ከአገር ውጭ ያሉ ዕድሎችን እንዲያስቡ እንደሚያደርግ በመግለጽ፣ የጨረታ አሰጣጥ ሥርዓቱ መፈተሽ እንዳለበት ነባር አማካሪዎች ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች