Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሜትር ታክሲዎች ቦሌ ኤርፖርት ውስጥ እንዳይሠሩ የፍርድ ቤት ዕግድ ወጣባቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ለቆሼ ተጎጂዎች የግማሽ ቀን ገቢያዎቸውን ለግሰዋል

በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በተሰጣቸው ፈቃድና ባደረጉት ስምምነት መሠረት በየትኛውም ቦታ ተዘዋውረው የመሥራት መብት እንደተጣቸው የሚገልጹት የአዲስ አበባ ሜትር ታክሲ ማኅበራት፣ ያለገደብ እንዲሠሩባቸው ከተፈቀዱላቸው ቦታዎች አንዱ አዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ይገኝበታል፡፡ ይህም ሆኖ ለሥምሪት የተመደቡ ተሽከርካሪዎች ባለፈው ሳምንት ወደ ኤርፖርት በሚገቡበት ወቅት የፍርድ ቤት ዕግድ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

ከቀረጥ ነፃ የገቡት ከ1000 በላይ ታክሲዎች ‹‹በከተማው የትኛውም ቦታ ተዘዋውረን እንድንሠራ ቃል ተገብቶልን ነበር፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች አንዱ ደግሞ ኤርፖርት ነው፤›› ያሉት የ‹‹ዘ ሉሲ›› ሜትር ታክሲ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ አንተነህ ትሪሎ ናቸው፡፡ አቶ አንተነህ እንደገለፁት፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በጉዳዩ በመግባት አዲሶቹ ሜትር ታክሲዎች ከሌሎቹ በኤርፖርት ውስጥ ከሚሠሩ ታክሲዎች እኩል በሚወጣላቸው ሥምሪት መሠረት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አሠራር ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በድልድሉ መሠረት ከቀናት በፊት ከኤርፖርቶች ድርጅትና ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ባለሥልጣኑ የተካተተበት አካል በጋራ የኤርፖርት ታክሲዎችንና የሜትር ታክሲዎች ባለንብረቶችን አነጋግረው እንደነበር የጠቀሱት አቶ አንተነህ፣ በድልድሉ ላይ ሁሉም ተነጋግሮና ተስማምቶ በዚያው መሠረት ሥራው ሊጀመር ቀን ተቆርጦ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በዚሁ መሠረት በየዕለቱ በኤርፖርት ውስጥ እንዲሠሩ ከሚፈቀድላቸው 150 ተሽከርካሪዎች ውስጥ ለሜትር ታክሲዎች 78 ተሸከርካሪዎችን በማስገባት እንዲሠሩ በተደለደሉት መሠረት ተሽከርካሪዎቻቸውን ለማስገባት ሲንቀሳቀሱ የፍርድ ቤት ዕግድ በመውጣቱ ወደ ቦሌ ኤርፖርት መግባት አትችሉም ተብለዋል፡፡ ለሥምሪት የወጡ ታክሲዎች በመጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን አቶ አንተነህ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ ባለሥልጣኑ ወደ ፊት በመራመድ ችግሮቹን ለመፍታት ቢሚክርም በተለይ ሜትር ታክሲዎች መግባት አትችሉም መባላቸው የሜትር ታክሲ ማኅበራት አባላቶችን እንዳሳዘናቸው ብቻም ሳይሆን ኪሳራ እንዳስከተለባቸው ተጠቅሷል፡፡ እንደ አቶ አንተነህ ማብራሪያ ከሆነ፣ ዕግድ ወጥቷል ተብለው እንዲመለሱ በተደረጉት ታክሲዎች ላይ ኪሳራ ደርሷል፡፡

‹‹እንደ ማኅበር ለእኛ ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ የፕሮግራሙ መስተጓጎልን በሚመለከት ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጽፈናል፡፡ ይህን ያደረገው አካል የደረሰብንን ኪሳራ እንዲከፍለን እንፈልጋለን፤›› ያሉት አቶ አንተነህ፣ ምክንያታቸው ደግሞ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ካላቸው አካባቢዎች በመጓዝ ወደ ኤርፖርት ያቀኑ ተሽከርካሪዎች አትገቡም ተብለው በመመለሳቸው ነው፡፡ በመሆኑም ነዳጃቸውንና ጊዜያቸውን አቃጥለው የመጡበትን የኪሳራ ማካካሻ በሕግ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

ዕግዱን ያወጣው አካል በሚመለከት ሪፖርተር ለማጣራት ቢሞክርም አጥጋቢ መረጃ ለማግኘት አልተቻለውም፡፡ ይህንኑ በማስመልከት ከባለሥልጣኑ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የሜትር ታክሲዎችን ጉዳይ በማስመልከት ከዚህ ቀደም ደጋግመው መግለጫ ሲሰጡ የሰነበቱት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ አማረም ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ለመጠየቅ ተሞከሮ ባለፈው ሳምንት ውጭ አገር እንደነበሩ ተገልጾ በዚሁ ምክንያት ሲጠበቁ ቆይተው፣ ሚያዝያ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ሪፖርተር በስልክ ሊያነጋግራቸው ሲሞክር በሕዝብ ግንኙነት በኩል ካልሆነ በቀር ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

የአዲሶቹ ሜትር ታክሲዎች የሰሞኑ አጋጣሚ ከዚህ ቀደም በሌሎቹ ታክሲዎች ዘንድም ሲያነታርክና የግጭት መንስዔ ሲሆን እንደቆየ የሚታወቅ ነው፡፡ ኤርፖርት ገብተው እንዳይሠሩ ጫና የሚደረግባቸው ነባሮቹ ሰማያዊ ታክሲዎች መግባት ተከለከልን እኩል አንታይም፣ መንግሥት ይህን ይፍታልን የሚሉ ስሞታዎችን ደጋግመው ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡

 በአንጻሩ ኤርፖርት ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መጥቶ እንደነበር የሚነገርለት ዝርፊያና ስርቆት መነሻው በታክሲዎች ምክንያት ነው በማለት በተለምዶ ከቦሌ ታክሲዎች በቀር ሌሎች ታክሲዎች እንዳይገቡ የሚከለክል ያልተጻፈ ሕግ ሲተገበር ቆይቷል፡፡ የሜትር ታክሲዎቹም መከልከል ከዚሁ የሰነበተ ክልከላ ጋር እንደሚገናኝ ቢገለጽም፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሜትር ታክሲዎችን ይቅርታ ከመጠየቅ በቀር እስካሁን ድረስ የተወሰደ ለውጥና ዕርምጃ አልታየም፡፡ እንደ አቶ አንተነህ ገለፃ ከሆነ ባለሥልጣኑ ነገሮችን ለማስተካከል ቃል ገብቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጋቢት ወር በቆሼ አከባቢ ቆሻሻ ተደርምሶባቸው በርካቶች ሲሞቱ፣ ብዙዎችም ቤትና ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡ በመሆኑም የ750 የሜትር ታክሲ ባለንብረቶች በመተባበር የግማሽ ቀን ገቢያቸውን ለተጎጂዎች እንዳዋሉ አቶ አንተነህ ገልጸዋል፡፡ ከ20 በላይ ማኅበራት የተሳፉበት ይህ የድጋፍ እንቅስቃሴ ለጊዜው ከ70 ሺሕ ብር ያላነሰ መዋጮ ለማሰባሰብ እንዳስቻለ አቶ አንተነህ ተናግረው፣ ተጎጂዎቹ ችግር እንደሆነባቸው በገለጹት መሠረት የምግብ ሸቀጦች፣ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶችና ሌሎችም መገልገያ ዕቃዎች ተገዝተው ለተጎጂዎቹ መከፋፈላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፈው ዓርብ በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ ተሳፋሪዎች ያደረጉትንም ትብብር አቶ አንተነህ አውስተዋል፡፡ ከተጓዙበት የገንዘብ ልክ በላይ አሳልፈው በመክፈል ለተጎጂዎች በሚደረገው የድጋፍ ላይ የተባበሩ በርካቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ወደፊትም ለቆሼ አካባቢ ተጎጂዎች ሜትር ታክሲዎች ድጋፍ ከመስጠት እንደማይቦዝኑ አቶ አንተነህ ተናግረዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች