- የተከበሩ ሚኒስትር በዓል እየተቃረበ እኮ ነው፡፡
- ያው እንደተመለደው እናከብረዋለን፡፡
- እንደተለመደው ምን ማለት ነው?
- ፋሲካ አይደል?
- እና?
- ዶሮና በግ ይበቃናል፡፡
- ይበቃናል?
- ምነው?
- የደላቸውማ በምን እንደሚያከብሩ ልንገርህ?
- እሺ፡፡
- የደላቸውማ ሙሉ የቤት ዕቃ ይለውጣሉ፡፡
- እ. . .
- አዲሱን ኤልጂ ቲቪ ያስገባሉ፡፡
- እ. . .
- ከጎልድ እስከ ብሉ ሌብል ድረስ በካርቶኖች ያስመጣሉ፡፡
- ህም. . .
- የዶሮውን ብዛት ትተህ ቢያንስ ሦስት የፍየል ሙክቶች ያርዳሉ፡፡
- ሦስት የፍየል ሙክቶች?
- አዎ!
- ምን ሊያደርጉላቸው?
- ወይ የእኛ ሞኝ?
- አልገባኝም፡፡
- አንዱ ፍየል ቁርጥ፣ ሁለተኛው ጥብስ፣ ሦስተኛው ደግሞ ወጥ ይሆናል፡፡
- ይህንን ሁሉ ፍየል ማን ነው የሚበላው?
- ዘመድ አዝማድና ወዳጆቻችን፡፡
- እሺ ለዚህ ሁሉ ወጪው ከየት ይመጣል?
- ወይ አንተ ሞኝ?
- እንዴት?
- ሌሎቹ ከየት እንደሚያመጡት አታውቅም?
- ከየት ያመጡታል?
- በስጦታ ይመጣላቸዋል፡፡
- እኔ የሚሰጠኝ ከሌለስ?
- ሥልጣንህን ተጠቀም፡፡
- ምን ማለትሽ ነው?
- ጓደኛህ ቤት እኮ ሄጄ ስንቱን ጉድ አየሁ?
- ምን አየሽ?
- አንድ የጭነት ተሽከርካሪ የማይበቃው የስጦታ ክምር ነዋ፡፡
- እነ ማን ናቸው የሚሰጡት?
- ተጠቅመው የሚጠቅሙ ልማታዊ ባለሀብቶች፡፡
- ሥልጣኔን ለዚህ እንድጠቀም ነው የምትመክሪኝ?
- ከዚያም በላይ ነው፡፡
- ለምሳሌ?
- በትንሹ የራሳችን የመኖሪያ ቪላ ከነመዋኛው፣ የምናከራያቸው ሕንፃዎች፣ የኮንስትራክሽን ማሽኖችና ተሽከርካሪዎች ያስፈልጉናል፡፡
- እነዚህ ሁሉ ከየት ይገኛሉ?
- ሌሎቹ ተሿሚዎች ከየት እንደሚያመጧቸው አታውቅም?
- ከየት ያመጣሉ?
- ሥልጣናቸውን በአግባቡ ተጠቅመውበት ነዋ፡፡
- ይኼማ ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ነው የሚባለው?
- የአንተ ሞኝነት እያበሳጨኝ ነው፡፡
- ቀዝቃዛ ውኃ ጠጪበት፡፡
- ውኃ ከምጠጣ አንተን ጥፊ ባልስህ ይሻለኛል፡፡
- ለምን ትናደጃለሽ?
- ኑሮህና ሥልጣንህ አይመጣጠኑም፡፡
- አንቺ ሴትዮ ምን አድርግ ነው የምትይኝ፡፡
- ኑሮህ ሥልጣንህን እንዲመስል ተጠቀምበት፡፡
- የምትይው ከእኔ መርህ ጋር አይሄድም፡፡
- የአንተ አጉል የድርቅና መርህ ይቀየራል፡፡
- በምንድነው የሚቀየረው?
- በሰጥቶ መቀበል መርህ፡፡
- ወይ ዕዳ?
[ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ወደ ቢሮአቸው እየወሰዳቸው ነው]
- ምነው ዛሬ ሙዚቃ አልከፈትክም?
- ክቡር ሚኒስትር ደብሮኛል፡፡
- ለምን ደበረህ?
- በዓሉ ቀዘቀዘብኝ፡፡
- ያለህን አብቃቅተህ በዓሉን ማሳለፍ ትችላለህ፡፡
- የድሮ ክቡር ሚኒስትር ሾፌር እኮ የነገረኝ ሌላ ነው፡፡
- ምን አለህ?
- በዓል ሲመጣ በሽበሽ ነው ነበር ያለኝ፡፡
- የአሁኑ ምን የተለየ ነገር አለው?
- ድርቅ ነው፡፡
- የምን ድርቅ?
- ሸጎጥ የሚያደርግ የለ፣ በግል የለ፣ ውስኪ የለ፣ ብቻ ምን አለፋዎት ደርቄያለሁ፡፡
- ማን ነው ለሾፌር ይህንን ሁሉ የሚያደርገው?
- ባለጉዳዮች ናቸዋ፡፡
- የማን ባለጉዳዮች?
- የክቡር ሚኒስትሩ፡፡
- ምን ለማግኘት?
- ለመጠቃቀም፡፡
- በምን ምክንያት?
- የሆነ ፕሮጀክት ይሰጣቸዋል በምትኩ ወረታውን ይከፍላሉ፡፡
- ለማን?
- ለክቡር ሚኒስትሩ፡፡
- አንተ ምን ቤት ነህ ታዲያ?
- የመረጃ ልውውጡ ከሾፌር እኮ ነው የሚጀምረው፡፡
- እና ምን ይሁን ነው የምትለው?
- ክቡር ሚኒስትር ለስለስ ይበሉ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ትንሽ ደረቅ ስለሚሉ ሰው ተቸግሯል፡፡
- በእናንተ ቤት ኃላፊነትን መወጣት የሚተረጎመው እንዲህ ነው?
- አይ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ዕድሜ ጠገቡን ተረት ረሱት መሰለኝ?
- ምንድነው የሚባለው?
- ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› ነዋ፡፡
- በአንተ ቤት ተርተህ ሞተሃል፡፡
- እኔማ በበዓሉ ፈንጥዤ ብሞት ነበር ደስ የሚለኝ፡፡
- ሆሆ. . .
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮአቸው ሲገቡ ጸሐፊያቸው ተከትላቸው ገባች]
- ክቡር ሚኒስትር የእንኳን አደረስዎት ፖስት ካርዶች ይቀበሉኝ፡፡
- ማን ነው የላከልኝ፡፡
- ከመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና ከኤምባሲዎች የተላኩ ናቸው፡፡
- ጥሩ፡፡
- በጣም ያሳዝናል፡፡
- ምን ተፈጠረ?
- የአንድ ክቡር ሚኒስትር ቢሮ የፖስት ካርድ መጋዘን በመሆኑ ነዋ፡፡
- ምን?
- የድሮ ክቡር ሚኒስትር የሚመጡላቸው የበዓል ስጦታዎች እኔ ነኝ ያለ አይሱዙ አይበቃቸውም ነበር፡፡
- ማን ነገረሽ?
- ጸሐፊያቸው፡፡
- አመንሻት?
- ምን ማመን ብቻ? ኑሮዋ እኮ ያስታውቃል፡፡
- እንዴት?
- እሷን ጸሐፊ ከማለት ሚኒስትር ማለት ይቀላል፡፡
- የእውነት?
- ለበዓል ከምታገኛቸው ስጦታዎች በተጨማሪ የራሷ ቤት፣ መኪና፣ ቡቲክና የሽቶ መሸጫዎች አሉዋት፡፡
- ምን ሠርታ አገኘች?
- የክቡር ሚኒስትሩ ቀኝ እጅ ነበረች፡፡
- ይገርማል፡፡
- እርስዎ ነዎት የሚገርሙት፡፡
- ምኔ ነው የሚገርመው?
- ወይ አይበሉ ወይ አያስበሉ፡፡
- አንቺ ምን አልሽ?
- ሁሉም ሰው የሚለውን ነው ያልኩት፡፡
- እንዲህ በቀላሉ ሀብት ማፍራት ይቻላል እንዴ?
- ሰው የሚነግርዎትን ቢሰሙ ይሻላል፡፡
- ምንድነው የሚነገረኝ?
- አዋጭ የሆኑ ምክረ ሐሳቦች፡፡
- ምንድናቸው እነሱ?
- መደራደርና ጥቅምን መተሳሰብ፡፡
- ምን?
- በድርድር ይሰጣሉ ጥቅምዎትንም ያገኛሉ፡፡
- ከዚያስ?
- ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
- ይኼ ምን የሚሉት መርህ ነው?
- የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ይባላል፡፡
- እቺን ይወዳል?
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠርተው እየተነጋገሩ ነው]
- ሪፖርቱን ጨረስክ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሁሉም ነገር ተሟልቷል?
- አልተሟላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን?
- ትንሽ ሙዴ ልክ አይደለም፡፡
- ምን ሆነሃል?
- በዓሉ ሲቃረብ ከፍቶኛል፡፡
- ለምን?
- የአሁኑ በዓል እንደጠበቅኩት አልሆነም፡፡
- ምንድነው የጠበቅከው?
- አለ አይደል. . .
- ምን?
- ያንን ፕሮጀክት ለሰዎቹ ብንሰጣቸው እኮ ደህና እንዘጋ ነበር፡፡
- ያለ ጨረታ?
- በድርድር፡፡
- ስማ ሕግ ጣስ ነው የምትለኝ?
- ድርድር ሕግ መጣስ ሆነ እንዴ?
- እንዴት ነው የምንደራደረው?
- ኮሚሽናችንን ይዘን ነዋ፡፡
- የምን ኮሚሽን?
- የተለመደ አሠራር ነው፡፡
- ኮሚሽን መቀበል?
- አዎ፡፡
- እንዴት እባክህ?
- የአገር አሠራር ነው እያልኩኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምሳሌ?
- የቱን ነግሬ የቱን ልተው?
- ማለት?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ነቃ ይበሉ?
- ምን ለመሆን?
- ይኼኔ እኮ በስጦታና በቼክ ተንበሽብሸን ነበር፡፡
- ምን አድርግ ነው የምትለኝ?
- በዓሉን እናድምቀው፡፡
- ከዚያስ?
- በአካባቢያችን ያሉት ሁሉ በደስታ ይጥለቅለቁ፡፡
- ደስታ የሚገኘው በዚህ መንገድ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ማዛጋት ሰልችቶኛል፡፡
- ምን ትሆን ታዲያ?
- ሪፖርቱን አዘግይተን ፕሮጀክቱን በአስቸኳይ እንስጥ ክቡር ሚኒስትር?
- ለማን?
- አሰፍስፈው ከሚጠበቁት መካከል የተሻለ ይዞ ለቀረበ ይሰጥ፡፡
- እንዲህ ነው የምታማክረኝ?
- የሚበጀው ይኼው ነው ክቡርነትዎ፡፡
- ባለቤቴ፣ ሾፌሬ፣ ጸሐፊዬና አማካሪዬ አንድ ዓይነት ነገር ነው የምታስቡት?
- በጭራሽ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከቤት ጀምሮ አንድ ዓይነት ነገር ነው የምሰማው፡፡
- ሐሳቡ አንድ ቢሆንም አቅጣጫው የተለያየ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- እርስዎ እንደ እግዜአብሔር፣ ባለቤትዎ እንደ ቄሳር፣ እኛ ደግሞ እንደ ዜጋ የሚገባንን ነው መጠየቅ ያለብን ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ማለት ነው?
- በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የሀብት ክፍፍል ለማለት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እና የሚገኘውን ኮሚሽን ደልድለሃል ማለት ነው?
- የመደልደሉ ሥልጣን ባይኖረኝም አሥልቼዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሥሌትህ ምን ይላል?
- 40/60 ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼ 40/60 እንዲህ መቀለጃ ይሁን፡፡
- የሁሉም ዓይን እዚያ ላይ ነው እኮ ያለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የ40/60 ሥሌት ይገለጽልኝ እስቲ፡፡
- እኛ 40 በመቶውን ስንቧጨቅ እርስዎ ከነቤተሰብዎ 60 በመቶውን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነው እባክህ የተሠላው?
- በዓሉን ታሳቢ በማድረግ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አሁን ይኼንን ሰው ቢሰማ ምን ይላል?
- ‹‹ጉድ አንድ ሰሞን ነው›› ሲባል አልሰሙም ክቡር ሚኒስትር?
- ወይ ጣጣ!