Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እስቲ አንነካካ!

እነሆ ጉዞ ከ‘ሲኤምሲ’ ወደ መገናኛ። የዛሬ ነገር ከትናንት በእጅጉ ይለያል። የፊቱ ወደኋላ የኋላው ወደፊት ሄዷል። ዱር የነበረው ከተማ፣ የአውሬው መንገድ የሰው ሆኗል። ከፍጥረት ሁሉ ሰው ብቻ የቀረ እስኪመስል ። ሽቅብ የነበረው ቁልቁል፣ ቁልቁሉም ሽቅብ ይጓዛል። ጉዞው የሚያልቅ አይመስልም። የነበረና ያለ ይኼን እውነት ይታዘባል። መታዘብ ብቻ አይደለም በዚህ የለውጥ ሒደት ውስጥ መዝለቁ ያመራምረዋል። በዚህ የኑሮ ስንክሳር በከባዱ የኑሮ ውጣ ውረድ፣ ሰው በመሆንና ባለመሆን ሲፍጨረጨር የማይታይ ሥጋ ለባሽ የለም። ሩጫው ደርቷል። አፍሶ ለመልቀም፣ ለትርፍ አልያም ደግሞ ለሙከራ። የማይሮጥ ግን የለም። መንገዱ በደማቅና በደብዛዛ ቀለማት የተዥጎረጎረ ነው።

ወያላው ገብቶ በሩን ይከረችማል። ታክሲያችን ከቆመችበት ተነስታ በአራት እግሯ ትጋልባለች። “ወይ ጉድ! ስንት የነፍስ ቁስልና የሐሳብ እከክ እንደማያስቸግረው ሁሉ ሙጀሌ የማያውቅ ትውልድ ተነሳ?” ይላሉ ወይዘሮዋ። ዞረው ዞረው ወደመጡበት፣ ኖረው አልያም አኗኑረው ወደ አፈር አይቀሬ መሆኑ የሕይወት ጎዳና ያሳመናቸው ይመስላሉ። ታዲያ ከመጨረሻ ወንበር አንድ ተሳላቂ ወጣት ይነሳባቸዋል። “መንገዱ አስፋልት በአስፋልት ሳይሆን፣ ዲግሪና ኑሮ የተጫነው ሳይቀር ድንጋይ እያነጠፈ፣ አቧራና ጭቃ ሳያራግፍ ነበረ ሙጀሌ። ዛሬ ልማት በልማት ሆነን፣ ቢጠበንም በቀለበት መንገድ ተሳስረን እያዩ ምን ፍጠሩ ነው የሚሉን?” ይላል። “እንዲያ በል አንተ! የሰው ፈንገስ አልጠረግ እንዳለን ቀረ እንጂ በመንገድማ አንታማም፤” አጠገቡ የተቀመጠች ጦር ጠማኝ ነገር ትቆሰቁሳለች። አተኩረን ስናያት አዕምሮዋ ጤነኛ እንዳልሆነ ገብቶናል።

”ኧ? ደግሞ የሰው ፈንገስ ማለት ምን ማለት ነው?” ሲሉኝ አዛውንቱ፣ “በሰው ሥጋ በሰው ቆዳ የሚጫወት ቫይረስ ማለት ነዋ። ምነው አውቆ እንዳላወቀ እየሆኑ ካሳበዱን ትልቅ ነን ባዮች ወንዝ ተጠምቀዋል መሰል?” ብላ ከታጠቀችው ቦላሌ ኪስ ፌስታል አወጣች። ፈታችውና የተቀነጣጠሱ ቅጠሎች አፏ ውስጥ እያጨቀች፣ “አሁን እኔን የመሰለች ቆንጆ ንክ ነች ሲሉ አያፍሩም? ነክተውኝ፣ ሳልደርስባቸው፣ ሳልጋፋቸው ‘ንክ’ ሲሉኝ ትንሽ ‘ሼም’ አያውቁም? እኔ አላበድኩም። ተደብቄ እንደ ፍየል የፈውሴን ቅጠል ስለማላመነዥክ ነው? ምነው እነሱ በአደባባይ የሰው እንጀራ ይበሉ የለም? በሰው ወርቅ እየደመቁ ትልቅ ሰው ይባሉ የለም? በሸሸኋቸው? ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም በቅጠልም እንጂ ባልኩ? ርስቴን፣ ድርሻዬን፣ ላቤን ስነጠቅ ይሁን ባልኩ? ለነገሩ ወትሮም ፈንገስ፣ ፈንገስ ነው፤” ብላ ስታበቃ ፌስታልዋን አንስታ እንደ ቡና ቁርስ ከጫቱ ካልዘገናችሁለት ትለን ጀመር። አይ መንገድና መገናኛው!

 እልፍ ብሎ ከጎዳና በቆሎ ጠባሾች የማንደጃቸውን እሳት ያራግባሉ። እሳት ያጣው ቅዝቃዜና ትርጉም ያጣ ሕይወት አሰላችቶት ከእግር አጣጣሉ ጀምሮ ቸልታ ይቀዳበታል። ስስ ካፊያ ምድርን ለመሰናበት ጥቂት ሰዓታት በቀራት ፀሐይ ታጅቦ ከመሬት ይወርዳል። ቀስ በቀስ የሞላናት ታክሲያችን መጓዝ መጀመሯ ነው። ከታዳጊ ልጇ ጋር የተሳፋረች ደርባባ ወይዘሮ ወደ ልጇ ዞር ብላ፣ “እንዲህ ፀሐይ ወጥቶ ዝናብ ሲዘንብ ምን ሲሆን ነው ብዬህ ነበር?” ብላ ስትጠይቀው እንሰማለን። “ጅብ ሲወልድ!” ይመልሳል ያጠናውን ተረት። ትንሽ ቆይቶ ግን ልጁ ለእናቱ ያቀረበው ጥያቄ ሁሉንም ተሳፋሪ ያስደነገጠ ነበር። “ማሚ? ግን የትኛው ጅብ ነው?” ሲል እናት፣ “ስንት ዓይነት ጅብ አለ ደግሞ?” ትመልሳለች። “ሁለት ነዋ! የሰውና የእንስሳ፤” ብሎ እርፍ። “ጉድ ፈላ! ኧረ ጎበዝ የአሉባልተኞች ሐሜት ሕፃናት ከማይደርሱበት ቦታ ይዘውተር፤” ይላል መሀል ወንበር ላይ ተቀምጦ አንድ ጎልማሳ። ሳቅ ያማረው ፈገግ ይላል። ወያላው ሙሉ ለሙሉ ተንሸራታቹን መዝጊያ ዘግቶ ታክሲያችን ስትፈተለክ፣ የነገው አገር ተረካቢ ዜጋ ተቀብሎ የሚገነባት ኢትዮጵያ በእዘነ ልቦናችን ውልብ ትላለች። ተስፋ አይሞትምና!

ወያላው ሒሳብ እየተቀበለ ነው። “ሕማማት ስለሆነ እጅ ለእጅ መነካካት ክልክል ነው፤” ይለናል። ተሳፋሪው ‘አልቀረብህም’ ዓይነት ያሽሟጥጠዋል። “ምናለበት ሁሉ እንዳንተ ሥራውን አክባሪ ቢሆን?” ትለዋለች አንዲት ወጣት። ቀና ብሎ እያያት ይስቃል። “እውነት ለመናገር እኮ የድህነታችንን ያህል አይደለም ሥራ ላይ ያለን ትጋት፤” ትላለች አስከትላ። “ታዲያስ!” ይቀበላል ከወዲያ፣ “ከአስተናጋጅ እስከ ሚኒስትር ድረስ እኮ ጥቂት ሠርቶ ብዙ ማረፍ የሚታየው ነው የተጠራቀመው። በመሠረቱ ያለጠንካራ የሥራ ባህል ልማትና ለውጥ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል አይገባኝም፤” እያለ ጎልማሳው። ከኋላ መቀመጫ ረድፍ ደግሞ ተሳፋሪው እርስ በእርሱ እንዲህ ይባላል። አንደኛው፣ “እኔን እኮ የማይገባኝ ያላደገብንን የሥራ ባህል በመርህና በፉከራ በአንድ ሌሊት ሊያሸክሙን ሲጥሩ ነው፤” ይላል።

አንደኛዋ ደግሞ፣ “ዝም በላቸውማ የስንቱን አገር ልምድና ተሞክሮ ሲያበጥሩ ምነው ሮም በአንድ ቀን እንዳልበቀለች ሳያዩት ቀሩ?” ስትል ይሰማል። “ወትሮም መሠረት ያለው አካሄድና ዕድገት ሲለምድብን እኮ ነው። መንግሥትስ ቢሆን ያው የዚህ ኅብረተሰብ ወኪል አይደል? ከፈረሱ ጋሪው ቢቀድምበት ያው የእኛንም ባህሪ ማንፀባረቁ እኮ ነው፤” ይላል ሦስተኛው ሰው። “ለማንኛውም የፀረ ሽብር ሕግ ቃል በቃል እንደሚተረጎምልን ሁሉ፣ ጠንካራ የሥራና የትጋት መንፈስ ባለቤት መሆን የምንችልበት ተሞክሮ ጭምር ቢያጠናልን ጥሩ ነበር፤” ስትል የመጨረሻዋ ከአገር ፖለቲካ የቀደመበት ዘመን መሆኑን ያወቀች አትመስልም። ከፖለቲካም ደግሞ ቀጣና ተኮር ፖለቲካ ነዋ!  

ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ነው። “ውይ! ኧረ አገር ስጡኝ ተው?! የት ሄጄ ልፈንዳ በፈጠራችሁ?” ይወራጫል። “ኧረ ቀስ! በተረጋጋ ቀጣና ውስጥ ምንድነው እንደዚህ ማተራመስ?” ወይዘሮዋ ናት። “ምንድነው የሚለው? የት አለና ነው እንቆቅልሹ አገር ስጡኝ የሚለን?” ከኋላዬ ከተደረደሩት አንዲት የቀይ ዳማ። “አይ! እንቆቅልሹንስ ተይው። እንዲያውስ ለእንቆቅልሾቻችን የሚበቃ አገር አለ እንዴ?” ሥጋ ባዳው አጉል ሰብቶበት፣ በከፊል ደመናማ የአየር ፀባይ ላብ የሚያጠምቀው ህያው ገፀ ባህሪ ከጎኗ ያሸሙራል። ተልባ ቢንጫጫ ባንድ ሙቀጫ ተብሏል። ምን እንቆቅልሾቻችን ቢበዙ በመልካም አስተዳደር ችግር ተጠቃለውና ዕውቅና ተሰጧቸው ተቀምጠናል። ከዚህ በላይ ምን ይምጣ?” ሲል ጋቢና መሀል ላይ የተቀመጠ ወጣት ዞሮ ታክሲያችን በምትሃት ወደ ክብ ጠረጴዛነት የተቀየረች መሰለች።

“ዓይኔ ነው ጆሮዬ?” ትላለች ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠችው ተደናግራ። “ምን የሆንነው?” ጎልማሳው መወራጨቱን ቀነስ አድርጎ ሲጠይቃት፣ “በአንዴ እንቆቅልሹን በፖለቲካ ፈቶ ያሳየኝ ወይ ያሰማኝ ነዋ?” ስትለው ጆከኛው ጎልማሳ “የለም የለም! የአላዲንና የፋኖሱ ነገር ነው። ሳናስበው ዴሞክራት ስናስበው ደግሞ አውቶክራትና ታይራንት የሚያደርገን፣ የአላዲንና የፋኖሱ ጂኒ ነው፤” ይላታል። ‹‹‘ዳዲ’ ጂኒ ምንድነው?›› ሲል ደግሞ ብላቴናው በከረሜላ ጥርሶቹን መጨረስ በሚገባው ዕድሜ ጌሙ ላይ እንዳፈጠጠ ዓይኑን ከስልኩ ባትሪ እኩል እያዳከመ ይጠይቃል። ወጋ ወጋ፣ ጠቅ ጠቁ፣ ጂኒ ጂኒ ቁልቋል ወሬ ቢመስልም ሰውን ግን ያስተነፍሰዋል። ታክሲ ሳንባን የመተካት አቅም እንዳለው ሳይንስ ደርሶበት ይሆን?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ ማለት እኮ ቀረ እናንተ፤” ይላሉ ሻሽ አስረው ነጠላ ያዘቀዘቁ ወይዘሮ። “ምን ያደርጉታል? ሞትና ትንሳዔያችን እኮ በየቀኑ ሆነ፤” ይላቸዋል ከጎናቸው። “ምነው ግን እንዲህ መጨካከን በዛ እናንተ?” ብለው ሲጠይቁ ደግሞ፣ “ምኑን አውቀነው? ፈርዶብን በተስፋ ቀንበር ታስረን ውለን ስንገባ ፈራሽ መሆናችን ትዝ አልለን ብሏል፤” ይላቸዋል ጎልማሳው። ከወደ መጨረሻ ወንበር ደግሞ፣ “ከሁሉ ከሁሉ እኔን የሚገርመኝ የመርሳት ጥበባችን ነው፤” ትላለች። “እንዴት?” ሲላት አንዱ፣ “በቃ ጉድ አንድ ሰሞን ነው እንደሚባለው። አታይም እንዴ ቆሻሻ ተጭኖን ስናልቅ እግዚኦ እንልና ገና ዕንባችን ሳይደርቅ ሳቃችን ያመልጠናል። ሰማይ ጨከነ ተብሎ ድርቅ ሲያደርቀን ከርመን ደግሞ ጎርፍ ሲጫወትብን ታያለህ። የሰማይና የምድር ቅኔን ተትተህ ደግሞ በዚህ በኩል አሠሪና ሠራተኛ አባትና ልጅ፣ መንግሥትና ሕዝብ ሲጨካከኑ ትስቅ ወይም ታዝን መላው ይጠፋኃል። ያለህ አማረጭ ታርዶ ነፍሱ እንዳልወጣች በግ ግፍህን እንደ ደም እያዘራህ በደመነፍስ መኖር ሆነ። ለዚህ ነው እኮ ለችግሮቻችን መፍትሔ መፈለጉን ትተን ችግሮቻችንን እንኳ በቅጡ መረዳት ያቃተን። መልመድ የምልህ ይኼን ነው፤” ስትለው መልስ አልመለሰላትም። ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ስትቆም ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። “ቸር ወሬ ያሳማችሁ” ብለው ወይዘሮዋ ቀድመውን ሲወርዱ ተሳፋሪው ‘አሜን’ ይላል። የትንሳዔና ሞት ቅደም ተከተል ለተዛባበት ለምርቃቱም ለእርግማኑም አሜን ቢል ይገርማል? እስቲ አንነካካ! መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት