«እመኑኝ በዚህ የሰቆቃ ወቅት ጽኑ ሕመምና ግራ መጋባት እየተሰማን ነው። ከእኛ ጋር በአንድ አገር የሚኖሩ፣ ፍቅርንና ጓደኝነትን የተጋራናቸውና ጠንቅቀን የምናውቃቸው እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ይፈፅሙብናል ብለን ፈጽሞ አልጠበቅንም፡፡»
በታንታ ከተማ የሚገኘው የኮፕት ኦርቶዶክስ ማር ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ካህን አባ ተውፊቅ ኮቤይሽ የተናገሩት፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ኢየሩሳሌም የገባበት መታሰቢያ የሆሳዕና (የዘንባባ እሑድ) በዓል፣ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. (በኮፕቲክ ካሌንደር በርሙዳህ 1 ቀን 1733 ዓመተ ሰማዕታት) በግብፅ ሲከበር ‹‹እስላማዊ መንግሥት›› በመባል የሚታወቀው ድርጅት ታንታና እስክንድርያ ከተሞች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ላይ በጣለው አደጋ 44 ንፁሃን ሲገደሉ 126 ቆስለዋል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸው በማግስቱ ሲፈጸም የሰለባው ቤተዘመዶች የመንግሥት ፀጥታ አካላት አስቀድመው ጥበቃና ከለላ አለማድረጋቸውን ተችተዋል፡፡ አሁን የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታላቁ በዓል ከመድረሱ በፊት መታወጅ ይገባው ነበር ሲሉም መሰማታቸው የዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡