Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርኢኮኖሚያዊ ኮማንድ ፖስት ያስፈልገን ይሆን?

ኢኮኖሚያዊ ኮማንድ ፖስት ያስፈልገን ይሆን?

ቀን:

  በእስክንድር ከበደ

ዩናይትድ ስቴት እ.ኤ.አ. በኦገስት 1929 ታላቅ የኢኮኖሚ ቀውስ (Great Depression) ውስጥ የገባችበት ዘመን ነበር፡፡ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ድቀት ተከትሎ ከፍተኛ የሥራ አጥነት፣ የከፋ ድህነት፣ የግብርና ምርት ገቢ መቀነስና ኢኮኖሚው ማንሰራራት በማይችልበት ማጥ ውስጥ በመግባቱ ሳቢያ በኢኮኖሚው ላይ ተስፋ መቁረጥ ፈጠሩ፡፡ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ድቀት ለሦስት ዓመት በመዝለቁ ፕሬዚዳንት ሀርበርት ሁቮር ቀውሱን ለመዋጋት አምብዛም አልሠሩም ተብለው ብርቱ ወቀሳ አጋጠማቸው፡፡ ቀውሱን ተከትሎ የተወሰኑ ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡  በርካታ የአሜሪካ ዜጎች ወደ ካናዳ፣ አውስትራሊያና ደቡብ አሜሪካ እስከ መሰደድ አደረሳቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1932 በተካሄደው ምርጫ “Roosevelt’s Economic Recovery Plan” (የሩዝቬልት የኢኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅድ) መነሻ ፍራንክሊን ዲላኖ ሩዝቬልት ቀዳሚውን ፕሬዚዳንት ሀርበርትን በከፍተኛ ድምፅ አሸነፉ፡፡

የሩዝቬልት ኢኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅድን “New Deal” የታሪክ ሙህራን “3Rs” “Relief” (ዕገዛ/ዕርዳታ) “Recovery” (ማገገም) እና “Reform” (ተሃድሶ) በማለት ይጠሩታል፡፡ “Relief” (ዕገዛ/ዕርዳታ) ለሥራ አጦች ዕርዳታ ማድረግ፣ “Recovery” (ማገገም) ኢኮኖሚው አገግሞ ወደ ጤናማ ደረጃ እንዲደርስ ማድረግንና “Reform” (ተሃድሶ/ማሻሻያ) በፋይናንስ ሥርዓቱ ተሃድሶ በማካሄድ ዳግም ወደ ቀውስ እንዳይገባ የሚያደርግ ዕቅድ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

- Advertisement -

“ኒው ዲል” ፖለቲካዊ ማስተካከያ በመፍጠር የዴሞክራቲክ ፓርቲ ከዘጠኝ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ሰባቱን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች (እ.ኤ.እ 1933 እስከ 1969) እንዲያሸንፍ አግዞት ነበር፡፡ ይኼ ማሻሻያ ፕሮግራም ሪፐብሊካኖች እንዲከፈሉ ያደረገ ሲሆን፣ ወግ አጥባቂዎቹ ‹ፕሮግራሙ የቢዝነስ ጠላት ነው› በማለት ተቃውመውት ነበር፡፡

በኒው ዲል ፕሮግራም “Work Projects Administration” (WPA) ፕሮግራሙን ለማስፈጸም ከተቋቋሙት ኤጀንሲዎች መካከል ግዙፉ ኤጀንሲ ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራ አጦችን (በአብዛኛው ያልሠለጠነውን የሰው ኃይል) እንዲቀጥር በማድረጉ ይጠቀሳል፡፡ ኤጀንሲው ሥራ አጦቹ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ሥራዎች ግንባታዎች እንዲሳተፉ በመቅጠር፣ የመንገድ ግንባታዎችና የሕዝብ መጠቀሚያ መሠረተ ልማቶችን በመጠነኛ ወጪዎች በመገንባት ተጠቃሽ ፕሮጅክቶችን እንዲሠሩ አድርጎ ነበር፡፡ በዚሁ ኤጀንሲ ሥር የነበረው “Federal Project Number One” ሙዚቀኞች፣ አርቲስቶች፣ ጸሐፍት፣ ተዋንያንና ዳይሬክተሮችን በታላላቅ የጥበብ፣ የድራማ፣ የሚዲያና የማስተማር ሥራዎች እንዲሳተፉ አድርጎ ነበር፡፡

ብሔራዊ የወጣቶች አስተዳደር (National Youth Administration) በኒው ዲል ፕሮግራም እ.ኤ.አ. ጁን 6 ቀን 1935 እስከ 1939 ዓ.ም “Work Progress Administration” (WPA) የሥራ ፈጠራ ማሻሻያ አስተዳደር መሥሪያ ቤት ሥር የተቋቋመ ሲሆን፣ ከ16 እስከ 25 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ደሃ የኮሌጅ ወጣቶችን በሥራና በትምህርት ፕሮግራሞች በማሳተፍ ይታወቃል፡፡

የኒው ዲል ፕሮግራም በሥራ ፈጠራና ሥራ አጥ ዜጎችን ሥራ የማስያዝ ሥራዎች በጀት ከመመደብ ጀምሮ ሕግ በመደንገግና ተቋሞችን በመፍጠር፣ ኢኮኖሚውን አነቃቅቶ አገሪቱን ከኢኮኖሚ ድቀት አውጥቷል፡፡ በፕሮግራሙ መነሻ የተቋቋመው “WPA” የፌደራል ሥራ ፈጠራ ማሻሻያ አስተዳደር በሥሩ በመላ አገሪቱ የሚተገበሩ የፕሮጅክት ኤጀንሲዎች (አወቃቀሮችን) ፈጥሯል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በተለያዩ በገጠርና በከተማ ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ መንገዶች፣ መኖሪያ ቤቶችና የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማት ግንባታዎች በመጠነኛ ወጪ ዝነኛና ተጠቃሽ ፕሮጅክቶችን እንዲያከናውኑ እንዳደረገ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት በድሬዳዋ ከተማ ከፍተኛ ቀጣሪ ድርጅቶች የነበሩት ጨርቃ ጨርቅ፣ ባቡር፣ ዱቄት ፋብሪካ፣ ፓስታ ፋብሪካ፣ ቻንድሪስ (የወታደር ምግብ ኮቸሮና በጣሳ የታሸጉ ምግቦች አምራች) ፋብሪካ፣ እንዲሁም የሲሚንቶ ፋብሪካ እንደነበሩ ትዝ ይሉኛል፡፡ ጨርቃ ጨርቆቹ ጥራት ቢኖራቸውም በቱርክና በሌሎች አገሮች መለያ ስም ‹‹Brand›› ስለሚሸጡ አገራችን ማግኘት የሚገባትን ሁሉ አግኝታ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ‹‹የድሬዳዋ ቆንጆ›› ምሥል የተለጠፈባቸው አቡጀዲ፣ ካኪ፣ ቦብሊንና ልዩ ልዩ ጨርቃ ጨርቆች ያመርት ነበር፡፡ አስናቀች የተባለች የፋብሪካው ሠራተኛ ባገኘችው ‹በፈጠረችው› የጨርቅ ዓይነት የተሰየመ ‹አስናቀች› በሚል ስያሜ ይጠራ የነበረ ምርት ነበረው፡፡ ደርግ የወታደር ልብሶችን በዚህ ፋብሪካ ያስመርት ነበር፡፡ የቻንደሪስ ፋብሪካ የግብርና ማቀነባበሪያ፣ የቆርቆሮ፣ በጣሳ የታሸጉ ምግቦችንና ደረቅ ቡስኩቶች በማምረት የሚታወቅ ነበር፡፡

በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ በእነዚህ ፋብሪካዎች ውስጥ ያልተቀጠረ አንድ ሰው ወይም ዘመዱ አይጠፋም፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም በላይ፣ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት ብርቱ ዕገዛ ነበራቸው፡፡ በዘመኑ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካና የኢትዮ – ጁቡቲ ባቡር ድርጅት እግር ኳስ ክለቦች ዛሬ በአዲስ አበባ ቅዱስ ጊዮርጊስና ቡና ሲጫወቱ እንደሚታየው የክለቦቹና የደጋፊዎቹ ፉክክር ከፍተኛ ነበር፡፡ የሁለቱ ድርጅቶች ቡድኖች ድጋፍ ምንጭና ከጨዋታ ክህሎታቸው በላይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን መገመት አይከብድም፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካውን ሰርቪሶች ብዛትና የምልልስ መጠን ለተመለከተ የከተማውን አብዛኛውን ሕዝብ የሚነካ ተፅዕኖ እንደነበረው መገንዘብ አያዳግትም፡፡ የባቡር ድርጅቱ ደግሞ አገራችን ከጂቡቲ ጋር የንግድ ትስስሩን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከማቀላጠፉ በላይ፣ ከከተማዋ አልፎ አካበቢውን በማነቃቃት ብርቱ ዕገዛ ነበረው ማለት ይቻላል።

በአንድ ወቅት መንግሥት ከባለሀብቶች ጋር ባደረገው ውይይት በአዲስ አበባ የሚካሄዱ የሕንፃ ግንባታዎች ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆኑት ፋብሪካ ቢሆኑ ኢኮኖሚው አሁን ካለበት በላይ ይበልጥ ምን ያህል ያሳድገው እንደነበር በመጥቀስ፣ አገሪቱ የምትሰበስበው ውስን የቀረጥ ገቢ በአገሪቱ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ውስን ሚና እንዳለውና መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ዘርፎች ላይ መተኮር እንዳለበት ተነጋግረው ነበር፡፡

የደቡብ አፍሪካ አገር አቀፍ የወጣቶች ልማት ኤጀንሲ የደቡብ አፍሪካ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶችና መሰናክሎች ወጥ በሆነ መንገድ የሚፈታ ተቋም ሆኖ እንዲሠራ፣ በአገሪቱ ፓርላማ እ.ኤ.አ. በ2008 በአዋጅ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ በደቡብ አፍሪካ አንድ አሃዳዊ መዋቅር ሆኖ የአገሪቱን ወጣቶች ችግሮች በአገር አቀፍ፣ በክፍለ አገርና በአካባቢያዊ መንግሥት አስተዳደር ደረጃ የሚፈታ እንዲሆን ተደርጎ መዋቀሩ ይነገራል፡፡ የደቡብ አፍሪካ አጠቃላይ የዕድገት ዓውድ ውስጥ የሚያጠነጥን ተልዕኮ ተሰጥቶታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ እንደ ማንኛውም ታዳጊ አገር ከ14 እስከ 35 ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች ከጠቅላላው ሕዝብ 42 በመቶ ይሆናሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ የሚያጋጥሙት ማኅበረ ኢኮኖሚ ችግሮች ማለትም ድህነት፣ ኢእኩልነት፣ ሥራ አጥነት፣ የጤና ችግሮች፣ ወዘተ በወጣቶች ላይ ሸክሙ ይበዛል፡፡

ኤጀንሲው የመሪነት ሚናውን የሚጫወት በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና ሲቪል ማኅበረሰቡ የሚያካሂዷቸው ፕሮግራሞች የወጣቶችን ሕይወት የሚያሻሽሉና የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር እንዲሠሩ ይመራል፡፡ ኤጀንሲው በመላ አገሪቱ የሚተገበሩ ዘጠኝ ግዙፍ ፕሮግራሞችና ሰባት አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡ የአገር አቀፍ የወጣቶች ሽልማቶችና የነፃ ትምህርት ዕድል በመስጠት ይታወቃል፡፡ የወጣቶች ክፍት ሥራዎችን ጨምሮ የሥልጠናና የምክር ድጋፎች የቢዝነስ ሙያዊ ክህሎት ማሳደጊያ ፕሮግራሞቹ ይጠቀሳሉ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራሉ መንግሥት በተሰጠው የሥልጣን ክልል ሕጎችን እንደሚያወጣ ተደንግጓል፡፡ በምክር ቤቱ ሥልጣንና ተግባር መሠረት የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት፣ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ወይም ከአንድ ክልል በላይ የሚያስተሳስሩ ወንዞችና ሐይቆች አጠቃቀም ሕግ እንደሚያወጣ ይጠቅሳል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 ንዑስ ሦስትና አራት ላይ እንደተጠቀሰው፣ ምክር ቤቱ የሠራተኛ ጉዳይ ሕግና የንግድ ሕግ (ኮድ) እንደሚያወጣ ይደነግጋል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን የሠራተኛና የንግድ ሕጎች ብቻ በመጥቀስ የሚታለፍ አይሆንም፡፡

ለወጣቶች የተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ በተመለከተ የገንዘቡን ክትትል ከባንክ ጋር መተሳሰሩ አንድ ነገር ቢሆንም፣ ፕሮግራሙን የሚመራ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ተደራሽ በመሆን የሚመራ፣ የሚያስተባበር፣ አቅም የሚገነባና ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጥ ጠንካራ አደረጃጀትና አሠራር መፍጠር ይጠይቃል፡፡ ከተመደበው የተወሰነ በመቶ ለዚህ ተቋም መመደብና በቀጣይም ተቋሙ አገር አቀፍ የወጣቶች ፈንድ (National Youth Fund) እንዲኖር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የግል ባለሀብቱ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚደግፉና በርካታ የፖሊሲና የምርምር ሥራዎች ሊተገብር ይችላል፡፡

አንዱ ክልል ይህን ያህል መሬት ለወጣቶች ሰጥቻለሁ፣ ሌላው ክልል የማዕድን ሥፍራዎችን አከፋፍያለሁ፣ አንዱ ደግሞ በዘመቻ ዞሮ ጥቅም ላይ ያልዋሉ የወጣቶች ሼዶች ነጥቄ ለሌሎች ወጣቶች እሰጣለሁ፣ ወዘተ በማለት በመገናኛ ብዙኃን የሚገለጽበት መንገድ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥትና ፖሊሲዎች ጋር ምን ያህል በጥንቃቄ ተጣጥሟል ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ መሬትና የተፈጥሮ ሀብቶች ለአንድ ክልል ብቻ የተሰጡ ሀብቶች ናቸው ብሎ ማሰብ አልፎ አልፎ ይታያል፡፡ በአገሪቱ በአንዱ ጥግ ያሉ ኦፓል፣ ወርቅ፣ ፖታሽ ወይም ማንኛውም ማዕድን በአንድ የተወሰነ ክልል ብቻ የሚታጠር ሳይሆን የአገሪቱ ሕዝቦች ሀብቶች ናቸው፡፡ አጠቃቀማችን ጊዚያዊ መፍትሔ በሚሰጥ ሳይሆን ለአገሪቱ አጠቃላይ ዕድገት በሚያመጣ ሁኔታ መሆን ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዳችን የተፈጥሮ ሀብቶችን ጥበቃ ኃላፊነት ያለብን ለዛሬው ብቻ ሳይሆን፣ ለመጪው ትውልድ ጠብቀን የምናቆይለት ጭምር ስለሆነ ነው፡፡

በአገራችን የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ብዙ ይነገራል፡፡ እንዴት? የሚለው ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ መንግሥት በቅርቡ አሥር ቢሊዮን ብር ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ መመደቡን አስታውቋል፡፡ በጣም ጠቃሚ ዕርምጃ ነው፡፡ ገንዘብ መመደቡ አንድ ነገር ሆኖ ይህንን ገንዘብ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ በሚጠቅም መንገድ መምራት ይጠይቃል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራው ብድር በመስጠት ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ ይኼንን ተዘዋዋሪ ፈንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ከመመርያ በላይ የሕግ ማዕቀፍና ተቋማዊ አደረጃጀትን ፈጥሮ ፈንዱን ማስተዳደር የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ሁሉም እየተደራጀ ሥራ ፈጥሮ ይምጣ ብሎ መተው ችግሩን በዘላቂት የሚፈታ አይሆንም፡፡ በወረቀት ላይ ጥሩ ፕሮጀክት ሊመጣ ይችላል፡፡

ጉዳዩ የፈጠራ ውድድር ተደርጎ የሚታይ ሳይሆን፣ ከዚህ ገንዘብ መንግሥት የሥራ መፍጠሪያ ተቋማትን እስከ መመሥረት የሚዘልቅ ጠንካራ ጣልቃ ገብነትም ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ለባንክ ብቻ የሚተው ከሆነ በየአምስት ዓመቱ ብድሩን ያልከፈሉትን ‹ሥራ ፈጣሪዎች› ማሽነሪ ወይም መገልገያ መሣሪያዎች በሃራጅ የሚሸጥበት አካሄድን መመርመር ይጠይቃል፡፡ ገንዘብ አቅራቢው መኖሩ መልካም ቢሆንም፣ ከፍተኛ ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጥ መንግሥታዊ ተቋም መፍጠርም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ አገር አቀፍ የሥራ ፈጠራ ማሻሻያ አስተዳደር ኤጀንሲ/ባለሥልጣን መመሥረት እስከ ክልሎች የሚዘልቅ ቅርንጫፍ ኖሮት እንዲዋቀር ማደረግ ሊጠይቅ ይችላል፡፡

ይኼ አገር አቀፍ ፕሮጀክት መሆን ይኖርበታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኀበረሰብ የመፍጠር ሥራ አካል በመሆኑ፣ ይህ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የተመደበው ‹ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ› ከሆነ ወጣትነት መነሻው ዕድሜ መሆኑ ግድ ነው፡፡ የአገሪቱ ፖሊሲ ለወጣትነት በሚሰጠው ብያኔ መነሻ መሆኑን ማረጋገጥ ሊጠይቅ ይችላል፡፡

በተለያዩ አገሮች ወጣቶች ዕድሜ ገደብ ይለያያል፡፡ ኡጋንዳ ከ12 እስከ 30፣ ደቡብ አፍሪካ ከ14 እስከ 28፣ ህንድ ከ15 እስከ 35፣ ናይጄሪያ ከ18 እስከ 35፣ ጂቡቲ ከ16 እስከ 30 ዕድሜ ያላቸውን በወጣትነት ይመድባሉ፡፡ በአገራችን እ.ኤ.አ. በ2004 የወጣው ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ወጣት ብሎ የሚመድበው ከ15 እስከ 29 ያሉትን ነው፡፡ ስለዚህ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ የተመደበው አሥር ቢሊዮን ብር የሚመለከተው ‹‹ሥራ አጥ›› ሁሉ ሳይሆን ከ15 እስከ 29 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን መሆናቸው ምን ያህል እየታየ ነው? ሥራ አጥነቱ ከወጣትነት ዕድሜም የሚያልፍ የበርካታ ዜጎች ጥያቄም ያለበት በመሆኑ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያካትት ፕሮግራም ያስፈልጋል፡፡ በቅርቡ በህንድ የገጠር ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል፣ ቢያንስ አንድ አርሶ አደር በዓመት 100 ቀናት በሥራ እንዲያሳልፍ የሚያስችለውን የአገሪቱ ፓርላማ አፅድቋል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በሚባል መጠሪያ ሁለት ግዙፍ ሥራዎችን በሚከታተል መሥሪያ ቤትና በመሰል የክልል ቢሮዎች ጉዳዩን ማስቀጠል ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የተመደበው ገንዘብ ለታለመለት ሥራ እንዲውል ሁሉም መረባረብ አለበት› በሚል የተለመደ ማሳሰቢያ ብዙ መዝለቅ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

በፌዴራልና በክልሎች የሚሰጡ በተለያዩ መግለጫዎች ጉዳዩን እየተሠራ መሆኑን ከመግለጽ ይልቅ ተጨማሪ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ አንድ ፕሮጀክት ደግሞ ተጀምሮ የሚጠናቀቅበት ጊዜ አለው፡፡ ወጣቶቹ በሚኖሩበት ክልል ብቻ ማደራጀት ሳይሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች በጋራ የሚያሳትፉ ፕሮጀክቶች የመምጣታቸው አማራጮች ዝግ አይሆንም፡፡ የአንደኛው ክልል ወጣቶች ያመረቱትን ወተት፣ ፍራፍሬ፣ ሥጋና ልዩ ልዩ ምርቶች ተቀብሎ የሚያከፋፍሉ የጎረቤት ወይም የሌላ ክልል አካባቢ ወጣቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

በመገናኛ ብዙኃን የተደራጁ ወጣቶች የመሥሪያና የመሸጫ ቦታዎችን በተደጋገሚ ያነሳሉ፡፡ ፈጠራ ሲባል በአንድ ወቅት በመካከለኛ ደረጃ በቴክኒክና ሙያ ከሚሰጡ 28 የሙያ ዘርፎች ሌላ የተለዩ ነገሮች እምብዛም ላይኖሩ ይችላሉ፡፡ በየክልሉ ለአነስተኛና መካከለኛ የማምረቻ ኢንተርፕራይዞች የሚጠቀሙባቸው በርካታ ፓርኮች መፍጠር፣ ወጣቶቹ በቀላሉ ወደ ማምረት እንዲገቡ ያግዛቸዋል፡፡ ሰፋፊ የመሸጫ ቦታዎችን አጥንቶ ማመቻቸት ሊጠይቅም ይችላል፡፡

በየከተማው የሚፈጠሩ የግብርና ምርቶችን ውድነት ለመቀነስ የከተማ ግብርና የሚሠራባቸውን ምቹ አካባቢዎች መርጦ የሚያመቻች ተጠያቂ አካል መፍጠር ሊጠይቅ ይችላል፡፡

እንደ አሜሪካ ልዩ ተቋማት አስፈላጊውን በማጥናት መተግበር ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ሆኖም በሁሉም ክልሎች ተደራሽ የሆነ አንድ አገር አቀፍ ግዙፍ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ይኼ በምንም ምክንያት በየክልሎችን ሥልጣን መጋፋት ወይም በክልል ሥራ ጣልቃ ከመግባት ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ ‹አገር አቀፍ የወጣቶች ሥራ ዕድል አስተዳደር› ወይም ሌላ ግብሩን የሚገልጽ ግዙፍ ተቋም ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ሥራ ከተመደበው ገንዘብ እንደ አንድ ፕሮጀክት ከ15 እስከ 30 በመቶ አስተዳደራዊ ወጪውን ሸፍኖ የሚሠራበት አማራጭ መፍጠሩ አግባብ ይመስለኛል፡፡ ይኼ ተቋም በአጠቃላይ ሚኒስትሩና የክልል ፕሬዚዳንቶች በሚመሩት አንድ ከፍተኛ አካል ቢመራ ብዙ ለውጥ ሊመጣበት ይችላል፡፡

በአገሪቱ አሉ የሚባሉ የሥራ ፈጠራ መሪዎችና ባለሙያዎች ያሉትን አዋጭ ፕሮጅክቶችና ፕሮፋይሎች ለወጣቶቹ የሚያቀርብ፣ አዋጭ የፈጠራ ሥራዎችን መምረጥ የሚችልና ሥራ ፈጣሪዎችን ማብቃት የሚችል የሕግ፣ የአሠራርና የተቋማዊ ቁመና መፍጠሩን መንግሥት አብዝቶ ሊያስብበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡

ልክ እንደ ፖለቲካው ዘርፍ በኢኮኖሚ ዘርፉም አንድ የኢኮኖሚ ማኀበረሰብ ለመፍጠር አንድ ወጥ አገር አቀፍ የወጣቶች ልማት ተቋም ሆኖ፣ በሁሉም ክልሎች ተመጣጣኝ አቅም ያለው ተደራሽ ዘመናዊ አደረጃጀት መፍጠር የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት የኢኮኖሚ ኮማንድ ፖስት ያስፈልገን ይሆን . . . ?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...