Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርስለ ዳያስፖራ ቤት ገዥዎች የቀረበው ዘገባ ተጋኗል

ስለ ዳያስፖራ ቤት ገዥዎች የቀረበው ዘገባ ተጋኗል

ቀን:

ሚያዚያ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. (ቅጽ 22 ቁጥር 1769 የረቡዕ ዕትም) በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ገጽ 8 ላይ ከ40 በላይ የሆኑ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ዳያስፖራ ቤት ገዢዎች ከ50 በመቶ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ የቅድሚያ ክፍያ ከ120,000.000 (አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ብር) በላይ ከፍለው ቢያጠናቅቁም፣ ሪል ስቴቱ ቤታቸውን ሊሰጣቸው አልቻለም በሚል ሐተታ ያወጣችሁት ዘገባ ላይ ያደረብንን ቅሬታ መነሻ በማድረግ የሚከተለው ጽሑፍ ለመላክ ተገደናል፡፡

በቅድሚያ ዘገባው ‹‹ዳያስፖራ ቤት ገዢዎች…›› የሚል የተጋነነ ይዘት ያለው ርዕስ ይዞ መቅረቡ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ከ40 በላይ ዳያስፖራውያን የተባለውም እውነት አይደለም፡፡ በእኛ ዕምነት ዘገባው ትኩረት ያገኛል በሚል እሳቤ የተቀመጠ የቃል አጠቃቀም ነው፡፡ ሪል ስቴታችን የተለየ፣ ዳያስፖራ ቤት ገዢዎችን ማዕከል ያደረገ የቤት ሽያጭ አላከናወነም፡፡ ከውጭ አገርም የተሰበሰበ ገንዘብ የለም፡፡ በውጭ ምንዛሪ የተሰበሰበ ገንዘብም፣ የተሰበሰበ ክፍያም የለም፡፡ ሪል ስቴታችን ባለው መረጃም ቤት ገዢዎቻችን የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ 40ም ሆነ ከ40 በላይ ዳያስፖራ ቤት ገዢዎችን አቅረቡልን ብትባሉ ልታቀርቡልን አትችሉም፡፡ በግንባታው ሳይት ከዘጋቢው ጋር ያገኘናቸው ቤት ገዢዎች ቁጥርም በጣም የተወሰኑ፣ ሰባት ያህል ሰዎች ስለነበሩ፣ ሁሉንም ቤት ገዢዎች ያካተተ በሚመስል መልኩ የገለጻችሁት ትክክል አይደለም፡፡ ሁሉም ቤት ገዥዎቻችን ላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አለያም ዳያስፖራ በማለት ልዩነት ሳናደርግ በአክብሮት የምንቀበላቸው ደንበኞቻችን ናቸው፡፡ የአንድም ደንበኛ ቅሬታ ቢሆን በበጎ ጎኑ የምንቀበለው ነው፡፡ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ግምት ውስጥ ሳታሰገቡ የተሳሳተና የተጋነነ ዘገባ ማውጣታችሁ ግን አሳዝኖናል፡፡

የቤት ገዢዎችንም ቁጥር በተመለከተ ከ80 በላይ ቤት ገዢዎች ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ፈጽመዋል የሚለው ዘገባችሁም ግንባታቸው ተጠናቅቆ ርክክብ በተደረገባቸውም ሆነ አሁን በመገንባት ላይ ባሉት አፓርታማ ቤቶች ተጠቃሎ 80 ቤት ገዢ የለንም፡፡ ተጠናቆ ርክክብ በተፈፀመበትና አሁን በግንባታ ላይ የሚገኘው ሕንፃ ላይ ያሉት ቤት ገዢዎች 60 ናቸው፡፡ እነዚህም የአንደኛው ብሎክ ቤት ገዢዎች የስም ዝውውር የተፈጸመላቸውና ቤታቸውን የተረከቡ ስለሆነ በሌሉበት ከዚህ ዘገባ ጋር መቀላቀላችሁ ተገቢ አልነበረም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ርክክብ በተፈጸመባቸውም ሆነ አሁን በመሠራት ላይ ካሉት የአፓርታማ ቤቶች ሽያጭ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል የተባለው የመረጃችሁ ምንጭ ምን እንደሆነ ባናውቅም ጨርሶ ሐሰት ነው፡፡ የተሰበሰበውን ገንዘብ በተመለከተ ከዚህ በፊት ከቤት ገዥዎች ጋር በተደረገ ውይይት ጥያቄ ተነስቶ ጠቅላላ የተሰበሰበው ገንዘብና ሥራውን ባቋረጠው ተቋራጭ የተወሰደው ገንዘብ ሒሳብ በማካተት በጥቅል በድጋሚ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዲጠቀስ መደረጉ ይህ ዘገባ እንዲሠራ የተደረገበት ዓላማ ላይ ጥያቄ ፈጥሮብናል፡፡ ቅሬታ ቀረበበት የተባለው ሕንፃ ጠቅላላ ሽያጭ ከ83 ሚሊዮን ብር በታች ነው፡፡ የተሰበሰበው ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ አይሆንም፡፡ ሙሉ በሙሉ የከፈለ ቤት ገዥ የለም፡፡

ከዘገባው ጋር የታተመው ተጠናቆ የባለቤትነት ስሙ የተዘዋወረውን ሕንፃና በመገንባት ላይ ያለውን ሕንፃ የሚያሳየው ፎቶ ለአንባቢ ተመዛዛኝ ግንዛቤ ይሰጣል ብለን እንገምታለን፡፡ ሆኖም ከፎቶ ሥር ‹‹ግንባታው የተስተጓጎለው ሕንፃ›› በሚል የተሰጠው መግለጫ ግን ሪል -ስቴታችን ግንባታውን በማካሄድ ላይ ያለ እንጂ ሥራው የቆመ ባለመሆኑ ዘጋቢውም በአካል የተመለከተው ስለሆነ፣ የሥራው ሒደት በዚህ ዓይነት መገለጽ አልነበረበትም፡፡ የማጠናቀቂያና የገጠማ ሥራዎችን በተመለከተ ዕቃዎችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ለባንክ ካቀረብን ረጅም ጊዜ ቢሆንም በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግራችን እስኪቃለል በመጠባበቅ ላይ ነን፡፡ ከችግሩ ጎን ለጎን መፍትሔ ለመፈለግ አንዳንድ የማጠናቀቂያ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ምንጮች ለማጠናቀቅ ትዕዛዝ ሰጥተን ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል ዘጋቢው በተገኘበት በወቅቱ ከነበሩት ጥቂት ቤት ገዢዎች ጋር ስለ ችግሩ ለመወያየት የአንድ ሳምንት ቀጠሮ ተይዞ ነበር፡፡ ዘጋቢውም ይህንኑ ያውቃል፡፡

የዘገባውን ሚዛናዊነት ለመጠበቅ ቢያንስ የውይይቱን ውጤት ቢጠብቅ የተሻለ ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በተመለከተ የውጭ ምንዛሪ የጋራ ችግር በመሆኑ በግልም ሆነ በአገር ደረጃ በመደጋገፍ የምንፈታው እንጂ የጥቂት ሰዎች ችግር ብቻ ተደርጎ የሚታይ አይደለም፡፡ ሪል ስቴታችን ከዚህ በፊት በሥራ ተቋራጩ የተፈጠረበትን ችግር ከደንበኞቹ ጋር በመነጋገር የመፍትሔ አቅጣጫ ይዞ ከውይይቱ በኋላ በዘገባው ላይ ፎቶው የታተመውን ሕንፃ አጠናቆ የስም ዝውውር በመፈጸም አስተላልፏል፡፡ ቅሬታ አቀረቡ ከተባሉት ገዢዎች ጋር ውይይት የተደረገው በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ የግንባታ ሥራው ከመስከረም 2009 ዓ.ም ጀምሮ የሚቀጥል መሆኑን መግባባት ላይ በደረስንበት መሠረት ግንባታው ቀጥሏል፡፡ በዘገባችሁ ላይ ግን ግንባታው እንዲቀጥል የተስማማንበት ጊዜ የግንባታው ማጠናቀቂያ በማስመሰል አቅርባችኋል፡፡ አሁንም በምናደርገው ውይይት የተሻለ አማራጭ ላይ እንደርሳለን ብለን እናምናለን፡፡ በችግርም ውስጥ ቢሆን ቤት ሠርቶ በማስረከብ ሌሎች ሳይሆኑ ሪል ስቴታችን ከውይይቱ በኋላ ሠርቶ ያስረከበው ፎቶው የሚታየው ሕንፃ በቅርብ የሚገኝ ማረጋገጫ ስለሆነ ሌሎች ሪል ስቴቶችን መጥቀስ የሚያስፈልግም አልነበረም፡፡

በመጨረሻም በዘገባው ላይ የተፈጠሩት ግድፈቶች እንዳሉ ሆነው በመደምደሚያው ላይ የተጻፈው የዘጋቢው የግል አስተያየት ግን ሪል ስቴታችንን የማይመለከትና ከዚህ ዘገባ ተለይቶ በማንም ላይ ጉዳት በማያስከትል መልኩ በሌላ ዘገባ ውስጥ መጻፍ የነበረበት መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ሪል ስቴታቻችን የማንንም አመኔታ አላስቀረም፡፡ በቅድሚያ ክፍያ ሰበብ የሰው ገንዘብ ሰብስቦ የውኃ ሽታ አልሆነም፡፡ መንግሥትን የሚያስወቀስ ሥራም አልሠራንም፡፡ መሥራት ባልተጀመረ ቤት የሽያጭ ቅስቀሳ አላደረግንም፡፡ ዘጋቢው ስለሌሎች ሪል ስቴቶች አሉታዊ አመለካከት ካላቸው የራሳቸውን ምርመራ አድርገው በተገቢው መልኩ በሌላ ዘገባ ላይ ቢጽፉ ይመረጣል፡፡ ይህ ሆኖ እያለ ከአንድ ሪል ስቴት ዘገባ ጋር ተያይዞ መቅረቡ ሊያስከትል የሚችለውን ተጓዳኝ ጉዳት ያገናዘበ አይደለም፡፡ ሪል ስቴታችን ላይ ተመሳሳይ ችግር ይገጥመናል ብለን ባንሰጋም ያልተስተካከሉ ዘገባዎች ችግሮችን በማባባስ ድርጅቶችን እስከማዘጋት የሚደርስ ውጤት ሊኖራቸው ስለሚችል ይህ ጉዳይ ሪል ስቴታችንን የማይመለከት መሆኑን እንገልጻለን፡፡ በዚሁ መሠረት ይህን ቅሬታችንን በተመሳሳይ ዕትም በተመሳሳይ አምድ በጋዜጣችሁ እንድታወጡልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

(ወ/ሮ ይርጋለም አስፋው፣ የይርጋለም ሪል ስቴት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ)

ከአዘጋጁ፡

በሪፖርተር የኤዲቶሪያል ነፃነትና መርኅ መሠረት በይርጋለም ሪል ስቴትና በቤት ገዥዎች መካከል ያለውን ቅሬታ በተመለከተ የቀረበው ዘገባ በሁለቱም ወገን የተንጸባረቁ ቅሬታዎችን በሚዛናዊነት ለማስተናገድ የሞከረ ነው፡፡ ቤት ገዥዎቹ ላቀረቧቸው ቅሬታዎች በሙሉ የይርጋለም ሪል ስቴት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ይርጋለም አስፋው ምላሽ እንዲሰጡ፣ ሪል ስቴቱም የመደመጥ መብቱ ተጠብቆ ለተነሱበት ቅሬታዎች በይፋ ምላሽ እንዲሰጥባቸው በማድረግ በቀረበው ዘገባ ከሁቱም ወገን ለተነሱ ነጥቦች ሽፋን ተሰጥቷል፡፡

ሆኖም ለሪፖርተር በተላከው የሪል ስቴቱ የቅሬታ ደብዳቤ ውስጥ በግልጽ ለመመልከት እንደቻልነው ማስረጃ አይገኙባቸውም ተብለው የተገመቱ አሐዝ ቀመስ እውነታዎችን በማጣቀስ የቀረበውን ዘገባ ለማስተባበል ተሞክሯል፡፡ ለአብነት ያህል 120 ሚሊዮን ብር እንደተከፈለ ስለሚገልጸው ክፍል ይርጋለም ሪል ስቴት ደጋግሞ ለማስተባበልና እውነትነት እንደሌለው ለማሳየት ሲሞክር ታይቷል፡፡ ይህ ጉዳይ ግን ከሪፖርተር ዘገባም ቀደም ብሎ ከቤት ገዥዎቹ ሲቀርብለት የነበረ ጥያቄ እንደነበረ ጠቅሷል ሪል ስቴቱ ጠቅሷል፡፡ ሪፖርተርም ይህንኑ የቤት ገዥዎቹን ጥያቄ በጥያቄነት አቅርቦ ምላሽ እንዲሰጥበት መጠየቁና መዘገቡ ከጀርባ ምን አለው ወዘተ. የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ሥራ አስኪጇም ይኸው ጥያቄ ቀርቦላቸው ማስተባበላቸውና የገንዘብ መጠኑ በተባለው መጠን እንዳልሆነ መናገራቸው በዘገባው ተካቷል፡፡ እንደ እውነቱ ሪፖርተር ልዩ የምርመራ ዘገባ አላካሄደም፡፡ ያደረገው ነገር ቢኖር ቅሬታ ያቀረቡ አካላት ያነሷቸውን ቅሬታዎች ማስተናገድ ነው፡፡ ቅሬታ የቀረበበት አካልም የመደመጥ መብቱን በማክበር እንዲያስተባብል ዕድል መስጠት ነው፡፡ የሪፖርተር ዘጋቢ ሪል ስቴቱ ግንባታ በሚያካሂድበት ቦታ ተገኝቶ ከሁለቱም ወገን የተነሳውን ሐሳብ ማንጸባረቁ ብቻም ሳይሆን፣ በስልክም ጭምር ለሪል ስቴቱ ባለቤት ደውሎ እንዲደመጡ ዕድል መስጠቱ የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና ሪል ስቴቱ የቀረቡበትን ትችቶችና ወቀሳዎች ወደ ጎን በመተው በኢዲቶሪያል ነጻነት ሳይቀር ጣልቃ መግባት በሚመስል መልኩ፣ ስለ ዘገባ አጻጻፍ ለማስተማር በሚቃጣው አኳኋን ‹‹ስለ እኛ ስትጽፉ ሌላው ሪል ስቴት ያጠፋውን መጥቀስ አልነበረባችሁም›› የሚል አንድምታ ያለው መልዕክት ሳይቀር ለማስተላለፍ መሞከሩ ለሚዲያ ሥራ የሚሰጠው ግምትና የተሳሳተ ግንዛቤ ነጸብራቅ በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡ ዳያስፖራዎች ቤት አልገዙንም፣ 80 ቤት ገዥዎች የሉንም የሚለው መከራከሪያ በወቅቱ በግንባታ ቦታው ከተገኙ ቤት ገዥዎችም ሲነሳ የነበረ፣ ከሪፖርተርም ለሪል ስቴቱ ጥያቄ ቀርቦበት የነበረ ሲሆን፣ ሊስተባበል ባለመቻሉ የተጠቀሰ አሐዝ ነው፡፡

በጠቅላላው ሪፖርተር እንደምንጊዜውም በሚያቀርባቸው ዘገባዎች ውስጥ ለሚነሱ ቅሬታዎችና ትችቶች በሩ ክፍት ነው፡፡ ስህተት ተፈጽሞም ከሆነ ማጣራት በማድረግ ተገቢውን ዕርምት እንደሚያደርግ የታወቀና ወደፊትም የሚመራበት አሠራር ነው፡፡ ከዚህ ነፃ አስተሳሰብና መርኅ በመነሳትም ይህንን ቅሬታ ማስተናገዳችንን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ይሁንና ስለ ሚዲያ አሠራር እናውቃለን፣ ዘገባ መሠራት ያለበት በዚህ መልኩ አይደለም ወዘተ. እየተባሉ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች የጋዜጠኝነትን ሙያ ካለማወቅ፣ የሙያውን ሚና ካለመገንዘብ የሚመነጩ ብቻም ሳይሆን አንዳንድ ጊዜም እናውቃለን ከሚሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች የሚመነጩ በመሆናቸው ቅሬታዎች ሲቀርቡ የቅሬታ መነሻ በሆኑት ነጥቦች ላይ በማተኮር እንጂ የሚዲያ ሥራንና ተልዕኮን በሚጋፋ አኳኋን መሆን እንደማይገባቸው በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...