የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በሚቀጥለው የትምህርት ዓመት ለሚሰጡት ስኮላርሽፕ፣ ኢትዮጵያውያን አመልካቾች በአጭበርባሪዎችና በአደናጋሪዎች እንዳይታለሉ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አስጠነቀቀ፡፡
ኤምባሲው ይህንኑ አስመልክቶ ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከተው አታላዮቹ ለማደናገር ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ስኮላርሽፕ ፈላጊዎቹ ለማመልከቻና ለቪዛ የሚሆን ገንዘብ በቅድሚያ እንዲከፍሉ የሚለው ይጠቀሳል፡፡
ከዚያም ከክፍያ በኋላ ቪዛ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል የሚገልጽ መመርያ እንሰጣለን የሚለውም አካሄድ፣ ሌላው የማታለያ ዘዴያቸው መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ትክክለኛውን ሁኔታ ለማረጋገጥ ወይም ለመረዳት ያመለከቱበትን ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽ ማጤንና ከሚመለከታቸው ጋር ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለቪዛ አመልካቾች ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና አስፈላጊ መረጃዎችን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡