በበርካታ አገሮች እግር ኳስ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ አስኳል ቦታ በመያዝ ተጨባጭ ለውጥና ውጤት እንዲመዘገብ ከሚያግዙ ግብዓቶች መካከል የቴክኒክ ዲፓርትመንት ወሳኝ ሆኖ ይገኛል፡፡ የቴክኒክ ሥራዎችን ለመምራት የተጫዋቾች ብቃትና ክህሎት እንዲዳብር ትልቁን ድርሻ የሚወጣው ይህ ክፍል፣ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእግር ኳሱ አካል ሆኖ መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁንና ክፍሉ ከተሰጠው የኃላፊነት ድርሻ ውስጥ ዋናውን ወደ ጎን በማለት የአሠልጣኝነት ፈቃድ (ላይሰንስ) በማደል ብዙውን ጊዜ ሲያባክን ቆይቷል፡፡ ይህም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ለትችትና ወቀሳ ዳርጎት ቆይቷል፡፡
የቴክኒክ ዳይሬክተር የሚለውን ስም ብቻ በመያዝ የዲፓርትመንቱ ትርጉም እየተዛባ በተለይም በአሁኑ ወቅት በርካታ ባለሙያዎች በክለቦችና በብሔራዊ ፌዴሬሽን ደረጃ የእግር ኳሱ አስኳል ተብሎ በሚጠራው ክፍል መካተት ጀምረዋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥም ይህን ዘርፍ የሚመራ ክፍል ከተቋቋመ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ስፖርቱን ወደፊት አንድ ዕርምጃ ሊያራምድ የሚችል ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ መናገር ይቻላል፡፡
በየጊዜው በዳይሬክተርነት የተሾሙ ኃላፊዎች ምክንያታዊ በሆነና ባልሆነ አሠራር ተፈራርቀውበታል፡፡ ጥያቄው ግን በሚፈለገው የቴክኒክ ደረጃ ልክ ውጤት አምጥተውበታል ወይ? ምን የፈየዱትና የለወጡት ነገር አለ? የሚለው ነው፡፡ እስካሁን እንደታየው ከሆነ የአብዛኛዎቹ ባለሙያዎች ምደባ ንድፈ ሐሳባዊ ዕውቃታቸውን መሠረት ያደረገ እንጂ ተግባራዊ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ብቃትና ክህሎት ልምድና ተሞክሮ ሚዛን ሲደፋ አለመታየቱ በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
የቴክኒክ ዳይሬክተሮች በብቃትና ባስመዘገቡት የሙያ ተሞክሮ ይመደቡ ቢባል በዚህ አግባብ ልምዱ ያላቸውን ማግኘቱ አዳጋች ባይሆንም፣ በአገሪቱ ስፖርት ውስጥ ባህል ሆኖ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ‹‹ወገንተኝነት›› ሙያና ሙያተኛውን ማገናኘት እንዳይቻል በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ በመሆኑም ማዕከላዊ ቁልፍ ድርሻ የሚሰጠው ይህ ዘርፍ የሚፈለገውን ውጤትና ለውጥ ማምጣት ተስኖት ቆይቷል፡፡ በአንፃሩ ውጤታማ የቴክኒክ ክፍል ያላቸው ጥቂት የአፍሪካና በብዛት የአውሮፓ አገሮች በእግር ኳሱ ምትሃታዊ ለውጥ እያስመዘገቡ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላለፉት አምስት ዓመታት የቴክኒክ ዘርፉን እንዲመሩ ኃላፊነት ሰጥቷቸው የቆዩት አቶ መኰንን ኩሩ እንደነበሩም ይታወሳል፡፡ በቅርቡ የኃላፊነት ሽግሽግ እንዲደረግላቸው ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ተቋሙ ግን ‹‹ቦታ የለኝም›› በሚል የኃላፊውን ስንብት ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ መነሻነት ማንነታቸው እንዲቀስ ያልፈለጉ የፌዴሬሽን ከፍተኛ አመራሮች አሁንም ፌዴሬሽኑ ከቆየው አሠራር ወጥቶ ለዲፓርትመንቱ የሚመጥን ትክክለኛውን ባለሙያተኛ ማግኘት ይቻል ዘንድ መስፈርት ወጥቶ ቅጥር እንዲፈፀም ይጠይቃሉ፡፡
ይሁንና በአሁኑ ወቅት የቆየውንና ያለውን ቀዳዳ በመጠቀም ውስጥ ለውስጥ የሚደረጉ ‹‹የቅጠሩኝ›› ሩጫዎች መጀመራቸውንና ይህም ሥጋት እንደፈጠረባቸው ጭምር ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ በአጠቃላይ እንደ ሌላው ዘርፍ ብቃትና ዕውቀትን እንዲሁም ዕድሜን በማካተት ትክክለኛውን አሠራር እንዲከተል ይጠይቃሉ፡፡