Friday, February 23, 2024

የግል ብሮድካስት ሚዲያውና ያንዣበቡበት ችግሮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሚዲያ የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶለት ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ሕገ መንግሥታዊ መብት የተሰጠው ተቋም ነው፡፡ በተቋምነቱም የተለያዩ አስተያየቶችና ሐሳቦች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ የተደረገለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ በመሆን በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዲገነባ መሥራት እንዳለበት የመንግሥት ፖሊሲ ያስቀምጣል፡፡

ይህንን የመንግሥትንም ሆነ የግሉን ሚዲያ የአሠራር ሥርዓት የሚከታተልና የሚቆጣጠረው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ነው፡፡ የኢፌዴሪ የብሮድካስት ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 533/1999 መሠረት የተቋቋመ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም ለፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ጥራቱ የተጠበቀ ቀልጣፋና አስተማማኝ የብሮድካስት አገልግሎት እንዲስፋፋ ማድረግና መቆጣጠር ነው፡፡

ይህ ባለሥልጣን ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መካከል አንዱ ደግሞ፣ የብሮድካስት አገልግሎት ዕድገትና መሻሻል እንዲያመጣ ጥናት ማድረግና አገልግሎቱን የሚመለከቱ መረጃዎችን አጠናቅሮ መያዝ እንዳለበት አዋጁ ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረትም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የግል ሚዲያው የሚገኝበትን ሁኔታ ለመገምገምና ለማወቅ ለሁለት ወራት ያህል የሞኒተሪንግና የኢንስፔክሽን ሥራ አከናውኗል፡፡ የእዚህን የሞኒተሪንግና የኢንስፔክሽን ግኝት ለሚመለከተው አካል ተደራሽ ለማድረግ ሲባል፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነትን በመወጣትና የዴሞክራሲ ሥርዓትን በመገንባት ረገድ የንግድ ብሮድካስት ሚዲያው የሚገኝበት ሁኔታ›› በሚል ርዕስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሚያዚያ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአንድ ቀን ያህል በሒልተን ሆቴል የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በባለሥልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዴሬሳ ተረፈ እንደገለጹት፣ የእዚህ ኢንስፔክሽን ዋና ዓላማ የንግድ ብሮድካስት አገልግሎቱ በሕገ መንግሥትና በብሮድካስት አዋጅ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ የሚታዩ መልካም ጅምሮችና ጥረቶችን በመለየት የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ ነው፡፡

ይህ ኢንስፔክሽን ከጣቢያ ሥራ አስኪያጆች፣ የፕሮግራምና ዜና ክፍል ኃላፊዎችና ኤዲተሮች ጋር ውይይት በማድረግ የተሠራ መሆኑን አቶ ዴሬሳ አስታውሰው፣ በዚህ መሠረት የ150 ዜናዎችና 800 ፕሮግራሞች ናሙና ተወስዶ የሞኒተሪንግና የኢንስፔክሽን ሥራው እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡

የሞኒተሪንግና የኢንስፔክሽን ግኝቶችን ደግሞ የባለሥልጣኑ የሕግና ማስታወቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ አቅርበዋል፡፡ እንደ አቶ ግዛው ገለጻ፣ በጥንካሬነት ከሚገለጹት ግኝቶች መካከል አገሪቱ በምታከናውናቸው የልማት እንቅስቃሴዎች (በህዳሴ ግድብና ሌሎች) ቀጣይነት ያለው በዜና፣ በፕሮግራምና በማስታወቂያ ሽፋን ሰጥተው መሥራት፣ በወቅታዊ፣ አካባቢያዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ የዜና ሽፋን የሚሰጡ መሆን፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸው፣ የሐሳብና የአመለካከት ብዝኃነትን በድፍረት በማስተናገድ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው አስተዋጽኦ በማበርከት ረገድ አልፎ አልፎ ጅምር ጥረት መኖሩ፣ የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችን ተከታትለው ሽፋን እየሰጡ መሆኑ የሚሉት እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡

አጀንዳ ቀርፀው በዓበይት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱ ፕሮግራሞችን ከማሠራጨት፣ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጠናክር ተከታታይነት ያላቸው ፕሮግራሞችን ከማቅረብ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመከላከል ትኩረት ሰጥተው ከመሥራት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ያለፉትንም ሆነ የቅርብ ታሪክ ሚዛኑን ጠብቆ ከማቅረብ፣ ወጣቱ በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ፣ ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የተላበሰ፣ በመከባበርና በመቻቻል፣ በእኩልነት፣ በሕግ የበላይነት፣ በምክንያታዊነት የሚያምን፣ መልካም ዜጋ እንዲሆን የሚያስችሉ ተከታታይ ፕሮግራሞችን ከማቅረብ አንፃር፣ የፈቃድ ስምምነት ተገዥ ባለመሆን በስፖርትና በመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ማተኮር በእጥረትነት የሚገለጹ ግኝቶች እንደሆኑ ዳይሬክተሩ አስረድዋል፡፡

ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሕጋዊ ለሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍትሐዊ የሆነ ዕድል አለመስጠት፣ የተለያየ አመለካከት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ ምሁራንን፣ የሙያና ሲቪክ ማኅበራትን በሚዲያ አለማስተናገድ፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሙዚቃና ባህል በፍትሐዊነት አለማስተናገድ፣ የሕፃናት፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ፕሮግራሞች የሚሰጣቸው ሽፋን አነስተኛ መሆን የሚሉት ደግሞ ብዝኃነትን በማስተናገድ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ ከማድረግ አንፃር በእጥረት የሚገለጹ ግኝቶች እንደሆኑ አቶ ግዛው ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ የብሮድካስት አዋጅ ድንጋጌዎችን አክብሮ በመሥራት ረገድ በእጥረት የሚገለጹ ግኝቶች ብለው ከዘረዘሯቸው መካከል በበቂ ጥናትና መረጃ ላይ የተመሠረተ የምርመራ ጋዜጠኝነት ፕሮግራሞችን በማቅረብ ረገድ ሰፊ እጥረት መኖሩ፣ የችግሮች መንስዔና መፍትሔን ከመጠቆም ይልቅ ችግሮቹን የማራገብ አዝማሚያ መኖሩ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን አለማካተት፣ ሚዛናዊ አድርጎ አለማቅረብ፣ በመረጃ ላይ ሳይመሠረቱ የተቋማትና የግለሰቦችን ስም ማጥፋት፣ ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት የግለሰቦችን ነፃ የመሆን መብት መንካት፣ የሕዝብ ሬዲዮ ሞገድን ለግል ጥቅምና ፍላጎት ማዋል (ለቤተሰብ ሠርግ የቀጥታ ሥርጭት መስጠት፣ ለሐዘንና ሌላ ፍላጎት ማዋል)፣ ከኅብረተሰቡ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች መልስ አለመስጠትና መብትን አለማስከበር፣ ባለሥልጣናት በሕግ መሠረት የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ አለማድረግ፣ ለባለሥልጣኑ ቦርድ ይግባኝ ከማቅረብ ይልቅ ጣቢያን በመጠቀም መቃወም የሚሉት በአንዳንድ ሚዲያዎች እንደሚስተዋሉ አብራርተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ማስታወቂያና ስፖንሰርሺፕን በተመለከተ በተወሰኑ ጣቢያዎች በእጥረት የሚገለጹ ግኝቶች ብለው ከዘረዘሯቸው መካከል፣ በማስታወቂያ አዋጁ ከተፈቀደው የጊዜ ምጣኔ በላይ እስከ 40 በመቶ ማስታወቂያ ማሠራጨት፣ የፕሮግራም ይዘትና ጊዜ በስፖንሰር ተፅዕኖ ሥር መውደቅ የሚሉት እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

የፈቃድ ስምምነትን አክብሮ በመሥራት ረገድ በእጥረት የሚገለጹ ግኝቶች ብለው ካስቀመጧቸው መካከል ደግሞ፣ አብዛኞቹ የንግድ ብሮድካስተሮችና የብሮድካስት ፈቃድ ለማግኘት ያቀረቡት የፕሮጀክት ሰነድና የፕሮግራም መርሐ ግብር ሲታይ የማይጣጣም እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በኢንዱስትሪው የሚታየውን ተግዳሮት በተመለከተ አቶ ግዛው ሲያብራሩ የማስፈጸም አቅም ውስንነት በአመለካከት፣ በሙያ፣ በክህሎት፣ በሥነ ምግባር፣ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትና ኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁ አለመስጠት፣ ወዘተ የሚሉት እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የጥናቱ ግኝቶች ከቀረቡ በኋላ መድረኩ ለተሳታፊዎች ክፍት ተደርጓል፡፡ አስተያየትና ሐሳብ ካቀረቡት መካከል የሚዲያና ኮሚኒኬሽንስ ሴንተርና የሚዲያ ካውንስል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አማረ አረጋዊ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ሚዲያው ላይ ችግሮች እየተስተዋሉ ስለሆነ ለወደፊት ለሚኖረው ስብሰባ የግሉንና የመንግሥት ሚዲያውን ያካተተ ቢሆን የተሻለ ነው፤›› የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የሚዲያ ካውንስሉ ከብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር አብሮ ቢሠራ የተሻለ ነው ተብሎ በጥናት አቅራቢዎች ለቀረበው ሐሳብ፣ የሚዲያ ካውንስሉ ከብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር አብሮ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሚዲያ ካውንስሉ እስካሁን የምዝገባ ፈቃድ ላይ እክል እንደገጠመው ጠቅሰው፣ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን አጢኖ መፍትሔ እንዲሰጥ አቶ አማረ ጠይቀዋል፡፡

የዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ተሾመ በበኩላቸው፣ አስፈጻሚው ከሚዲያ ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ሪፖርቱ አሳስቶ እንዳለፈ ከገለጹ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ መረጃ ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድ አብራርተዋል፡፡ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ለሚዲያዎች ያላቸው አመለካከት አነስተኛ በመሆኑ የመረጃ ደንቃራነትን እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሪፖርቱ ላይ የግል ሚዲያዎች የሐሳብ ብዝኃነትን በማስተናገድ ረገድ ውስንነቶች እንዳሉባቸው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ለተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ከማድረግ አኳያ ደካማ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ከኢዴፓ የተወከሉት አቶ አዳለ ታደሰ እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ የሐሳብ ብዝኃነት እንዳይስተናገድ እክል ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የመንግሥት ሚዲያው እንደሆነ ነው፡፡ ‹‹የመንግሥት ሚዲያ ፍርኃትን ለግሎችም አውርሷል፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህም አንፃር የመንግሥት ሚዲያ የሐሳብ ብዝኃነትን በማስተናገድ ዙሪያ ሰፊ ሥራ ማከናወን እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የግል ሚዲያው የሐሳብ ብዝኃነትን ለምን አላስተናገደም ብለው ለመተቸት ሞራል እንደማይኖራቸው አሳስበዋል፡፡ በግል ሚዲያው በኩል ያለውን የስፖርት ነክ ፕሮግራሞች ነፃነት በሌሎችም ለማምጣት ቢሞከር የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወልዱ ይመስል በበኩላቸው፣ ሪፖርቱ ምንጩን እንደማይጠቁምና ለምን እንደዚህ ሆነ ብሎ መልስ እንደማይሰጥ ካብራሩ በኋላ፣ በአገሪቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታ በሚዲያው ላይ ረጅም ጉዞ ለመጓዝ አስቸጋሪ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በማሳያነት የመንግሥት ባለሥልጣናት በጎ ጎናቸው እንጂ ደካማ ጎናቸው እንዲወራባቸው እንደማይፈልጉና መረጃ ለመስጠት ያለው ሁኔታም በዚህ ልክ ገና ያልዳበረ መሆኑን አክለዋል፡፡

አንድ ተሳታፊ በበኩላቸው ይህ ሪፖርት አስፈጻሚ አካላት የሚጠቀሟቸውን ቃላት እንደ መሥፈርት ወስዶ የተደረገ ግምገማ መሆኑን ጠቁመው፣ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሊናገር የሚገባው ግን ከዚህ ከፍ ባለ ሁኔታ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ሚዲያው ይህንን ሽፋን ሰጥቷል፣ ይህንን ያህል የሐሳብ ብዝኃነት አስተናግዷል፣ በዚህ ላይ አስፈጻሚውን ሞግቷል፣ ወዘተ ማለት እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ የጥናቱ ግኝቶች ደግሞ በጣም  ሰፊ፣ ረጅም፣ አከራካሪና ክፍተት ያለባቸውና በትክክልም የግል ሚዲያው ያለበትን ሁኔታ የማይጠቁሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የሕዝብና ውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፣ የሚዛናዊነት ጉዳይ በደንብ መታየትና እንዳለበት ጠቁመው ሚዛናዊነትን ጠብቆ ከመሄድ አንፃር የግል ሚዲያዎች ብዙ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የሐሳብ ብዝኃነትን ከማስተናገድ አንፃርም ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ጊዜ እኩል የአየር ሰዓት እንደሚሰጥ አስታውሰው፣ በኢሕአዴግ እምነት ዋና ተቃዋሚና ሁለተኛ ተቃዋሚ የሚባል ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በጥናቱ እንደ ድክመት ከተቀመጡት ጉዳዮች መካከል አንዱ የታሪክን ሚዛናዊነት ጠብቆ ለማቅረብ ያለው ክፍተት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ከትናንት እስከ ዛሬ ታሪክ የሚቀርብበት ሚዛን የተዛባ ነው፡፡ ይህ ግን ለወደፊት መስተካከል እንዳለበትና ለዚህም የብሮድካስት ባለሥልጣን ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የጥናቱ ሪፖርት በቀረበበት ወቅት በአብዛኛዎቹ የግል ሚዲያዎች ስሜት ቀስቃሽ እንደሆኑና ነገሮችን እንደሚያረግቡና ይህም ወደፊት መስተካከል እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ አንስማማም ካሉት መካከል ደግሞ አንዱ ድምፀ ወያነ ትግራይን የወከሉ ግለሰብ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ችግሮቹን ማራገብ ሲባል የችግሮቹን ሥር መሠረት መለየትና ኋላ ላይ ማስተማር እንዲቻልና መፍትሔ ይዞ እንዲመጣ ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በዚህ የሞኒተሪንግና የኢንስፔክሽን ግኝት ላይ በተደረገው የውይይት መድረክ የግል ሚዲያዎች ያሉባቸውን ችግሮች የጠቆሙ ሲሆን፣ ከመረጃ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጉዳይ ግን ዋነኛውና ትልቁ እንቅፋት እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት መረጃ ለመስጠት ያላቸው ፈቃደኝነት እጅግ አነስተኛ መሆን፣ ሚዲያን መፍራት፣ መረጃ ሲጠየቁ ነገ ዛሬ ማለት፣ ወዘተ ችግሮች እንዳሉ በስፋት ተነስቷል፡፡ ይህም ለግሉ ሚዲያ ደንቃራ ጉዳይ መሆኑ፣ ዜናና ፕሮግራሞች ደግሞ ቋንጣ ሆነው እንደማይጠብቁ ባለድርሻ አካላት ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የክብር እንግዳ የነበሩትና የማጠቃለያ ሐሳብ ያቀረቡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡ እሳቸውም በማጠቃለያ ሐሳባቸው ላይ ሚዲያ ዴሞክራሲን በመተግበርና እንዲተገበር በማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ ሚዲያው ሊሠራቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በተመለከተ ብዙ ሐሳብና አስተያት የተሰጠ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ብሔራዊ መግባባት ሲባል የገዥው ፓርቲ ፖሊሲና ስትራቴጂ ትክክል ነው፣ ትክክል አይደለም ብለን መናገር ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ ያለውን መሠረታዊ መርህ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው፣ በምን መልክ ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ለኅብረተሰቡ የማስረዳትና የማስረፅ ሥራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተመቻቸ ሁኔታ እንዲኖር በመንግሥትም ሆነ በግል ሚዲያዎች የተለያዩ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባ አቶ አስመላሽ ጠቁመዋል፡፡  አክለውም የብዝኃንና የሙያ ማኅበራት፣ ምክር ቤቶች፣ ሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት የተለያየ ሚና ቢኖራቸውም ድምር ውጤታቸው ግን አንድ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ሲባል የሚቃወመው ይኖራል፣ የሚደግፈውም ይኖራል ማለት እንደሆነና መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ግን እንደ ሕዝብና አገር እንዴት እንኑር በሚለው ላይ መተማመን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

አቶ አስመላሽ የሚዲያውን ሚና በተመለከተ ሲያብራሩ ሚዲያው ሕዝቡ ለልማትና ለዴሞክራሲ እንዲነሳሳ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ በትንተና ላይ የተመሠረተ መረጃ በመስጠት፣ የተለያዩ አማራጮችን በማቅረብ ሚዲያው የክርክር መድረክ ሆኖ እንዲያገለግል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

አስፈጻሚው አካላት በሚዲያው ላይ እየፈጠረ ያለውን ችግር በተመለከተ አቶ አስመላሽ ሲመልሱ፣ ‹‹እከሌ..ፈጠረ፣ እከሌ ተቋም መረጃ እንቢ አለ ብለን በጅምላ ከመፈረጅ ተላቅቀን ሚዲያው አራት የዴሞክራሲ እሴቶች መገንቢያ መሣሪያ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ አራቱ የዴሞክራሲ እሴቶችም የሕግ የበላይነት፣ ምክንያታዊ መሆን፣ መቻቻልን መፍጠርና ሰጥቶ መቀበል እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ እነዚህ እሴቶች በሚዲያዎች በኩል መሥራት እንዳለባቸው በመጠቆም፣ አስፈጻሚው አካል እንደዚህ ነው ብሎ የሚፈረጅ ከሆነ መፈረጅ፣ ይህ ካልሆነ ግን መንግሥት እንደ መንግሥት አልሠራም ማለት ነው ብለዋል፡፡

አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ችግር እንዳለ ፈልፍሎ ማውጣትና ማስረዳት ተገቢ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ባለሥልጣን ተጠይቆ አልመልስም ካለ እገሌ የሚባለው ኃላፊ ዘንድ ደውለን መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ብለን እንናገራለን፡፡ ይኼ ለማሳጣት ይጠቅማል፡፡ ይኼ መሣሪያ እስካለ ድረስ አስፈጻሚ ብሎ መጮህ አይጠቅምም፡፡ መንግሥት ዓመኔታ እንዲያጣ የሚደረግ እንቅስቃሴ ከሆነ ሌላ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በ2007 ዓ.ም. በነበረው ምርጫ ኢሕአዴግ አንዳንድ ዕጩዎችን ሲያስመዘግብ ሕጉን አልተከተለም፡፡ ምርጫ ቦርድ በዚህ የተነሳ ለኢሕአዴግ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ይኼንን እንዴት ነው የማስተላልፈው ብሎ ተጨንቆ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ኋላ ላይ ግን ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ መሰለኝ ዜናው ተላለፈ፡፡ ይህ ፍርኃት በእያንዳንዳችን ውስጥ የዴሞክራሲ ባህል ችግር ተደርጎ ነው መወሰድ ያለበት፡፡ ይኼ የሥርዓት ችግር አይደለም፡፡ ሕጎቻችን እንደዚህ አይሉም፡፡ አልፎ አልፎ ግን በአስፈጻሚው ዘንድ ችግሮች አሉ፡፡ ብዝኃነት በሚገባ ተስተናግዷል ማለት አይቻልም፤›› ሲሉ አቶ አስመላሽ አክለዋል፡፡

‹‹እዚህ አገር የሚያስቸግረው ጉዳይ ድክመትን ከነምንነቱ፣ ምክንያቱና መፍትሔው ተንትኖ የማቅረብ ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ባለሥልጣን  መሥሪያ ቤቱ ራሱን እያጠናከረና ከመድረኮች ትልቅ ትምህርት እየወሰደ እንደሚሄድ ተስፋቸውን ገልጸው ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡

በዕለቱ የመጨረሻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም ናቸው፡፡ በንግግራቸውም መረጃ መስጠትን በተመለከተ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ የተነሱ ችግሮች የአስፈጻሚው መገለጫ አይደሉም ብለዋል፡፡ ‹‹ለምን ቢባል እንኳንስ ለወዳጅ፣ እንኳንስ ራሱ ፈቃድ ሰጥቶ ላቋቋማቸው የመንግሥትም ይሁኑ የግል ሚዲያዎች፣ ለጠላትም አንዳንዴ የማይደብቃቸው መረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ራሱን የገመገመበትን መረጃ ለወዳጅም ለጠላትም ነው ይፋ የተደረገው፡፡ ራሱን የገመገመበት ፀረ ዴሞክራሲ አዝማሚያ፣ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል፣ ጠባብነትና ትምክህት የመሳሰሉ ችግሮችን እንደ መንግሥት  አለብኝ ብሎ በማንም ላይ ሳያላክክ ራሱን ነው ያስቀመጠው፡፡ አንዱ መስተዳድር በሚናገራቸው ላይ ተመርኩዘው የሚፈረጁ አገላለጾች መስተካከል አለባቸው፡፡ ይህ  እንደተጠበቀ ሆኖ ለመንግሥትም ሆነ ለግል ሚዲያ በትጋት፣ በተጠየቁበት ጊዜ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ሆኑ የመሥሪያ ቤት ኃላፊዎች መረጃ የማይሰጡ አሉ ወይስ የሉም ከተባለ አሉ፡፡ ከሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሁን እንደሰማነው እገሌ የተባለ ኃላፊ መረጃ አልሰጠኝም ብሎ ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያቀረበ ሚዲያ በሌለበት ሁኔታ፣ እንደዚህ ብሎ መፈረጁ ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሁለቱ በኩል ችግር አለብን ብለን ብንወስድ ነው ጥሩ የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዘርዓይ ጋዜጠኛውን በተመለከተ ሲናገሩ፣ ‹‹በጋዜጠኝነት ዓለም ተጨባጭ መሆን የመጀመሪያውም፣ የመጨረሻውም ጉዳይ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ በስሜታዊነት የሚነጉድና ችግር የሚፈጥር ሳይሆን ችግር የሚፈታ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡፡

ማራገብን በተመለከተ አቶ ዘርዓይ ሲያብራሩ፣ ‹‹እንደኛ ዓይነት ኋላ ቀር የሆኑ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ባሉበት ኅብረተሰብ፣ ብዝኃነት ባለበት ኅብረተሰብ፣ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ እሴቶች የበላይነት ባልፈጠረንበት ኅብረተሰብ  ማራገብ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ችግሮች መተንተን የለባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ችግሩን ብቻ አራግበህ መንስዔውንና መፍትሔውን ሳታስቀምጥ ስታስጮኸው፣ በእንደዚህ ዓይነቱ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፤››  ብለዋል፡፡

ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ አቶ ዘርዓይ ሲገልጹ፣ ‹‹ብሔራዊ መግባባት ስንል የተቀመጡ መርሆች ማለታችን ነው፡፡ ሚዲያው በዚህ ጉዳይ በአገሪቱ ልማት እንዲመጣ፣ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት፣ ወዘተ የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸውን ግለሰቦች ጋብዞ ማወያየት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ለዚህ ሁሉ መፍትሔው የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያ የአቅም ግንባታ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ አስተሳሰቡ እንዲዳብር፣ በሙያው እንዲጎለብት፣ በክህሎትም እንዲያድግ፣ በሥነ ምግባርም በተመሳሳይ የሚያድግበትና የሚጠነክርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ከድክመቶቻችንና ከጠንካራ ጎኖቻችን ተምረን፣ ጠንካራ ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ለተባለው ዓላማ ሊያገለግል የሚችል የሚዲያ ኢንዱስትሪ መገንባት አለብን፤›› በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

በዚህ የሞኒተሪንግና የኢንስፔክሽን ግኝት ላይ የመፍትሔ ሐሳቦች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የንግድ ብሮድካስት ሚዲያው ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩሉን ሚና የሚጫወት፣ ሙያዊና ቴክኒካል ብቃቱ የዳበረ እንዲሆን የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በመሥራት የብሮድካስተሮችን የማስፈጸም አቅም መገንባት፣ ባለሥልጣኑ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት፣ ባለሥልጣኑ በኢንዱስትሪው የሚታዩ ተግዳሮቶችን አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ ለመንግሥት ማቅረብ፣ ዓመታዊ የሚዲያ የጋራ ፎረምና የልምድ ልውውጥ ማካሄድ፣ የመንግሥት ማስታወቂያ በፍትሐዊነት የሚከፋፈልበት አሠራር መዘርጋት፣ በሚዲያና በመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤቶች መካከል የሚታየውን ችግር ለመፍታት የግንኙነት መድረክ እንዲመቻች ማድረግ፣ በመረጃ ነፃነት አዋጅ የሠፈሩ የተጠያቂነት አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ፣ የሚዲያ ዘርፍ ራሱን በራሱ የሚቆጣጠርበትን ሥልት መቀየስ፣ ሚዲያው የአመለካከት ብዝኃነትን በማስወገድ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ የድጋፍና ክትትል ሥራ ማከናወን፣ ተሻሽሎ የተዘጋጀውን የፈቃድ ስምምነት በጋራ ተሳትፎ በማዳበር ተግባራዊ ማድረግና የማስፈጸም አቅምን መገንባት የሚሉት በዋና ዋና የመፍትሔ ሐሳብነት እንደሚገኙና፣ እነዚህን የመፍትሔ ሐሳቦች ሁሉም የሚመለከተው አካል በመውሰድ ያሉትን ችግሮች በመፍታት የሚዲያውን ኢንዱስትሪ ማዘመን ተገቢ እንደሆነ አቶ ግዛው ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -