Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ2.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅሱ የአዲስ አበባ ሸማች ማኅበራት የበዓል ምርቶችን አቀረቡ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ኑሮ ለማረጋጋት ያቋቋማቸውና ባለፉት ስድስት ወራት 2.7 ቢሊዮን ብር ያንቀሳቀሱ 141 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ለትንሳዔ በዓል (ፋሲካ) የሚሆኑ ምርቶች በሰፊው ማቅረባቸው ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ቀጥተኛ ክትትል ያደረገባቸውና ለበዓሉ የሚሆኑ 800 የዕርድ ከብቶች አፋር ክልል ከሚገኘው አዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ገብተዋል፡፡ እነዚህ ከብቶች በሸማቾች ማኅበራት ሥር ለሚገኙ ሉካንዳዎች ተከፋፍለዋል፡፡ ተጨማሪ ዕሴት ታክስ በሚያስከፍሉ ልኳንዳዎች ሥጋ በኪሎ 92 ብር፣ በማያስከፍሉ ልኳንዳዎች ደግሞ 80 ብር በኪሎ የሚሸጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲላሞ አቶሬ ለሪፖርተር እንደለጹት፣ አስተዳደሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሳይቸገሩ በዓሉን እንዲያሳልፉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በበቂ ደረጃ እንዲያቀርቡ አድርጓል፡፡

‹‹ንግድ ቢሮ አዋሽ አርባ ከሚገኙ ከብት አደልበው ከሚያቀርቡ አካላት ጋር ሸማች ማኅበራትን አስተሳስሯል፤›› ሲሉ አቶ ዲላሞ አስረድተዋል፡፡

ከከብት አቅርቦት በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሸማቾች በክልል ከተሞች ከሚገኙ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ጋር በማስተሳሰር የስንዴ ዱቄት፣ ዶሮዎች፣ ሽንኩርትና እንቁላል በሰፊው እንዲገበያዩ በመደረጉ የገበያ ዋጋ ንረት እንዳይከሰት መደረጉን አቶ ዲላሞ ተናግረዋል፡፡

ለክብረ በዓሉ ተፈላጊ ከሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶች መካከል ዘይትና ስኳር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በድጎማ የሚቀርብ ዘይት በመላ አገሪቱ እንዲያከፋፍሉ ዘጠኝ መንግሥታዊ፣ የግልና የኢንዶውመንት ኩባንያዎች መመረጣቸው ተገልጿል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ዘይት በማቅረብ ላይ የሚገኙት አልሳም ትሬዲንግ፣ አፋ ትሬዲንግ (ሆራይዘን ፕላንቴሽን)፣ በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ፣ አማሬሳ ዘይት ፋብሪካና አለ በጅምላ ናቸው፡፡

የዘይት አቅርቦት በጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች አለ በጅምላ ተጠቃሚዎችን ማርካት ባለመቻሉ፣ በሆራይዘን ሥር የሚገኘው አፋ ትሬዲንግ ክፍተቱን እንዲሸፍን እየተደረገ መሆኑን አቶ ዲላሞ ጠቁመዋል፡፡

ስኳርን በሚመለከት ለአዲስ አበባ ከተማ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በወር 112 ሺሕ ኩንታል ይከፋፈላል፡፡ ፍላጎትና አቅርቦት ባለመመጣጠኑ አቅርቦቱ 120 ሺሕ ኩንታል እንዲሆን መወሰኑን፣ የከተማው ንግድ ቢሮ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃና ግብይት ዋና የሥራ ሒደት መሪ አቶ ሙሉሸዋ በቀለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹የዱቄትና የዘይት ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ አቶ ሙሉሸዋ ገልጸዋል፡፡ ካለፈው ሳምንት በፊት በ116 ወረዳዎች የሚገኙ ማኅበራት ምርት እንደሌላቸው ገዢዎች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ አቶ ዲላሞ ቅሬታው ትክክል መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን በአቅርቦት ሳይሆን በሥርጭት የሚያጋጥም ችግር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሳምንተ ህማማት ወቅት ግን ይህ ችግር የተፈታ መሆኑንና ንግድ ቢሮው የተለያዩ የቁጥጥር ቡድኖች አቋቁሞ እየተከታተለ ክፍተቶችን እየሞላ እንደነበረ አቶ ዲላሞ አረጋግጠዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት 141 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት 275 ሺሕ አባላት አሏቸው፡፡ ማኅበራቱ አገልግሎት የሚሰጡት ለአባላቶቻቸው ብቻ ሳይሆን፣ ግብይት ለመፈጸም ለሚፈልጉ የከተማው ነዋሪዎች ጭምር ነው፡፡ ማኅበራቱ ለሁሉም ዜጎች አገልግሎት የሚሰጡ በመሆኑና አባላትን ማብዛት ባለመቻላቸው፣ ካፒታላቸውን በሚገባ ማሳደግ እንዳላስቻላቸው አቶ ሙሉሸዋ ገልጸዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ማኅበራት የሚያንቀሳቅሱትን ገንዘብ ለበዓሉ የሚሆኑ ምርቶች ግዥ ፈጽመውበታል፤›› ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች