ለም የሆነው ቀይ አፈር ወድቆ የተገኘ ፍሬ ሁሉ የሚያበቅል ይመስላል፡፡ አቀበታማና ቁልቁለታማ የሆነው ሥፍራው ሙሉ በሙሉ አረንጓዴ ለብሷል፡፡ ከፊሉ የከብቶች ግጦሽ፣ የተቀረው ደግሞ የተለያዩ ጥራጥሬዎችና ሰብሎች ለምተውበታል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የጫካ ቡናም ይለማበታል፡፡ ቦታው ፍፁም አረንጓዴ ነው፡፡
ከማዶ የሚታዩት ሰንሰለታማ ተራሮችም ለሥፍራው ልዩ ሞገስ ሰጥተውታል፡፡ በአዶቤ ተውቦ ለዕይታ እንዲማርክ የተደረገ ፎቶግራፍ እንጂ በእርግጥ በቦታው ተገኝተው በዓይንዎ የሚመለከቱት አይመስልም፡፡ የወፎች ዝማሬ፣ ከዛፍ ዛፍ የሚዘሉት ጦጣዎችና ዝንጀሮዎችም ልዩ የአካባቢው ድምቀት ነበሩ፡፡
የጫካ ቡና ወደሚገኝበት ጎራ አቋርጠን መሄድ ስንጀምር ካፊያ መጣል ይዞ ነበር፡፡ ቦታው ከዳር እስከ ዳር ለበቀሉበት ልዩ ልዩ ሰብሎችና ምርቶች የተመቸ ቢሆንም፣ እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ ያስቸግራል፡፡ ገደላገደልም ይበዛዋል፡፡
የቡና ማሳ ወዳለበት ጫካ ለመግባትም በአንዱ ጎን ተራራ በተቃራኒው ደግሞ ገደል የሚያዋስናትንና በአንዴ ከአንድ ሰው በላይ ማሳለፍ የማትችለውን ቀጭን መንገድ ያዝን፡፡ የተቦረቦረውና የሚያዳልጠው መንገድ ከአሁን አሁን ወደቅን የሚል የጭንቀት ስሜት ያሳድራል፡፡ በእርግጥም በግራና ቀኝ ያሉት ቀጫጭን የቡና ዛፎች ባይኖሩ መውደቃችን አይቀርም ነበር፡፡
ከጅማ ከተማ 14 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ገሩኬ የተባለች ቦታ የተጓዝነው ቅዳሜ መስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ከአሥር በላይ የሚሆኑ ነጮች ማልደው ነበር ገሩኬ የደረሱት፡፡ አብዛኛዎቹ ተመራማሪዎች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑትና በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ገዛኸኝ በሬቻ (ዶ/ር) ከሁሉም በመቅደም ስለ ቦታው እንዲሁም በአካባቢው ስለሚለሙ ምርቶች መረጃ እየሰጡ ይሄዳሉ፡፡ ከኋላቸው የሚከተሏቸው ደግሞ እሳቸው የሚነግሯቸውን ከማዳመጥ ይልቅ ፈታኙን መንገድ ሳይወድቁ ለማለፍ ለሚያደርጉት ትግል ቅድሚያ የሰጡ ይመስላሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንዳይወድቁ በግራና በቀኝ የበቀሉ ተክሎችን የሙጥኝ ብለው እየታከኩ ያልፋሉ፡፡ የሞት ሽረት የሆነባቸው ደግሞ ከዛፍ ዛፍ እንደሚዘሉት ጦጣዎች መሬቱን በእጃቸው ይዘው በአራት እግር ለማለፍ ሞክረዋል፡፡
በተራራማውና ገደላማው የገሩኬ ምድር ከበቀሉ የቡና ዛፎች ፍሬ ለሚለቅሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን መንገዱ የለመዱትና ብዙም የማያስጨንቃቸው ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ በየምርት ወቅቱ ጥሩ ምርት መሰብሰብና በጥሩ ዋጋ መሸጡ ነው፡፡
በገሩኬ ህልውናቸውን በግብርና ላይ ያደረጉ ጥቂት የማይባሉ አባወራዎች ይኖራሉ፡፡ አማካይ የእርሻ ቦታቸው ስፋትም ከአንድ ሔክታር ያነሰ ነው፡፡ ዋነኛ መተዳደሪያቸው የቡና ምርት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በአካባቢው ካለው የጫካ ቡና ይልቅ ሌሎች የአገዳና የሰብል ምርት እርሻዎች ይበልጣሉ፡፡
በ1965 ሜትር ከፍ ብላ የምትገኘው ገሩኬ ከ70 እና 80 ዓመታት በፊት ሙሉ ለሙሉ በጫካ የተሸፈነች እንደነበር ዶክተር ገዛኸኝ ይናገራሉ፡፡ ለነገሩ የተራራው አናት ላይ ሆነው ቁልቁል ሲመለከቱ እውነታውን ማስተዋል አይከብድም፡፡ ገላጣ ሆነው የሚታዩ ሜዳዎች እንዲሁም የእርሻ ማሳዎችና እዚህም እዚያም ተበጣጥሰው የሚታዩ ቋጥኞችና አነስተኛ ጫካዎች አካባቢው ሁነኛ የጫካ ቡና ምንጭ እንደነበር ይመሰክራሉ፡፡
ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ የሚነገርለትን ቡና ምርታማነት ለማሳደግ የተለየ ትኩረት ተደርጎበት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በተለይም ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የጫካ ቡና ምርት መጨመር ከተያዙ ስትራቴጂዎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ ጫካዎች በተመነጠሩ ቁጥር አብረው የሚጠፉ የሥነ ምኅዳር ሀብቶች ብዙ ናቸው፡፡ የጫካ መመንጠር ለጫካ ቡና መጥፋትም ትልቅ ሥጋት ነው፡፡ ‹‹በገሩኬ ያለውን የጫካ ቡና ምርታማነት ለመጨመር የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ እኔም እዚህ አካባቢ የቡናውን ምርታማነት ከፍ እንዲል የአበባ ዓይነትን በመጨመር የንብ ማነብ ፕሮግራም አስጀምሬያለሁ፤›› አሉ ዶክተር ገዛኸኝ ወደ አንዱ አቅጣጫ በእጃቸው እየጠቆሙ፡፡
በዓለም ገበያ የተረጋጋ የቡና ዋጋ አለመኖሩ ለብዙዎቹ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ በቡና ላይ የሚፈጠሩ የተለያዩ በሽታዎች የህልውናው ሥጋት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በስፋት የነበረ አሁንም በከፊል ያለ ኮፊቤሪ የተባለው የቡና በሽታ ትልቁ ፈተና ነው፡፡ አንዳንዴ ገበሬዎች “ኮሌራ” ይሉታል፡፡ ይኼ ቡናን በጣም በማጥቃት የሚታወቅ ነው፡፡
ሌላውና በጣም አስቸጋሪው ‹‹ኮፊ ዊልት ዲዚዝ›› የተባለው የቡና በሽታ ነው፡፡ ይኼ በሽታ አንዴ ከተከሰተ አይድንም፡፡ ያለው አማራጭ ወደ ሌላ እንዳይዛመት በሽታው የያዘውን ግንድ ነቅሎ ማቃጠል ነው፡፡ ሌላው ኮፊ ሊፈረስት የሚባለው ነው፡፡ ይኼ በሽታ ለአገሪቱ በተለይም ካለው የአየር ለውጥና ከሙቀቱ ጋር ተዳምሮ ትልቅ ሥጋት ሆኗል፡፡
ከዚህ ቀደም እንደ ቴፒና በበቃ ባሉ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ብቻ ይታይ የነበረው ችግር አሁን ወደ ሌሎቹ የቡና አብቃይ ቦታዎች በስፋት እየታየ ነው፡፡ በዓለም ደረጃም አንደኛ ሥጋት ነው፡፡ ለምሳሌ ከዓመት በፊት 34 በመቶ የሚሆነው የኮሎምቢያ ቡና በዚህ በሽታ ምክንያት እንዲወገድ ተደርጓል፡፡
እንዲህ ላሉ ችግሮች መፍትሔ መስጠት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተነድፈው እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የቤልጅየም መንግሥት ፋይናንስ የሚያደርገውና በአምስት የቤልጅየም ዩኒቨርሲቲዎችና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የሚተገበረው የቭሊር አይዩሲ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ ፕሮግራሙን በማስተባበር ረገድ የቤልጅየሙ ገንት ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነቱን ወስዶ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ላለፉት 12 ዓመታት ሲተገበር የቆየው የቭሊር አዩሲ (Institutional University Collaboration With Jimma University) ፕሮጀክት 118 ሚሊዮን ዩሮ በጀት ተይዞለት ሲተገበር የቆየ ነው፡፡ በሥሩ ሰባት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ሲያስተገብርም ቆይቷል፡፡
በቡና ምርምር ላይ የሚሠራውን የኢኮሎጂ ፕሮግራም ጨምሮ፣ ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታዎች፣ የሕፃናት ጤናና ሥርዓተ ምግብ፣ እንደ ወባ ባሉ በሽታዎች ላይ የሚሠራ ኢንፌክሺየስ ዲዚዝ፣ የአፈር ለምነት፣ የተለያዩ ማኅበራዊና ፆታዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በአይሲቲ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት መጠናቀቁ ይፋ ሆኗል፡፡
ባለፉት 12 ዓመታት ፕሮግራሙን በማስተባበር ሲሠሩ የቆዩት ፕሮፌሰር ሉክ ዱሻቱ ፕሮጀክቱ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቁን፣ ተቋማዊ አቅም በመገንባት ረገድም ትልቅ ሥራ መሥራት እንደተቻለ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከፕሮግራሙ ዓላማዎች መካከል የዩኒቨርሲቲውን አቅም መገንባት አንዱ ነው፡፡ የተማረ የሰው ኃይል በማጠናከር ረገድ የድኅረ ምረቃና የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞች የትምህርት ዕድል በመስጠት ጥሩ ለውጥ መፍጠር ተችሏል፤›› ያሉት የፕሮግራሙ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ኤባ ናቸው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ በፕሮግራሙ ከ50 በላይ የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት ዕድል ማግኘት ተችሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 25ቱ ጥናታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል፡፡ የተቀሩትም በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በስድስት ፋኩልቲዎች ማለትም በቬትርነሪ ሜድስን፣ በአኒማል ሄልዝ ኤንድ ኒውትሪሽን፣ በቻይልድ ሄልዝ ኤንድ ኒውትሪሽንና በመሳሰሉት የድኅረ ምረቃ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ የሆኑም ጥቂት አይባሉም፡፡ በፕሮግራሙ ከ100 በላይ የቤልጅየም ፕሮፌሰሮች አብረው ምርምር በመሥራት የተሳተፉ ሲሆን፣ አጋጣሚው የምርምርና አብሮ የመሥራት ባህሉን አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል ያደረገውም ነበር፡፡
ጥናቶች በሚደረጉበት ጊዜ ያሉትን ችግሮች ለይቶ በማውጣት ምላሽ የመስጠት ሥራዎች እንደተሠሩ አቶ ካሳሁን ይናገራሉ፡፡ ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች ዴስክ የማሟላት፣ የመጠጥ ውኃ እንዲያገኙ የማድረግ፣ መፀዳጃ ቤቶችን የማስገንባት ሥራዎች ማኅበረሰቡ ላይ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከዚህ ባሻገርም የላቀ ምርምር ለመሥራት የሚረዱ የምርምር መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ አጋጣሚው ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ በተለይ ለሞለኪውላር ባዮሎጂ፣ ለማይክሮ ባክቴሪያ፣ ድረግ ኳሊቲ ላቦራቶሪ ምርምር የሚረዱ ላቦራቶሪዎችን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እንደተቋቋመና በዚህም ለውጥ መፍጠር እንደተቻለ አቶ ካሳሁን ይናገራሉ፡፡
በሥራው ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ለምርምር የሚሆኑ የተለያዩ ኬሚካሎችና ልዩ ልዩ ግብዓቶች በተገቢው መንገድ አለመገኘት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህም የምርምር ሥራዎች በተገቢው ጊዜ እንዳያልቁና በሥራ ላይ መንጓተት እንዲፈጠር ምክንያት ነበሩ፡፡
የመጀመርያው ፕሮጀክት እንደተጠናቀቀም በአገሪቱ የሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያሳትፈው ሁለተኛው ፕሮግራም ተጀምሯል፡፡ አዲሱ ፕሮጀክት አምቦ፣ ሐዋሳ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ዓላማውም ጅማ ዩኒቨርሲቲ በመጀመርያው ፕሮጀክት ያካበተውን ልምድ እንዲያካፍል ማድረግ ነው፡፡ “Universities Collaboration For Better Health Ethiopia” የሚል ስያሜ የተሰጠው ፕሮግራሙ፣ በጤና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፡፡
ይህም የሆነው በዩኒቨርሲቲው ሲተገበሩ ከቆዩ ፕሮጀክቶች መካከል በጤናው ላይ የላቀ ውጤት በመመዝገቡ እንደሆነ አቶ ካሳሁን ያብራራሉ፡፡ ለአሥር ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ለጊዜው ስምምነቱ የተፈጸመው ለመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ነው፡፡ የቀጣዩ አምስት ዓመታት የሚወሰነው የዚህኛው ውጤታማነት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ‹‹ይህኛው ፕሮግራም ከበድ ይላል፡፡ ምክንያቱም የተመደበው በጀት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለመጀመርያው የተመደበው ስምንት ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፣ ለዚህኛው ፕሮጀክት ደግሞ 2.5 ሚሊዮን ዩሮ ወይም በየዓመቱ 250,000 ዩሮ ብቻ ነው፤›› ያሉት ፕሮፌሰር ሉክ የበጀቱ አነስተኛ መሆን እንዳሳሰባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡