ሰላም! ሰላም! ሰው ዘንድሮ ምን እንደበላ ወይ ምን እንዳበሉት አላውቅም፣ ከራስ በላይ አዋቂ ሆኗል። ለራስ የሚያውቅ ጠፍቶ ምክር በዱላ በሆነበት አገር ሰው ለመምከር የሚያዘው ሠልፍ የታክሲ ሠልፍ ያስንቃል። እውነቴን ነው የምላችሁ። እናት ልጃቸው ሞተ አሉ። በዕንባ ዓይናቸው ሊጠፋ ደረሰ። ኋላ ቀብረው ሲመለሱ ማልቀሱን ትተው ኩላቸውን ተኳሉ። ወዳጅ ዘመድ ነኝ ባይ አሽሟጠጣቸው። በኩሉ ነዋ። ኋላ ምን አሉ? ‹‹እንግዲህ ከእኔ የቀረበው ሄዶ ለእናቱ ይንገራት፤›› ሲሉ፣ ከእናት በላይ አውቃለሁ ያለ አፉ እንደተጠመዘዘ ቀረ። ታዲያ እኔን እኮ የከበደኝ ይኼ ነው። ድሮ ድሮ ሰው አንድ ነገር ብሎ ተንኩሷችሁ የመልስ ምት ስትሰነዝሩለት ገብቶት ዝም ይል ነበር። የዛሬ ሰው ግን እሱና እሱ ብቻ ከሚያስበውና ከሚያወራው በላይ ሌላው የሚለውን መስሚያ የለው። ‹መስሚያዬ ጥጥ ነው› ሲል ለካ ትውልዱ ወዶ አይደለም አትሉም?
እናላችሁ በቀደም አንዱ፣ ‹‹አንበርብር ለምን ለራስህ አታውቅም?›› አለኝ። ይኼውላችሁ ነገር ፍለጋ። ‹‹እሺ ምን ብዬ ልወቅ?›› ስለው፣ ‹‹አለ የተባለ ሁላ ገንዘቡን ወደ ውጭ አገር እያሸሸ በዶላርና በዮሮ እያስቀመጠ አንተ ለምንድነው ዝም ብለህ የምታየው? ይኼ አገር ተስፋ አለው ብለህ?›› ብሎ ገና ምንም ሳልለው በአገሬና በእኔ ላይ እኩል ሳቀ። ‹‹አይ ምን መሰለህ . . . ምናምን . . .›› እያልኩ ገና መናገር ስጀምር፣ ‹‹ዝም ብለህ እኔን ብትሰማኝ ይሻልሃል። ከአንተ የበለጠ ስለገንዘብ የሚያውቅ የለም። ምን አለፋህ ይኼን አገር አምነህ የላብህን ለማንም ከምትበትነው አሽሸው . . .›› ሲለኝ ቀስ ብዬ እንደምንም ሰበብ አሳብቤ ከእሱ ከራሱ ሸሸሁ። ለዓይን ከአፍንጫ የቀረበ አለ እስኪ አሁን? ታዲያ ምን ዓይነት ልክፍት ነው አፍ አፋችንን እያለ አላስቀምጥ የሚለን? ኧረ ምን ጉድ ነው!
መቼም ይህቺ ጨዋታ ብዙ ሳታስወራን አትቀርም። ከራስ በላይ ራሳችን ንፋሱን ካላሸነፍን እያሉ የሚገጥሙት ትግል ለማን ልንገረው የሚያስብል ነው። ይኼውላችሁ እኛ ሠፈር አንድ የጎረቤቴ ልጅ አለች። ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ ዘንድሮማ ካላገባች ጉድ ነው ይባባላል መንደርተኛው። ከሚባባለው መሀል ደግሞ ስንቱ መሰላችሁ ተፋቶ የሚኖረው። ልጅቷ መቼም ሲፈጥራት ውብ ናት። አንድ ቀን ተስቶኝ ማንጠግቦሽ ፊት ስለዚችው ሸጋ ልጅ ሲወራ፣ ውቤ ከረሜላ የተዘፈነው መቼም ለእሷ መሆን አለበት፤›› ብዬ ሳምንት ሙሉ ምስር ብቻ በልቻለሁ። ኩርፊያ መሆኑ ነዋ። መቼም የማትቀና ሚስት ስጠኝ አይባል ነገር። ሚስት ለባሏ፣ ባል ለሚስቱ፣ ዜጋ ለአገሩ፣ አገር ለዜጎቿ ካልተቀና ምኑን ኑሮ ምኑን ትዳር ይባላል? ታዲያ ይህቺው ትዳር ፈላጊ ስትወጣ ስትገባ ያም ያም አውቆ፣ ጓደኛሽን አታስተዋውቂንም እንዴ አንቺ? የት ነው የምትደብቂው›› እያለ ይጠዘጥዛታል።
ልጅት ደግሞ ‹ማማዬ ማማዬ . . .› ሲዘፈን ተወልዳ መሥፈርቷ በቡጢ የማይማታ፣ የት ወጣሽ የት ገባሽ የማያበዛና እንዲያው ኮራ ያለውን ነው ምትፈልገው። ትወጣና መንገድ መንገዱን ስታይ ትውላለች። አንቺ ልጅ ማግባት የምትፈልጊው ትራፊክ ነው መንገደኛ? እያሉ እናቷ ሳይቀሩ ያሾፋሉ። እህሳ? መንገዱ ግጭት ብቻ አይደል? ነጂው ይጋጫል። እግረኛውም ይሞታል። ይኼን ዓይታ አላገባም አለች። ለምን? ስትባል፣ ‹‹ከዚህ ሁሉ ገጪና ተገጪ አንዱ ባሌ ቢሆን መንገድና ዓመል አይለቅምና ማታ ቤቱ ገብቶ ነይ ልግጪሽ ማለቱ አይቀርም፤›› ብላ አረፈችው። ጉድ እኮ ነው? ይኼ ወሬ ተነዛ ማለት እንግዲህ አስቡት። በትራፊክ አደጋ አንደኛ መሆናችን አልበቃ ብሎ ባለመጋባት ሰንጠረዥም ቀዳሚ ልሆን ነው ማለት ነው? ወይ እነ ማማዬ!
ለማንኛውም ዕድልና ትግል በሁለት ተቃራኒ የዕጣ ፈንታ መስመር ዕጣ ሲጣጣሉብን እንደርሳለን። ምን ሆነ መሰላችሁ? ማንጠግቦሽ ለውድ ባለቤቷ አምበርብር ምንተስኖት ምሳ ለማቅረብ ጓዳዋን ትንጎዳጉዳለች። አልፎ አልፎ በብስጭት፣ ‹‹ኤድያ ዘንድሮስ. . .›› ስትል እሰማታለሁ። አሳዝናኝ፣ ‹‹አይዞሽ እናቴ እኛ ጤና፣ ጤና እኮ ይበልጣል?›› ስላት፣ ‹‹ምን አባቱንስ ጥንቅር ይላል እንጂ ጤናንማ አናጣም፤›› ስትለኝ ደስታ የውስጤን ጉብጠት ያቃናዋል። ይብላኝ ላላገባ እንጂ ሚስት ያለውማ ይኼው እንደዚህ አይዞህ ሲባል በአንዴ ሌላ ሰው ይሆናል። ‹ሴት የላከው ሞት አይፈራም› አይደል? አሁን ደግሞ ሴት ያፀናው ኪሳራ አይፈራም፣ ቫት አይፈራም፣ ብድር አይፈራም ይባላል አሉ። ጉድ እኮ ነው። እና ምንድን ነበር የምናወራው? አዎ መታደልና ትግል ስላችሁ ነበር።
ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ይልቅ እስካሁን ሳልነግርህ?›› ብላ ወሬ ጀመረች። ‹‹ምኑን ማንጠግቦሽዬ?›› ስላት፣ ‹‹እስኪ እንደገና በለኝ?›› ‹‹ምንድነው የምልሽ?›› ስላት፣ ‹‹አሁን ያልከኝን›› ስትለኝ፣ ‹‹ምን ማንጠግቦሽዬ?››፣ ‹‹አዎ እሱን››፣ ‹‹ማንጠግቦሽዬን?››፣ ‹‹ወይዬ? ለምንድን ነው ግን እንዲህ ለረጅም ጊዜ የተውከው?›› ብላ ከንፈሬን ስትነክሰው የጎረቤታችን ሚስት ሠፈሩን በጩኸት ቀውጢ ስታደርገው አንድ ሆነ። ተሯሩጠን ስንወጣ ከቅንድቧ አካባቢ ቡልቅ እያለ ደም ይፈሳል። የታደለው ከንፈር ሲነካከስ ትዳር ትግል የሆነበት ደግሞ ዘንድሮም በዚህ በሠለጠነ ጊዜ ይቧቀሳል። እኛ ደግሞ ጥሎብን የሚቀናን የጨበጣ ውጊያ፣ ሠልፍና ፍቅር ነው። ምን እንደሚሻለን ብቻ እንጃ!
ካነሳሁት አይቀር ታዲያ ከሰሞኑን ገጠመኜ ጋር አስማምቼ ይኼን የፍቅር ነገር ልፍተለው። በመጀመሪያ እንደ ነገርኳችሁ የዘንድሮ ሰው ትዳር በሁለት የተከፈለ ነው፡፡ ምንና ምን? በጣም ጥሩ! ምን ሆነ መሰላችሁ ሁለት አዲስ ሙሽሮች መሆናቸው ነው። ከተጋቡ ገና አንድ ዓመታቸው ነው። በተጋቡ በስድስት ወራቸው ኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ወጥቶላቸዋል። በዚህ አያያዛቸው ገና ለእኛ ይተርፋሉ ሲል ቤተ ዘመድ እንዳልኳችሁ ‹አንቨርሰሪ› ደረሰ። በአማርኛ ፍቅራቸው የተጀመረበት ቀን ዓውደ ዓመት ማለት ነው። ያዛችሁኝ? ከዛስ? እንኳን አደረሳችሁ ልትል የሚስት ጓደኛ ከተፍ። በሉ ጠጡ፣ ሳቁ ዘፈኑ፣ ዘፈኑ ጠጡ፣ ጠጡ።
‹‹ለምን እኛ ጋ አታድሪም ዛሬ?›› በማለት ሚስት ወዳጇን ስትጠየቅ። እሺ አለቻት፡፡ መስማማት። ማደር። ባል ሌሊት የሚስቱ ጓደኛ የተኛችበት ክፍል ዘው ማለት። ውሎ አድሮ የሚስት አብሮ አደግ ሆድ መግፋት። ነገሩ ፍርጥርጡ ሲወጣ ያቺ ኮንዶሚኒየም ቤት ለሽያጭ ቀረበች። አንበርብር የተጠራውና ነገረ ታሪኩን የሰማው ይኼኔ ነው። አይገርምም ግን? ‹‹የባሻዬ ልጅ ይኼን ታሪክ ሰምቶ ምን እባክህ የዘንድሮ ትዳር ራዳር የሌለው የአየር ክልል ሆኗል፤›› አለኝ። ሳቅ ብዬ ምን ማለት ነው? ስለው፣ ‹‹በቃ በአየር ክልሉ ውስጥ የሚበሩ ብዙ ነፍሶች አሉ። ገሳጭና፣ ገዢ፣ ቆንጣጭ እሴቶች እያደር ተረስተው ተረስተው፣ በየጓዳው በየቤቱ የማትሰማው የማታየው ጉድ የለም እኮ፤›› ብሎኝ ብክንክን አለ። ‹ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም› ያለው ጥላሁን ገሰሰ ወዶ አይደለም? ግን እንዲያው እንዲህ የትዳርና የአገር ጉዳይ ቅልል ያለብን ለምን ይሆን?
በሉ እንሰነባበት! የሚያተርፈው አትርፎ የሚከስረው ከስሮ በብቅል ጭማቂ የትካዜ አምሮቱን፣ የጨዋታ ጉጉቱን ሊወጣ የሰርክ መቃጠሪያችንን ግሮሰሪ የሚሏት አለችን። አስቴር አወቀ ‹ወይ ኑሮ ወይ ኑሮ . . .› ትላለች። አድማጭ እንዲያ በይ እያለ ይወዛወዘል። ‹ሀብታም ደሃ ሳይል ሁሉን አስተካዡ . . .› ስትል ጋባዥና ተጋባዥ ብርጭቆውን እኩል እያነሳ ይውረገረጋል። የባሻዬ ልጅና እኔ ጥጋችንን ይዘን በትዝብት ስንቀላውጥ አንድ የሚያውቀን ግን የማናውቀው ሰው ጠጋ ብሎ፣ ‹‹መታዘብ ክልክል ነው፤›› ብሎ ጆሯችን ላይ ጮኸ። የባሻዬ ልጅ ጠጋ ብሎ በጆሮዬ፣ ‹‹በዓለም ላይ ሐበሻ ብቻ እንደሆነ ታውቃለህ ከሰኞ እስከ ሰኞ የሚጠጣው?›› ይለኛል።
‹‹ኑሮ . . .›› አልኩት ከአስቴር አወቀ ኮርጄ። ይኼን ስለው፣ ‹‹ኀሊናና ሆድ አላረጅ እያሉ ዕድሜ ፍሬን እንደ በጠሰ መኪና ቁልቁል ወደ ማብቂያው ሲገሰግስ ስታይ፣ አንዳንዴ አንተም ብትሆን እኮ መተንፈሻ ያምረሃል . . .›› እያለኝ ሳለ ደግሞ ሌላው ብድግ ብሎ፣ ‹‹አንዱ እኮ ነው ስም አልጠራም። ደግሞ እኮ አብሮ አደጌ ነው። ምጥ እንደ ያዛት ሴት በጭንቅ በጥብ እግሬ ላይ ወድቆ ቤትህን አስይዘህ ብር ካልተበደርክልኝ አለኝ። በወር በሁለት ወር ውስጥ ካልመለስኩልህ ከምላሴ ፀጉር አለ። በአብሮ አደግ ይጨከናል?›› ሲል አድማጩ በተማሪ ቤት ድምፅ ‹‹አይጨከንም!›› ይላል። እኔም አልጨከንኩም። ‹‹በወሩ ምን ሰማህ አትሉኝም?›› ሲል አሁንም ጀማው ‹‹ምን?›› ይለዋል። ‹‹አሜሪካ ገብቷል ለካ? እኔና ቤቴ ሐራጅ ቀርበናል ለካ?›› ሲል የሆታ ሳቅና ፉጨት ተከተለው። ሁሉም ብርጭቆውን አንስቶ ‹ቺርስ› ሲለው እኔና የባሻዬ ልጅ ተያይተን በሐዘኔታ አንገታችንን ነቀነቅን። ክህደት፣ እምነት፣ ፍቅር፣ ደባ፣ ማጣትና ማግኘት በየቤቱ ስንቱን ታሪክ ፈትለው ስንቱን እንደ ሸመኑት ለማሰብ ስሞክር ራሴ ሊፈነዳ ደረሰ። ኧረ ጀማው እስቲ እንደማመጥ? ሰውየው ብሶቱን ሲተርክ ልክ እንደ ፌስቡክ ታዳሚዎች ‹ላይክ›፣ የሆታ ‹ላይክ› ሲርከፈከፍበት አንገቱን እየወዘወዘ ጥጉን ያዘ፡፡ መልካም ሰንበት!