Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየባህል ገበታው

የባህል ገበታው

ቀን:

‹‹መስቀልን በጉራጌ›› በሚል ከመስከረም 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በደቡብ ምዕራባዊቷ ኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ፌስቲቫል እስከ መስቀል በዓል ይዘልቃል፡፡ ቤተ ጉራጌዎችን ጨምሮ በመላው ደቡብ በድምቀት የሚከበረውን የመስቀል በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ፌስቲቫል ለመስቀል የሚከናወኑ ባህላዊ ሥርዓቶች በወልቂጤ ከተማ የሚታዩበት እንደሆነ ከአዘጋጆቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

መስቀል በኢትዮጵያ ሲከበር ልዩ ልዩ መጠሪያ አለው፡፡ በዓሉ በአማራና በትግራይ መስቀል ሲባል፣ በተለያዩ ብሔረሰቦች እንደየአካባቢው ቋንቋ የተለያየ መጠርያ አለው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሞ ‹‹ጉባ›› ወይም ‹‹መስቀላ››፣ በሐድያ፣ በወላይታ፣ በዳውሮና በጋሞ ‹‹መስቀላ››፣ በከምባታ ‹‹መሳላ››፣ በየም ‹‹ሔቦ››፣ በጉራጌ ‹‹መስቀር››፣ በካፊቾ እና ሻኪቾ ‹‹መሽቀሮ›› ይባላል፡፡

 በዓሉ በደቡብ ክልል ሲከበር፣ ለሥራ፣ ለትምህርትና በሌላም ምክንያት የትውልድ ቀያቸውን ለቀው ወደ ሌላ አገር  የሄዱ የአካባቢው ተወላጆች ወደ መንደራቸው መመለሳቸውን ጨምሮ ከመስቀል ጋር የሚያያዙ ሥርዓቶች በርካታ ናቸው፡፡ የ‹‹መስቀልን በጉራጌ›› ፌስቲቫል ትኩረትም ይኸው ነው፡፡

በመላው ክርስቲያኖች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል በዓል (በምሥራቆች መስከረም 4 ቀን ተከብሯል) በተለይ በደቡብ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን፣ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ጎን ለጎን ባህላዊ እሴቶችም የበዓሉ መገለጫ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የቤተ ጉራጌ ተወላጆች ከሌላው ወቅት በበለጠ ወደ ትውልድ ቀያቸው በመመለስ የሚያከብሩት በዓል ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የደመራ ሥነ ሥርዓቱና የዕድሜ ባለፀጎች ምርቃት በዓሉን ልዩ ያደርጉታል፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው የዕድሜ ባለፀጎች የምርቃት ሥነ ሥርዓት በፌስቲቫሉ ለዕይታ ከሚበቁ ባህላዊ እሴቶች አንዱ ሲሆን፣ የተለያዩ የማኅበረሰቡ አባላት ለበዓሉ የሚያደርጉት ዝግጅትና የደመራ ሥነ ሥርዓትም የመርሐ ግብሩ አካል ናቸው፡፡ የቤተ ጉራጌ የመስቀል አከባበር ያለውን አገርና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማሳደግ በፌስቲቫሉ የጆካ ባህላዊ የፍትሕ አሰጣጥና የዳኝነት ሥነ ሥርዓትም ይቀርባል፡፡ አዘጋጆቹ የበርካቶችን ቀልብ ይስባል ብለው ያመኑት ግን ለመስቀል የሚሰናዱ ምግቦች ከዝግጅት አንስቶ እስከ አመጋገብ ያለውን ሒደት ነው፡፡

መስቀልን ልዩ ከሚያደርጉ ባህላዊ ምግቦች መካከል ክትፎ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡ ክትፎ ተዘጋጅቶ ለተመጋቢዎች እስከሚቀርብ ያለው ባህላዊ ሥርዓት ማራኪ ነው፡፡ ክትፎ ከማኅበረሰቡ በዘለለ በአገር ውስጥና በውጪም ከሚወደዱ ምግቦች አንዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ አገሮች ሼፎችም ከኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች መካከል በተቀዳሚነት ይመርጡታል፡፡ ፉድሪፐብሊክ በተባለውና የተለያዩ አገሮች ምግቦች የሚተዋወቁበት ድረ ገጽ ከሰፈሩ የምግብ ዝርዝሮች መካከል ክትፎ ይገኝበታል፡፡ በድረ ገጹ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች በዓለም እየታወቁ መምጣታቸው ተገልጾ፣ የአሜሪካው ተከታይ ሲትኮም ‹‹ዘ ሲምሰንስ›› አንድ ክፍል የኢትዮጵያን ምግብ ያማከለ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ከፊልሙ ዋና ገፀ ባህሪያት አንዷ ማርጅ ልጆቿን ወደ ኢትዮጵያ ሬስቶራንት ወስዳ በአንድ ማዕድ የኢትዮጵያን ምግብ ከተቋደሱ በኋላ፣ በመብል ወቅት የተለመደውን ጉርሻ ተለዋውጠዋል፡፡ በድረ ገጹ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ምግቦች ቅመም የበዛባቸው መሆናቸው ልዩ ጣዕም እንደሚሰጣቸው ተመልክቷል፡፡

‹‹ክትፎን ልዩ የሚያደርገው የቅቤውና የሚጥሚጣው ውህድ ነው፡፡ ማባያ ቆጮው፣ አይቤና ጎመኑም ክትፎን ተወዳጅ ያደርጉታል፤›› በማለት ነበር ስለምግቡ በድረ ገጹ የተነበበው፡፡ ክትፎ ምግቡ በበዓላትና በልዩ መሰናዶዎች የሚዘወተረውም ለዚሁ ነው ይላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተዘወተሩ የመጡ እንደ ቴስት ኦፍ አዲስ ያሉ የምግብ ፌስቲቫሎች የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ዕውቅና እያሳደጉ ነው፡፡ የሙዚቃም ይሁን የሌሎች ኪነ ጥበባት መርሐ ግብሮች ሲዘጋጁም ኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ የተካኑ ሬስቶራንቶች ይሳተፋሉ፡፡ ምግቦችም ያስቀምሳሉ፡፡

በቴሌቪዥን የሚተላለፉ የምግብ ዝግጅቶች የቱባ ባህሉ ባለቤቶች ባህላዊ ምግቦችን የሚያሰናዱበትን መንገድ በማስተዋወቅ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንደ ማርከስ ሳሙኤልሰን ያሉ ኢትዮጵያዊ ደም ያላቸው ዓለም አቀፍ ሼፎች ያላቸው ሚናም ቀላል አይደለም፡፡

ከእንሰት ተክል የሚዘጋጀው ቆጮ ክትፎን አጅበው በተመጋቢ ማዕድ ከሚቀርቡት ውስጥ ነው፡፡ በመስቀል ወቅት በሚዘጋጀው መጠን ባይሆንም በሌሎች ጊዜያትም የሚሰናዳ ሲሆን፣ ሒደቱ ዘለግ ያለ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ደቆ የተከተፈ ጎመን በቅቤና አይብም ገበታውን ያጣፍጡታል፡፡ የክትፎ ዝግጅትና በሚቀርብበት ወቅት አገልግሎት ላይ የሚውሉ እንደ ጣባ ያሉ ባህላዊ ቁሳቁሶችን ያስተዋሉ ዓለም አቀፍ ሼፎች ክትፎን ከዶሮ ወጥና ጥብስ ጋር የአገሪቱ መገለጫ አድርገው ይወስዱታል፡፡

እንሰት በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ ከሚሰጣቸው ተክሎች አንዱ መሆኑን ከግምት በማስገባት ሰይፉ ኃይሌ የተባሉ ተመራማሪ በኖርዌይ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ትሮምሶ ‹‹እንሰት፤ ሶል ኦፍ ዘ ጉራጌ›› (እንሰት፤ የጉራጌ ህልውና) የሚል የጥናት ጽሑፍና ፊልምም አዘጋጅተዋል፡፡ ከእንሰት የሚዘጋጁት ቡላና አሚቾም ከቆጮ ባሻገር ይታወቃሉ፡፡

 የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ካሰፈራቸው የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የመስቀል በዓል፣ ልዩ ልዩ ምግቦች የሚዘጋጁበት ወቅት ነው፡፡ የደመራ ሥነ ሥርዓትና የመስቀል በዓል በዋነኛነት መስከረም 16 እና 17 ቀን ቢከበርም፣ በደቡብ በዓሉ ከሁለቱ ቀናት በዘለለ ይከበራል፡፡ ለቀናት በሚዘልቀው የመስቀል አከባበር አካል ከሆኑ ባህላዊ ክንውኖችም የምግብ ሥርዓቱ ዋናውን ድርሻ ይይዛል፡፡

መስቀል ከሚከበርበት ቀን በፊትና በኋላም ከሚከናወኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ጎን ለጎን ባህላዊ እሴቶችም ድርሻ አላቸው፡፡ የምግብ ባህል የአንድ ማኅበረሰብ መገለጫ ከሆኑ እሴቶች አንዱ እንደመሆኑም በዓሉን የማድመቅ ሚናን ይጫወታል፡፡ ለምሳሌ ጋሞ ጎፋ አካባቢ ለመስቀል በዓል የሚዘጋጁ ምግቦች ትልቅ ቦታ ስለሚሰጣቸው መሰናዶ ከሳምንታት በፊት ይጀመራል፡፡

ወንዶች ከበዓሉ ቀደም ብለው በግ ወይም በሬ የሚገዙበት ገንዘብ ማጠራቀም ሲጀምሩ ሴቶች ደግሞ የቅቤ መግዣ ብር መቆጠቡን ይያያዙታል፡፡ በዓሉ ሲደርስ ሁሉም በየቤቱ ያሰናዳውን ከወዳጅ ዘመድና ከጎረቤቱ ጋር ይካፈላል፡፡ በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚያመሳስለው ሥርዓት እንዳለ ሁሉ፣ አንዱን ማኅበረሰብ ከሌላው የሚለዩ እሴቶችም ይጠቀሳሉ፡፡

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የባህላዊ ቅርሶች መድበል እንደተገለጸው፣ በሸከቾ ብሔረሰብ የማሽቃሮ በዓል አሮጌ ዓመት አልፎ አዲስ ዓመት መቀበያ ተደርጎ ይከበራል፡፡ የሚከበረው ከመስከረም 16 ቀን ጀምሮ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ ቆጮ ተፍቆ ይዘጋጃል፣ ጠጅ ይጣላል፣ ጠላ ይዘጋጃል ለእርድ የሚሆን ከብትም ይዘጋጃል፡፡ በበዓሉ ቀን ጧፍ በማብራት በየጓዳው በየእህል ማስቀመጫው ይዞ በመግባት ‹‹መጥፎ ነገር ከቤት ውጣ፣ ሀብት ግባ›› እያሉ ከመረቁ በኋላ ጎረቤት ተጠራርቶና ተሰባስቦ ችቦ ይበራል፡፡ በነጋታው የእርድ ሥርዓት የሚከናወን ሲሆን ቤተሰብና ጎረቤት በመስቀል ይጠራራል፤ ይገባበዛል፡፡

አቆጣጠሩ በዋናነት ባህላዊ ሲሆን አዲስ ዘመን የሚጀምረውም መስከረም 17 ከሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓል (መሽቀሮ) ላይ ነው፡፡ መሽቀሮ በብሔረሰቡ አባላት ዘንድ ከዋዜማው ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል በድምቀት የሚከበር በዓል ሲሆን፣ መስከረም 16 ምሽት ላይ የባህላዊ እምነት መሪው፣ እሱ በሥፍራው ከሌለም ታዋቂ የሆነ የአገር ሽማግሌ ቤት ውስጥ በዓሉን አስመልክቶ የተዘጋጀ ዳቦ ይበላል፡፡ ቡና በቅቤና ዶጮ (ቦርዴ ጠላ) ይጠጣል፡፡ ከዚያም ከበሮ እየተመታ ይዘፈናል፣ ይጨፈራል፡፡

የደመራ በዓሉም የሚበከረው በባህላዊ እምነት መሪው ግቢ ውስጥ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ሰው ችቦ በየቤቱ ለኩሶ በራሱ ቤት ዙሪያ በመዞር ድህነት ውጣ፣ ሀብት ግባ ብሎ መልካም ምኞቹን ከገለጸ በኋላ የተቀጣጠለውን ችቦ የባህላዊ እምነት መሪው ግቢ በተዘጋጀው ደመራ ላይ ወስዶ ይለኩሳል፡፡ በማግስቱ ሰንጋ ይታረድና የደመራው እሳት በነደደበት ቦታ ላይ እሳቱን ለማቀዝቀዝ ሲባል ደም ይፈስበታል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ደሙን በእጁ መንካትና ከአመድ ጋር በመለወስ ግንባሩ ላይ ይቀባል፡፡

በኢሮብ ብሔረሰብ በዓሉ ከመድረሱ በፊት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ለከብት የሚሆን ግጦሽ መሬት ከማንኛውም እንስሳ ይከለከላል፡፡ ከመስከረም መጀመርያ አንስቶ ወጣቶች ለበዓሉ የሚሆኑ ጌጣ ጌጦችን፣ ከበሮ፣ ችቦ ወዘተ ያዘጋጃሉ፡፡ አባቶችና እናቶች ለበዓሉ የሚሆን ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡

ለከብቶች ቀንድና ሻኛ መቀብያ ቅቤ ይዘጋጃል፡፡ ለቤተሰብም እንዲሁ፡፡
ወንዶች፣ ልጃገረዶችና ሙሽራዎች ለውበትና ባህላዊ ጨዋታ ልዩ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ከመስከረም 15 ወደ 16 በሚያነጋው ለሊት በግምት ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ከብቶቹ ለግጦሽ ተሰማርተው ከጧቱ 12 ሰዓት አካባቢ ወደ በረታቸው ይመለሳሉ፡፡ ፈርጠም ፈርጠም ያሉ ወጣቶችና ጎረምሳዎች ከብቶችን አንድ በአንድ መያዝ ይጀምራሉ፡፡ ሴቶች በእልልታ አጅበው ያልነጠረ ቅቤ ያቀርባሉ፡፡ ታላላቆቹ ፀሎት አድርሰው ከብቶቹን እየመረቁና ባህላዊ ግጥሞችን እየገጠሙላቸው ቀንዳቸው፣ ሻኛቸውና ጀርባቸውን ባልነጠረ ቅቤ ይቀባሉ፡፡

 ይህን ካደረጉ በኋላ የሙሉ ቤተሰብ አባላት ያልነጠረ ቅቤ ተቀብተው በልዩ ልዩ ቅርፃ ቅርፅ የተዋበውን በነጠረና በተቃመመ ቅቤ የተሠራ ገንፎ ቁርስ ይበላሉ፡፡ ወንዶች ከብቶቻቸውንና የሚታረድ በግ ወይም ፍየል ይዘው መስቀል የሚከበርበት መንደር ይሄዳሉ፡፡

በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ሲደርሱ እንጨት ይለቀማል፡፡ እንስሳው የሚታረድበት የልዩ ዛፍ ቅጠል ወይም ድንጋይ ምንጣፍ ይዘጋጃል፡፡ የመንደር ሰዎች ከተሰበሰቡ በኋላ በዕድሜ የገፋው የባህል አዋቂ ተመርጦ ፀሎት ይመራል፡፡

 በመቀጠል እንጨት በእኩል አንድ ሜትር ተኩል ተቆርጦ ከመሬት 4 ሳ.ሜ ከፍ ተድርጎ በአራት መዓዘን ይደረደርና በላዩ ላይ ትንንሽ እኩል መጠን ያለው ባልጩት ድንጋይ ወይም ጠንካራ ጥቁር ድንጋይ ይደረደራል፡፡ ንፋስ የሚነፍስበት አቅጣጫ ታይቶ እሳት ይለኮስበታል፡፡ ሥጋም ተጠብሶ ይበላል፡፡

ሴቶች በቅቤ የተሠራውን ገንፎ ተመግበው ባህላዊ ጨዋታ እየተጫወቱ ይውላሉ፡፡ ምሽት ላይ የተዋበ ከቅቤ የተሠራ ገንፎ አዘጋጅተው ወንዶችን ይጠብቃሉ፡፡ ወንዶቹ ሥጋ ለሴቶች ይሰጣሉ፤ ሴቶች ለወንዶች ገንፎውን ይሰጣሉ፡፡
ወደ ማታ የመንደሩ አባወራዎች ከነቤተሰቦቻቸው በቤተክርስቲያን አማካይ ቦታ ይሰባሰቡና ደመራ ይበራል፡፡ ባህላዊ ጨዋታ እየተጫወቱም ያድራሉ፡፡

ጥንተ ነገር

የመስቀል በዓል አጀማመር የክርስትና እምነት መሠረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተቀበረበት ተቆፍሮ መገኘትና በተለይም የመስቀሉ አንድ ክንፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ዐምባ መቀመጥ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ቁርኝት ቢኖረውም፣ ኅብረተሰቡ በዓሉን የሚያከብረው እንደየብሔረሰቡ ባህል፣ አኗኗር፣ ወግ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ገጽታ ነው፡፡

የመስቀል በዓል መለያው ደመራው ነው፡፡ ደመራ ንግሥት እሌኒ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል በአይሁዶች ከተቀበረበት ለማውጣት በኢየሩሳሌም ቀራንዮ በሚባል አካባቢ በጎልጎታ ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ለማሰብ የሚከበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡

የደመራ ሥነ ሥርዓት በመጠኑም ቢሆን ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በትግራይ፣ በላስታና ላሊበላ፣ በአክሱም፣ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ በዋግ ሕምራ፣ በከፊል ጎጃምና በአዊ ዞን ደመራው መስከረም 16 ቀን ቢደመርም ሥርዓተ ጸሎቱ የሚካሄደውና ደመራው የሚለኮሰው መስከረም 17 ቀን ንጋት ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በሸዋና በከፊል ጎጃም ደመራው የሚበራው በዋዜማው መስከረም 16 ቀን ምሽት ነው፡፡ የደመራው አደማመርና አበራር ሥነ ሥርዓት ግን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡

ደመራው ወደ አመድነት እስኪለወጥ ይነዳል፡፡ በዚሁ ወቅት ሕዝቡ ‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ›› በማለት ይዘፍናል፡፡ ሴቶች እልል ይላሉ፡፡ ደመራው የተጸለየበትና የተባረከ ስለሆነ ሕዝቡ አመዱንና ትርኳሹን እየተሻማ ወደቤቱ ይዞ ይሄዳል፡፡ አንዳንዶቹ በአመዱ ግንባራቸው ላይ የመስቀል ምልክት ያበጃሉ፡፡ አመዱ ለሰውም ሆነ ለከብቶች ፍቱን መድኃኒት ነው የሚል እምነት አለ፡፡ በደመራው ማግስት መስከረም 17 ቀን በሚከበረው ዋናው የመስቀል በዓል ምዕመኑ ቤተ ክርስቲያን አስቀድሶ ከተመለሰ በኋላ ሲበላና ሲጠጣ፣ ከጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ሲገባበዝና ሲጠያየቅ በፍቅርና በደስታ በዓሉን ሲያከብር ይውላል፡፡

(ለዚህ መጣጥፍ ሔኖክ ያሬድ አስተዋጽዖ አድርጓል)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...