Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቅኝት የተካሄደባቸው የአዲስ አበባ ተቋማት መንግሥትን ለአላስፈላጊ ወጪ መዳረጋቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግሥት በጀትና ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በ26 ባለበጀት የከተማው አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ላይ ባካሄደው ግምገማ አስተዳደሩን ለአላስፈላጊ ወጪዎች የዳረጉ ክስተቶች መታዘቡን አመለከተ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ረቡዕ መስከረም 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ውይይት፣ እነዚህ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን የካፒታልና የመደበኛ በጀት ደንብና መመርያ ከሚፈቅደው ውጪ መጠቀማቸውን እንደታዘበ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ባለበጀት መሥሪያ ቤቶቹ የሚያካሂዷቸውን ፕሮጀክቶች በዕቅዱ መሠረት በወቅቱ አለመጀመር፣ ከተጀመሩም በኋላ በወቅቱ አለመጠናቀቅና ከዚህ በተጨማሪ በግዥና በንብረት አወጋገድ ክፍተት መኖሩ ተመልክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመንግሥት በጀትና ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ራውዳ ሡልጣን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቶቹ በተመደበላቸው ወጪ እየተጠናቀቁ ባለመሆናቸው ተጨማሪ በጀት እየወጣ ነው፡፡

‹‹ይህ አሠራር የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት አባክኗል፡፡ መስተካከል ያለበት  በመሆኑም እኛ በጽሑፍ አሳውቀናል፤›› ሲሉ ወ/ሮ ራውዳ ገልጸዋል፡፡ ያሳወቁትም ፕሮጀክቶቹን ለሚመሩት መሥሪያ ቤቶችና ለምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የተቋቋሙ ቋሚ ኮሚቴዎች በሚከታተሏቸውና በሚቆጣጠሯቸው መሥሪያ ቤቶች ባካሄዱት ግምገማ የተገኙ ግኝቶች ላይ በመምከር ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአብዛኞቹ መሥሪያ ቤቶች በተቀመጡ ሕግጋት መሠረት የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ጥቅም ላይ አለማዋል፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንሰራፋት፣ ተገልጋዮችን በአግባቡ አለማስተናገድ፣ የሕግ፣ የደንብና የመመርያ ክፍተቶች መስተዋላቸው ባለፈው ሳምንት በተካሄዱ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ ተገልጿል፡፡

በቋሚ ኮሚቴዎቹ ስብሰባዎች የማስተካከያ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ ጥፋተኛ አካላትም እንዲጠየቁ እንዲደረግና በተያዘው በጀት ዓመትም ይህንኑ ሥራ ለማካሄድ ማቀዳቸው ታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች