Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናተቃዋሚ ፓርቲዎች በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ ሥፍራዎች የተከሰተው ግጭት አሳስቦናል አሉ

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ ሥፍራዎች የተከሰተው ግጭት አሳስቦናል አሉ

ቀን:

የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰሞኑን በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ሥፍራዎች የተከሰተው ግጭት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳስባቸው፣ መንግሥትም በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠውና በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አመራሮችና ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) ናቸው፡፡

መድረክ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ሐሙስ መስከረም 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአገር ውስናጥ ለውጭ አገር ጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው የዴሞክራሲ ምኅዳሩ እንዲሰፋ፣ መንግሥት ያወጣውን ሕገ መንግሥት እንዲያከብር ጥሪውን አቅርቧል፡፡

- Advertisement -

‹‹ኢሕአዴግ በባህሪው በሕዝቦች ስቃይ የራሱን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል የማይጠቀምባቸው ሥልቶች የሉም፡፡ አሁንም በየቦታው ዳር ድንበርን በማካለል ሥልት ሕዝቦችን በካድሬዎች አማካይነት እያጋጨና እያለያየ ለጊዜ ማራዘሚያ የሚጠቀምበት ሥልት ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ዜጎች ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ችግሮቻቸውን ከሌላ ጣልቃ ገብነት ውጪ ራሳቸው ተቀራርበው ሊያጋጩዋቸው በሚችሉት ጉዳዮች ላይ በመግባባት ተወያይተው እንዲፈቱ እናስገነዝባለን፤›› በማለት መድረክ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች መቋቋሚያ እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡ ለተፈጠረው የዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል፣ ለጠፋው ሕይወትና ለደረሰው ውድመት ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችና አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ፣ ከቤት ንብረታችው የተፈናቀሉ ዜጎች በአስቸኳይ ወደነበሩበት ቀዬአቸው ተመልሰው የቀድሞ ሰላማዊ ኑሮአቸውን እንዲቀጥሉ እንዲደረግ መድረክ መንግሥትን በአጽንኦት ጠይቋል፡፡

በተመሳሳይ ዓርብ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመኢአድ ዋና ጽሕፈት ቤት በጋራ መግለጫ የሰጡት መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲዎች ‹‹አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በዘር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ባመጣው ቅጥ ያጣ የጎሳ ፌዴራሊዝም ምክንያት ያልተፈለገ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ትገኛለች፤›› በማለት ጉዳዩ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከስህተቱ መታረምና መመለስን እንደ ሽንፈት የሚቆጥረው ገዥው ቡድን መቶ በመቶ ሕዝብ መርጦኛል እያለ የሚነግድበትን ሕዝብ በቂ ጥበቃ ሊያደርግለት ባለመቻሉ፣ በጎረቤት አገሮች እንደምንሰማው ሕዝባችን ለሞትና ለስደት እየተዳረገ ይገኛል፡፡ ችግሩንም በቸልተኝነት በመመልከቱና በአፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠቱ በገንዘብ ሊተመን የማይችል ውድ የሆነው የንፁኃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ ሊያልፍ ችሏል፤›› በማለት፣ ሁለቱ ፓርቲዎች በሰሞኑ ግጭት ምክንያት እየደረሰ ያለው የሕይወት መጥፋትና የዜጎች መፈናቀል እንዳሳዘናቸውና እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡  

‹‹ቀደም ሲል በሲዳማና በወላይታ፣ በጉጂና በቦረና፣ በአማራና በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በወልቃይት የፈሰሰው የንፁኃን ደም ዕልባት ሳያገኝና መፍትሔ ሳይበጅለት በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ክልሎች ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው መኢአድንና ሰማያዊን በእጅጉ ያሳሰባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

የሁለቱ የክልል መሪዎች የፖለቲካ ሽንገላና ጨዋታ ትተው ችግሩ በሕዝባዊ ውይይት እንዲፈታና ከሚፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት እንዲቆጠቡ፣ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ የኖረው የኦሮሞና የሶማሌ ማኅበረሰብ በአገሪቱ ባህልና ወግ መሠረት በአገር ሽማግሌዎች በኩል ችግሩ እንዲፈታ፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከጎሳ መሪዎች የተውጣጣ በገለልተኛ ወገን የሚመራ አጣሪ አካል እንዲቋቋምና ሁኔታውን በጥልቀት እንዲመረምር ሁለቱ ፓርቲዎች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ግጭቱን ምክንያት በማድረግ በጅምላ የታሰሩ ዜጎች በአስቸኳይ ጉዳያቸው ተጣርቶ ከእስር እንዲለቀቁ፣ እንዲሁም የውጭ አገር ዲፕሎማቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ዕርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...