Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፍርድ ቤት ለዓቃቢያነ ሕግ የመጨረሻ የተግሳጽ ቅጣት ሰጠ

ፍርድ ቤት ለዓቃቢያነ ሕግ የመጨረሻ የተግሳጽ ቅጣት ሰጠ

ቀን:

  • በገንዘብ ሚኒስቴርና በስኳር ኮርፖሬሽን ተጠርጣሪዎች ላይ የመጨረሻ ቀጠሮ ተሰጠ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት፣ ዓርብ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሙስና ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዓቃቢያነ ሕግ ላይ የመጨረሻ የተግሳጽ ቅጣት ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤት የተግሳጽ ቅጣቱን የሰጠው በዕለቱ የነበረውን ቀጠሮ ለማስተናገድ ሲሰየም፣ በዕለቱ ክስ ለመጠባበቅ ቀጥሮት የነበረውን የገንዘብና ኢኮኖሚክ ትብብር ሚኒስቴር ኃላፊዎችን የምርመራ መዝገብ በማንሳት ዓቃቤ ሕግ እንዲሰየም ሲጠራ፣ ዓቃቢያነ ሕግ በችሎት ባለመገኘታቸው ነው፡፡

በዕለቱ የሚታዩት መዝገቦች የዓቃቤ ሕግን መሰየም የሚጠይቁ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ በመግለጽ፣ ችሎት አስቻይ ፖሊስ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን እንዲጠራቸው ትዕዛዝ በመስጠት ችሎቱ ለአሥር ደቂቃዎች እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ ተካ ገብረየስና የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክተር አቶ መዝሙር ያሬድ በችሎት እንደተገኙ፣ ፍርድ ቤቱ ተመልሶ ተሰይሟል፡፡

አቶ መዝሙር ለፍርድ ቤቱ ለምን ዓቃቢያነ ሕጉ እንደዘገዩ እንዳስረዱት ሲጠየቁ በተያዘው የክስ መዝገብ ላይ ሥራ ስለበዛ፣ ክስ ለማስተካከል ሲሠሩና ቀድመው እንዲሰየሙ የተነገራቸው ዓቃቤ ሕግ በተመሳሳይ ሥራ ላይ ስለነበሩ ሊዘገዩ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለፍርድ ቤቱ ሥራ መሆን ቢገባም፣ ዓቃቢያነ ሕግ ግን ችሎት የሚቀርቡት በተደጋጋሚ እያረፈዱ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ለጥቃቅን ነገሮች ታማኝነትን ወይም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ካልተቻለ ለትልልቅ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ተብሎ ስለማይታሰብ፣ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማስረዳት በመጨረሻ የተግሳጽ ቅጣት እንዳለፋቸው በመንገር ኃላፊዎቹን ፍርድ ቤቱ አሰናብቷል፡፡

በመቀጠልም በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ በእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ ላይ ክስ ለምን እንዳልተመሠረተ የቀረቡትን ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቃቸው፣ መዝገቡ ሰፊና ውስብስብ በመሆኑ በተሰጣቸው የክስ መመሥረቻ ጊዜ ሊደርስላቸው እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡ በሕጉ መሠረት የተፈቀደውን ክስ የመመሥረቻ ጊዜ 11 ቀናት እንደተሰጣቸው ዓቃቤ ሕጉ አስታውሰው፣ ቀሪዎቹ አራት ቀናት ከተፈቀዱላቸው ክስ መሥርተው እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የጠየቁትን አራት ቀናት በመፍቀድ ለመስከረም 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሌላ የምርመራ መዝገብ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ተጠርጣሪዎች በእነ አቶ መስፍን መልካሙ ላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ መመሥረት አለመቻሉን፣ ሐሙስ መስከረም 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ችሎቱ ከተሰየመ በኋላ ዘግይተው የተሰየሙት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክተር አቶ መዝሙር ያሬድ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ የክስ መዝገቡን የሚከተታሉት ዓቃቤ ሕግ መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ወደ ቤታቸው ሲገቡ ማስፈራራት ደርሶባቸው ነበር፡፡ በመሆኑም በዕለቱ ቀርበው መሰየም ባለመቻላቸው እሳቸውን ሲጠባበቁ ሊዘገዩ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ግን ተቋሙ ትልቅ መሆኑንና በአንድ ሰው ብቻ እንደማይሠራ አስታውቆ፣ ያም ቢሆን እንኳን ቀርበው በሰዓቱ ለፍርድ ቤት ማሳወቅ እንደነበረባቸው በማስረዳት እንዳይደገም በማለት አስጠንቅቋል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ለመመሥረት አለመቻላቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ጉዳዩ ከባድና ውስብስብ በመሆኑ፣ በተፈቀደው ጊዜ ሊደርስላቸው ስላልቻለ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡ በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ቀሪ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን፣ ለፎረንሲክ ምርመራ የላኩትን ሰነድ እየተጠባበቁና የትርጉም ሥራም እንደሚቀራቸውም በመግለጽ ሰባት ቀናት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ፖሊስ ምርመራ ጨርሶ ለዓቃቤ ሕግ ካስረከበና ዓቃቤ ሕግም መረከቡን ካረጋገጠ በኋላ መዝገቡ መዘጋቱን አስታውሶ፣ በተዘጋ መዝገብ ላይ ለሌላ ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ የሚፈቀድበት የሕግ አግባብ አለመኖሩን ገልጿል፡፡ በመሆኑም ምርመራ ይቀረናል በማለት ዳይሬተክሩ ያቀረቡትን መከራከሪያ ሐሳብ ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበለው ገልጾ፣ በክስ መመሥረቻ ቀኑ ላይ ብቻ የተጠርጣሪዎቹን አስተያየት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸውና በጠበቆቻቻው አማካይነት ተጨማሪ ቀናት መሰጠት እንደሌለበትና ተቃውሞ የለንም የሚሉ አስተያየቶች ከሰጡ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ ለመስከረም 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...