Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየመንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ከሁለት ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ጋር ክስ ተመሠረተባቸው

የመንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ከሁለት ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ጋር ክስ ተመሠረተባቸው

ቀን:

  • ለሁለቱም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያላግባብ ክፍያ መፈጸሙ ተገልጿል
  • ሳትኮንና ሀዚ አይአይ ሥራ ተቋራጮች በክሱ ተካተዋል

ከሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ሲካሄድባቸው በከረሙት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሰባት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ በገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገምሹ በየነ (በሌሉበት) እና በዲኤምሲ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ማሞ (በሌሉበት) ላይ ዓርብ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቀድሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልና የሥራ ባልደረቦቻቸው ላይ አምስት የክስ መዝገቦችን ማደራጀቱን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ከገለጸ በኋላ፣ በተፈቀደለት ጊዜ ክስ መመሥረት የቻለው በሁለቱ መዝገቦች ላይ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በአንደኛው የክስ መዝገብ ላይ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ የምህንድስና ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዶ መሐመድ፣ የዕቅድና አይሲቲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ንጉሤ፣ የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገምሹ በየነ (በሌሉበት)፣ የዲኤምሲ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ማሞ (በሌሉበት)፣ የባለሥልጣኑ አሲስታንት ኦፊሰር አቶ ገብረ አናንያ ፃድቅ፣ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች አቶ አማረ አሰፋ፣ አቶ ሀዲስ ተስፋዬና አቶ ደበበ ሞገስ (በሌሉበት) ናቸው፡፡

- Advertisement -

ዓቃቤ ሕግ በሌላው የክስ መዝገብ ያካተታቸው ተከሳሾች ደግሞ፣ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ የሳትኮን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ተክላይ (በሌሉበት)፣ የሀዚ አይአይ ጠቅላላ ኮንስትራክሽንና የንግድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዛኪር አህመድና የሳትኮን ፋይናንስ መምርያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሐ ታደለ (በሌሉበት) ናቸው፡፡

የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ከኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤቶችና ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር የግዢ መመርያዎች ከሚፈቅዱት ውጪ በድምሩ 2,150,382,908 ብር ክፍያ በመፈጸም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በሁለት የክስ መዝገቦቹ ላይ አብራርቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ዘጠኝ ተከሳሾች በተጠቀሱበት የክስ መዝገብ እንዳብራራው፣ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ከአቶ ገምሹ በየነ ጋር በጥቅም በመመሳጠር በ2002 ዓ.ም. የወጣውን የግዥ መመርያ በመጣስ፣ ለገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 462,385,763 ብር ክፍያ እንዲፈጽም አድርገዋል፡፡ በተለያየ ኃላፊነት ላይ በነበሩ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ክፍያው እንዲፈጸም የተደረገው ከማይፀብሪ-ዲማ የመንገድ ፕሮጀክት በጠጠር እንዲገነባ 258,721,412 ብር የተከፈለ ቢሆንም፣ የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ሳይሠራ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ድርጅቱ አስፋልት የመሥራት አቅሙ ሳይገመገም፣ መንገዱ አስፋልት እንዲሆን መወሰናቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም ከምህንድስና ግምት ስምንት በመቶ ብልጫ እያለው 183,454,445 ብር ተጨማሪ ክፍያ በመጨመር በድምሩ 462,385,763 ብር ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ፣ የመንግሥትን ሥራ በሚያመች አኳኋን በመምራት በመንግሥትና ሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡

ሌላው ኃላፊዎቹ 907,392,511 ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም አድርገዋል የተባለው ደግሞ ከአቶ ዳንኤል ማሞ ጋር በመመሳጠር፣ ለዲኤምሲ ኮንስትራክሽን ኩባንያ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ዲኤምሲ በ2006 ዓ.ም. ከአላባ-ሶዶ-ሁምቦ-አርባ ምንጭ ለሚገነባው መንገድ ባቀረቡት የጨረታ መወዳደሪያ ዝቅተኛ ዋጋ በ380,204,197 ብር ያሸነፉ ቢሆንም፣ የድርጅቱ ባለቤትና ኃላፊዎቹ በመመሳጠር በተደጋጋሚ የለውጥ ሥራ (Variation Order) በመስጠት 141,579,224 ብር ጭማሪ ሥራ ያላግባብ መሰጠቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ ሥራው በተደጋጋሚ እንዲራዘም በማድረግ ለማስተካከያ በማለት ተጨማሪ 392,474,366 ብር በመክፈል፣ የሥራውን ማጠናቀቂያ ዋጋ 907,392,511 ብር ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ተንትኗል፡፡ ለጥገና ብቻ የተሰጠውን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ደረጃውን ከፍ አድርጎ ለመሥራት ኃላፊዎቹ በአግባቡ ሳያቅዱ ከአቶ ዳንኤል ጋር ውል በመፈራረምና ወደ ትግበራ በመግባታቸው፣ እንዲሁም ዝርዝር የዲዛይን፣ የአካባቢ የኃይድሮሎጂና ሃይድሮሊክ ጥናት ባለመሥራታቸው በአካባቢው ከሁምቦ አርባ ምንጭ ያለው 31.5 ኪሎ ሜትር መንገድ በጎርፍ ተጠራርጎ መወሰዱን ክሱ ያስረዳል፡፡ የዲዛይን ለውጥ በማድረግ የመንገዱን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ቀይሮ ለመሥራት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ለቦርድ ያቀረቡት አቅጣጫ ውድቅ ተደርጎ፣ አዲስ ጨረታ ወጥቶ ለሌሎች ተጫራቾች እንዲሰጥ ሌላ አቅጣጫ የሰጠ ቢሆንም፣ ለዲኤምሲ ኮንስትራክሽን ኩባንያ 700,567,447 ብር ተጨማሪ ክፍያ በመስጠት የ780,604,634 ብር የሀብት ብክነት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛው የክስ መዝገቡ ክስ የመሠረተባቸው አቶ ዛይድ፣ የሳትኮን ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅና የፋይናንስ መምርያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ተክላይና አቶ ፍስሐ ታደለ (በሌሉበት)፣ እንዲሁም የሀዚ አይአይ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት አቶ ዛኪር መሐመድ ናቸው፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ከሳትኮን ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር፣ ሳትኮን ኮንስትራክሽን ከደልበና እስከ ጂንካ ለሚሠራው መንገድ በብድር የወሰደውን አስፋልት ሳይመልስ መቅረቱን ክሱ ያስረዳል፡፡ ብድር ለመስጠት የሚፈቅድ መመርያ በሌለበት ወይም ለመያዣ የሚሆን ዋስትና ሳያቀርብ፣ ዋና ዳይሬክተሩ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ብድሩን መፍቀዳቸውን ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ሳትኮን ከእንደ ሥላሴ-ደጀና-ዳንሻና ቀብሪደሃር-ሽላቦ ለሚሠራው መንገድ የአስፋልት ብድር ሲጠይቅ፣ የመንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001ን በመተላለፍ ግምቱ 23,456,880 ብር የሆነ አስፋልት እንዲበደር ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ብድሩን ባለመመለሳቸውም በፍትሐ ብሔር ክስ ተመሥርቶባቸው 17,592,361 ብር እንዲከፍሉ ቢፈረድባቸውም፣ 6,812,046 ብር እስካሁን እንዳልመለሱ ክሱ ያብራራል፡፡

የሀዚ አይአይ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤትም ከመካኒሳ-ዓለም ገና ለሚሠሩት የመንገድ ፕሮጀክት 400 በርሜል አስፋልት የተበደሩ ቢሆንም፣ ባለመመለሳቸው በፍትሐ ብሔር ክስ ተመሥርቶባቸው መመለሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ የአስፋልቱ ግምት 3,135,200 ብር መሆኑንና የተመለሰ ቢሆንም፣ ገንዘቡን ለማስመለስ መንግሥት ሕግ ለማስከበር የሰው ኃይልና ሀብት እንዲባክን በማድረጋቸው፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል በፈጸሙት ከባድ የሙስና ወንጀል እንደ ከሰሳቸው ዓቃቤ በክሱ ገልጿል፡፡ ኮንትራክተሮቹም በፈጸሙት ከባድ የማታለል ወንጀልና በመንግሥት ሠራተኞች ብቻ ሊፈጸም በሚችል ልዩ ወንጀል ላይ ልዩ ተካፋይ በመሆናቸው፣ በከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን አብራርቷል፡፡

ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስና የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ ዋስትና የሚከለክል መሆኑን በመጥቀስ፣ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ክስ ባልተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ ለመስከረም 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ክስ መሥርቶ እንዲቀርብ የመጨረሻ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቶ ዛይድ ወደፊት በሚመሠረተውም ክስ ውስጥ እንደሚካተቱ ዓቃቤ ሕግ በመግለጹ፣ ባሉበት በፖሊስ ማረፊያ ቤት ቆይተው እንዲቀርቡ በመንገር ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...