Wednesday, April 17, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

መደማመጥ ቢኖር የት ይደረስ ነበር!

 ለመደማመጥ ሰከን ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ስክነትና ትዕግሥት በሌለበት ከመጯጯህ የዘለለ ቁም ነገር አይገኝም፡፡ አስተሳሰቤ ተሸናፊ ይሆንብኛል ወይም በዓይኔ እንኳ ማየት የማልፈልገው ሰው ሊሞግተኝ ይችላል ተብሎ ከውይይት መሸሽ ተቀባይነት የለውም፡፡ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ፣ በፓርቲ ፖለቲካም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች መነጋገር ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ይከበር የሚል ማንም ሰው ውይይትን ማደፋፈር አለበት፡፡ የሐሳብ ልውውጥ ሲኖር በዕርጋታ መደማመጥ ይከተላል፡፡ ማንም ሰው የራሱ የፖለቲካ አቋም፣ የሕይወት ፍልስፍና ወይም የኑሮ ዘይቤ ሊኖረው ይችላል፡፡ ከሌሎች ጋር በሚያደርገው ውይይት የተለያዩ ሐሳቦችን ይጋራል እንጂ፣ ከሚፈልገው አመለካከት የግድ እንዲላቀቅ ይደረጋል ማለት አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት የሐሳብ ገበያ ነው ሲባል፣ የመነጋገርና የመደማመጥን አስፈላጊነት ለማሳየት ነው፡፡ የራስን ጠቃሚ የሚባል ሐሳብ ይዞ የሌሎችን ምልከታ መረዳት ይጠቅማል እንጂ፣ በነውጠኝነትና በእንቢ ባይነት ማጣጣል ከአምባገነንነት ተለይቶ አይታይም፡፡ መነጋገርንና መደማመጥን የመሰለ ፀጋ በመተው ለዘመናት መናቆር ጤነኝነት አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን ጤና የጠፋው ደግሞ እናውቃለን የሚሉት ዘንድ መሆኑ ችግሩን ያከፋዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት በነበሩት መስታጋብሮቹ ቋንቋዎች ሳይገድቡት በዓይኖቹ ጭምር በመግባባት ክፉና ደግ ዘመናትን በጋራ አሳልፏል፡፡ እምነት፣ ባህልና የተለያዩ ፍላጎቶቹን በመከባበርና በመተሳሰብ አቻችሎ ኖሯል፡፡ እየኖረም ነው፡፡ ሰብዓዊ ፍጡር መሆን ምንም ዓይነት እንከን ሳይገጥመው የጋራ እሴቶችን አክብሮና አስከብሮ መኖር የኢትዮጵያዊያን ትልቁ የጋራ መገለጫ ነው፡፡ ድሮም የነበረ አሁንም ያለ፡፡ ማንነት እየተከበረና ትልቁ ምሥል ኢትዮጵያዊነት እየተዘከረ እስካሁን ዘልቋል፡፡ ይህ ታላቅ ሕዝብ ከንግግር የበለጠ የሚግባባው የሥነ ልቦና አንድነት ስላለው ነው፡፡ አገሩን ከወራሪዎች በአንድነት ሲከላከል የነበረው እርስ በርሱ ባለው የጠነከረ ፍቅር ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ አገሩን በጣም ስለሚወድ ነው፡፡ የአገር ህልውና ከምንም ስለማይበልጥበት ነው፡፡ ይህ ትንግርታዊ ተምሳሌትነት በታላቁ ፀረ ቅኝ አገዛዝ የዓደዋ ድል ያሸበረቀ ነው፡፡ ለዓለም ጥቁሮች ነፃነት ትንሳዔ የሆነ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ምን አለ? ምንም!

አሁንስ? አሁንማ በተለይ ፖለቲከኞችና በፖለቲካው ዙሪያ የተኮለኮሉት ግራ ያጋባሉ፡፡ ለሐሳብ ነፃነት እታገላለሁ የሚለው ሳይቀር ይቀናቀነኛል የሚለውን ተገዳዳሪውንና በገዛ ፓርቲው ውስጥ ሙግት የሚያነሳውን የትግል አጋሩን የተለየ ሐሳብ ለማዳመጥ ይተናነቀዋል፡፡ ድጋፍና ተቃውሞ ጭልጥ ብለው ጠርዝ እየያዙ ገደል አፋፍ ላይ ሆኖ በነገር መቋሰል፣ በዘር መሰዳደብ፣ ሕዝብን ማንጓጠጥና መዝለፍ፣ መለስተኛ ቅራኔዎችን መሠረታዊ በማድረግ ሕዝብን ለግጭት መቀስቀስ፣ የአገር ህልውናን በመናድ ለሶሪያ ዓይነት ውድመት ማመቻቸት፣ ለታሪካዊ ጠላቶች ሚስጥር መሸጥና ተላላኪ መሆን፣ አምባገነንትን የሚያበረታቱ ቅስቀሳዎች ማድረግ፣ የግለሰብንም ሆነ የቡድን መብት መጨፍለቅ፣ የሐሳብ ነፃነትን መጋፋት፣ ተቃውሞን ማፈንና መብታቸውን የሚጠይቁትን በማሰቃየት አገርን ለነውጥ ማጋለጥ፣ የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በአግባቡ አለመመለስ፣ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች አለማክበር፣ ማኅበራዊ ፍትሕ አለማስፈን፣ ወዘተ. ዙሪያ ገባውን የወረሩን በሽታዎች ናቸው፡፡ አገር የሚያስተዳድር መንግሥት ሥልጣኑ በሕግ የበላይነት ሥር ካልሆነ፣ የፖለቲካ ሥልጣን የሚፈልገው የተቃውሞ ጎራ ሕገወጡን መንገድ ከመረጠ በጣም አደገኛ ነው፡፡ በሁለቱም ጎራ ያሉት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ መሽገው የሚረጩት መርዝ አዲሱን ትውልድ እየመረዘ ነው፡፡ ይህ ለማን ይጠቅማል? ለማንም!

የተለያዩ ሐሳቦችን ይዞ መነጋገር መለመድ አለበት፡፡ መደማመጥም እንዲሁ፡፡ አንደኛው ጎራ ሌላውን በጅምላ እየፈረጀ የተመጣበት መንገድ ለማንም አልጠቀመም፡፡ በዚያ አሰልቺ መንገድ ላይ ለዓመታት መመላለስም ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ተቀራርቦ መነጋገር ማለት ሥልጣኔ ነው፡፡ የግድ አሸናፊና ተሸናፊ ይኑር ማለት አይደለም፡፡ አንድ አገር ፅኑ የሆነ መሠረት የሚኖረው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ በተሟላ መንገድ ይኖሩ ዘንድ ደግሞ እየመረረንም ቢሆን ተቃራኒ ሐሳቦችን ማዳመጥ ይገባል፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች አደባባይ ሲወጡ ጉድለትን ይሞላሉ፡፡ በነበረን ምልክታ ላይ ተጨማሪ ዕይታ ይሰጡናል፡፡ ነጭና ጥቁር መሀል ያለውን ግራጫ ማወቅ የሚቻለው በሁለቱ መኖር ነው፡፡ የአንድ ወገን አስተሳሰብ የበላይነት ይኑረው ከተባለ ከአምባገነንነት ውጪ ምን ሊሆን ይችላል? ገዥው ፓርቲ እውነትና ቀናው መንገድ እኔ ብቻ ነኝ ካለ ችግር አለ፡፡ በተቃውሞው ጎራ በየፈርጁ ይህ ከተቀነቀነ የበለጠ ችግር ነው፡፡ አገር በዚህ ዓይነቱ ግትርነትና ድርቅና መጓዝ አትችልም፡፡ አኩራፊ ይበዛል፡፡ ኩርፊያ ሲበዛ እንኳን መነጋገርና መደማመጥ ዓይን ለዓይን መተያየት ያዳግታል፡፡ ሒደቱ በዚሁ ሲቀጥል መሣሪያ ወልዋይ ይነሳል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ እየተገባ የግጭት ፕሮፓጋንዳ ይነዛል፡፡ የሚከተለው ዕልቂትና መፈናቀል ይሆናል፡፡ ምልክቶቹን ከመጠን በላይ እያየናቸው ነው፡፡ በቃ መባል የለበትም? ኧረ ይብቃ!

በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ሥፍራ ከሚይዙ ዓበይት ክንውኖች መካከል ዋነኛው ጦርነት ነው፡፡ ወራሪዎችን ለመከላከልና በዘመነ መሳፍንት የተደረጉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በየመሀሉ ዕፎይታዎች ቢገኙም በተለያዩ ንቅናቄዎች ሳቢያ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ በየዘመናቱ በተነሱ ገዥዎች የተቀሰቀሱ ናቸው፡፡ እነዚያ የታሪካችን አካል የሆኑ ድርጊቶች የፈጠሩት ጠባሳ ቀላል ባይሆንም፣ ጠባሳውን ለታሪክ መዛግብት ትቶ የተሻለውን ይዞ ለበለጠ አኩሪ ተግባር መነሳት ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ መልካም አጋጣሚዎች በተለያዩ ምክንያቶች ያመለጧት ዕድለ ቢስ አገር መሆኗን መዘንጋትም አይገባም፡፡ እነዚያ መልካም አጋጣሚዎች ካለፉ በኋላ ይከተል የነበረው ፀፀት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የዛሬ 43 ዓመት ገደማ የፈነዳው ግብታዊው የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት በስክነት የሚመራው በማጣቱ ለመተላለቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሚያሳዝነው ከአንድ የርዕዮተ ዓለም መጽሐፍ ያጣቅሱ የነበሩ በቀጭን የመስመር ልዩነት ምክንያት ተፋጅተዋል፡፡ ብዙዎች እስር ቤት ማቀዋል፡፡ ብዙዎች ተሰደዋል፡፡ የመጣው ይምጣ ያሉ በረሃ ገብተዋል፡፡ ለአሥራ ሰባት ዓመታት ደም እንደ ጅረት ፈሰሰ፡፡ መነጋገርና መደማመጥ ጠፍቶ አገር ተመሰቃቀለች፡፡ ሕዝብ አሳሩን በላ፡፡ አገሪቱ የጦርነትና የረሃብ ምሳሌ ተደረገች፡፡ ማን ተጠቀመ? ማንም፡፡ የመነጋገርና የመደማመጥ መጥፋት በሽታ ግን ቀጠለ፡፡

በ1983 ዓ.ም. ወታደራዊው አገዛዝ በትጥቅ ትግል ተንበርክኮ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ በሽግግሩ ጊዜ ተስፋ ፈነጠቀ፡፡ ግን የተሟላ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ድርሻ የነበራቸው ተገለሉ፡፡ ይህም ሆኖ ለፌዴራላዊ ሥርዓት መሠረት የሆነው ሕገ መንግሥት ተረቅቆ ፀደቀ፡፡ ገዥው ፓርቲ ሥልጣኑን እያፀና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመጠኑም ቢሆን የፓርላማ መቀመጫ እያገኙ መጠነኛ ብልጭታ ታይቶ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ግን መነታረኩ፣ መጋጨቱ፣ መታሰሩ፣ መሰደዱ፣ ወዘተ. ቀጠሉ፡፡ ምርጫ 97 መጥቶ የተስፋ ጭንላንጭል ቢታይም ወዲያው እልም ብሎ ጠፋ፡፡ ከዚያ በኋላ ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ በስተቀር ፓርላማው በገዥው ፓርቲና በአጋሮቹ ቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡ እያለ እያለ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት እየጠፋ በሚቀሰቀሱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች መሞት ጀመሩ፡፡ በቅርቡም በአሳዛኝ ሁኔታ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጡ፡፡ ሁለት ፍላጎቶች ያሉዋቸው ወገኖች መሣሪያ ከመማዘዛቸው በፊት ለመነጋገር ለምን ያቅታቸዋል? አገር ከሚመራው መንግሥት ጀምሮ እስከ አንድ ዜጋ ድረስ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ለምን ትኩረት አይሰጥም? ክቡር የሆነው የንፁኃን ዜጎች ደም እየፈሰሰና የአገር ህልውና እየተናጋ ለምን ይቀጥላል? መነጋገርና መደማመጥ የተከበረው ሕዝባችን የዘመናት ፀጋ መሆኑ እየታወቀ፣ እናውቃለን የሚለው የኅብረተሰብ ክፍል አገር ለምን ይበጠብጣል? በእልህና በቂም ዴሞክራሲ ይፀናል ወይ? በጥላቻና በኩርፊያ የአገር ህልውና ይከበራል እንዴ? ከጠቅላይነትና ከአገልጋይነት ስሜት ውስጥ መውጣት ካልተቻለ እንዴት ይዘለቃል? መልካም አጋጣሚዎችን ብቻ ሳይሆን ክፉ አጋጣሚዎችን ጭምር በቅንነት መንፈስ በመነሳሳት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማጠናከሪያ ለማድረግ ለምን አይሞከርም? በብሔርና በእምነት በመከፋፈል ይህንን ኩሩ ሕዝብ ማጋጨትና አገርን ችግር ውስጥ መክተት ለምን አያበቃም? ካሁን በኋላ የፅንፈኛ ወገንተኝነት አስተሳሰብ ተገቶ የመከፋፈል መስመርን በማቋረጥ ለመነጋገርና ለመደማመጥ መድፈር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ድፍረት እየጠፋ በየጎራው ሆኖ በነገር መቋሰልና ከዚያም ለመፋጀት ማሴር ዕብደት ነው፡፡ ተቃራኒ ሐሳቦችን እያስተናገዱ መነጋገርንና መደማመጥን ባህል ማድረግ ይገባል፡፡ አለመነጋገርና አለመደማመጥ የጥቻላና የክፋት ብቻ ሳይሆን የኋላቀርነት መገለጫ ነው፡፡ እስካሁን ለደረሰው ጥፋት ሁሉም ወገን በመፀፀት ለመነጋገርና ለመደማመጥ ከልብ መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ይህች አገር የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ቤት መሆኗን መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካውያን ጭምር የጋራ ቤት መሆኗን ማመን የግድ ይላል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ግን እንደማመጥ! መደማመጥ ቢኖር የት ይደረስ ነበር!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...