Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሞያሌ ድንበርን ማለፍ ያልቻለው የኤክስፖርት ስኳር ውዝግብ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የኬንያ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ተጠይቋል
  • መፍትሔ ካልተገኘ ስኳሩ ወደ ወንጂ ሊመለስ ይችላል

ከአንድ ወር በፊት ወደ ኬንያ ኤክስፖርት ተደረገ የተባለው ስኳር የኢትዮጵያ ሞያሌ ድንበርን አለማለፉን፣ የስኳር ምርቱን የገዛው መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው ኩባንያ ችግሩን መፍታት አለመቻሉን ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች አመለከቱ፡፡

ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ እያንዳንዳቸው 400 ኩንታል በጠቅላላው 44 ሺሕ ኩንታል ስኳር የጫኑ 110 ተሽከርካሪዎች፣ በኢትዮጵያ ሞያሌ ድንበር ከቆሙ 45 ቀናት እንዳለፋቸው መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡  

ከመጀመርያው በጥራት ደረጃው ላይ ጥያቄ ተነስቶበት የነበረው ይኼው ስኳር፣ በአካባቢው እርጥበት አዘል ወበቅ በመበላሸት ላይ እንደሚገኝም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የስኳር ግዢውን የፈጸመው ተቀማጭነቱ ዱባይ የሆነው አግሪ ኮሞዲቲስ ኤንድ ፋይናንስ የተባለ ኩባንያ ሲሆን፣ ይኸው ኩባንያ ከብራይት ድንበር ተሻጋሪ ደረጃ አንድ የጭነት ማመላለሻ ማኅበር ጋር የትራንስፖርት አገልግሎት ውል መግባቱን፣ የማኅበሩ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረሰልኝ አበጀ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ ጭነቱን ለማመላለስ 110 ተሽከርካሪዎችን በማሰማራት ኬንያ ለማድረስ፣ በኩንታል 35 ብር በአጠቃላይ ለአንድ ተሽከርካሪ 94 ሺሕ ብር ውል መፈጸሙን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሠረት ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ ስኳሩን ጭነው ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ፣ የጥራት ችግር አለበት በሚል ምክንያት ለአሥር ቀናት በወንጂ ለመቆየት መገደዳቸውን ያስታውሳሉ፡፡

የጥራት ደረጃውና ማንኛውንም የጉዞ መሥፈርትና ሰነድ መሟላቱ ከተገለጸ በኋላ ጉዞ ጀምረው የኢትዮጵያ ሞያሌ ድንበር ከደረሱ 45 ቀናት እንዳለፉ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሞያሌ ድንበር የደረሱት ተሽከርካሪዎች ወደ ኬንያ ማለፍ ያልቻሉት የጉምሩክ ሥነ ሥርዓቶችን ባለመፈጸማቸው እንደሆነ ቢገለጽም፣ ይህንና ሌሎች ጉዳዮችን ለማስጨረስ የስኳር ምርቱን ያስጫነው ኩባንያን በኢሜይልም ሆነ በማንኛውም መንገድ ለማግኘት አለመቻላቸውን አቶ ደረሰልኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹መፍትሔ ስንጠብቅ ላለፉት 45 ቀናት ቆይተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ኬንያ ጉዞውን አንቀጥልም፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ውላችንንም አቋርጠናል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ስኳሩን ይረከበን፤›› ሲሉ ለኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ጥያቄያቸውን በደብዳቤ አቅርበው፣ ታገሱ የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

ለማኅበሩ 110 ተሽከርካሪዎች በአጠቃላይ አገልግሎቱን ለመስጠት 10.3 ሚሊዮን ብር የተዋዋሉ ሲሆን፣ የዚህ መጠን 50 በመቶ ክፍያ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳወቅ ሀብቴ ሰኞ መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ለኬንያ የግብርናና የምግብ ባለሥልጣን የስኳር ዳይሬክቶሬት የጻፉትን ደብዳቤ ለማግኘት ተችሏል፡፡

‹‹ወደ ኬንያ ኤክስፖርት ያደረግነውን 4,400 ቶን ስኳር አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ደብዳቤዎችን ብንለዋወጥምና ድርድር ብናደርግም፣ በኬንያ በኩል የተሰጠን ምላሽ አጥጋቢ አለመሆኑን ስንገልጽ እናዝናለን፤›› በማለት የሚጀምረው የአቶ እንዳወቅ ደብዳቤ፣ ‹‹የገጠመንን ችግር በወንድማማችነትና በሁለትዮሽ ውይይት መፍታት ለወደፊት የንግድ ግንኙነታችን ይጠቅማል፤›› ይላል፡፡

ወደ ኬንያ ኤክስፖርት የሚደረገውን 4,400 ቶን ስኳር አግሪ ኮሞዲተስ ኤንድ ፋይናንስ የተባለ ኩባንያ በውል EX-FS 01 SC/2017 መሠረት ግዥ መፈጸሙን የሚጠቅሰው ደብዳቤው፣ ይህ ኩባንያ ላስጫነው ስኳር ክፍያ እንዲፈጽም ዱባይ ለሚገኘው ባንክ አስፈላጊውን ሰነዶች ኮርፖሬሽኑ የላከ ቢሆንም፣ መክፈል ያለበትን 2.2 ሚሊዮን ዶላር እስካሁን ማግኘት እንዳልተቻለ ይገልጻል፡፡

‹‹ገንዘባችንን በተመለከተ ከኩባንያው ጋር በውሉ መሠረት መጠየቃችን እንዳለ ሆኖ፣ የእርስዎ ምክርና ጣልቃ ገብነት ችግሩን ሊፈታው ይችላል ብለን የምናስብ በመሆኑ ይህንኑ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፤›› ሲል ደብዳቤው የኬንያው ባለሥልጣን ሚስተር አልፍሬድ ቡሶሎን ይጠይቃል፡፡

የተጫነው ስኳር ከኢትዮጵያ ሞያሌ ድንበር ማለፍ አለመቻሉንና የብልሽት አደጋ እየገጠመው በመሆኑ ችግሩ በፍጥነት እንዲቀረፍም ይጠይቃል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የስኳር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉም በበኩላቸው፣ የስኳር ሽያጩ ትራንስፖርትን የማይመለከት በመሆኑ ስኳር ኮርፖሬሽኑ የተፈጠረው ችግር አይመለከተውም ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ መንግሥት ተቋም ችግሩን ለመፍታት ኮርፖሬሽኑ ኬንያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመሆን ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ ዋናው ችግር በብራይት ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ማመላለሻ ማኅበርና ስኳሩን በገዛው ኩባንያ መካከል ነው፡፡ የጉምሩክ ሰነዶችን በተመለከተ የመጨረሻው ጉዳይ የተፈታ ቢሆንም፣ በኬንያ የመንገድ አጠቃቀም ሕግ መሠረት 400 ኩንታል የጫነ ተሽከርካሪ ማለፍ አይችልም ያሉት አቶ ጋሻው፣ በዚህ መሠረት ትራንስፖርተሮቹ 280 ኩንታል ጭነው ቀሪውን ድንበር ላይ አራግፈው እንዲያልፉ በገዥው ኩባንያ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ተሽከርካሪዎቹ ለደረሰባቸው መጉላላትና ቀሪውን በድጋሚ ተመልሰው ለሚያጓጉዙበት እንደሚከፍል ቃል መግባቱን አክለዋል፡፡ እንደ መንግሥት ተቋም ጉዳዩን ለመፍታት ትራንስፖርተሮቹ የመጨረሻ አቋማቸውን እንዲያሳውቁን በተደረገው ጥረት፣ ዓርብ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. አቋማቸውን ግልጽ እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው የገባው ቃል የተካተተበት አዲስ የትራንስፖርት ውል ከተዋዋሉ ወይም ለቀሪው ክፍያ የባንክ ዋስትና የሚሰጣቸው ከሆነ ወደ ኬንያ ጉዞ ማድረግ የሚችሉ መሆናቸውን የብራይት ትራንስፖርት ማኅበር ቢገልጹም፣ ግዥውን የፈጸመው ኩባንያ ግን አዲስ ውል አልዋዋልም ማለቱን አቶ ጋሻው ጠቁመዋል፡፡

ብራይት ድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት ማመላለሻ ማኅበር ወደ ኬንያ ጉዞ እንደማያደርግ በማሳወቁ፣ ስኳሩ ወደ ወንጂ እንዲመለስ ለመወሰን ኮርፖሬሽኑ እየመከረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ለኮርፖሬሽኑ መከፈል የሚገባው 2.2 ሚሊዮን ዶላር ከትራንስፖርቱ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከገዥው ኩባንያ ባንክ ጋር በመነጋገር እንደሚፈታው አስረድተዋል፡፡

ስኳሩ ወደ ወንጂ እንዲመለስ የሚደረግ ከሆነም፣ ኩባንያው በማንኛውም ጊዜ ከወንጂ በሌላ ትራንስፖርት ማጓጓዝ ይችላል ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች