Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት የሰላም ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት የሰላም ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው

ቀን:

በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ደም አፋሳሽ ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት፣ የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው፡፡ ኮንፈረንሱን ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተቋቋመው ግብረ ኃይል፣ በሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የመጀመርያው በሁለቱ ክልሎች መካከል የተነሳውን ግጭት መከላከልና ማብረድ ነው፡፡ ሁለተኛው ከሁለቱም ክልሎች ከቀዮአቸው የተፈናቀሉ 60 ሺሕ ለሚደርሱ ዜጎች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ማቅረብ ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አሁን እየተሠራ ያለው ማረጋጋትና የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ማቅረብ ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን ወደ ቀድሞ ቦታቸው ወስዶ ማቋቋም ነው ብለው፣ ዋናውና ዘለቄታዊ ሰላም የሚያመጣውን የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ በሁለቱም ክልሎች በጋራ ማካሄድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የሰላም ኮንፈረንሱ መቼ እንደሚካሄድ የጊዜ ሰሌዳ አልወጣለትም ብለዋል፡፡  

ደም አፋሳሽ ግጭቱን ለማብረድና ለመከላከል የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊነት ትጥቅ ማስፈታት፣ በግድያና በንብረት ውድመት የሚጠረጠሩ አካላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል ለሕግ ማቅረብ፣ ተጨማሪ ጥቃቶች እንዳይካሄዱ መቆጣጠር፣ የሥጋት ቀጣና በሆኑ ሥፍራዎች ጥብቅ የሆነ ጥበቃ ማድረግን ያካትታል ተብሏል፡፡ የሁለቱን ክልሎች ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎችንም እየተቆጣጠረ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠውን ጉዳይ በሚመለከት የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሐረርና በጅግጅጋ ከተሞች የሚገኙ ተፈናቃዮች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡

አቶ ምትኩ ጨምረው እንደገለጹት፣ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ኮንፈረንስ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ግጭቱ በቁጥጥር ሥር የዋለ ቢሆንም፣ ሥጋት ያደረባቸው ዜጎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በአጠቃላይ እየተፈናቀሉ ለሚገኙ ዜጎች ከብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በተጨማሪ፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በጅግጅጋ፣ በጭናክሰንና በመሳሰሉ አካባቢዎች ለተፈናቃዮች የዕለት ደራሽ ዕርዳታና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንደሚያስፈልጓቸው እየተነገረ ነው፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት የተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት እያጠናሁ ነው ቢልም፣ የኦሮሚያ ክልል የ18 ዜጎች ሕይወት ማለፉን፣ የሶማሌ ክልል ደግሞ የ50 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል፡፡

ተፈናቃዮችም ቢሆኑ ከ50 እስከ 60 ሺሕ ሊሆኑ እንደሚችሉ አቶ ምትኩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አካባቢው ወደ ቀድሞው ሰላም እስኪመለስ ድረስ ተፈናቃዮች ባሉበት የሚቆዩ ሲሆን፣ በዚህ ሒደትም መንግሥትና ሕዝብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ፣ በግጭቱ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በጊዜያዊ ማረፊያ ቦታዎች በማቆየት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን፣ በቀጣይም ወደ ቀድሞ መኖሪያ አካባቢያቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋሉ ብሏል፡፡

‹‹በዚህ አጋጣሚ የሁለቱ ክልሎች ወንድማማቾች ሕዝቦች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በጊዜያዊ ግጭት ሳይረበሹ፣ ችግሩን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ አግባብ ለዘለቄታው ለመፍታት ሲያካሂዱ የነበረውን ጥረት አጠናክረው በመቀጠል ለችግሩ ዘላቂ እልባት መስጠት ላይ አተኩረው እንዲሠራ፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

ደም አፋሳሹ ክስተት ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን፣ ሁለቱም ክልሎች ድርጊቱ ዳግሞ እንዳይከሰት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...