Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርየኦሮሚያን ልዩ ጥቅም የሚያስከብረው አዋጅ በእርግጥ የሕዝቡን ጥቅም ያስከብራልን?

  የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም የሚያስከብረው አዋጅ በእርግጥ የሕዝቡን ጥቅም ያስከብራልን?

  ቀን:

  አብዛኛውን ጊዜ ችግሮች የሚገጥሙን እኛ እንዲሆንልን የምንፈልገውን ነገር ለማድረግ የሌሎችን ሐሳብም ሆነ ፍላጎት ሳንረዳ፤ ብንረዳም ከቁም ነገር ባለመቁጠር እንደዋዛ ወደ ጎን በመግፋት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ደግሞ ሁልጊዜ ችግር ማስከተሉ አይቀርም፡፡ የደረሰውን ችግር ለማረም ብንፈልግ ግን የሚከፈለው ዋጋ እጅግ የሚጎዳ ነው፡፡ ለእነዚህ ማሳያ የሚሆኑ ጥቂት አብነቶችን ብቻ እንይ፡፡

  ከዚህ በፊት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ አዳማ ተዛውሮ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ከነገሥታቱ ዘመን ጀምሮ የአፍሪካ መዲና፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት (ክፍለ አገር) ዋና ከተማ፣ የመናገሻ አውራጃ ዋና ከተማ ነበረች፡፡ በወቅቱ እነዚህ ሁሉ አካላት ያለአንዳች ችግር በእኩልነት ሲስተናገዱባት ነበር፡፡ ሁሉም ደስተኞች ነበሩ፡፡ አንድም ቀን አንዱ በሌላው ላይ ቅሬታ አቅርቦ አያውቅም፡፡ ነባሩ የመንግሥት መዋቅር ፈርሶ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝም በአዲሱ አወቃቀር የኦሮሚያ ዋና ከተማ እንድትሆን ተደርጋ ነበር፡፡ ነገር ግን ያለምንም የሕዝብ ጥያቄ ወይም ያስከተለው ችግር ሳይኖር የኦሮሚያ ዋና ከተማ ወደ አዳማ ተዛወረ፡፡ ይኼ የዋና ከተማነት ዝውውር ለምን እንደተደረገ የክልልም ሆነ የፌዴራል ባለሥልጣናት የሰጡት አንድም አጥጋቢ መልስ አልነበረም፡፡ ሕዝቡ ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ተቃውሞውን ቀጥሎበት ነበር፡፡ ውሎ አድሮ ግን ያን ሁሉ የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የሠራተኞች ሞራልና የፖለቲካ ኪሳራ ካደረሰ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል፡፡ እንደዋዛ፡፡ ይኼ ስህተት ቢታረምም በመንግሥትና በሕዝቡ መሀል የፈጠረው መጥፎ ስሜት ነበር፡፡

  የ40/60 መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሲጀመር ከአንድ እስከ ሦስት መኝታ ቤቶች ያላቸውን ቤቶች መንግሥት አሠርቶ በቅድመ ክፍያ አፈጻጸማቸው መሠረት ውል የገቡለትን ቤት ለማስረከብ ነበር፡፡ ይኼን ቅድመ ክፍያ ለመፈጸም በአገር ውስጥ ያሉት ተመዝጋቢዎች ከየትም ብለው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ከአምስት ዓመት በፊት ለመንግሥት አስረክበዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ወደ አገር ቤት ለመመለስ እንደ ዋና ችግር አድርገው የሚቆጥሩትን የቤት ዕጦት መንግሥት የሚቀርፍላቸው መስሏቸው የተጠቀሰውን ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ከፍለዋል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በማን አለብኝነት ውላቸውንና ቃላቸውን አፍርሰው ለአንድ መኝታ ቤት የተመዘገቡትን ሁሉ ከውድድር ውጭ አድርገው፣ ማንም ያልተመዘገበለትን ባለአራት መኝታ ሠርተው እነሱን በሚመስላቸው መንገድ ለሚመስላቸው ሰዎች አስረክበዋል፡፡ መንግሥት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብን ለዚህ ሁሉ ዘመን ከግለሰብ ወስዶ ሲሠራበት ከቆየ በኋላ፣ በዚህ መንፈስ ውሉን ማፍረሱ እኛ አገር በመሆኑ ባይጠየቅም በሕግ የሚያስጠይቀው መሆኑን መገንዘብ አለበት፡፡ ኃላፊዎቹም እንደዋዛ ውላቸውን አፍርሰው እንደዋዛ አልተጠየቁም፡፡

  ከሰሞኑ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮችን በተመለከተ በባለሙያ የተተመነ የሕዝብን አቅም ያገናዘበ የመንግሥት ገቢ እንዲሰበሰብ መደረግ ሲገባው፣ መንግሥትን የጠቀሙ መስሏቸው ወይም መንግሥትና ሕዝብን ለማቋቋር ታስቦ ሕዝብ ላይ የማይታመን የግብር ዕዳ ተጭኖበታል፡፡ ‹‹እንደዋዛ›› ይኼ የግምት ተመን 40 በመቶ ስህተት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ‹‹እንደዋዛ›› ለመሆኑ ከመቶ አርባው ከፋይ በስህተት የተወሰነበት ከሆነ በዚህች አጭር ጊዜ ይኼ ሁሉ ከፋይ ትክክለኛ ግምቱን አውቋል ማለት ይቻላል? ለእንደዚህ ዓይነት ግድፈቶች እስካሁን እንደተደረገው ሕዝቡ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተቃውሞዎች የሚደጋገሙና በአጥፊዎች ላይ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ስለማይታወቅ በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ የጥላቻ መንፈስ እየተፈጠረበት ነው፡፡ እነዚህን የመሰሉ በርካታ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡

  መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎች፣ ደንቦችና አሠራሮች ሁልጊዜ በጥልቀት ተጢነው፤ ጥቅማቸውና ጉዳታቸው ተለይቶ፤ ወደፊት ሊያስከትሉት የሚችሉት አደጋዎች ተተንብየው፤ ወደፊት የሚሰጡት ጥቅም የተረጋገጠ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ዋናው ግብዓት የሆነው ሕዝቡ ለይስሙላ ሳይሆን ከልብ የሆነ ተሳታፊነት ሲኖር ነው፡፡ ሕዝብ ሳያምንበት ከላይ ወደ ታች በባለሥልጣኖች ይሁንታ ብቻ ሕግን ለማስፈጸም መሞከር ከተቃውሞን በተጨማሪ ጥላቻና ሁከትንም ይፈጥራል፡፡ አንዳንድ ሕጎች ወይም በውስጣቸው የያዙት አንዳንድ አንቀጾች ባይወጡ ምንም የማይጎዱ ሲሆን፣ ቢወጡም ይኼ ነው የሚባል የጎላ ጥቅም የላቸውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያለጊዜያቸውና ያለቦታቸው ተደንግገው ተቃውሞን የሚያስነሱ አሉ፡፡ ሕግ የሚያስፈልገው ችግሮችን ለመፍታት እንጂ ተጨማሪ ችግር ለመፍጠር አይደለም፡፡ እንደ ግብር ትመናው ዓይነት አሠራር ከጥራትና ከጥናት ጉድለት ትንሽም ቢሆን ሌላ ተቃውሞና ችግር የሚፈጥር ከሆነ ማዘግየት ወይም ማስቀረት ተገቢ ነው፡፡

  ከላይ የተጠቀሱትን አወዛጋቢ አሠራሮችና ደንቦችን ያነሳሁት ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘው ልዩ ጥቅም ተደጋጋሚ ክስተቶችን እንዳይፈጥር በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ያለኝን የግል ምልከታዬን ለማስቀመጥ ነው፡፡

  ይኼ ረቂቅ አዋጅ ከውጣቱ በፊት በተደጋጋሚ ስለፊንፊኔ ዙሪያ አርሶ አደሮችና ከአዲስ አበባ ጋር ስለሚያስተሳስራቸው አንድነትና ልዩነት በተለይ የጥቅም ግጭት የማውቀውን በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አቅርቤያለሁ፡፡ አንባቢ እንዲረዳልኝ የምፈልገው ይኼንን አጀንዳ በተደጋጋሚ ባነሳውም፣ ክልሉ የትውልድ ወይም የመኖርያ አካባቢዬ እንዳልሆነና ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለኝ ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡

  ሁሉም እንደሚረዳው ፊንፊኔና ኦሮሚያ ሊለያዩ የማይችሉ አንዱ በሌላው ውስጥ የሚኖሩ በመሆኑ፣ እንደ አንድ አካል ተቆጥረው በመካከላቸው ልዩነት እንዳይኖር ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ችግርም ከተፈረጠ ደግሞ ግልጽና ፍትሐዊ የሆነ የማያዳግም መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱም የከተማው ዕድገት በአካባቢው ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ በመገመት ለሚደርሰው ጉዳት ልዩ ጥቅም ፈቅዷል፡፡ ተገቢም ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚነሱ ቅራኔዎች አፈታታቸውን ሳናውቅበት ቀርተን ወይም ከላይ እንደተጠቀሱት አብነቶች እንደዋዛ ተፈጻሚ ለማድረግ ብንሞክር ውጤቱ አገር አቀፍ ጉዳት ያስከትላል፡፡

  አንዳንድ ሰዎች ይኼንን የልዩ ጥቅም መብት ኦሮሚያ ከሌላው ክልል በተለየ ሊደረግለት እንደማይገባ ይገልጹና ጉዳዩን ከፖለቲካ ጨዋታ ጋር ያያይዙታል፡፡ ይህን ሐሳብ የሚያነሱት አንዳንዶቹ ሕገ መንግሥቱን በማጽደቅ ሒደት ውስጥ የነበሩና የደገፉም ናቸው፡፡

  ፊንፊኔ አንዳንዶችን እንደምናስበው በለገጣፎና በሰበታ፤ በቡራዩና በአቃቂ መካከል ታጥራ የምትቀር ከተማ አይደለችም፡፡ ብንፈልግም ባንፈልግም መስፋቷና ማደጓ አይቀርም፡፡ ይኼ የማንኛውም ከተማ የተፈጥሮ የዕድገት ባህሪ ነው፡፡ በአዋጅ ልናስቆመውም አንችልም፡፡ ስታድግና ስትሰፋ ደግሞ ዕድገቷ በፊንፊኔ ዙሪያ በሚገኙት የኦሮሚያ መሬት ላይ ብቻ ነው፡፡ በሐዋሳ ወይም በባህር ዳር ላይ አትሰፋም፡፡ ስለዚህ ነው ሕገ መንግሥቱ ለኦሮሚያ ልዩ ጥቅም የሰጠው፡፡ በሌሎች ክልሎችም ይኼ ልዩ ጥቅም ያልተሰጠው ለዚህ ነው፡፡ ልዩ ጥቅም የሚሰጠው ደግሞ ልዩ ጉዳት ለደረሰበት ወገን ብቻ ነው፡፡ ኢንሹራንስ የሚከፈለው ለደረሰ ጉዳት ነው፡፡ ካሳ የሚከፈለውም ለተጎጂው ወገን ብቻ ነው፡፡ በዚህ አንስማማም? ከተስማማን የሚያነጋግረንና የሚያከራክረን ዋናው ጉዳይ ኦሮሚያ ውስጥ የአዲስ አበባ መፈጠርና ማደግ ጉዳት ያደረሰው በማን ላይ እንደሆነ አንጥሮ ማውጣትና የረቂቅ አዋጁ መንፈስም የተቃኘው ከዚህ አኳያ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡

  ተጎጂውን አካል ለመለየት ዋናው መመዘኛ የሚሆነው በከተማዋ መስፋፋት ምክንያት መኖርያቸውን ያጡና መሄጃ አጥተው ያለምትክ ከመኖርያ ቄያቸው ተፈናቅለው መላና መድረሻ ላጡት የአዲስ አበባ ዙሪያ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች መሆን አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች የከተማው መኖር በሚያስከትለው የአካባቢ ብክለት የማኅበራዊ እስቶቻቸው መናጋት እንዲሁም በባህሎቻቸውና በቋንቋቸው ላይ ለሚደርስ ተጨማሪ ጉዳት ተጋልጠው የኖሩ ናቸው፡፡ ይኼ ሕግ ሲጠበቅ የነበረውና የተገመተው በዋናነት የእነዚህን ተጎጂዎች ችግር ሙሉ በሙሉ ይፈታል ከሚል እሳቤ ነው፡፡ እነዚህ ተጎጂዎች መሬታቸውን ለሌላ ተጠቃሚ ሲያስረክቡና ሲለቁ ተረካቢው ያገኘውን የሚያህል ጥቅም እነሱም ማግኘት አለባቸው፡፡ ተረካቢውና አስረካቢው እኩል ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ ከእኩል ተጠቃሚነት ውጪ ሒደቱ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የሚጎዳ ከሆነ እንደ ከዚህ በፊቱ ተቃውሞ፣ ግርግር፣ እልቂት እንደሚፈጠር መጠራጠር የለብንም፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ በተለይም በፊንፊኔና በዙሪያዋ የሚነሳውን ሁከት ለዓላማቸው መጠቀሚያ ለማዋል አሰፍስፈው የሚጠብቁ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ በአገር ውስጥም ቢሆን ኢሕአዴግን ለመጣል ችግሩን የሚፈልጉ አሉ፡፡ ኢሕአዴግ በእስካሁን አካሄዱ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሔ ከማስቀመጥ ይልቅ ችግሮቹን እያባባሰ ነው የመጣው፡፡ ይኼ ሕግ ከላይ የተገለጸውን ችግር ለመፍታትና አደጋን ለማስቀረት ሲጠበቅ የቆየ የመጨረሻ መፍትሔ እንደሆነ መንግሥት ሊያውቀው ይገባል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49/5 በዋናነት እንዲያውም በብቸኝነት ሊባል በሚችል ደረጃ የተቀመጠው፣ እነዚህን ያለጥፋታቸው በአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ በመፈጠራቸው ከሌሎች የአገሪቱ ክፍል ነዋሪዎች የተለየ ልዩ ጉዳት የሚደርስባቸውን ሰዎች ለመታደግ ያስቀመጠው ልዩ ጥቅም መሆን አለበት፡፡ ወለጋና ባሌ ሲጠብም አምቦና አዳማ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአዲስ አበባ መስፋፋት ከሌሎች ክልሎች የተለየ ጉዳት አላደረሰባቸውም፡፡

  የሕጉ ረቂቅ ግን የማኅበራዊ አገልግሎቶች ማለትም ትምህርትን፣ ሕክምና፣ ባሕላዊና ታሪካዊ እሴቶችን በተመለከተ የተቀመጡ በርካታ ግር የሚያሰኙ አንቀጾች አሉ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ይህን ረቂቅ አዋጅ የሚያነብ ሁሉ ፊንፊኔ የኦሮሚያ ዋና ከተማ አይደለችም ወይ? የሚል ጥያቄ ሊያጭርብት ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በራሱ ክልል ዋና ከተማ ውስጥ ለተለያዩ መንግሥታዊና ሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንፃዎችን ለመገንባት መሬት ከሊዝ ነፃ እንዲሰጠው የፌዴራል መንግሥትን አዋጅ ፈልጓል፡፡

  ይኼ ሁሉም ክልሎች በየዋና ከተማቸው የሚያደርጉት ግንባታ ስለሆነ ኦሮሚያን ለይቶ የሚከለክል ሕግ አለ? ወይስ ሁሉም ክልሎች ይኼን የሚፈጽሙት በፌዴራል መንግሥት አዋጅ ነው? ሁሉም ክልሎች ይኼን ጉዳይ የሚፈጽሙት ከየከተማዎቹ አስተዳደር ጋር በመመካከር በማስተር ፕላኑ እየተመሩ ነው፡፡ የኦሮሚያም ጉዳይ ከዚህ መለየት የለበትም፡፡ ነገር ግን ፊንፊኔ ከፌዴራልና ከክልል ዋና ከተማነት በተጨማሪ የአፍሪካ መዲናም በመሆኗ በጥንቃቄ እየተናበቡ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ተቋማት የመገንባት ጉዳይ በሁሉም ክልሎች የሚደረግ በመሆኑ፣ ለኦሮሚያ እንደሚደረግ ልዩ ጥቅም በዚህ አዋጅ መካተቱ ተገቢነት የለውም፡፡

  በአብኛዛው አዋጁ ታሳቢ ያደረገው በፊንፊኔ ውስጥ ለሚኖሩ ኦሮሞዎች ነው፡፡ መግለጫ እንደሚያሳየው ትምህርት ቤት፣ ሐኪም ቤት፣ የባህል ማዕከላት ሁሉም የሚገነቡት ፊንፊኔ ውስጥ ነው፡፡ በርካታ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ፊንፊኔ ውስጥ አሉ ይላል፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሮቹ ያሉት በፊንፊኔ ዙሪያ እንጂ በውስጧ አይደሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ግንባታዎች በፊንፊኔ ዙሪያ ነው መሆን ያለባቸው፡፡ በከተማው ውስጥ እንደማንኛውም ዜጋ ለሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ሊደረግ የታሰበው ድጋፍ ከጥቂቶች በስተቀር መነሻው ግልጽ አይደለም፡፡

  በፊንፊኔ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞችና ዙሪያው የሚገኙ ነዋሪዎች በከተማ ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት እንደማንኛውም የከተማ ነዋሪ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ተደንግጓል፡፡ ይኼ ማለት እነዚህ ነዋሪዎች ቀደም ሲል በከተማዋ የሕክምና ተቋማት ለመገልገል የማይፈቅድላቸው ያስመስላል፡፡ ይኼ ሲፈጸም የነበረ ከሆነ ደግሞ በቅኝ ግዛት ዘመን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሲደረግ ከነበረው አድሎ የባሰ ነው፡፡ ግን አይመስለኝም፡፡ ቀድሞም ቢሆን ያለምንም አድሎ ከከተማ ነዋሪዎቹ ጋር በእኩልነት የሚጠቀሙ ከሆነ ይኼ ድንጋጌ ለምን አስፈለገ? ለኦሮሞ ቅድሚያ ለመስጠት ከሆነ ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ የሚጠቅም አሠራር ሳይሆን ከሌሎች ብሔረሰቦች ለመነጠልና ለማቃረን መንገድ መክፈት ነው የሚሆነው፡፡

  ሌላው ማኅበራዊ ልዩ ጥቅም ተብሎ የተቀመጠው አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ ሠፈሮችና የመሳሰሉት በቀድሞ የኦሮሞ ስማቸው እንዲጠሩ የሚደነግግ ነው፡፡ እንዲያው ለነገሩ አራት ኪሎ፣ አስኮ፣ ሳሪስ፣ መገናኛና የመሳሰሉት ስሞች ከከተማዋ መመሥረት ጋር ዕድገቱ የፈጠራቸው ስሞች እንጂ እንደ አዳማና አምቦ በመንግሥት ትዕዛዝ የተቀየሩ አይደሉም፡፡ በመጀመርያ ከረዥም ጊዜ በፊት የነበሩትን የቀድሞ ስሞች በትክክል ፈልጎ ማግኘቱ ከባድ ነው፡፡ ቢቻል እንኳ ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅሙ ምንድነው? በሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ላይስ የሚፈጥረው ስሜት ተጠንቷል? ይኼ ጉዳይ በአዋጁ ከወጣ ሕግ ነውና ምን ያህል ይተገበራል? የእነዚህን ቦታዎች ስም የሚያወቁ ሰዎች በዚያው በቀድሞ ስሙ ቢጠሩት ማን ከልካይ አለባቸው? ከዚህ የምንረዳው መንግሥት ሄዶ ሄዶ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ነው፡፡ ሁሉን ነገር ወደ ዱሮው ለመመለስ መሞከር ዕድገትን ያለመቀበል ነው፡፡ የሚወጡ ሕጎች የሕዝብን አዕምሮ የሚረብሽ ይዘት ካላቸው የመንግሥት መዋቅሮች አንድን አደጋ ለመጋፈጥ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ከዚህ ለመሸሽ በቅርቡ የኦሮሞያ ክልላዊ መንግሥት የወሰደውን አንድ በሳል ዕርምጃ ለአብነት እንጥቀስ፡፡ የክልሉ መንግሥት በቁቤ የሚሰጠውን ትምህርት ጥራት ለማሻሻል በላቲን ፊደል የተቀመጡትን ቁቤዎች ቅደም ተከተላቸውን ብቻ በመቀየር ቀላል የመማርያ መጻሕፍትን በብዛት በከፍተኛ ወጪ አዘጋጅቶ አቅርቦ ነበር፡፡ ጉዳዩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የክልሉ መንግሥት ምሁራን ያጠኑት መሆኑን በተደጋጋሚ በኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ቀርበው ገልጸዋል፡፡ የሜቴዶሎጂው ጉዳይ እነዚህን ባለሙያዎች የሚመለከት የመሆኑ ጤናማ አሠራር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይኼ ጉዳይ የአፋን ኦሮሞን ትምህርት በማይፈልጉ ሰዎች የተጠነሰሰ ሴራ ነው በማለት ከየአቅጣጫው ከውጭም፣ ከውስጥም ተቃውሞ በመነሳቱ የክልሉ መንግሥት ጥናቱና ዝግጅቱ በሥራ ላይ እንዳይውል እንዲሁም የተዘጋጁት መጻሕፍትም እንዳይሠራጩ አግዷል፡፡ የሕዝብን ስሜት ዓይቶ ይኼንን ዕርምጃ መውሰዱ የክልሉን መንግሥት ያስመሰግነዋል፡፡ የሚያስወቅሰው ነገር ቢኖር ሕዝቡ ሳይወያይበትና ሳያምንበት ይኼንን ከፍተኛ ሀብትና የሰው ጉልበት ማባከኑ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥትም የሕዝቡን ስሜት መከተል ቢችል ያስመሰግነዋል፡፡

  ልዩ ጥቅምን በተመለከተ በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ቅርንጫፍ ላይ ተንጠልጥለን ዋናውን ጉዳይ ረስተናል፡፡ ባለፈው ዓመት ኦሮሚያ ውስጥ የተነሳውና በርካታ ሕይወቱን ያጠፋው ረብሻ መነሻው የአዲስ አበባ መስፋፋት ኑሮዋችንን ብቻ ሳይሆን ህልውናችንን አሳጣን፡፡ መኖሪያ አሳጣን፡፡ ሥራ አሳጣን፡፡ ልጆቻችን ማስተማር ሳይሆን መሰብሰብና መመገብ አቅቶን ተበተኑ፡፡ እኛም ተሰደድን የሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ልዩ ጥቅሙ እነዚህን ጥያቄዎች ነው በተገቢው ሁኔታ መመለስ ያለበት፡፡ የዚህ አዋጅ ማጠንጠኛም ይኼ መሆን አለበት፡፡ ግን ጥያቄዎቹ አልተመለሱም፡፡

  ይኼን ችግር ለመፍታት የተቀመጠ የሚመስለው አንቀጽ ዘላቂ ማቋቋሚያ የሚሆን ካሳ የማግኘት መብታቸውን ለማስከበር የተቀመጠ ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ አንቀጽ ግልጽነት የጎደለው ስለሆነ፣ ቀደም ሲል የነበረውን አሠራር የሚያስቀጥል ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ደንብ በቂ ካሳ በሚል ሽፋን በካሬ ሜትር ከሁለት ብር ተነስቶ 50 ብር አካባቢ ደርሷል፡፡ ይኼ ግን ከላይ የተጠየቀውን የሕዝብ ጥያቄ ሊያሟላ ቀርቶ የአንድ ዓመት መንደርደሪያም አይሆንም፡፡

  በማጠቃለያ ላይ ግን ማወቅ ያለብን የሕዝብ ጥያቄዎች የሆኑት ዋና ጉዳዮች ሕዝቡ አንድም ቀን ጠይቆት በማያውቀውና ቢፈጸሙም ደንታ በማይሰጠው ግን በማይቃወማቸው አንቀጾች መሸፈን እንደማይገባው ነው፡፡ አስኮና አራት ኪሎ የሚለው ስም ጎረበጠኝ የሚል ጥያቄ ከኦሮሞ ሕዝብ ተደምጦ አያውቅም፡፡ በአጠቃላይ ከሌላው የአገሪቱ ሕዝቦች የተለየ ጥቅምም ፈልጎም ጠይቆም አያውቅም፡፡ የሚጠይቀው ለልዩ ጉዳቱ ልዩ ጥቅም ነው፡፡ የተወሰኑ የኦሮሞ ልሒቃን የሚያነሱዋቸው በርካታ የንድፈ ሐሳብ ጥያቄዎች ለአሁኑ ተጨባጭ ችግር መሸፈኛ እንዳይሆኑ ይታሰብበት፡፡ የረቂቅ ሕጉን አንቀጾች አንድ በአንድ ዓይተን ልዩ ጥቅም ናቸው ወይስ አይደሉም? ከሚለው መነሻ ብንመረምረው ጥሩ ነው፡፡ በሕግ ያልተከለከለን የልማት ሥራ ሁሉ በልዩ ጥቅምነት ማስቀመጥ ተገቢነት ይጎድለዋል፡፡ ከአዋጁ በፊት ኦሮሚያ በርካታ መሥሪያ ቤቶችንና ውብ የባህል ማዕከሉን በከተማው እምብርት ላይ ሲሠራ እንደ ልዩ ጥቅም ተቆጥሮ በአዋጅ አይደለም፡፡ ቅሬታም ሆነ ተቃውሞም አልቀረበበትም፡፡ ሊቀርብበትም አይገባም፡፡ በዋና ከተማው ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚሠራቸው ማንኛውም የልማትና የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት ግንባታ ልዩ ጥቅም ተብለው በአዋጅ የሚቀመጡ አይደሉም፡፡ እነዚህ ተቋማት እንደ ልዩ ጥቅም ሳይሆን እንደ መብት በፊንፊኔ ዙሪያ አርሶ አደሮች መኖሪያ አካባቢ ቢገነቡ የተሻለ ትርጉም ይኖራቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩ ኦሮሞዎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደመሆናቸው ከሌላው የከተማ ነዋሪ የተለየ መብትም ሆነ ጥቅም አይገባቸውም፡፡ ፍትሐዊም፣ ሕጋዊም ስለማይሆን አዋጁ ከፀደቀ በኋላ ተግባራዊነቱ መጤን ያለበት ከወዲሁ ነው፡፡   

  (ሳሙኤል ረጋሳ፣ ከአዲስ አበባ)

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...