Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ከዕለታት በአንዱ ቀን ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ የሚያሳፍረው ታክሲ ውስጥ ገባሁ፡፡ ወያላው እየደጋገመ፣ ‹‹ካዛንቺስ በአቋራጭ…›› እያለ ሲጣራ አንድ ዕድሜው ከአሥር ዓመት የማይበልጥ ልጅ ጠጋ ብሎ በራፉ አጠገብ ቆመ፡፡ ልጁ ፊቱ የቆሸሸ፣ ፀጉሩ የተንጨባረረ፣ ልብሱ ከመቀዳደዱና ላዩ ላይ ከመቆሸሹ የተነሳ ቀለሙን ለመናገር ያዳግታል፡፡ ለምፅዋት እጁን ሲዘረጋ አንዱ በቁጣ፣ ‹‹ለምንድነው የምትለምነው? ትምህርት ቤት አትሄድም?›› ይለዋል፡፡ ይኼኔ ታክሲው ውስጥ የመገረምና የመናደድ አስተያየቶች ተሰነዘሩ፡፡

  ለታዳጊው ልጅ ድፍን አምስት ብር ከቦርሳዋ ውስጥ አውጥታ የሰጠችው ቆንጅዬ ወጣት፣ ‹‹ድህነት አፈር አስመስሎት እያየህ እንዴት እንዲህ ዓይነት የማይገባ ነገር ትናገራለህ?›› በማለት ሰውየውን ገላመጠችው፡፡ ሌሎች ተሳፋሪዎች የቻሉትን ያህል ታዳጊውን ልጅ ከመፀወቱት በኋላ ታክሲው ተንቀሳቀሰ፡፡ በልጁ የተነሳ የተቀሰቀሰው ውይይትም ቀጠለ፡፡ በታዳጊው ልጅ ጉስቁልና ልቡ የተነካ ሌላ ጎልማሳ፣ ‹‹አትፍረድ ይፈረድብሃል ይባላል፡፡ ይህ የረሃብ ጠኔ ከሰው ተራ ያስወጣው ሕፃን የሚበላውና የሚጠጣው ቢኖረው ኖሮ እንዲህ ሆኖ ለልመና ይወጣ ነበር? የልጅነቱ ወዘና ተሟጦና ከሰውነት ተራ ወጥቶ ዓይኖቹን ያቁለጨልጭ ነበር? እዚህ አገር ብዙ ጊዜ በሰዎች ላይ የሚሰጡ አስተያየቶች ከእውነታ ጋር አይመሳሰሉም፡፡ ግልጽና ወለል ብሎ በሚታይ ጉዳይ ላይ ዕይታችን ለምን ይንሸዋረራል? ይህንን ጎስቋላ ጨቅላ ልጅ ለምን ትለምናለህ? ለምን ትምህርት ቤት አትሄድም? እያሉ መመፃደቅ የጤና ነው?›› ብሎ ተብሰከሰከ፡፡ አነጋገሩ ለሰውየው ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡን በሰላ ትችት የሚሸነቁጥ ይመስል ነበር፡፡

  ልጁን አስደንብሮ ለማባረር የቃጣው ሰውዬ ቆንጅዬዋ ወጣትና ጎልማሳው ሲፈራረቁበት አንዲትም ቃል አልወጣውም፡፡ ይልቁንም ‘አልሰማችሁም’ በሚል ስሜት ስልኩን አውጥቶ በኢርፎን ጆሮውን ደፍኖ ሌላ ዓለም ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህ መሀል ወያላው፣ ‹‹እናንተ የሚለምነውን ጎስቋላ ልጅ ብቻ መሰላችሁ እንዴ? ይኼን ሰሞን አንዱ ዘመናዊ ነኝ የሚል ዘናጭ ቢጤ ‘ስማ ታክሲ ላይ ስትጮህ ከምትውል ለምን አትማርም?’ ሲለኝ ነዶኝ ስለነበር፣ ከዘመኑ የተማርን ነን ከሚሉ ያንተ ቢጤዎች እኛ ምንም የማናውቀው እንሻላለን ብዬ አፉን አስያዝኩት፡፡ ሠርተን ቢያንስ በቀን አንዴ ለመጉረስ ስንጣጣር የአደናቃፊው መብዛቱ…›› እያለ ብሶቱን ዘረገፈው፡፡ ‘ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ’ ነው የሚባለው ለካ ልክ ነው፡፡

  ሾፌሩ በኋላ መመልከቻ መስተዋቱ አጨንቁሮ እያየን፣ ‹‹አንዱ ደግሞ ‘ታክሲ መንዳት እኮ ሥራ አይመስለኝም’ እያለ ሲዘባነንብኝ፣ መቀመጫህን ፀሐይና ንፋስ እያስመታህ መሳቂያ ከምትሆን ና ወያላ ላድርግህ ስለው በስንት ገላጋይ ነው የተለያየነው፡፡ ሾፌር ሲሆኑ መከራ፣ ወያላ ሲሆኑ መከራ፡፡ የእኛ ሰው እከሌ እኮ ኃይለኛ ሞጭላፋ ነው ሲባል ‘በቀን ስንት ይዘጋል?’ ብሎ በጉጉት ይጠይቅሃል፡፡ ከንቱ ብቻ…›› እያለ የታክሲውን ፍጥነት ጨመረ፡፡ ታክሲው ውስጥ ሁሉም አጠገቡ ካለው ጋር ወግ ይዟል፡፡ በአማካይ ማለት ይቻላል ሰዎች ያለምንም ማገናዘብ በሚሰጡት አስተያየት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ለነገሩ በደመነፍስ በይመሻል በይነጋል ዘይቤ ያለማስተዋል የሚኖሩ በዝተው የለ? ወይ ግሩም፡፡

  ታላቁን ቤተ መንግሥት አልፈን ወደ መናኸሪያ ስናቆለቁል የታክሲያችንን አጀንዳ የቆሰቆሰው ሰውዬ ስልክ ጮኸ መሰል መነጋገር ጀመረ፡፡ ‹‹እባክህ ተወኝ፡፡ የመሰለህን ስትናገር ሐበሻ ምሳሩን ይዞ ይነሳብሃል፡፡ እኔ እኮ እሷን ለማስቀየም ብዬ ሳይሆን የመሰለኝን ነው የተናገርኩት፡፡ በቃ ልጅሽ ዱባ ይመስላል ነው ያልኩት፡፡ ይህ የሚያናድዳት ከሆነ አይ አም ቬሪ ሶሪ…›› ብሎ ስልኩን ሲዘጋው ታክሲው ውስጥ የነበርን ሁሉ በድንጋጤ ክው አልን፡፡ የፈለገውን ያህል ሠልጥነናል ቢባል እንዲህ ይባላል? ‹‹ሐበሻ የሠራውን ካልበሉለት፣ የወለደውን ካልሳሙለት…›› በሚባልበት አገር ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን አስከፊ አባባል መስማት ያሳዝናል፡፡ የድሮ ሰዎች ‘ወፍ ዘራሽ’ የሚሉት እንዲህ ዓይነቱን ነው እኮ፡፡

  የሚወራውን ሁሉ በዝምታ ሲያዳምጡ የነበሩ አንድ ትልቅ ሰው ያንን ነገር ቀስቃሽ ሰው፣ ‹‹ሰማህ ወዳጄ? እኔ ካንተ አላውቅም፡፡ ነገር ግን በረሃብ የተጎሳቆለ ሕፃን ለምን ትለምናለህ? ከዚያም አልፈህ ተርፈህ እንዴት ትምህርት ቤት አልሄድክም? እያልክ ስትቆጣ በትዝብት ሰማንህ፡፡ አሁን ደግሞ ከተከበረው የጋራ ባህላችን አፈንግጠህ የአንዲት ሕፃን እናትን ልጅሽ ዱባ ይመስላል ብያታለሁ ትላለህ፡፡ ምን ነካህ ልጄ? ምን የገጠመህ ችግር አለ?›› በማለት ጠየቁት፡፡ ግራ የሚያጋባ ነገር ሲፈጠር ከመጠየቅ ሌላ ምን ይደረጋል?

  ሰውየው ምንም ነገር ያልተፈጠረ ይመስል ትከሻውን እየሰበቀ፣ ‹‹የእኔ የግል አስተያየት ለምን እንደገረማችሁ አልገባኝም፡፡ አገሪቱ ውስጥ ስንትና ስንት አፀያፊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ዝም እያላችሁ በአንድ ግለሰብ አስተያየት ምን ያንጨረጭራችኋል?›› ብሎ የስልኩን ኢርፎን ጆሮው ውስጥ ወትፎ ፊቱን ወደ መስኮቱ አዙሮ ፀጥ አለ፡፡ በሰውየው አነጋገርና አኳኋን የተናደደችው ቆንጅዬዋ ወጣት፣ ‹‹እንዲህ ዓይነቶቹ ኃላፊነት የማይሰማቸው ከንቱዎች እኮ ናቸው በየቦታው እየተሾሙ ሲያምሱን የሚኖሩት፡፡ መንግሥት መሥሪያ ቤት፣ የግል ድርጅትና የመሳሰሉት ብትሄዱ የምታገኙት እንዲህ ዓይነቶቹን ከንቱዎች ብቻ ነው፡፡ በቴሌቪዥን በአጓጉል ንግግራቸው ያበግኑናል፡፡ ከንቱ ማስታወቂያ እየለፈፉ ያበሳጩናል፡፡ እንጨት እንጨት የሚል ፕሮፓጋንዳ እየጋቱን ያደነቁሩናል፤›› ካለችን በኋላ፣ ‹‹ለዓለምም ሆነ ለአገር ጠንቅ የሚሆኑት እነማን እንደሆኑ ታውቃላችሁ? ሥነ ምግባር የሌላቸውና ኃላፊነት የማይሰማቸው ህሊና ቢሶች ናቸው…›› ብላ ስታሳርግ አዛውንቱ በበኩላቸው፣ ‹‹አንዳንቺ ዓይነቶቹ ፈሪኃ እግዚአብሔር ያላቸው ባይኖሩ ደግሞ ምን ይውጠን ነበር?›› ብለው የተረባበሸ ስሜታችንን አሰከኑት፡፡ በእርግጥም ህሊና ቢሶች በበዙበት ዘመን ደህና ሰዎች ባይኖሩን ምን ይውጠን ነበር? በተለይ በዚህ ዘመን በግልብ አስተሳሰብ መርዝ ሲረጩ የሚኖሩትን የሚያስታግሡልንና ጀርባቸውን የሚሰጡ ታጋሾች ባይኖሩን ምን እንሆን ነበር? እኔ እንጃ!

  (መኮንን አለማ፣ ከለም ሆቴል)

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...