Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክረቂቁ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ስለመጥሪያና ተከሳሽ በሌለበት ጉዳይ ስለማየት

  ረቂቁ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ስለመጥሪያና ተከሳሽ በሌለበት ጉዳይ ስለማየት

  ቀን:

  በታምራት ኪዳነማርያም ዶሜኒኮ

  እየተረቀቀ ያለው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ረቂቅ ሕግ በአንቀጽ 247(1) ላይ ከቀላል የወንጀል ጉዳዮች ውጪ ባሉ ጉዳዮች ተከሳሽ መጥሪያ ተልኮለት ወይም ደርሶት ካልመጣ በሌለበት ሊታይ ይችላል ሲል ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል አሁን በሥራ ላይ ያለው በ1954 ዓ.ም የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 161 (2) (ሀ) እና 162 (ሀ) ከ12 ዓመት በታች በማያንስ ጽኑ እስራት በሚያስቀጣ ወንጀል የተከሰሰ ሰው ወይም በመንግሥት የቀረጥ፣ የግብር ገቢዎችና የገንዘብ ጥቅሞች ላይ ወንጀል በመፈጸም (ከግብርና ታክስ፣ ከሕጋዊ የመገበያያ ገንዘብ ኖቶች ጋር የተያያዘ ወንጀሎችን በመሥራት) የተከሰሰ ሰው ሊቀርብ ካልቻለ፣ በኦፊሰላዊ ጋዜጣ ተጠርቶ ካልመጣ ጉዳዩ በሌለበት ሊታይ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

  በሁለቱ ሕጎች መካከል ያለው ልዩነት በ1954ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ (አሁን ሥራ ላይ ባለው) በወንጀል የተከሰሰ ሰው ያልቀረበ እንደሆነ በሌለበት ጉዳዩ ሊታይ የሚችለው ወይ በከባድ ወንጀል ከተከሰሰ (እንዲያውም እንዳንዳንድ የሕግ ምሁራን መነሻ ወለሉ ከ12 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ ወንጀል ክስ ከቀረበበት) ያለበለዚያም በመንግሥት የኢኮኖሚና የገንዘብ ጥቅሞች ላይ ወንጀል በመፈጸም ከተከሰሰ ብቻ ነው፡፡ በአንፃሩ እየተረቀቀ ባለው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ግን ማንኛውም ከቀላል ወንጀሎች ውጪ ባሉ ተራና መደበኛ የወንጀል ጉዳዮች የተከሰሰ ሰው ሁሉ ካልቀረበ ጉዳዩ በሌለበት ይታያል፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ ከሁለቱ የትኛው ይሻላል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡

  ይህንን ለመመለስ በወንጀል ጉዳይ የተከሰሰ ሰው ራሱ በአካል እንዲቀርብ የሚጠራው (የሚፈለገው) ለምንድን ነው ብለን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ረቂቁ የወንጀል ሥነ ሥርዓቱ ሕግ አንቀጽ 240 (1) (ሀ) በወንጀል ለተከሰሰ ሰው መጥሪያ የሚላክበት ምክንያት የተከሳሽን የመስማትና የመከላከል መብት ለማክበርና የተጠያቂነት ግዴታውን እንዲወጣ ለማስቻል መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ሁለት ነገሮችን እንረዳለን፡፡ በወንጀል የተከሰሰ ሰው እንዲቀርብ የሚደረግበት ምክንያት አንድም የተከሳሹን የመሰማትና የቀረበበትን ክስ የመከላከል (የመጋፈጥ) (ፍትሐዊ ዳኝነት የማግኘት መብት) (Due Process of Law) ለማክበርና ከሌላ አቅጣጫ ደግሞ እሱም በበኩሉ የተጠያቂነት ግዴታውን እንዲወጣ ለማስቻል ወይም የኅብረተሰቡን፣ የመንግሥትንና የተጎጂዎችን የመፋረድ መብትና ፍላጎት ለማሟላት ሲባል ነው፡፡ በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 20 (5) ላይ ማንኛውም በወንጀል የተከሰሰ ሰው የቀረበበትን ክስ የመከላከል (በእሱ ላይ የቀረበበትን ማስረጃ የመመልከት፣ መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ፣ የራሱን ማስረጃ የማቅረብ ወዘተ.) መብት እንዳለው የተደነገገ ሲሆን፣ ይህ ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ የሰብዓዊ መብት ቃልኪዳኞችና ስምምነቶች ላይም የተረጋገጠ መብት ነው፡፡ ስለዚህም በወንጀል የተከሰሰ ሰው ጉዳዩ በሚታይት ጊዜ የግድ እንዲቀርብ የሚደረገው አንድም ተከሳሹ የመከላከል ሰብዓዊ መብቱን እንዲጠቀም ለማድረግና ለራሱ ለተከሳሹ ጥቅም ሲባል መሆኑን ለመረዳት እንችላለን፡፡

  በፍርድ ቤት አንድ የወንጀል ጉዳይ ተከሳሹ ሳይቀርብ በሌለበት የታየ እንደሆነ ግን ተከሳሹ ባለመቅረቡ ብቻ የመሰማትና የቀረበበትን ክስ የመከላከል መብቱን ሊጠቀምበት እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ የወንጀል ተከሳሾቹን ሳይቀርቡ በሌሉበት ዳኝነት የማየት አሠራር የመስማትና የመከላከል ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንደሚገድብ ምንም አያከራክርም፡፡

  በእርግጥ መብቶች በሙሉ (ሕገ መንግሥታዊ ሰብዓዊ መብቶችም ጭምር) ፍፁማዊ እንዳልሆኑና በሕግ ሊገደቡ እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ሕግ አውጪው ሕገ መንግሥታዊ መብቶችንም ጭምር የመገደብ ሥልጣን ቢኖረውም፣ ይህ የሕግ አውጪው ሥልጣን በራሱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተገደበ ነው፡፡ ለመሆኑ ሕግ አውጪው በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ ሰብዓዊ መብቶችን ሊገድብ የሚችለው ምን ድረስ ነው? ምን ምን ሁኔታዎችስ ሲሟሉ ነው? ብሎ መጠየቅ መልካም ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡት ሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር ተጣጥመው እንደሚተረጎሙ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13(2) ላይ ተደንግጓል፡፡ በዓለም አቀፍ ስምምነት የተረጋገጡ ሰብዓዊ መብቶች ደግሞ (በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች የመከላከልና የመስማት መብትን ጨምሮ) የሚገድቡት የተወሰኑ የሕግ መስፈርቶች ሲሟሉ ነው፡፡ እነኚህም አንደኛ ገደቡ በሕግ መደንገግ አለበት፡፡ ሁለተኛ ሕጉ ለሕዝብ ይፋ መሆን አለበት፡፡ ሦስተኛ ሕጉ በተቻለ መጠን ግልጽ መሆን አለበት፡፡ አራተኛ መብቱን መገደብ ያስፈለገበት አጥጋቢ ምክንያት ወይም ተቀባይነት ያለው ግብ መኖር አለበት፡፡ አምስተኛ መገደብ ያስፈለገበትን ግብ ለመምታት ሰብዓዊ መብት ከመገደብ ውጪ ሌላ አማራጭ መኖር የለበትም፡፡ ስድስተኛ ገደቡ በተቻለ መጠን መስፋት የለበትም፤ ገደቡ ሊያሳካው ያለመው ግብና ገደቡ የሚያስከትለው ጉዳት ተመጣጣኝ መሆን አለባቸው፡፡

  በ1954 ዓ.ም. የወጣው አሁን እየተሠራበት የሚገኘው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓታችንም ሆነ እየተረቀቀ ያለው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ የመንግሥትን፣ የኅብረተሰቡንና የተጎጂዎችን ጥቅምና የመፍረድ መብት ለማስከበር ሲሉ ሳይቀርቡ በቀሩ የወንጀል ተከሳሾች የመስማትና የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ መብት ላይ ገደብ አስቀምጠዋል፡፡ ነገር ግን ተመጣጣኝነቱን ስንመዝን እየተሠራበት ያለው የ1954ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት ሕጋችን የገደበው የሁሉንም በተለያየ ምክንያት ሳይገኙ ወይም ሳይቀርቡ የቀሩ የወንጀል ተከሳሾችን የመከላከልና የመሰማት መብት ሳይሆን በከባድ ወንጀል (ቢያንስ ከ12 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ) የተከሰሱ ሰዎችን (ለምሳሌ በከባድ (በግፍ) አገዳደል፣ በዘር ማጥፋት፣ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፣ በጦር ወንጀለኛነት ወዘተ) እና በመንግሥት የኢኮኖሚና የገንዘብ ጥቅሞች ላይ (ግብር እና ታክስ መሰወር፣ ኮንትሮባንድ፣ የተጭበረበሩ የገንዘብ ኖቶች ማዘዋወር ወዘተ) ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩ ሰዎችን ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን ተከሳሽ ግለሰቦቹ የመከላከል ሰብዓዊ መብት ቢኖራቸውም፣ ከወንጀሎቹ ክብደትና በኅብረተሰቡም ሆነ በመንግሥት ላይ ደርሷል ተብሎ ከሚገመተው ጉዳት ክብደትና የመፋረድ ፍላጎት አንፃር በሌሉበት ጉዳዩ እንዲታይ መደረጉና መብታቸው ለከባድ ጉዳዮች ብቻ መገደቡ (በ1954 ዓ.ም. የወጣውና እየተጠቀምንበት የምንገኘው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ያስቀመጠው ገደብ) በጽሑፍ አቅራቢው እምነት ተመጣጣኝ ነው፡፡ ረቂቅ ሕጉ ግን ከቀላል ወንጀሎች በስተቀር በተራና በመደበኛ ወንጀሎች ሳይቀር ሁሉንም ሳይቀርቡ የቀሩ ተከሳሾችን ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ በመደንገግ የመከላከልና የመስማት ሰብዓዊ መብታቸውን መግፈፉ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ፣ እንደ ጽሑፍ አቅራቢው እምነት ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫል፡፡ በዛ ላይ በተራው ወንጀል ሁሉ ሳይቀር ያልቀረቡ ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት የሚታይበት አሠራር ከመጣ ተከሳሾቹ እያሉ አንዳንዴ በተንኮል አንዳንዴም በቸልተኝነት አልተገኙም እየተባለ ተፈርዶባቸው የሚቀጡበት ሁኔታ ስለሚፈጠር፣ ለብልሹ አሠራር በር እንደሚከፍትም ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በወንጀል ጉዳይ ተከሳሽ በሌለበት ዳኝነት የማየት አሠራር የሕዝብንና የመንግሥትን እንዲሁም በጣም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ተፋራጆች መብትን ጥቅም ለማስከበር ሲባል አልፎ አልፎ የሚካሄድ እንጂ መደበኛ አሠራር መሆንም የለበትም፡፡ ያውም በከባድ ጉዳዮችም ቢሆን በሌለበት ማየት ተገቢነት የሚኖረው መጥሪያ ተቀብሎ የቀረውን ተከሳሽ ይዞ ለማቅረብ በቂ ጥረት ከተደረገ በኋላ ብቻ ነው፡፡   

  ነገ ከዛሬ የተሻለ ፍትሕ የሚገኝበት ጊዜ እንዲሆን ከፈለግን ዛሬ የምናወጣቸው ሕጎች ከትላንቱ የተሻሉ ፍትሐዊና ሰብዓዊነትን የተላበሱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ስለዚህ ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 247(1) ሕጉ ከመጽደቁ በፊት ሊሻሻል (አሁን ባለበት ሁኔታ ሊቀጥል) ይገባል፡፡

  ካነሳነው አይቀር የወንጀል ተከሳሾች በሌሉበት ጉዳያቸው በሚታይበት ጊዜ እነሱ ባይቀርቡም ጠበቃ እንዲያቆሙ ሊፈቀድላቸው ይገባል አይገባም የሚል ጥያቄም በአዕምሯችን ሊመጣ ይችላል፡፡ የጽሑፍ አቅራቢው በአንድ ወቅት በዳኝነት በምሠራበት ጊዜ አንድ ግብር በመደበቅ የተከሰሱ ተከሳሽ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ከአገር እንዲወጡ በመደረጋቸው የተነሳ የግብር ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩ በሌሉበት ይቀጥልልኝ አለ፡፡ ሰውዬው ይቀርቡ በነበሩ ጊዜ ይከራከሩላቸው የነበሩ ጠበቃቸው ደግሞ እንዲህ ከሆነ እኔም እንድቆምላቸው ይፈቀድልኝ የሚል ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ዳኞቹም ጠበቃውን ‹‹እንዴት እርስዎ ለሌሉ ተከሳሽ ጥብቅና ልቁም ይላሉ? ለመሆኑ እርስዎ ከቆሙላቸው ጉዳዩ በሌሉበት ታየስ ለማለት ይቻላል ወይ?›› አልናቸው፡፡ እሳቸውም ተከሳሹ በሌሉበት የሚታይበት ምክንያት እኮ ተከሳሹን ለመጉዳት ሳይሆን ከጉዳዩ ክብደት አንፃር ዳኝነት ሳይሰጥ እንዳይቀር ለማድረግ ነው፡፡ ሰውዬው ባይኖሩም ጠበቃ የማቆም ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ግን ሊከበር ይገባል በማለት ተከራከሩ፡፡ የችሎቱ ዳኞች ቀጠሮ ሰጥተን ብዙ አሰብንበት፤ መጽሐፎችም ተመለከትን፤ በመጨረሻም ጠበቃው ቢቆሙ የተሻለ ፍትሕ እንዲገኝ ከሚረዳ ውጪ የማንንም መብት እንደማይጎዳ ስምምነት ላይ ስለደረስን ጠበቃው እንዲቆሙ ፈቀድንላቸው፡፡ በእርግጥም ሰብዓዊ መብቶች ሲገደቡ በተቻለ መጠን ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ መሆን አለበት፤ ገደቡ ከሚፈለገው በላይ መስፋትም የለበትም፡፡ ስለዚህ ጉዳያቸው በሌሉበት የሚታዩ ተከሳሾች ከጉዳዩና ከወንጀሉ ክብደትና ከመንግሥት ጥቅም አንፃር የመከላከልና የመሰማት መብታቸው መገደቡ ሳያንስ፣ ጠበቃ የማቆም መብታቸው የሚነፈግበት ምንም ምክንያት ባለመኖሩ ቤተሰቦቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው ጠበቃ ሊያቆሙላቸው እንደሚችሉና በተለይ የፍትሕ መነፈግ ይደርሳል ተብሎ ከተገመተና ቤተሰብ ጠበቃ ሊያቆም ካልቻለ እንዲያውም መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመድብ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል በረቂቅ ሕጉ ውስጥ ሊካተት ይገባል፡፡

  ሌላም ሳናነሳ መለያየት የሌለብን ነገር በረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 247 (4) ላይ ጉዳዩ በሌለበት የታየ ተከሳሽ ሳይቀርብ የቀረው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት መሆኑን ያስረዳ እንደሆነ፣ ጉዳዩ እንደገና እንደሚታይለት የሚደነግግ ሆኖ ሳለ ወረድ ብሎ በዚሁ በአንቀጽ 247 በንዑስ ቁጥር 6 ሥር ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ማለት ማንኛውም ምክንያታዊ ሰው አስቀድሞ ሊገምተውና በፍጹም ሊያስቀረው የማይችለው ምክንያት ነው በማለት ያስቀምጣል፡፡ በንፅፅር የ1954 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓቱን ስንመለከት አንቀጽ 199 (ለ) ከአንቀጽ 197 ጋር ሲገናዘብ ተከሳሹ ወይም ጠበቃው ከአቅም በሆነ ኃይል ምክንያት መቅረብ አለመቻላቸውን ማስረዳት የተቻለ እንደሆነ በሌለበት የተሰጠው ፍርድ ውድቅ ሆኖ ጉዳዩ እንደገና ይታያል ሲል ይደነግጋል፡፡ የ1954ቱ ሕግ ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል ምንድነው የሚለውን ለዳኞች ሚዛን ከሚተወው ውጪ ምክንያታዊ ሰው ሊገምተውና ፍጹም ሊያስቀረው የማይችለው ነገር ነው በማለት አያጠበውም፡፡ ለምሳሌ ጀርመን አገር ለትምህርት የሄደ ሰው መጥሪያው በፖስታ ቢላክለትና ፈተና ስለደረሰበት፣ የአውሮፕላን ወጪውም ቅርስ ካልሸጠ በስተቀር የማይወጣው ሆኖ ስላገኘው ሳይመጣ ቢቀርና በሌለበት ታይቶ ቢፈረድበት በኋላ መጥቶ አንሱልኝና ልከራከር ብሎ ቢጠይቅ ፍጹም ልታስቀረው የማትችለው ነገር አላጋጠመህም፣ ያለህን ከፍለህ፣ ፈተናህን ትተህ መምጣት ትችል ነበር ተብሎ በመብቱ እንዳይጠቀም ሊከለከል ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ረቂቁ ከአቅም በላይ የሆነን ምክንያት ሲተረጉም ፍጹም ለማስቀረት (ለመቋቋም) የማይቻል ነገር ነው ብሎ ከሚጠብቀው ይልቅ ትርጉሙን እንደ 1954ቱ ሕግ ለዳኞች ቢተወው ወይም ምክንያታዊ ሰውን ቀጠሮውን አክብሮ እንዳይቀርብ የሚያውከው ማናቸውም ከባድ ሁኔታ ነው በማለት ቢተረጉመው የተሻለ ነው እላለሁ፡፡  

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ፡፡

   

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img