ዓውደ ዓመት ሊመጣ ነው ሲባል የበግ፣ የፍየል፣ የቅቤ፣ የዶሮና የእንቁላል ገበያ ይጦፋል፡፡ የአልባሳት መደብሮች ገበያ ይሞቃል፡፡ ሌላው ቀርቶ የቤት ዕቃዎችን ሁሉ የሚሸጡ ድርጅቶች የበዓል ሰሞን ገበያቸው ይደራል፡፡ ይህ የተለመደ ነው፡፡ አዳዲስ የሙዚቃ ካሴቶችና ሲዲዎችም እንደልብ የሚሸመቱበት ወቅት ቢኖር የዓውደ ዓመት ወቅት ነው፡፡
ነገር ግን የሌላው ገበያ ሲቀጥል ዓውደ ዓመትን ታከው ገበያውን ያጨናንቁ የነበሩ የሙዚቃ ሥራዎች ዛሬ እምብዛም አይታዩም፡፡ እንደውም የሉም ወደሚል መደምደሚያ እየወሰደን ነው፡፡ አንድ ወይም ሁለት ዓመታትን ጠብቀው ካሴት ወይም ሲዲ ያወጡ የነበሩ አቀንቃኞችም፣ ዓውደ ዓመት ሰሞን አዳምጡልን የሚሉትን ሥራዎቻቸውን አቁመዋል ማለት ይቻላል፡፡ እንደው የዓውደ ዓመት ማግስት ሆኖ ይህንን ላስታውስ እንጂ ከበዓላት ውጪም ቢሆን ወጣት ድምፃዊያንም ሆኑ በሙዚቃ ሥራቸው የምናውቃቸው ድምፃውያን አዳዲስ ሥራዎቻቸውን ለማግኘት አስቸጋሪ ሆነኗል፡፡ እንደ ሙዚቃ ሥራዎች ሁሉ አንድ ሰሞን ርዕሳቸውን እንኳን በቅጡ ለመያዝ እስኪያቅተን ድረስ በአናት በአናቱ ይወጡ የነበሩ ፊልሞች ዛሬ ዛሬ እልም ብለው ጠፍተዋል፡፡ እነዚህ የጥበብ ሥራዎች እልም የማለታቸው ምክንያት ለሚዜም ሙዚቃ፣ ለፊልም የሚሆን ድርሰት ጠፍቶ እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኧረ ካሴት የሚያሳትም ጠፋ ሲባል ግን፣ የምንሰማው ከቅጂ መብት ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ችግር ስለመሆኑ ሁላችንም የምንስማማበት ነው፡፡ እረግጥ ነው እንደቀድሞው አዳዲስ አልበሞች ላለመኖራቸው እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚወሰደው ይኼው የቅጂ መብት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ባለሙያዎች ‹‹ነጠላ›› የሚባሉ ዜማዎችን በመልቀቅ ብቻ እየተወሰኑ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን አሁን አሁን እየታዘብኩት የመጣሁት ሌላው ጉዳይ ደግሞ ለሙዚቃ አልበሞች እንደልብ ያለመታተም ምክንያት የሆነውን የቅጂ መብት ችግር ተቋቁመው የሚታተሙ አልበሞችም ቢሆኑ ለአድማጭ የሚደርሱበት መንገድ የተምታታ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ እንደውም የሙዚቃ አልበሞችና የፊልም ሥራዎች የግብይት ሥርዓት እጅግ አሳሳቢ ከሆነ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ላይ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡
በግሌ ወቅታዊው የሙዚቃና የፊልም ሥራዎች አጠቃላይ የግብይት ሒደት ኢንዱስትሪው የገባበት ችግር ስፋት ዘርፈ ብዙ እየሆነ መምጣቱንም እንድገምት አድርጎኛል፡፡ ይህንን ለማለት የደፈርኩት ከሰሞኑ የታተሙ የሙዚቃ ሥራዎችን ለመግዛት ያየሁት ውጣ ውረድ ነው፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ወጡ የተባሉትን የሙዚቃ አልበሞች ለመግዛት ከዚህ ቀደም ወደማውቃቸው ‹‹ቪዲዮ ቤት›› ወይም ‹‹ሙዚቃ ቤት›› ወደሚባሉ መደብሮች ባቀናም፣ አይደለም ሲዲዎቹን ራሳውን እንኳን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ መደበሮቹ ለሌላ አገልግሎት ውለዋል፡፡ ነገሩ ገርሞኝ በቅርብ የማውቃቸውን ሰዎች እስቲ በአቅራቢያችሁ የቪዲዮና የሙዚቃ መደብሮች አሉ ወይ? ብዬ እስከመጠየቅ ደርሻለሁ፡፡ የጠየቅሁዋቸው በሙሉ እነዚያ የሚያውቋቸው የመዚቃና የቪዲዮ መደብሮች የሌሉ መሆኑን አረጋግጠውልኛል፡፡
ትልልቅ ስፒከሮች ደጃፋቸው ላይ አስቀምጠው ወይም ሰቅለው ድምፁን ከልክ በላይ ለቀው የሙዚቃ አልበሞችን ያከራዩና ይሸጡ የነበሩ መደብሮች፣ አሁን ታሪክ እየሆኑ ስለመምጣታቸው ያስገነዘበኝን አጋጣሚም ተፈጥሯል፡፡ በቀደመው ጊዜ ብዙዎቻችን ካሴት ወጣ ወይም የእከሌ ሲዲ ተለቀቀ ሲባል፣ ከእነዚያ የሙዚቃ መደብሮች ስፒከሮች በጨረፍታ ሰምተን ጆሯችን ከወደደው ጎራ ብለን እንገዛ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በወሬ በወሬ እከሌ የሚባለው ድምፃዊ አዲስ አልበም ለቀቀ ከተባልንም፣ ሲዲውን የምናገኝበት ቦታ ይታወቃልና በቀላሉ ወደ ሙዚቃ መደብሮቹ ሄደን መግዛት ይቻል ነበር፡፡ ዛሬ ነገሮች ተለዋውጠዋል፡፡ የሙዚቃ አልበሞች ቋሚ የሽያጭ አድራሻ የሌላቸው ሆነው በየመንገዱ የሚቸበቸቡ ተራ ነገሮች ሆነዋል፡፡ ከመደብር ወጥተው ጎዳና ወድቀዋል ማለት ይቻላል፡፡ ከሰሞኑ ትዝብቴ የተረዳሁትም ይኼ ነው፡፡ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋሉ የተባሉ የሙዚቃ ሥራዎችን ለመግዛት ቢያንስ አራት አምስት የአዲስ አበባ የተለዩ መንደሮችን አስሻለሁ፡፡ መደብሮቹ የሉም፡፡ በአጋጣሚ ግን ሲዲዎችን ይዘው ከሚዞሩ አግኝቼ ገዝቻለሁ፡፡ ይህ የሚሳየው የኢንዱስትሪው የግብይት ሥርዓት ቅጥ ያጣ እየሆነ ስለመምጣቱ ነው፡፡
አሁንም የሰሞኑን ገጠመኜን እንደ ምሳሌ ልጥቀስ፣ የምገዛበት መደብር ሳጣ ምናልባት ብዬ በመንገዴ ላይ ወዳገኘዋቸው ታዋቂ የሚባሉና ምንም ዓይነት ዕቃ የማይታጣባቸው ሱፐር ማርኬቶችም ውስጥ ገብቼ ጠይቄያለሁ፡፡ የተሰጠኝ ምላሽ ግን ኧረ እንዲህ ዓይነት ዕቃ እዚህ አይሸጥም የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ባዶ ሲዲዎቸ የሚሸጡ ሱፐር ማርኬቶች አጋጥሞኛል፡፡
ይህ ኢንዱስትሪ ከመዝናኛና ባህልን ከማስተዋወቅ ባሻገር እጅግ ሰፊ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በዘረፉ የሚንቀሳቀሰውም ገንዘብ ቢሆን እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ተያይዥ ቢዝነሶችምንም ይዞ የሚጓዝ ነው፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራም ቢሆን ቀላል የማይባል ሚና አለው፡፡ ዘርፉ የሚያመነጨው ገንዘብ በሕግና በአግባብ ከተሠራበት ለአገር የግብር ምንጭ ነው፡፡ ነገር ግን ኢንዱስትሪው እንደ ትልቅ ኢንዱስትሪ ታይቶ በዕድገት እንዳይጓዝ በችግር ተተብትቧል፡፡ ይህን ችግር መፍታት ካልተቻለ ኢንዱስትሪው አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም፡፡
በእኔ እምነት ስለቅጂ መብት ብዙ የመነገሩን ያህል ኢንዱስትሪው ቋሚ የግብይት ቦታ እንደሌለው ሲገለጽ አልተሰማም፡፡ ከቅጂ መብት ችግር ጋር ተጋፍጠው ለሕዝብ የሚቀርቡ ሥራዎች እንዴት እየተሰራጩ እንደሆነ እንኳን ሲገለጽ አይሰማም፡፡ በየመንደሩ በቀላሉ የምናገኛቸውና የሙዚቃና የፊልም ሥራዎችን የሚቸረቸሩ መደብሮች ሲጠፉ፣ የእነዚህ መዘጋት ምን ሊያስከትል እንደሚችል እንኳን አውቆ መፍትሔ ወደ ማፈላለግ አልተገባም፡፡
የእነዚህ መደብሮች መጥፋት ሊሸጥ የሚችለውን ያህል እንዳይሸጥ ማድረጉ ግልጽ ነው፡፡ የመደብሮቹ መጥፋት አሁን እንደ ችግር ለሚቆጠረው የሙዚቃ ሥራዎችን በሕገወጥ መንገድ ለማባዛትና ለማሠራጨት ወንጀል በር ሊከፍት መቻሉን መዘንጋት የለብንም፡፡ ኦርጅናል ሲዲ በመግዛት ኢንዱስትሪውን ለማበረታታት፣ ሕጉም እንዲጠበቅ የሚል እምነት ያለውም ቢሆኑ ገበያ ላይ የሚፈለገውን ካላገኙ ሊወሰዱ የሚችሉት ዕርምጃ እንደሌላው ሙዚቃውን ወይም ፊልሙን በፍላሽ መቀባበል ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ስለዚህ ቢያንስ የሙዚቃ ሥራዎች ግብይት ምን መምሰል እንደሚገባቸው አሁንም ብዙ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሙዚቃ ሥራዎችን አሳትመው የሚያከፋፍሉ ድርጅቶችም ቢሆኑ፣ ኅብረተሰቡ ዘንድ እንዴት ማድረስ እንዳለባቸው መዘየድ ይኖርባቸዋል፡፡ በጎዳና ላይ አዟሪዎች ብቻ መጠቀም የትም እንደማያደርሳቸው ማመን አለባቸው፡፡ ጊዜው ዘምኗልና ሥራዎቹ በሲዲ ብቻ ተቀርጸው መሠራጨት የሌለባቸው በመሆኑ፣ ተጠቃሚዎች በኢንተርኔት እንዲገዙ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ማላመድም ግድ ከሆነም ይህንኑ በቀላሉ ለማስፋፋት ራሳቸውን ከቴክኖሎጂው ጋር ማራመድ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ እስኪላመድ ግን በሲዲ ታትመው የሚቀርቡ ሥራዎች ቋሚ አድራሻ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡
ለምሳሌ ዛሬ በአዲስ አበባ በአራቱም አቅጣጫ ዘመናዊ የሚባሉ ሱፐር ማርኬትቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሱፐር ማርኬቶች የማይዙት ነገር የለም፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ ምርት አንድ ሼልፍ ቢይዙ ተጠቃሚዎች በቀላሉ ሊገዙ የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ እነሱም ይህንን እንደ አንድ የገበያ ግብዓት መመልከት አለባቸው፡፡ ሙዚቃ የሚሸጡ መደብሮች እየከሰሙ ከመጡ የጥበብ ሥራዎች ከአንዱ የንግድ ዘርፍ ጋር ተጣምረው እንዲሠሩ ማድረግም ሌላው አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የሞባይል መሸጫ መደብሮች፣ ስቴሽነሪዎች ሌላም ሌላም ሊሆን ይችላል፡፡
በጥቅሉ ሲታይ ለጥበብ ሥራዎች ግብይት መዘበራረቅ አንዱ ምክንያት የራሳቸው የሆነ ቦታ ማጣት በመሆኑ፣ የኢንተርኔት ግብይቱ እስኪጎለብት ድረስ እንዲህ ያሉ አማራጨች መታየት ይኖርባቸዋል፡፡
በሲዲ ታትመው ስለሚወጡ ሙዚቃዎችና ፊልሞች ከተነሳ ሌላው ቁልጭ ብሎ እየታየ ያለው ጉዳይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሙዚቃ ማጫወቻችን ምን ዓይነት ናቸው የሚለው ነው፡፡
ይህንን ለማወቅ እያንዳንዳችን በመኖሪያ ቤታችን ያሉ የሙዚቃ ማጫዎቻዎችን መመልከት ብቻ ይበቃል፡፡ የሙዚቃ ማጫዎቻዎችን የሚሸጡ መደብሮች ውስጥም በአብዘኛው የምናገኘው ሲዲ የሚቀበሉ አይደሉም፡፡
እነዚህ ማጫዎቻዎች ፍላሽ ብቻ የሚቀበሉ ከሆነ በሲዲ የሚቀርቡልንን ሙዚቃዎች እንዴት ልናዳምጥ ነው? ስለዚህ ኢንዱስትሪው እንዲህም ባለው ፈተና ውስጥ በመሆኑ፣ ለመፍትሔውም እነዚህን ጉዳዮች ጭምር ከግምት በማስገባት መሥራት አለበት፡፡ ሥርዓት ያለው ግብይት እንዲፈጠር ሁሉም መድከም አለበት፡፡