Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ምክር ቤቱ ለሚያዘጋጃቸው ንግድ ትርዒቶች በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአገሪቱ ትልቁ የሚባለውን የአዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚያካሂዳቸውን አራት የንግድ ትርዒቶች ከቀደመው ጊዜ በበለጠ ለማሰናዳት መዘጋጀቱን ገለጸ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ይኼን ያስታወቀው ባለፈው ሐሙስ የሦስቱን የንግድ ትርዒቶች መርሐ ግብር ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ ነው፡፡

አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት የግብርናና ምግብ ንግድ ትርዒትና ማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ የንግድ ትርዒት የሚል መጠሪያ ያላቸው የንግድ ትርዒቶችን ለማካሄድ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ተናግረዋል፡፡

በሦስቱም የንግድ ትርዒቶች የተሻለ ተሳታፊ እንዲኖር ጥረት እየተደረገ መሆኑን፣ በተለይ በአዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ የሚሳተፉ አገሮችን ቁጥር 25 ለማድረስ መታቀዱንም የንግድ ትርዒቶችን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በሚያዘጋጃቸው የንግድ ትርዒቶች ላይ የአፍሪካ አገሮች ተሳታፊዎች እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ለምን ሆነ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ጌታቸው፣ ይኼንን ክፍተት ለመሙላት ከአፍሪካ አገሮች የሚመጡ ኩባንያዎች ቁጥር እንዲጨምር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን አፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነታቸው እንብዛም በመሆኑ፣ እንዲሁም በአመዛኙ የንግድ ግንኙነታቸው ከአፍሪካ ውጪ ካሉ አገሮች ጋር በመሆኑ በርካታ የአፍሪካ ኩባንያዎች በንግድ ትርዒቶች ላይ መሳተፍ አለመቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ባለፈው ሐሙስ የንግድ ትርዒቶቹን በተመለከተ በተሰናዳው ፕሮግራም ላይ ከተገኙ አፍሪካውያን ዲፕሎማቶች፣ የአፍሪካውን ተሳትፎ ማነስ ሊታሰብበት የሚገባ ነው የሚል አስተያየት እስከመሰንዘር ደርሷል፡፡ አቶ ጌታቸውም የአፍሪካውያን ቁጥር በተፈለገው ደረጃ ባይሆንም፣ ዘንድሮ ይኼንን ለማሳደግ በተለያዩ መንገዶች ጥሪዎችን በማስተላለፍ ይሠራል ብለዋል፡፡

በአዲስ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከ200 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበትና ትልቁ የንግድ ትርዒት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ይህ የንግድ ትርዒት ዘንድሮ ለ22ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የግብርናና ምግብ የንግድ ትርዒቱ ደግሞ ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ የማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ የንግድ ትርዒቱ ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመቱን ይይዛል፡፡ የቱሪዝሙ የንግድ ትርዒት ደግሞ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡

ዘንድሮ የአዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከየካቲት 15 እስከ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የሚደረግ ሲሆን፣ የግብርናው የንግድ ትርዒት ደግሞ ከግንቦት 2 እስከ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የሚካሄድ ነው፡፡ የቱሪዝም ትራቭል የንግድ ትርዒቱም ከግብርናው የንግድ ትርዒት ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡

ሁለተኛው የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ የንግድ ትርዒት ደግሞ ከሰኔ 14  እስከ 18 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይደረጋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች