Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ140 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ሥራ አቆሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአራት ክልሎች 140 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸው ከዓመታት በፊት እንዲገነቡ የተደረጉ የማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ሥራ እንዳቆሙ ማወቅ ተቻለ፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት በዋናነት በቀድሞ ግብርና ሚኒስቴርና ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የተገነቡት ፋብሪካዎች፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች ይገኛሉ፡፡

ፋብሪካዎቹ ከመገንባታቸው በፊት በሁለቱ ተቋማት በ162 ወረዳዎች ላይ  የአፈር ምርታማነት ጥናት የተደረገ ሲሆን፣ በጥናቱ መሠረት ለአፈሩ ምርታማነት አስፈላጊ የሆኑ እንደ ሰልፈር፣ ፖታሽየም፣ ቦሮንና ዚንክ ያሉ ንጥረ ነገሮች እጥረት እንዳለበት ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም እንደ ኤንፒኤስቢ፣ ኤንፒኤስ ዚንክቦሮን፣ ኤንፒኤስ ፖታሽየም ያሉ የተቀነባበሩ ንጥረ ነገሮች ያሉት ማዳበሪያዎች አፈሩ እንደሚያስፈልገው ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በጥናቱም መሠረት የተጠቀሱትን ማዕድናትን በማዳበሪያ መልክ ነጣጥሎ ከውጭ በማምጣት፣ አገር ውስጥ ማቀነባበሩ አዋጭ መሆኑ ታምኖበት ፋብሪካዎቹ እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡

በዚህ መሠረት በወቅቱ ወደ 12 የሚሆኑ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ለመሥራት ታቅዶ አራት የሚሆኑት ሊሠሩ ችለዋል፡፡ ለእያንዳንዳቸውም 1.2 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡

ግንባታቸው ሲደረግና ሥራ ከጀመሩ በኋላ ዩኤስኤአይዲን ጨምሮ የዓለም ባንክ እገዛ አድርገዋል፡፡ በዋናነት በዩኤስኤአይዲ ሥር ፊድ ዘ ፊዩቸር በተባለው ፕሮግራም በኩል እገዛ ተደርጎለታል፡፡

በዚህም እገዛ መሠረት አራቱ ፋብሪካዎች በጊቤ ደዴሳ (ኦሮሚያ)፣ መርከብ (አማራ)፣ እንደርታ (ትግራይ) እንዲሁም መለቅ (ደቡብ) የገበሬ ኮኦፕሬቲቭ ዩኒየን ሥራ ሊገነቡ ችለዋል፡፡

ለዓመታትም ፋብሪካዎቹ የማቀነባበር ሥራውን እየሠሩ የተጠቀሱትን ማዳበሪያዎች ለገበሬው ሲያሠራጩ ነበር፡፡ ነገር ግን ከወራት በፊት ከዚህ ቀደም  የሚቀነባበሩት የተለያዩ ማዕድናት አቅርቦት በመቆማቸው ምክንያት ሥራቸውን ካቆሙ ሰንብተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ማዳበሪያዎችን ገዝቶ እያቀረበ የሚገኘው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ አሁን ላይ አገር ውስጥ የሚቀነባበሩትን ማዳበሪያዎች እየገዛ እንዳልሆነና ከዚህም በኋላ የመግዛት ዕቅድ እንደሌለው ማወቅ ተችሏል፡፡

አሁን ላይ ከግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በመጣ ትዕዛዝ፣ ከውጭ አገር የተቀነባበሩ ማዳበሪያዎችን እየገዛን ነው ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኮርፖሬሽኑ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ኮርፖሬሽኑ ከሳምንት በፊት 1.3 ሚሊዮን ቶን የሚሆኑ ማዳበሪያዎችን ከውጭ ለመግዛት ዓለም አቀፍ ጨረታ መክፈቱ ይታወሳል፡፡

ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመጣው ውሳኔ መሠረት ነው ከውጭ የተቀነባበሩት ማዳበሪያዎች እየተገዙ ያሉት ኃላፊው፣ ይህ ማለት ፋብሪካዎቹ ሥራ እንዲያቆሙ ወይም እንዲዘጉ መፍረድ ነው ሲሉ ሌላ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳን የተቀነባበረውን ማዳበሪያ በቀጥታ መግዛት አገር ውስጥ ከሚቀነባበረው የዋጋ ቅናሽ ቢኖረውም፣ አገር ውስጥ የሚቀነባበረው ለገበሬው የሚሆነውንና ለአፈሩም ተስማሚውን ማዳበሪያ ለማቅረብ ያስችላል ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያብራራሉ፡፡

‹‹አሁን ሥራ ካቆምን ከአራት ወራት በላይ ሆኗል፤›› ሲሉ የጊቤ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋሽ ቤቲ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እኚሁ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊ ግብርና ሚኒስቴር ምናልባት ከማዳበሪያ አቅራቢዎች በመጣ ጫና ከውጭ ተቀነባብረው የመጡ ማዳበሪያዎችን ብቻ ለመግዛት ተገዶ ሊሆን ይችላል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ይህ ውሳኔ በተቃራኒው አራቱን የማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ዕጣ ፈንታ ውሳኔ ሳይሰጥበት የመጣ ነው፡፡

በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብንና የፋብሪካዎቹ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን ያሳወቀን የለም ሲሉ የእንደርታ ገበሬዎች ኅብረት ኃላፊ አቶ ጐይቶም ከሰተ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም የኅብረት ሥራ ማኅበሩ ሥር ያለው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባጋጠመው ችግር ማሽኖቹ ችግር ደርሶባቸው ሥራቸው ተስተጓጉሎ ነበር፡፡ በወቅቱ እንደ ምክንያት ቀርቦ የነበረው በ2007 ዓ.ም. እና በ2008 ዓ.ም. ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ የተደረገ የቦሮን ንጥረ ነገር ማዳበሪያ ከሚጠበቀው የፊዚካል ደረጃ በታች ወጪ ሆኖ ስለተገኘ፣ ማቀነባበሪያው ማሽኖቹ ውስጥ ሲገባ ማዳበሪያው ጉዳት ማድረሱ ነበር፡፡

ይህ የቦሮን ማዕድን ማዳበሪያ የግብርና ኤጀንሲውና የግብርና ሚኒስቴር በሰጡት ደረጃ መሠረት የተገዛ ቢሆንም፣ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ከሚፈለገው ደረጃ በታች ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በዚህ ምክንያት በግዢው ምክንያት አገሪቱ ላይ ወደ 500 ሚሊዮን ብር አካባቢ ኪሳራ መድረሱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በዚህ ምክንያት በግዥው የተሳተፉ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ከቦታቸው የተነሱ ሲሆን፣ ጉዳዩም በሕግ እየታየ ይገኛል፡፡

እንደርታ ብቻ የ30 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶበታል፡፡ የቦሮኑ ንጥረ ነገር በዋናነት ያራ በተባለው የዓለም አቀፍ የማዳበሪያ አቅራቢ ኩባንያ ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡

አሁን ላይ ሥራቸውን ካቆሙት አራቱ የማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ውጪ ኦሮሚያ ክልል የሚገኘው በቱሉ ቦሎ ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥር የሚገኝ ማቀነባበሪያ ብቻ በሥራ ላይ ሲሆን፣ እሱም ከሚጠበቅበት መጠን በታች ማዳበሪያ እያቀነባበረ ይገኛል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች