በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በመንግሥት የተፈቀዱ ከቀረጥ ነፃ መብቶች ማስፈጸሚያ መምርያ ኃላፊ ዓለም ፀሐይ ግርማይ (ዶ/ር) በነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው ሲመረመሩ ከቆዩ በኋላ፣ ጉዳዩን እያየው የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት የ50,000 ብር የዋስትና መብት ቢፈቅድላቸውም ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ይግባኝ ያስቀርባል ተባለ፡፡
ተጠርጣሪዋ በባለሥልጣኑ በኃላፊነት በሚሠሩበት ወቅት ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ንኮማድ፣ ራማና ሲአርቢሲ ለሚባሉ ድርጅቶች የቀረጥና የታክስ ነፃ መብት በመስጠት በመንግሥት ላይ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ገልጾ ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ ለመርማሪ ቡድኑ ተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ ከፈቀደ በኋላ ክስ መሥርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ግን ክስ እንዲመሠረት ለዓቃቤ ሕግ መዝገቡን ማስተላለፉን ቢገልጽም ክስ አልተመሠረተም፡፡
ዓቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡ እንደደረሰው ለፍርድ ቤቱ ያረጋገጠ ቢሆንም፣ በተጠርጣሪዋና በሌሎች ስድስት ግብረ አበሮች ላይ ተጨማሪ ምርመራ በማስፈለጉ እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡፡
የተጠርጣሪዋ ጠበቃ ባሰሙት ተቃውሞ፣ በኢትዮጵያም ሕጎች ሆነ በሌሎች አገሮች ሕጎች መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ ክስ ለሚመሠርተው ዓቃቤ ሕግ ካስረከበ በኋላ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሚፈቀድበት የሕግ አግባብ እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ መርማሪ ፖሊስ ባስረከበው የምርመራ መዝገብ መሠረት ክስ መመሥረት ካልቻለ፣ ደንበኛቸው ነፃ የመሆን መብታቸው ተከብሮላቸው ወይም ሊያስከስሳቸው የሚችል ተግባር እንዳልፈጸሙ ተቆጥሮ በነፃ እንዲሰናበቱ፣ ወይም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የተጠርጣሪዋን ጠበቃ አቤቱታ በመቀበል፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ተጨማሪ የምርመራ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ሕጉ የሚፈቅደውን ክስ የመመሥረቻ 15 ቀናት ሙሉ በሙሉ ተጠቅሞ ክስ እንዲመሠርት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡
ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው ጊዜም ክስ ሊመሠርት ባለመቻሉ፣ ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ የምርመራ መዝገቡን ሲቀጥር ከርሞ መጨረሻ ላይ ተጠርጣሪዋ በ50,000 ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡
ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ የሚል ከሆነ ለመጠባበቅ ተጠርጣሪዋ ለሁለት ቀናት በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ፣ ይግባኝ የማይልባቸው ከሆነ ዋስትናውን አስይዘው ከእስር እንዲፈቱም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡
ዓቃቤ ሕግም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርቦ ተቀባይነት ማግኘቱንና ቀጠሮ ማስያዙን ለጊዜ ቀጠሮ አስቻይ ፍርድ ቤቱ አሳውቋል፡፡