ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል በተሠሩ ሥራዎች፣ በተገኙ ውጤቶች፣ ተግዳሮቶችና በዘርፉ ባለው መቀዛቀዝ ላይ ያተኮረና አጠቃላይ ሥራውን የሚገመግም አገር አቀፍ ጥናት መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚጀመር የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በአገሪቱ ለመጀመርያ ጊዜ በኤችአይቪ ዙሪያ ማኅበረሰቡን ማዕከል የሚያደርገው ጥናት የሚካሄደው በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት ከአሜሪካ መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ በአሜሪካ መንግሥት የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) እና በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አይካፕ የቴክኒክ ድጋፍ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አይካፕ የኢትዮጵያ ፖፑሌሽን ቤዝድ ኤችአይቪ ኢምፓክት አሴስመንት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ኃይለኛው እሽቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አገር አቀፍ ጥናቱ የኤችአይቪ መከላከል፣ እንክብካቤና ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትንና በአገር አቀፍ ደረጃ ያስገኘውን ውጤት ይለካል፡፡
ከተሞችን የሚያማክለው የቤት ለቤት ጥናት ዋና ዓላማው የኤችአይቪ ሥርጭት በአዋቂዎች እንዲሁም በልጆችና ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ በሚገኙ ወገኖች የቫይረሱን መጠን ለመገመት ነው፡፡ የጥናቱም ውጤት በኢትዮጵያ ውስጥ በአገር አቀፍና በእያንዳንዱ ክልል የኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራም ያለበትን ደረጃና ወደፊትም እንዴት መሻሻል እንዳበት ለማወቅ ይረዳል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የኤድስ ልዩ ቢሮ/ዩኤንኤድስ እ.ኤ.አ. በ2020 ዘጠና በመቶ የኅብረተሰቡ ክፍል የኤችአይቪ ምርመራ እንዲያደርግ፣ ቫይረሱ በደማቸው ከተገኘባቸው ውስጥ ዘጠና በመቶ ሕክምና እንዲያገኙ፣ ሕክምናውን ከሚከታተሉት ውስጥ ዘጠና በመቶ በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠን በቁጥጥር ሥር እንዲውል ለማድረግ ያለመውን ዕቅድ ኢትዮጵያ የተቀበለች ሲሆን፣ ለዚህ ዕቅድ መሳካትም ጥናቱ አዎንታዊ ትርጉም ይኖረዋል፡፡
ጥናቱ ሥልጠና በተሰጣቸው የሕክምና ባለሙያዎች የሚከናወን ሲሆን፣ መረጃውም በዕጣ በተመረጡና 12 ሺሕ በሚሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ ከሚገኙ 25 ሺሕ ያህል አዋቂዎችና ሕፃናት የሚሰበሰብ ይሆናል፡፡ ጥናቱን ለማከናወን የደም ናሙና የሚወሰድ ሲሆን፣ ከኤችአይቪ በተጨማሪ በተጓዳኝነት የጉበትና የአባላዘር በሽታ ምርመራዎችን የሚያካትት ይሆናል፡፡
ውጤቱም በተመሳሳይ ዕለት በጥናቱ ለተሳተፉ ግለሰቦች ይሰጣል፣ የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው በአካባቢያቸው ካለ የጤና ተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር ለጥናቱ የሚያስፈልጉ ሠራተኞን በመቅጠርና የአስተዳደርና ሎጂስቲክስ ክፍሎችን በማስተባበር እንደሚሠራ፣ ለጥናቱ የሚያስፈልጉ ልምድ ያላቸው ነርሶችና መረጃ ሰብሳቢዎችም ከመላ አገሪቱ እንደተመለመሉና ባለፈው አንድ ወር ተከታታይ ሥልጠና ሲሰጣቸው እንደቆየ ፕሮጀክት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤችአይቪን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለፉት 15 ዓመታት የተካሄዱት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በመንግሥት የተካሄዱት እነዚሁ እንቅስቃሴዎች ካስገኟቸው ውጤቶች መካከል አዲስ ኤችአይቪ/ኤድስ የሚያዙ ግለሰቦች ቁጥር 65 በመቶ እንዲሁም የሞት መጠኑ 45 በመቶ መቀነሳቸው እንደሚገኙበት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በ1998 ዓ.ም. የኤችአይቪ/ኤድስ ሕክምና ይሰጡ የነበሩት የጤና ተቋማት 353 ብቻ እንደነበሩ፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ቁጥራቸው ወደ 1,043 ከፍ ማለቱና በ2003 ዓ.ም. በመላው አገሪቱ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሠረት የኤችአይቪ ሥርጭት 1.5 በመቶ መሆኑ ከተመዘገቡት ውጤቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡