Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልሴቶች በጊቻዌ

ሴቶች በጊቻዌ

ቀን:

በኢትዮጵያ ሙዚቃ ስማቸው ከገነነ ድምፃውያን መካከል መሐሙድ አህመድ በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ በአገር ውስጥና በውጪም ዕውቅናና ተወዳጅነት ካተረፈባው ዘፈኖቹ መካከል የጉራግኛ ሥራዎቹ ይገኙበታል፡፡ በጉራግኛ ጭፈራ ታጅቦ የሚያዜመው ‹‹ጊቻዌ›› ከነዚህ መካከል ሲሆን፣ በጉራጌ ማኅበረሰብ የሚዘወተር ሥርዓትን ያንፀባርቃል፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ ያቀነቀነለት ሥርዓት ለረዥም ዓመታት በጉራጌ ሴቶች የተከናወነ ነው፡፡

‹‹ኑና ግጠሙኝ›› የሚል ትርጓሜ ያለው ጊቻዌ፣ የጉራጌ ሴቶች በሙያ፣ በውበትና በሌላም እርስ በርስ የሚፎካከሩበት ነው፡፡ ሥርዓቱ የሚከናወነው ለተለያዩ በዓሎች ሲሆን፣ የማርያም ክብረ በዓል አንዱ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የሚታወቅበት ክትፎ በቆጮ፣ ቡና በቅቤና ሌሎችም ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ይዘጋጃሉ፡፡ ከጎረቤታሞች በአንድ ሰው ቤት ተሰባስበው ተበልቶና ተጠጥቶ ሥርዓቱ ይካሄዳል፡፡ ፉክክር እንደመሆኑ ሴቶች በሁለት ቡድን ተከፍለው አንዳቸው ከሌላቸው እንደሚበልጡ ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡

ይህ አገር በቀልና ዕድሜ ጠገብ ባህላዊ ሥርዓት ትኩረታቸውን ከሳቧቸው ተመራማሪዎች መካከል የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት መምህርና የዩኒቨርሲቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አስተዋይ መለሰ አንዱ ናቸው፡፡ ባህሉ በአካባቢው ስለሚሰጠው ቦታና በማኅበራዊ መስተጋብሩ ያለውን ሚና የዳሰሱበትን የጥናት ጽሑፍ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ያቀረቡት የቴአትር ትምህርት ክፍል ባዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ ነበር፡፡

- Advertisement -

የጉራጌ እንስቶች (በዋነኛነት እናቶች) አንዳቸው ከሌላቸው በተሻለ ያከናወኑትን በማንሳት እርስ በርስ የሚፎካከሩት በተለያየ ወቅት መሆኑን አጥኚው ያስረዳሉ፡፡ እንደ አስተርዮ ማርያም ባሉ ክብረ በዓሎች ሥርዓቱ የሚከናወነው ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ ለሌሎች በዓሎች በአንድ የማኅበረሰቧ አባል ቤት ይከናወንና ተሳታፊዎች ሲደክማቸው እዚያው ቤት ያድራሉ፡፡ ሥርዓቱ በሠርግ ወቅት ሲካሄድ ፉክክሩ በሙሽራዋና ሙሽራው ቤተሰቦች መካከል ይሆናል፡፡ሴቶች በጊቻዌ

አስተዋይ እንደሚናገሩት፣ በባህሉ መሠረት ሥርዓቱ ሲከናወን የድራማ ዓይነት ቅርፅ ይይዛል፡፡ ከእናቶች ጥቂቱ አንበሳን ሲያስመስሉ፣ የተቀሩት ጠባቂና ከለላ የሚደረግላቸው ልጆችን ወክለው ይጫወታሉ፡፡ አንበሳው ልጆችን ለመብላት ሲያደፍጥ ጠባቂዎቹ ይከላከላሉ፡፡

በጉራጌ ማኅበረሰብ የእናቶች ቀን የሚከበርበት ቀን ያለ ሲሆን፣ በዕለቱ እናቶችን ለማወደስና ለዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦዋቸው ምሥጋና ለማቅረብ ሥርዓቱ ይከናወናል፡፡ የአካባቢው ተወላጆች ተሰባስበው ከተበላና ከተጠጣ በኋላ፣ በቀዬው ውብ ድምፅ ያላት ሴት ተመርጣ ለተከበሩ እናቶች ታዜማለች፡፡ እናቶች ከቤተሰባቸው ባሻገር ለኅብረተሰቡ ያበረከቱት እየተጠቀሰም ይሞገሳሉ፡፡

ማኅበረሰቡ ‹‹አንትሮሽት›› እያለ በየዓመቱ የሚያከብረው የእናቶች ቀን፣ ከ300 ዓመታት በላይ እንደተካሄደ ይነገርለታል፡፡ በዕለቱ እናቶች ታጥበው፣ ያልተነጠረ ቅቤ ተቀብተው፣ በልዩ የበዓል ልብስና ጌጣ ጌጥ ይዋባሉ፡፡ የእናቲቷ የመጀመርያ ልጅ ወንድ ከሆነ ወይም ሴት ከሆነች የተለያየ ሥርዓት ይከተላሉ፡፡ ለምሳሌ ሴት የበኩር ልጆች እናታቸውን ቅቤ ይቀባሉ፡፡ ልጅ የሌላቸው ሴቶች በዓሉን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያሳልፋሉ፡፡ ጊቻዌም አንዱ የበዓሉ መገለጫ ነው፡፡

በአካባቢው ተወዳጅ ከሆኑት ምግቦች አንዱ ቆጮ በሚዘጋጅበት ወቅትም ጊቻዌ ይከናወናል፡፡ ለምሳሌ መስቀልን በመሰለ በማኅበረሰቡ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው ዐውደ ዓመት ወቅት ቆጮ ይዘጋጃል፡፡ ከእንሰት ተክል የሚዘጋጀው ቆጮ በሚሰናዳበት ወቅትም ሥራውን ቀላልና አዝናኝ ለማድረግ ሥርዓቱን ይጠቀሙበታል፡፡ አጥኚው እንደሚሉት፣ ከጊቻዌ በተጨማሪ ኩፍዌና ነቅዌ የተባሉት አገር በቀል ባህላዊ ሥርዓቶችም የሰባት ቤት ጉራጌ ሴቶች ማንነት መሠረትና መገለጫም ናቸው፡፡

ሴቶች ከግለሰባዊ ማንነታቸው በተጨማሪ በማኅበረሰቡ ውስጥ የጋራ ማንነታቸውን የሚያሳዩባቸው ሥርቶች ናቸው፡፡ ባህላዊ ሥርዓቶቹ በዓመት ውስጥ በተለያየ ወቅት ሴቶች በጋራ የሚያካሂዷቸው ሲሆኑ፣ በማኅበረሰቡ እንስቶች ማንነት ላይ አሻራቸውን እያኖሩ ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡

እንሰት የሚዘጋጅበት ወቅት ልዩ ጊዜ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከጭፈራው ጎን ለጎን የደረሰ እንሰት ቆርጦ አዲስ የመትከል ልማድም አለ፡፡ ሥራው የሚከናወነው በደቦ ስለሆነ የመንደሩ እናቶች ተጠራርተው ይሰባሰባሉ፡፡ በዘፈን ስለ እንሰት ተክል አቆራረጥ እንዲሁም ደቦ ተጠራርተው የመጡ ሰዎች እንዴት እንክብካቤ ሊረግላቸው እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ በባህላዊ ጨዋታው የተለመደው የእናቶች ፉክክርም አይቀርም፡፡ የእንሰት ተክልን የመንከባከብ ሥራ ከባድ እንደመሆኑ ፉክክሩ የማን እንሰት ተክል የተሻለ እንደሆነ እየገለጹ በማድነቅ የሌላውን የሚያጣጥል ነው፡፡

የነቅዌ ዝግጅት የመስቀል በዓል ካለፈ በኋላ የሚጀመር ሲሆን፣ ሴቶች ያሻቸውን የሚያደርጉበት ነው፡፡ ክንውኑ በቤት ውስጥና ከቤት ውጪም ይካሄዳል፡፡ የመስተንግዶውን ኃላፊነት የምትወስድ እናት ሌሎቹን ወደ ቤቷ ጋብዛ ሥርዓቱ ከተከናወነ በኋላ በገበያ አካባቢ ይቀጥላል፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚዘወተሩት ባህላዊ ክንውኖች እንደየሚካሄዱበት ወቅት የተለያየ ትርጓሜ አላቸው፡፡ ከባህላዊ አንድምታቸው ባሻገር ሃይማኖታዊ በዓሎችን አስታከው የሚመጡባቸው ጊዜያትም አሉ፡፡

ጊቻዌ ሴቶች ስሜታቸውን በነፃነት የሚገልጹበትም ሥርዓት ነው፡፡ ለምሳሌ የጉራጌ ወንዶች ለሥራ ከትውልድ ቀዬአቸው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ከሄዱ በኋላ የመጀመርያ ሚስቶቻቸውን ቸል ብለው በየሄዱበት ሌላ የሚያገቡበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ሚስቶቻቸውን የሚጨቁኑበት ጊዜ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ሴቶች በደላቸውንና የተሰማቸውን ሐዘን የሚገልጹት በባህላዊ ሥርዓቶቹ እንደሆነ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ ለመብታቸው የሚታገሉበትና እኩልነታቸውን የሚያስከብሩበት መንገድ መሆኑም ታክሏል፡፡

ከዛሬ 150 ዓመት በፊት ይህንኑ የሴቶች ጭቆና የተቃወመችው የቃቄ ወርድወትን ታሪክ አያይዞ ማንሳት ይቻላል፡፡ ምንጊዜም ያልተገደበ መብት እንዳላቸው የሚያምኑ ወንዶች ሴቶችን የሚጨቁኑበት ሥርዓት በማኅበረሰቡ ዘንድ ትክክል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ኢፍትሐዊነቱን በአደባባይ የተጋፈጠችው የቃቄ ወርድወት፣ በማኅበረሰቡ ጾታን መሠረት ያደረገ ልዩነት እንዳይኖርና ሰዎች በሰውነታቸው ብቻ እኩል መሆናቸውን በመናገር ኅብረተሰቡን ሞግታለች፡፡ የእኩልነት ጥያቄዎቿም ዛሬም በሚከናወኑ ባህላዊ ሥርዓቶች ውስጥ ይስተጋባሉ፡፡

ባህላዊ ሥርዓቶቹ በዓላትን ከማድመቅ ባሻገር፣ ሴቶች በነፃነት ሐሳባቸውን የሚገልጹባቸው መሆኑን የሚያስረዱት የጥናቱ አዘጋጅ፣ ‹‹ባህሉ ከማኅበረሰቡ ሴቶች ማንነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው፤›› ይላሉ፡፡ በሥርዓቶቹ ወቅት ጎልተው የሚወጡ እናቶች ‹‹አጃየት›› የተሰኘ የክብር ስም ይሰጣቸዋል፡፡ ፉክክሩን በተሻለ ደረጃ ያጠናቀቁ ድል መቀዳጀታቸው የሚገለጽበት መንገድም ነው፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚዘወተሩ ባህላዊ ምግቦች የሥርዓቶቹ ልዩ ገጽታ ናቸው፡፡ እናቶች ክትፎ፣ ጎመን፣ ዓይብና ቆጮ የሚመገቡበት ወቅትም ባህላዊ ቅደም ተከተል አለው፡፡ በመስቀል እናቶች ቤተሰባቸውን ይመግባሉ፡፡ በጭፈራው ወቅት ደግሞ እናቶቹ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይበላሉ፡፡ ‹‹ምሽቱን በሙላ ያወራሉ፣ ይጫወታሉ፣ ስለ ችግሮቻቸው እየተነጋገሩ መፍትሔ ይፈልጋሉ፤›› ሲሉ አስተዋይ ሥርዓቱን ይገልጹታል፡፡

የማኅበረሰቡ ባህላዊ ሥርዓቶች በዕድሜ ክልል ተወስነውም ይከናወናሉ፡፡ የክንውኖቹ ዋና መለያ የሴቶች ነፃነት ሲሆን፣ እኩልነቱ ከጭፈራው ባሻገር በመላው ሕይወታቸው መዝለቅ መቻልም አለበት፡፡

አጥኚው እንደሚሉት፣ ባህላዊ ሥርዓቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዙ መጥተዋል፡፡ በሠርግ ወይም በበዓላት ከመካሄድ በዘለለም እምብዛም አይታዩም፡፡ ዛሬ ዛሬ በተለይም በከተማ ቀመስ አካባቢዎች ባህላዊ ሥርዓቶችን ማግኘት ይከብዳል፡፡ አንዳንዶቹ ክንውኖች ከባህላዊ እምነት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ስለሚታመን የማይቀበሏቸው አሉ፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሚናቸው ከፍ ያለ ባህላዊ ሥርዓቶች እንዳይጠፉ በአካባቢው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጥረቶች መደረጋቸውን ይጠቅሳሉ፡፡  ሆኖም ባህሉን ጠብቆ ለማቆየት በሚያስችል መልኩ ጥናቶች አልተሠሩም፡፡ የሚመለከታቸው የባህልና ቱሪዝም አመራሮችም ኃላፊነታቸውን ሙሉ በሙሉ እየተወጡ አይደለም፡፡

 መሰል ግዙፍነት የሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ከጊዜ ብዛት እንዳይጠፉ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ስለ ሥርዓቶቹ በጽሑፍና በቪዲዮ የተዘጋጁ ሰነዶች ተዘጋጅተው ለቀጣዩ ትውልድና ለተቀረው ዓለምም መተላለፍ እንደሚገባቸው አስተዋይ ይጠቁማሉ፡፡ እንደነዚህ ያሉ ዕድሜ ጠገብ ማኅበረሰባዊ መገለጫዎች በሉላዊነት ሳቢያ እንዳይደመሰሱም ያሳስባሉ፡፡ ሥርዓቶቹ የጉራጌ ሴቶች በዓመት ውስጥ ለጥቂት ቀናት በእኩል ዓይን የሚታዩባቸው ብቻ ሳይሆን፣ ዘለቄታዊ እኩልነትና ፍትሕን የሚያሰፍኑ መሆን እንደሚገባቸውም ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...