Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም በሕግ ይፈቀድ እንዴ?

ኢትዮጵያ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም በሕግ ይፈቀድ እንዴ?

ቀን:

ክፍል ሁለት

በዳንኤል አረጋዊ ኃይሉ

በክፍል አንድ ጽሑፌ የአደንዛዥ ዕፅ ችግርን ዓለም አቀፋዊነት፣ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት ምንነትን፣ ዓይነታቸውንና የጎንዮሽ ጉዳቶቹን፣ አደንዛዥ ዕፅ በአሜሪካና በላቲን አሜሪካ አገሮች ላይ የጋረጠውን ፈተናና እነዚህ አገሮች ከችግሩ ስፋት፣ ከተጠቃሚው መብዛትና ከቁጥጥር ውጭ መሆን በመነሳት አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምና ማሠራጨትን ሕጋዊ ለማድረግ እየቀሰቀሱና ድጋፍ እያሰባሰቡ ያሉ ሰዎችን እንቅስቃሴ ማስተናገድ መጀመራቸውን ገልጫለሁኝ፡፡ በክፍል ሁለት ጽሑፌ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ ሽያጭና ተጠቃሚነት በአገራችን ምን ያህል እየተስፋፋ መሆኑን፣ አደንዛዥ ዕፅ በአገራችን የደቀነው ፈተናና ችግሮቹን ለማስወገድ ይረዳሉ ብዬ ያሰብኳቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚከተለው አቅርቤያቸዋለሁ፡፡

አደንዛዥ ዕፅ በአገራችን ላይ የደቀነው ፈተናና ዝምታችን

ከተለያዩ ጥናቶችና ከፌዴራልና ከክልሎች የወንጀል ፍትሕ አካላት የየዕለት ውሎ ቅኝት መገንዘብ እንደሚቻለው፣ በተለይ በአገራችን በሚገኙ ከተማዎች ያለው የአደንዛዥ ዕፅ ሥርጭትና ተጠቃሚነት እየተስፋፋ ነው፡፡

መስፍን ካሳዬና ባልደረቦቹ በአዲስ አበባና በቡታጅራ ከተማ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ በ1990 ዓ.ም. አንድ ጥናት አከናውነዋል፡፡ በዚህ ጥናት ከአዲስ አበባ 241 ተማሪዎች፣ ከቡታጅራ 187 ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹ መካከል 1.7 በመቶ የገጠር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና 2.7 በመቶ የከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ካናቢስ ተጠቅመው እንደሚያውቁ ገልጸዋል፡፡ በጥናቱ ከተሳተፉ ተማሪዎች መካከል 48.9 በመቶ የሚሆኑት የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎችና 31.1 በመቶ የሚሆኑት የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ካናቢስና ሲጋራ ተጠቅመው የሚያውቀ መሆኑ ገልጸዋል፡፡

ሞገስ ቸኮል ግንቦት 2002 ዓ.ም. ባከናወኑት ጥናት በ1995 ዓ.ም. ሞሪሸስ ውስጥ በተከናወነ ብሔራዊ የመድኃኒት ሕግጋት አስፈጻሚ ተቋማት ኃላፊዎች ጉባዔ ላይ ፀሐዩ (የአባታቸው ስም፣ የሥራ ድርሻ. . . ያልተገለጸ) የተባሉ ሰው ያቀረቡትን የኢትዮጵያ ፖሊስ የፀረ አደንዛዥ ዕፅ ግብረ ኃይልን እንቅስቃሴ ሪፖርት ጠቅሰዋል፡፡ በሪፖርቱ መሠረትም ኢትዮጵያ የፀረ አደንዛዥ ዕፅ ግብረ ኃይል በ1985 ዓ.ም. 720 ግራም የሔሮይን ዕፅ፣ አንድ ኪሎ ግራም ከ462.356 ግራም የካናቢስ ዕፅ፣ ሁለት የሔሮይን ዕፅ አዘዋዋሪዎችና 164 የካናቢስ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን ይዟል፡፡ በ1995 ዓ.ም. 27 ኪሎ ግራም  ከ293.40 ግራም የሔሮይን ዕፅ፣ 1,155 ኪሎ ግራም ከ302.047 ግራም የካናቢስ ዕፅ፣ 36 የሔሮይን ዕፅ አዘዋዋሪዎችና 640 የካናቢስ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን ይዟል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ከ1985 እስከ 1995 ዓ.ም. ካለው አሥር ዓመት ሲነፃፀር የሔሮይን ዝውውር ከ25 እጥፍ በላይ አድጓል፡፡ የካናቢስ ዝውውር ከ1,150 እጥፍ በላይ አድጓል፡፡ የሔሮይን ዕፅ አዘዋዋሪዎች ቁጥር ከሁለት ወደ 36 አድጓል፡፡ የካናቢስ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ቁጥር ከ164 ወደ 640 አድጓል፡፡

በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ በገዛኸኝ ተስፋዬና ባለልደረቦቹ ተሠርቶ ሚያዚያ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. የታተመ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በጥናቱ ተሳትፈው መልስ ከሰጡ 1,022 ተማሪዎች መካከል 17.4 በመቶ (175 ተማሪዎች) ሐሺሽና የመሳሰሉ አደንዛዥ ዕፆችን ቢያስ አንድ ጊዜ መጠቀማቸውን የገለጹ ሲሆን፣ 7.4 በመቶ (75 ተማሪዎች) ደግሞ ባለፉት 30 ቀናት ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ የተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጥናቱ ጊዜ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል 44.4 በመቶ (79 ተማሪዎች) አልፎ አልፎ አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀሙ መሆኑንና 55.6 በመቶው (15 ተማሪዎች) ዘወትር አደንዛዥ ዕፅ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 57.3 በመቶ (102 ተማሪዎች) ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም መጀመራቸውን 42.7 በመቶው (76 ተማሪዎች) ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2014 አንዷለም ደረሰና አሰፋ ስሜ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ባደረጉት ጥናት መሠረት፣ በጥናቱ ከተሳተፉ 725 ተማሪዎች መካከል 3.9 በመቶ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ላይ በጥላሁን በቀለና ባልደረቦቹ ተሠርቶ ሚያዚያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የታተመ ጥናት እንደሚያሳየው በጥናቱ ተሳትፈው መልስ ከሰጡ 150 ተማሪዎች መካከል 3.3 በመቶ (5 ተማሪዎች) ካናቢስ የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ፣ ሁለት በመቶ (ሦስት ተማሪዎች) ደግሞ ኮኬይን የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ እንደሚጠቀሙ ይገልጸል፡፡

በፖሊስ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ በሚቀርቡ ዘገባዎች መሠረት ከቅርብ ዓመታት በፊት ሻሸመኔ ውስጥ ሰፊ የአደንዛዥ ዕፅ ማሳ ተገኝቶ ተመንጥሯል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥም ባምቢስ አካባቢ ያለው ወንዝ ውስጥ በሸንበቆ ተከቦ የበቀለ ሰፊ የአደንዛዥ ዕፅ ተክል ተጨፍጭፎ አብቃዮቹም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ነበር፡፡ የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽኖች በተለያዩ ጊዜያት ባደረጓቸው ክትትሎችና ቁጥጥሮች ወደ ተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ሊሠራጩ የነበሩ፣ በተለይም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲገቡ የነበሩ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን አደንዛዥ ዕፆችን በቁጥጥር ሥር አውለዋል፡፡ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና በኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት በኩል የተለያዩ መጠንና ዓይነት ያላቸው አደንዛዥ ዕፆች በተለያየ ሥልት ከኢትዮጵያ ሊወጡና ሊገቡ ሲሉ በተደጋጋሚ ተይዘዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ሲጋራና ማስቲካ በመሸጥ ከሚተዳደሩ ወጣቶች መካከል በማስቲካ ንግድ ሥራቸው ሽፋን እጅግ በጣም ውድ ዋጋ ካለው ኮኬይን ከተባለው አደንዛዥ ዕፅ ጀምሮ፣ ካናቢስ የሚባለውን አደንዛዥ ዕፅ ሲሸጡ ተደርሶባቸው በእስራት የተቀጡ ወጣቶች አሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች በሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎችና በፌዴራል ፖሊስ አማካኝነት ተጣርተው በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ አማካይነት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ፣ አራዳ፣ ቃሊቲና ልደታ ምድቦች የሚቀርቡ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር የተያያዙ የወንጀል ክሶች ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በቦሌ ምድብ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የነበረውን ሁኔታ ብንመለከት፣ በቀን አንድ ወይም ሁለት ተከሳሽ/ሾች አደንዛዥ ዕፅ ተጠቅመዋል፣ ይዘው ተገኝተዋል፣ ወይም ሸጠዋል የሚል የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው በወቅቱ በምድቡ ከነበሩ ፈጣን ችሎቶች ቢያንስ ለአንዱ ችሎት ይቀርቡ ነበር፡፡ በሁሉም ፈጣን ችሎቶች የሚቀርቡትን ተከሳሾች ቁጥር ብንመለከትም በተለያዩ መዛግብት ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸው ለችሎቶቹ የሚቀርቡ ተከሳሾች ቁጥር፣ በአንድ ቀን እስከ ስድስት የሚደርስባቸው ቀናት ጥቂት አልነበሩም፡፡ በቦሌ ምድብም ሆነ በሌሎች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎቶች በክርከር ላይ ያሉትም ሆነ ውሳኔ የተሰጠባቸው ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ክሶች ቁጥር ቢደመር እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ በአሥሩም ክፍላ ከተሞች ባሉ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ከእሑድ በስተቀር በየዕለቱ ከሚቀርቡ የጊዜ ቀጠሮ የምርመራ መዝገቦች መካከል ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ወንጀል ተጠርጥሮ የሚቀርብ ተጠርጣሪ አለማግኘት ዘበት ነው፡፡ ሌሎች የፖሊስ ምርመራና የፍርድ ቤት የወንጀል ክስ ጉዳዮችን ጠቃቅሼ የችግሩን ጥልቀት ለማሳየት ልሞክር፡፡

በታኅሳስ ወር 2009 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ዕድሜው ከ16 ዓመት ገና ፈቅ ያለ ታዳጊ አደንዛዥ ዕፅ ሲጠቀም ተይዟል ተብሎ የወንጀል ክስ ቀርቦበት በቦሌ ምድብ ችሎት ይቀርባል፡፡ ችሎቱ ዕድሜውንና ተማሪነቱን ከግምት አስገብቶ ክርክሩን በዋስ ሆኖ እንዲከታተል ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ የታዳጊው እንደ ንፁህ የመገመት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዋስ ከተፈታ አንድ ሳምንት እንኳን ሳይሞላው በድጋሚ አደንዛዥ ዕፅ ሲጠቀም ተገኝቷል የሚል ሌላ ክስ ቀርቦበት እዚያው ችሎት በመቅረቡ፣ ሁለቱንም ክሶች በእስር ላይ ሆኖ እንዲከታተል ትዕዛዝ ተሰጥቶበት ጉዳዩን በመከታተል ላይ ነበር፡፡

አደንዛዥ ዕፅ ሲጠቀም ተይዟል የሚል ክስ ቀርቦበት የነበረ ወጣት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርቦ የከሳሽ ምስክሮች በሚሰሙበት ወቅት፣ የተከሳሹ ጠበቃ ተከሳሹ የሚያክለው ሌላ ጥያቄ ካለ ብሎ “ምስክሮቹ በመሰከሩብህ ነገር ላይ የማነሳልህ ሌላ መስቀለኛ ጥያቄ አለ ወይ?” ይለዋል፡፡ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ያላወቀው ተከሳሽ ወደ ጠበቃው ጠጋ ብሎ፣ “እባክሽ እነሱን ተያቸው፡፡ ይልቅ አንድ፣ 20 ብር ካለሽ ግጪኝ፤” ብሎታል፡፡

አደንዘዥ ዕፅ ሲጠቀም እየተያዘ በተደጋጋሚ ተቀጥቶ የተፈታ አንድ ወጣት በድጋሚ አደንዛዥ ዕፅ ሲጠቀም ተይዟል ተብሎ ወደ ልደታ ፖሊስ ጣቢያ ሲመጣ፣ በጣቢያው የተመደቡ የፌዴራል ዓቃቢያነ ሕጎች “ቆይ ግን ገንዘብ ከየት እያመጣህ ነው ሐሺሽ የምትገዛው?” ይሉታል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎችን እያጠመደ እንደ ምንም አንድ ቀን ከትምህርት ቤት አስቀርቶ አደንዛዥ ዕፅ እንደሚያስጠቅማቸው፣ ከዚያ በኋላ ሱስ ሆኖባቸው አደንዛዥ ዕፅ እናጭስ እያሉ የእሱንም ወጪ እንደሚሸፍኑለት በሚያስደነግጥ ሁኔታ መለሰላቸው፡፡ ዓቃቢያነ ሕጎቹ “ቆይ ማረሚያ ቤት በነበርክበት ጊዜ [አደንዛዥ ዕፅ ሳታጨስ] አርፈህ ተቀምጠህ አልነበረ? ለምን ስትወጣም አርፈህ አትቀመጥም?” ሲሉት፡፡ ማረሚያ ቤት ያለልፋት አደንዛዥ ዕፅ ማጨስ እንደሚችል የባሰ በሚያስደነግጥ ሁኔታ መለሰላቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና በማረሚያ ቤቶች ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ጥቅም ላይ እንደሚውል ወይም ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት የሚደረግ ለመሆኑ ማሳያዎቹ፣ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች በሚገኙ የፖሊስ ማረፊያ ቤቶችና በማረሚያ ቤቶች ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ አስገብተው ሲጠቀሙ ወይም ለማስገባት ሙከራ ሲያደርጉ ተይዘው የወንጀል ክስ የቀረበባቸውና የተቀጡ ተከሳሾች መኖራቸው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በወንጀል ድርጊት ውስጥ ተገኝተው ለመታረም ወደ ሕፃናት የተሃድሶ ማዕከል ገብተው የነበሩ ሕፃናት፣ ከተሃድሶ ማዕከሉ እየተመላለሱ በሚማሩበት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ይዘው ስለተገኙ መምህራኖቻቸው ወደ ፖሊስ አምጥተዋቸው የወንጀል ምርመራ ተደርጎባቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ለፖሊስ በሰጡት የተከሳሽነት ቃል ድርጊቱን መፈጸማቸውን አምነው፣ ኪሳቸው ውስጥ የቀረውን አደንዛዥ ዕፅ አውጥተው በኤግዚቢትነት አስረክበዋል፡፡ 

ከዚህ በላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በአገራችን የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚው ቁጥር ከጊዜ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነ አመላካች ነገሮቹ እየበዙ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች ድርጊት በአደንዛዥ ዕፅ ምክንያት እየደረሱብን ያሉትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ለመገንዘብ በቂ ሥዕል ይሰጣሉ፡፡ ሆኖም እንደ አገር ለዚህ ጥፋት እየሰጠነው ያለው ትኩረት በእኔ ዕይታ እጅግ አናሳ፣ አሳዛኝና ቀውሱን የማይመጥን ነው፡፡ በአብዛኛው የፍትሕ አካላቱ ዘንድ ሲቀርቡ የሚታዩት አንድ ግራም እንኳን የማትሞላ አደንዛዥ ዕፅ ይዘው፣ ሲጠቀሙ ወይም ሲሸጡ የሚገኙ ሰዎች እንጂ ዋነኞቹ የአደንዛዥ ዕፅ አምራቾች፣ አከፋፋዮችና ሻጮች አይደሉም፡፡ የአደንዛዥ ዕፅ ሥርጭትንም ሆነ የተጠቃሚውን ቁጥር ማስቆም ያልተቻለው የዋነኞቹን አብቃዮች የግብይት ሰንሰለት በመበጠስ ምንጩን ማድረቅ ባለመቻሉ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡

ለ47 ዓመታት ያገለገለው የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ተሽሮ የኢፌዴሪ  የወንጀል ሕግ ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ከተሻሻለባቸው ምክንያቶች አንዱ “ከአደገኛ አደንዛዥ ዕፆች” ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ከፍተኛ ቀውስ ቢያስከትሉም፣ አሳሳቢ በሆኑበት ደረጃ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በብቃት አለመታቀፉቸው እንደሆነ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ መግቢያ ያትታል፡፡ የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አደንዛዥ ዕፅን በተመለከተ የሚሸፍናቸው ነገሮች አሁን ካለው ሕግ ያነሱ ናቸው፡፡ በተሻረው ሕግ መሠረት ድርጊቱን የፈጸመ ሰው እንደነገሩ ሁኔታ የሚቀጣው ከፍተኛ ቅጣት አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ወይም/እና ከ30,000 ሺሕ ብር የማይበልጥ መቀጮ ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ መሠረት ድርጊቱን የፈጸመ ሰው የሚቀጣው ከፍተኛ ቅጣት ከአሥር ዓመት የማያንስ ጽኑ እስራት ወይም/እና ከሁለት መቶ ሺሕ ብር የማይበልጥ መቀጮ ነው፡፡ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ የአደንዛዥ ዕፅ ሥርጭትን ስፋትና የተጠቃሚውን ብዛት ለመቀነስና ችግሩን ለመዋጋት የያዘው አቋም የተሻለ መሆኑ ባያጠራጥርም የአደንዛዥ ዕፅ አምራቾች፣ አዘዋዋሪዎች፣ ሻጮች፣ ይዘው የሚገኙ ሰዎችና ተጠቃሚዎች በእስራት መቀጣታቸው ችግሩን ለማስወገድ ብቸኛ መፍትሔ ሊሆን አልቻለም፡፡ የሚቀጣው ሰው ጥቂት ባይሆንም ሥርጭቱና የተጠቃሚውን ቁጥር ሲቀንስ አይስተዋልም፡፡

በየመገናኛ ብዙኃኑ የሮናልዶን የእግር ኳስ ክህሎት፣ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ከፍታና ውድቀት. . . ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተተነተነ በየቀኑ በግድ ስንጋት እንውላለን፣. . . መሰል የቲቪና የሬዲዮ መርሐ ግበሮች በስፖንሰር አድራጊ ብዛት ሲጨናነቁ፣ አድማጭና ተመልካቾቻቸውን በሽልማት ሲያንቆጠቁጡ፣ የሰው ሕይወትን ለመታደግና ለማበልፀግ የሚተጉና የላቀ ዋጋ ያላቸው የቲቪና የሬዲዮ መርሐ ግብሮች   ሰሚ በማያገኙበት ሰዓት ተወሽቀው ያለስፖንሰር አድራጊ ድጋፍ የኪሳቸውን ብር እያሟጠጡ እንዲሠሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ የስካርና የዳንኪራ ማስታወቂያን እንደ ታላቅ ግኝት ሲለፍፉ የሚውሉትን “ጋዜጠኞች” የሩብ ሩብ ያህል እንኳን ስለአድንዛዥ ዕፅ አስከፊነት፣ መስፋፋትና ጥልቀት የሚተነትኑ ሩቅ አሳቢ ጋዜጠኞች መቼ ይሆን የምናገኘው?

“ወጣቱ የልማታችን ተጠቃሚ ሆኗል!” ከሚል የፖለቲካ ፍጆታ ወጥቶ፣ “ወጣቱ ራሱን ከአደንዛዥ ዕፅ ራሱን እንዲጠብቅ እመክራለሁ!” እያለ የሚወተውት ባለሥልጣን መቼ ነው የምናገኘው? የወጣቱም ሆነ የሌላው የአገራችን ሕዝቦች ሕይወት የተሻለ እንዲሆን የራሳችውን ጥረት እያደረጉ ያሉ የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃንን ጥረት ለማገዝ የሚሽቀዳደም ባለሀብት የምናገኘው መቼ ይሆን? ወደየቤተ እምነቱ ቀርቦ ፈጣሪውን ሊያመልክና ምሥጋና ሊያቀርብ የሚችለው ወጣት በአደንዛዥ ዕፅ ችግር እየታመሰ በየሜዳው ሲወድቅ፣ ቤተ እምነቱ ለሚገነባው የገበያ ማዕከል ሕንፃ ወይም አጥር ማሠሪያ ገንዘብ ከምዕመኑ ከሚለምንበት አንደበቱ ቀንሶ ወጣቱ ሕገ ፈጣሪን ጠብቆ ራሱን ከአደንዛዥ ዕፅ እንዲጠብቅ የሚገስጽና የሚወተውት የዕምነት አባት/እናት የምናገኘው መቼ ነው? የዝምታችን ማብቂያ ጥግ የቱ ነው? አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀም ስንት ሕፃን? ስንት እናት? ስንት አባት? ስንት ወንድም? ስንት እህት?. . . ስንት ዜጋ? ሲገኝ ነው በአደንዛዥ ዕፅ ላይ አገራችን ክተት የምታውጀው? የምለውን ነገርም ሆነ የችግሩን ስፋት ያጋነነኩት የመሰላችሁ ትኖሩ ይሆን? አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀሙ ልጆቻቸው በሚያደርሱባቸው ጉዳት በመሳቀቅ፣ በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ምክንያት በልጆቻቸው ላይ የሚደርሰውን የዘወትር ቀውስ ላለማየት በመሻት ልጆቻቸው እንዲታሰሩላቸው በየፖሊስ ጣቢያውና በየፍርድ ቤቱ የሚማፀኑ እናቶችን ሳግና እንባ ብታዩ ሐሳባችሁን ትቀይሩ ይሆን?

የመፍትሔ ሐሳቦች

የችግሩ መኖር የሚካድ ነገር አይደለም፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ችግሩን እንዳላየ እንዳልሰማ መሆናቸውን ትተው አደጋ ላይ መሆናችንን በማመን፣ ችግሩን ለመዋጋት ታጥቀው ተነስተው ሊያስነሱን ይገባል፡፡ ችግሩ መኖሩ ዕሙን ቢሆንም የችግሩን ስፋትና መንስዔ በጥልቀት የሚመረምሩ ጥናቶች በባለሙያዎች፣ በግልና በመንግሥት ተቋማት ጥምረትና ርብርብ በፍጥነት ሊከናወኑ ይገባል፡፡ አደንዛዥ ዕፅን የተለመከተ ግልጽ የሆነ አገራዊ ፖሊሲ ሊኖር ይገባል፡፡ ከታች እስከ ላይ ያሉ የትምህርት ተቋማት ከአድንዛዥ ዕፅ ነፃ የሆኑ ቀጣናዎች መሆናቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡ የፖሊስ ተቋማትን አቅም ከፖሊሳዊ ሥነ ምግባር ጋር በከፍተኛ ሁኔታ በመገንባት የአደንዛዥ ዕፅን ዝውወር፣ ሽያጭና ተጠቃሚነትን በስፋት ሊከላለኩ ይገባል፡፡ በአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ትስስር ውስጥ ያሉትን ሰዎች መለየትና ዘርፉን ከሙስና ማፅዳት በሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሊፈጸም ይገባል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትና የሃይማኖት አባቶች/እናቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ መምህራን፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ወላጆችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ ዜጎች. . . ችግሩን መኖሩን ተገንዝበው ከፍተኛ አገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር ልጆቻቸውንና ወጣቱን ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠብ ማስተማርና መገሰጽ አለብን፡፡ በሱስ ውስጥ የገቡ ሰዎች የሚያገግሙባቸውና ከችግሩ የሚወጡባቸው ተቋማት በግልም ሆነ በመንግሥት ደረጃ አሁን ካለው እጅግ በተሻለ አቅምና ቁጥር ተደራሽ ሆነው በስፋት ሊቋቋሙ ይገባል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶችም አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀማቸው እስራት የተፈረደባቸውን ታራሚዎች አስሮ ከማቆየትና ከተሃድሶ ሥልጠና ባሻገር፣ መሰል ታራሚዎች ከሱስ የሚያገግሙበት መንገድን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ በመሥራት ታራሚዎች ከሱስ የሚወጡበትን ዕድል መፍጠር አለባቸው፡፡

የአደንዛዥ ዕፅን ቀውስ ለመቀነስ ተመራጩ መንገድ መከላከል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ የአሜሪካው ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦን ድራግ አቢዩዝ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ የአደንዛዥ ዕፅን ቀውስ ለመከላከል የሚወጣው አንድ ዶላር ቀውሱ ከተከሰተ በኋላ ለሕክምና፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርንና ተጠቃሚዎችን ለመከታተልና ለማስቀጣት በወንጀል ፍትሕ አካላት ይወጣ የነበረን ሰባት ዶላር ማዳን ይቻላል፡፡ አበው “ሳይቃጠል በቅጠል” እንደሚሉ እኛም ከዚሁ ተምረን መከላከል ላይ ልናተኩር ይገባል፡፡ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ እየተጋፈጥን ያለነው ችግር ከባድ በመሆኑ ቃጠሎው ተነስቷል፡፡ ያለን ዕድል ቃጠሎው ሰደደ እሳት እንዳይሆን ኢትዮጵያውያን/ት በሙሉ ሆ ብለን መረባረብ ነው፡፡ ለችግሩ ተመጣጣኝ መፍትሔ የሚያመጣ እንቅስቃሴ አለማድረግ ከዝምታ የተለየ አይደለም፡፡ ጉዟችንን ዛሬ ካልጀመርን፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም በሕግ ይፈቀድ!” የሚል እንቅስቃሴ የሚጀመርበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡

ትዝብቴን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሌላ ሐሳብ ብቻ የምንዋጋ፣ ከግል ክብርና ጥቅማችን በላይ ለአገራችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች ያድርገን፡፡ ብሩሃን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ፡፡ ሰላም፡፡                                                                   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን (LL.B, LL.M, MSW) አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን አየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው                [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ