Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርሕልሟን የተነጠቀች አገር

ሕልሟን የተነጠቀች አገር

ቀን:

በይነገር ጌታቸው

ፈንድ ፎር ፒስና ፎሬን ፖሊሲ መጽሔት በጋራ ባወጡት እ.ኤ.አ. የ2017 የመበተን አደጋ ሥጋት ያለባቸው አገሮች ዝርዝር (Fragile State Index) ኢትዮጵያ ከ178 አገሮች 15ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡ ይህም ከቀደመው ዓመት 2016 ጋር ሲነፃፀር አሥር ያህል ደረጃዎችን ያሽቆለቆለ ነበር፡፡ ዓመታዊ ጥናቱ በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት ባወጣው ትንበያ፣ ኢትዮጵያ ከየትኛውም የዓለም አገር በበለጠ በ2017 አደጋ ውስጥ መሆኗን ጠቁሟል፡፡

ይህ ጥናት የተለያዩ የሜቴዶሎጅ ጥያቄዎች የሚነሱበት ቢሆንም በድምዳሜ ደረጃ ግን አሁን ካለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚቀራረብ ውጤትን የገለጸ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ በተለይም ከአሥር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጠናቀቅ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ብልጭ ድርግም ሲል የቆየው ግጭት ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልሎች መልኩን በመቀየር ወደ ለየለት ደም አፍሳሽ ግጭት አድጓል፡፡ እንዲህ ያለው የአገራችን ሁኔታም ቀደም ብዬ በጠቀስኩት ጥናት ላይ 2017 ለኢትዮጵያ አዳጋች ነው የሚለውን ሪፖርት እንድንቀበል የሚያስገድደን ይመስላል፡፡ በአንዲት ፌዴራላዊ ሥርዓትን ከሁለት አሥርታት በለይ በመተግባር ላይ ነኝ ለምትል አገር በክልሎች መካከል በተነሳ ግጭት ከ50 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉና ቁጥሩ በውሉ ያልተለየ ዜጋ ሕይወቱን እንዳጣ መስማት በእርግጥም ወዴት እየሄድን ነው? የሚል ውይይትን በቀናነት እንድናደርግ ያስገድደናል፡፡

- Advertisement -

ይህ ጽሑፍም ኢትዮጵያ እንደ አገር ምን ተመኘች?  ምንስ አገኘች? የሚለውን በግርድፉ በመመልከት ዛሬ የደረስንበትን ነባራዊ ሁኔታ ይቃኛል፡፡ በዘመናዊው የአገራችን ታሪክ ውስጥ ያልተፈታውን ሕልም ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎችን ይዳስሳል፡፡

ምን ተመኘን? 

በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አፄ ቴዎድሮስ የመጀመርያው ሕልመኛ መሪ መሆናቸው ከሞላ ጎደል የሚያሰማማ ነው፡፡ በዘመነ መሳፍንት ወቅት የተበጣጠሰችውን አገር አንድ ለማድረግ የደከሙት ንጉሡ በኋላ ላይ በኃይልም ቢሆን አንዲት ኢትዮጵያን ለመመሥረት ችለዋል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ሕልም ግን በዚህ ብቻ የተገታ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ሥርዓት ሊበጅላት ይገባል የሚል ሐሳብ ነበራቸው፡፡ ንጉሡ በወቅቱ በኃይል አንድ ያደረጓትን አገር በሥርዓት ወደፊት ጠንካራ ለማድረግም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አካሂደዋል፡፡ ነገር ግን ውጥናቸው ከዳር የደረሰ አልነበረም፡፡ ገብረ ሕይወት ባይካድኝ “አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በተሰኘ መጽሐፍ አፄ ቴዎድሮስ በሕልፈታቸው ሰሞን “የአገሬው ሰው በእኔ ላይ የተነሳው ሥርዓት ስለሌለው ነው፤›› ማለታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እዚህ ላይ ግን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ያስፈልጋል የሚሉት ሥርዓት ምን ነበር? በተለይም በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ገዥዎች በአመፁ ጊዜ የወሰዱት ዕርምጃስ ምን ይመስላል? በታሪክ ላይ ምርምራቸውን ያደርጉ ምሁራን አፄ ቴዎድሮስ ምኞታቸው እንጂ የሄዱበት መንገድ ተገቢ አልነበረም ይላሉ፡፡ ባህሩ ዘውዴ ‹‹What Did We Dream? What Did we Achtive? And where are we heading?›› በተሰኘ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር በቀረቡት ጥናታቸው የአፄ ቴዎድሮስ መንገድ በዘመኑ ዓውድ ሲታይ በተቀናቃኝ ላይ የታወጀ ቀይ ሽብር ነው ይሉታል፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ሕልማቸውን ለመፍታት የሄዱበት መንገድ ስህተት ቢሆንም፣ ሕልማቸው ግን እንደ ሕልም ስህተት አልነበረም፡፡ በመሆኑም ድኅረ የጣሊያን ወረራን ተከትለው የመጡት የአገሪቱ ልሂቃን የአፄ ቴዎድሮስን ሕልም ለመፍታት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩም አፄ ቴዎድሮስን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራትን ሲፈጽሙ ተስተውለዋል፡፡ በርካታ መጻሕፍትና ተውኔቶችም የንጉሡን ታላቅነት ለማንፀባረቅ ተደርሰዋል (በእኔ ግምት አፄ ቴውድሮስ እንደዚያ ዘመን የተሞገሱበት ወቅት የለም)፡፡ በአውሮፓ ያሉ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ኅብረትም ያሳትም የነበረውን መጽሔት በንጉሡ የፈረሰ ስም “ታጠቅ” ያለበት ምክንያት ለጊዜው ፖለቲካዊ ጉዞው ከአፄ ቴዎድሮስ በላይ መደላደል ስላጣ ነበር፡፡

በ1960ዎቹ መባቻ የንጉሡን ሕልም ሕልማቸው ያደረጉ የወቅቱ ተማሪዎች በፖለቲካው በኩል የነበራቸው ተሳትፎ እየጎላ የመጣ ሲሆን፣ በአገሪቱ ያለው ሥርዓት ኢትዮጵያን ወደ ኋላ እየጎተተ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባዋል የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ አንስተዋል፡፡ ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በ1961 ዓ.ም. መረን እያለፈ የሄደ ሲሆን፣ የተቃውሞ ሠልፎችን ማካሄድና ትምህርት ማቋረጥን በመሰሉ ተግባራት የታጀበ ነበር፡፡ ይህን ዘመን ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሕልሟን ለመውለድ ምጥ የበዛበት ጊዜዋ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ዋለልኝ መኮንን “የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ” የተባለ ጽሑፉን ለንባብ ያበቃበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት አፄ ቴዎድሮሳዊት ኢትዮጵያ በምትቀነቀንበት በዚያን ዘመን፣ ከዚህም ከፍ ሲል በንጉሡ ፈረስ ስም በሚጠራው ታጠቅ መጽሔት ላይ ከአንድነት ማዶ ያለን ሐሳብ የያዘ ጽሑፍ መውጣቱ ብዙ ጥያቄን ያስከተለ ነበር፡፡ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖራቸው ሳይሆን፣ ከሆነ ብሔር በመፈጠራቸው ነው ጭቆና የሚደርስባቸው የሚል ክርክርም መነሳት ጀመረ፡፡ ዋለልኝ መኮንን የብሔር ጭቆናን ሐሳብ ፈጠረው ወይስ የብሔር ጭቆናው ሐሳብ ነው ዋለልኝን የፈጠረው? የሚለው ግን መሠረታዊ ጥያቄ ሆኖ ዛሬም ሲነሳ ይስተዋላል፡፡

ዋለልኝ እንደ ሮማን ፕሮቻዝካ 

ሮማን ፕሮቻዝካ  ከጣሊያን ወረራ ዘመን በፊት አዲስ አበባ ላይ የከተመ ኦስትሪያዊ የሕግ ባለሙያ ሲሆን፣ “Abyssinia the Power Barrel” የተባለ መጽሐፍ በወረራው ዋዜማ ሰሞን በ1928 ዓ.ም. ለንባብ አብቅቷል፡፡ ፕሮቻዝካ ከፊል እውነት ከፊል ተረት በሚመስል መጽሐፍ ኢትዮጵያዊያን ለነጮች ያላቸው ንቀት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ይተርካል፡፡ በዚህ ሳያበቃም ኢትዮጵያ እንደ አገር ወደፊት ለዓለም ሥጋት መሆኗ አይቀርም በማለት የራሱን ምክር ለአውሮፓውያን መንግሥታት ያስተላልፋል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች ያሏት አገር በመሆኗ እነሱን በመከፋፈል አገሪቷን ማድከም ይቻላል ሲል ይገስጻል፡፡ ፕሮቻዝካ የብሔሮችን ልዩነት ካጎላን ኢትዮጵያ እንደ አገር አትቀጥልም ሲል ይሞግታል፡፡ አንዳንድ ምሁራን ይህን የፕሮቻዝካ ሐሳብ በመተግበር በኩል የዋለልኝን ያህል ባለውለታ የለም የምል ሐሳብ ይሰነዝራሉ፡፡

ዓለም እሸቴ “On the Question of Ethiopian Nationa Liyes” ‹‹Walelegn as Roman Prochazka›› በተሰኘ ጥናቱ፣ “የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ” የሚለው ጽሑፍ በዋለልኝ ብቻ የተቀነባበረ ነው ለማለት እንደሚቸገር ይገልጻል፡፡ ለዚህ ሐሳቡ ደግሞ ጠንካራ መከራከሪያ አድርጎ የሚያቀርበው የወቅቱን የሲአይኤ ኢትዮጵያ የማፈራረስ ሴራ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በ1961 ዓ.ም. ሲአይኤ በኢትዮጵያም ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የነበረው ተሳትፎ እያደገ የመጣበት ወቅት ነው፡፡ ለአብነት ያህል የኤርትራን ትግል ውስጥ ለውስጥ በመደገፍ በኩል የዚህ ድርጅት ሚና የጎላ እንደነበር ሲገለጽ ይሰማል፡፡

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አቀንቃኙ ፖል ሔንዝ በኢትዮጵያ ኑሯቸውን ማድረጋቸውና ይህን አስተሳሰባቸውን በይፋም ባይሆን ውስጥ ለውስጥ መንዛታቸው፣ ሲአይኤና ኢትዮጵያ በወቅቱ የነበራቸውን ጉዳይ በድጋሚ በውል እንድናጤን ያስገድዳል፡፡ አለም እሸቴ ቀደም ተብሎ በተጠቀሰ ጥናቱ ዋለልኝ ያነሳውን ሐሳብ ከሲአይኤ ተልዕኮ የተለየ አይደለም የሚል ክርክር ያነሳል፡፡ የዓለምን መከራከሪያ ሙሉ በሙሉ መቀበል አዳጋች ቢሆንም እንኳን፣ ከዋለልኝ ጀርባ ማን ነበር የሚለውን ጥያቄ መልሶ መላልሶ ማንሳት ግን ኃጥያት የሚሆን አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ፍንጮች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል  ኢቪሊን ፋረከስ ‹‹Fractured States and U.S. Foreign Policy›› በተባለ መጽሐፉ፣ አሜሪካ በ1960ዎቹም ቢሆን በኢትዮጵያ የነበረውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሐሳብ ትደግፍ እንደነበር መግለጹን ልብ ይሏል፡፡

ልደቱ አያሌው “መድሎት” በተባለው መጽሐፍ ሶሻሊዝምን ለሚያቀነቅነው ዋለልኝ በበቂ ሁኔታ ለመደብ ትግል መሠረት የሚሆን ነገር በማጣቱ፣ ብሔር የሚል ጉዳይን ተጠቅሞበታል ይላል፡፡ ዋለልኝ ኢምፔራሊስትም ይሁን ሶሻሊስት በአንድ ነገር ላይ ግን መስማማት ያስፈልጋል፡፡ እሱም የብሔር ጭቆና ዋለልኝ ስላነሳው ብቻ ፖለቲካዊ መሠረት ኖሮት ወደፊት ሊራመድ አይችልም፡፡  በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ አገር ሁለተኛ ምኞቷ ወይም ሕልሟ የብሔሮችን እኩልነት ማረጋገጥ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሁለቱ ሕልሞች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መሆናቸውን እንመለከታለን፡፡ ሕልሞቹ ብቻ ሳይሆኑ ሕልሞቹን ለመፍታት የተሄደበት መንገድ በተቃርኖ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ሁለቱን ሥርዓቶች ደርግና ኢሕአዴግን ብንመለከት እንኳን አሃዳዊ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የተከተሉ በመሆናቸው የሕልም አፈታታቸው ተቃርኖ አለበት፡፡

መረራ ጉዲና (ዶ/ር) ‹‹የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችና የሚጋጩ ሕልሞች የኢሕአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ›› ‹‹በተሰኘ መጽሐፋቸው ይህ ዓይነቱ የሕልም ፀብ በሥርዓቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚው ጎራም  ላይ የሚስተዋል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በእርግጥም ጆዋርና ታማኝ አንድ ሠልፍ ላይ የሚይዙት ሰንደቅ ዓላማ መለያየትም፣ የሕልማችን ኩሪፊያ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ  የፖለቲካ አስተሳሰብ ኩርፊዎች ‹‹Centrifuglim›› እና ‹‹Centripetalism›› በሚባሉ ሁለት የፖለቲካ ምሁራን ቃላት የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡ የሕልማችን ማቀፊያዎችም እንደ አገር እነዚህ ቃላት ናቸው፡፡ አንደኛው ወገን አንዲት ኢትዮጵ እንጂ ብሔር የለኝም የሚል ክርክር ሲያነሳ፣ ሌላኛው ብሔር ከሌለ ኢትዮጵያ  አትኖርም ሲል ይሞግታል፡፡ እነዚህ ሁለት ሕልሞች ከፊት ላለው ጉዟችን የቤት ሥራ ናቸው፡፡

ምን አገኘን?

ባህሩ ዘውዴ ከላይ በተጠቀሰስ ሥራቸው ኢትዮጵያ ሦስት ነገሮች ተመኘች ይሉናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመሬት ላራሹ ጥያቄ ብቻ በውሉ የታየ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው መረራ ጉዲና ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሕልሞች  በቁጥር  ሦስት መሆናቸው ላይ ቢስማማም፣ ሕልሙ ግን ከባህሩ ዘውዴ የተለየ ጉዳይንም ይካትታል፡፡ በዚህ መሠረትም አንዲት ኢትዮጵያ የሚለው ሕልም፣ የብሔር ጥያቄን የሚያስቀድመው ሕልምና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሥልጣን ላለመልቀቅ ያለው ሕልም ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ምሁራን ከሞላ ጎደል ከላይ እኔ ያነሳሁት የአገሪቱ ሕልምን የጠቀሱ ስለሆነ፣ በሁለቱ ላይ ብቻ አተኩረን ሕልሙን እንዴት ፈታነው የሚለውን እናንሳ፡፡ ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ 60 ያህሉን በንጉሣዊ አስተዳደር ያሳለፈች በመሆኗ፣ በረዥም ደረጃ 60 ዓመት በአንድ መልክ የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ ተነስተንም ንጉሣዊው የአገዛዝ ዘመን አንድነትን እንጂ ልዩነትን የማይቀበል አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡ የፍትሐዊነት ጥያቄ ሲነሳ እንኳን መጀመርያ አማርኛ ቻሉ የሚሉ ምላሾች ሳይቀር ሲሰጡ መኖራቸውን ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ በደርግ ወቅትም የነበረው አሃዳዊ መንሥት በመንግሥታዊ ሥርዓት ደረጃ ይህን ሊፈታበት የሚችል መንገዱ ከባድ ነበር፡፡ ደርግ በመጨረሻም ሰዓት ራስ ገዝ አስተዳደሮችን ለመፍጠር ቢሞክርም፣ የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ በመነፋቱ ሁሉም ነገር አበቃለት፡፡

ካልተፈቱት ሕልሞች ጋር ጉዞ የቀጠለችው ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም. ከኢሕአዲግ ጋር ተዋወቀች፡፡ አዲሱ መንግሥታዊ ሥርዓትም ለዘመናት የዘለቀውን የሕልም ኩርፊያ ለመፍታት ፌደራላዊ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመተግባር ጉዞ ጀመረ፡፡ በዚህ ወቅት መጀመርያ ኢትዮጵዊ ነኝ ያሉ ቡድኖች ኢሕአዴግን በአገር አፍራሽነት ወነጀሉ፡፡ ብሔሮች ራሳቸውን ችለው መከለላቸው ኢትዮጵያን የማፍረስ ዘመቻ ነው በማለት ለፈፉ፡፡ ይህ ዓይነቱን ትችት መቀመጫቸውን አገር ውስጥ ያደረጉ ተቃዋሚዎችም ሳይቀር ተያያዙት፡፡ በተለይም የአማራ ፖለቲከኞች ብሔር ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያ ነገ ጠፊ ናት የሚል ሙግትን ያዙ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የደቡብ ፖለቲካ ኃይሎች በብሔር ላይ የተመሠረተው ሥርዓተ ተገቢነት ያለው ነው የሚል ሐሳብ ሰነዘሩ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ንትርኮች መሀል ግን ሕገ መንግሥቱ ፀድቆ ወደ ተግባር ተገባ፡፡

በዚህ ሕገ መንግሥት ላይም በግልጽ እንደሰፈረው የአገሪቱ ባለቤቶች ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ሁነው ብቅ አሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነትም በብሔር ጥላ ሥር ወደቀ፡፡ እዚህ ላይ ኢሕኢዴግ የአፄ ቴዎድሮስን ሕልም ዘንግቶ ለዋለልኝ መኮንን ህልም የተገዛ መሰለ፡፡ ገዥው ፓርቲ ግን ሁለቱን ሕልሞች አንድ ላይ ማስኬድ እንደሚችል መግለጹን ቀጠለ፡፡

ይህ ግን ሕልሜን ተነጠቅሁ ላለው ቡድን የሚያረካ መልስ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያትም ፌዴራሊዝም ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ የበረሃ አጀንዳውን የትግራይ ሪፐብሊክን ምሥረታ ሊያካሂድ የፈጠረው መሰሪ ሴራ ነው የሚል ዘመቻ ተጀመረ፡፡ (በነገራችን ላይ ይህ የትግራይን ሪፐብሊክ ምሥረታ ሐሳብ ለኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ከሆኑ ያለመግባባቶች አንዱ ሳይሆን እንደማይቀር ማርቲን ፕሎት ‹‹Understanding Eritrea›› በተባለ መጽሐፍ በእግረ መንገዱ ይነግረናል፡፡ በተለይም የትግራይ ክልል ትህምርት ቢሮ የትግራይን ክልል ካርታ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ለማሰራጨት ጂቲዜድ ከተባለ ድርጅት ጋር በ1990 ዓ.ም. ተዋውሎ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በዚህ ካርታ ዝግጅት ወቅት የተሠራው ካርታ የኤርትራን ግዛቶች በከፊል ማካተቱ ላለመግባባቱ ተጨማሪ ግብዓት ሆኖ አገልግሏል፡፡ በወቅቱ የኤርትራ ባለሥልጣናት ይህን ስህትተ ተራ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ኤርትራን በመጠቅለል ታላቋን ትግራይ የመመሥረት ዓላማ ነው በሚል አጋነው ተመልክተውታል)፡፡

ወደተነሳንበት ሐሳብ ስንመለስ አንዲት ኢትዮጵያ እንጂ የብሔር ጉዳይ አያስፈልግም ያለው ኃይል፣ በተለይም የወቅቱ መጽሔቶች በመንግሥት ላይ መጠነ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት አፋፋሙ፡፡ ለዚህ ፌዴራሊዝምን የማናናቅ መንገድ ድግሞ አወዛጋቢው የሕወሓት የአንድ ወቅት አጀንዳ ማዳመቂያ ሆኖ አገለገለ፡፡ መንግሥት ግን ነገሩን ወደ ጎን በመተው በ1985 ዓ.ም. ብሔሮችን ማካለል ጀመረ፡፡

እዚህ ላይ ሀብታሙ አለባቸው ‹‹ታላቁ ተቃርኖ›› በሚባለው መጽሐፍ ታዬ ንጉሴን በመጥቀስ ያሰፈረውን መመልከት ተገቢ ይመስላል፡፡ ታየ ማርኩስን ዋቢ በማድረግ እንደሚሞግተው ተራውንና ያልተማረውን ሕዝብ በቋንቋ መሥፈርት ብቻ ለፖለቲካ ዓላማ ማንቀሳቀስ፣ ልሂቃኑ የብሔር መስመሮችን ተከትለው ለራሳቸው አጀንዳ እንዲያውሉት መፍቀድ ነው፡፡ በውጤቱም ሕዝቦች በመሀላቸው ያለው መቀራረብ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ታዬ እንደሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው መሠረታዊው  ችግር መሠረቱ ይኼ ነው፡፡

በእርግጥም ይህ ሐሳብ የወቅቱን የአገራችንን ፖለቲካ ለተመለከተ ሰው በቀላሉ ታይቶ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በአማራና ኦሮሚያ፣ በአማራና ትግራይ፣ በኦሮሚያና ጋምቤላ፣ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያና በሱማሌ ክልል፣ በሱማሌና በአፋር መሰል ክልሎች መካከል ያለው የግጭት መነሻም ተራ የነዋሪዎች የድንበር  ግጭት ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲከኞቻችን የመነጣጠል ግንባታ አካል ነው፡፡

በርካታ ፓርቲዎችን ለምሥረታ ያበቃቸውም ይኼው ብሔርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰንም በገዥውም ሆነ በተቃዋሚው በኩል ያሉ ፖለቲከኞች ብሔርን ለህልውናቸው መሠረት አድርገው ያስባሉ፡፡ ጆን አቤንክ እንደሚለው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በየክልሉ ላለ አነስተኛ ማኅበረሰብ የሚሆን መብት የሰጠ አይደለም፡፡ ሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተለያየ ብሔረሰብ የያዙ ሆነው ሳለ በመብት ደረጃ ግን ለአነስተኛ ማኅበረሰቦች የተሰጠው ቦታ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህን የአቤንክን ሐሳብ በሁለት ማሳያዎች ማጠናከር ይቻላል፡፡ የመጀመርያው በአማራ ክልል ያሉ የቅማንት ማኅበረሰብ አባላት በተለያዩ ወቅቶች ወደ ግጭት መግባት ሲሆን፣ ሌላው በቅርቡ የነበረውን የኮንሶ ግጭት ሊነሳ ይችላል፡፡

ጉሩ የፌዴራል ሥርዓት በውሉ ባልዳበረባቸው አገሮች የተለያዩ ጉዳዮች ለግጭት መነሻ መሆናቸው አይቀርም ይላል፡፡ ለአብነት ያህል ሁለቱን እንመልከት፡፡ የመጀመርያው ለዘመናት የኖሩ ቅሬታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቅሬታዎች ለዘመናት ተዳፍነው የቆዩና እንደ እሳተ ጎሞራ ጊዜው ሲፈቅድላቸው የሚፈነዱ ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ፖለቲከኞች ነገሩን በማስታወስና ረመጡን በመነካካት በኩል ለእሳቱ መፈጠር ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ መጥፎ ትውስታዎችን በመነካካት በብሔረሰቦች መካከል ያለውን ድልድይ ይሰብራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች በብሔር ፖለቲካ ካርድ ሲጫወቱ በብዛት የሚጠቀሙበት መንገድ ይህን ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምርጫ 97 ትክክለኛ ማስረጃ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን የነፈጠኛውን ሥርዓት  ዳግም ለመመሥረት የሚጥሩ ስብሰቦች ሲል፣ ተቃዋሚዎች በአንፃሩ የብሔር ፖለቲካ ትግራይን በተለየ ሁኔታ ጠቅሟል የሚል ውንጀላ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ዓይነቱ የፖለቲካ ጨዋታም በጊዜ ሒደት ወደ ሰፊው ሕዝብ ሲወርድ ተስተውሏል፡፡

ሁለተኛው የብሔረሰብን ወሰን ማካለል በተመለከተ የሚነሱ ግጭቶች ናቸው፡፡ ሀብታሙ እንደሚለው በ1985 ዓ.ም. የተደረገው የብሔረሰቦች ወሰን ማካለል በፍጥነት የተደረገና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ያለበት ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም በየጊዜው በድንበር ይገባኛል የሚነሱ ግጭቶች ይስተዋላሉ፡፡ በቅርቡ ከ50 ሺሕ በላይ ሰዎች ለተፈናቀሉበት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ  ሱማሌ ክልል ግጭት መነሻ በመሆን ያገለገለውም ይህ ጉዳይ ይመስላል፡፡ በእርግጥ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ 80 በመቶ ያህሉ ወደ ኦሮሚያ ለመጠቃለል ከመመረጡ በኋላ ይህ መከሰቱ፣ ተጨማሪ ምርመራዎችን በጉዳዩ ላይ እንዲዳረጉ የሚያስገድድ ይመስላል፡፡ ግን እዚህም ላይ ከላይ ያነሳነውን የብሔር ድንበርን ለፖለቲካ ድንበር ማስመሪያነት የሚጠቀሙ ሰዎች መኖራቸውን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ የክልሎቹ ገዥ ፓርቲዎች አባላት ሳይቀር መሳተፋቸው እዚህም እዚያም እየተሰማ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ነገን

የመበተን አደጋ ሥጋት ያለባቸውን አገሮች ዝርዝር የያዘውን ‹‹Fragile State Index›› ለተመለከተ ሰው ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ውስጥ መግባቷን ይመለከታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም. 91.6 የነበረው የመበተን ሥጋቷ ድምር በ2017 ከፈ ብሎ 101.1 ደርሷል፡፡ ይህ ተራ የቁጥር ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ አገሪቱን ባለፉት ዓመታት ለተመለከተ ሰው ተገቢ መከራከሪያ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የተጣሉትን ሕልሞች ማስታረቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕርቅ የሚፈጠረውም ቁጭ ብሎ ከተቃዋሚው ጎራ ጋር በማውራት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ላይ ተጨባጭ የፖለቲካ ዕድገትን በማምጣት ነው፡፡

ፍራንሲስ ፈክያማ ‹‹Poltical Order and Poltical Decay›› በተባለ መጽሐፍ የፖለቲካ ዕድገት በሁለት ነገሮች በመሠረታዊነት ይለካል ይላል፡፡ እነሱም የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት 26 ዓመታት በፖለቲካው በኩል ያለው ዕድገት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በተለይም የመንግሥት የልብ ትርታ ተደርገው በሚወሰዱ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ቀበሌ በሚደርሱ አስፈጻሚ አካላት በኩል ያለው ኢዴሞክራሲያዊ አሠራር፣ የአገሪቱ ፖለቲካ ዝቅጠት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በከፍተኛው አመራር በኩልም የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነትን አምኖ ለመቀበልና ለተግባራዊነቱ ለመንቀሳቀሱ ከአፍ ያለፈ ቁርጠኝነት አይስተዋልም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ፖለቲካዊ ዕድገትን በአገሪቱ ማምጣት አለመቻሉን ያሳየናል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አገር ለመቀጠል ካስፈለጋት ከኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ባለፈ ፖለቲካዊ ዕድገት ማምጣት የግድ ይላታል፡፡ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ሁለት ቃላት ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያን የሚታደጉና ሕልሟንም የሚፈቱ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ዕደገት መደላድሎች ከአስፈጻሚ አካል ጀምሮ ሕግ አውጭና ሕግ ተርጓሚውን በድጋሚ እንድንፈትሽ ያስገድዱናል፡፡ ይህ ደግሞ የአገሪቱን ሕልም ለሚፈታው ፌዴራሊዚም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን መተግበር ተስኖን ከአገር ይልቅ ግለኝነትንና ተራ የፖለቲካ ሽኩቻን ካስቀደምን ግን፣  የዚህች አገር መጨረሻ የዩጎዝላቪያ ዕጣ ፋንታ መሆኑ ብዙ አብነት የሚያስፈልገው አይመስልም፡፡ እንዲህ ማለት ግን ኮሽ ባለ ቁጥር ‹‹ኢትዮጵያ አለቀላት፣ ፌዴራሊዝሙ በተነን፣ ኢሕአዴግ የሥራውን ይሰጠው. . .›› እያሉ ሙሾ የሚያወርዱትን ጎራ መቀላቀል አይደለም፡፡ ብሔሮች በተጣሉ ቁጥር አገር ብትፈርስ ኖሮ የዴሞክራሲ ቁንጨዋ ህንድ እዚህ አትደርስም ነበር፡፡ ነገር ግን ፌዴራሊዝም በውሉ ካልተተገበረና የፖለቲካ ዕድገት ካልመጣ ፌዴራሊዝም በራሱ የመፍረስ ጀማሮ እንጅ የአንድነት መሠረት አይደለም፡፡ ይኼ ደግሞ የአገሪቱን ሕልም መንጠቅ  ሳይሆን የምናልምላትን አገርም ማፍረስ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን አየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...