Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በቀን ሰላማዊ ንግግር በሌሊት ሰላማዊ ዜጋ ላይ የሚተኩሱና ግጭት የሚቀሰቅሱ በዚህ ሁኔታ...

‹‹በቀን ሰላማዊ ንግግር በሌሊት ሰላማዊ ዜጋ ላይ የሚተኩሱና ግጭት የሚቀሰቅሱ በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማይችሉ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል››

ቀን:

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ ሰኞ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኃላ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ከቀናት በኋላ ስለሚከበረው የኢሬቻ በዓል፣ በኦሮሚያና  በሶማሌ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት፣ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሰማራት መንግሥት የበጀተውን አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በየዓመቱ መስከረም መጨረሻ ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ረዥም ዓመት ያስቆጠረ ነው፡፡ በዓሉ ሃይማኖታዊ በዓል ከመሆኑ ባሻገር ሁሉም የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከልጅ እስከ አዋቂ ወጥቶ የሚያከብረውና ፈጣሪውን የሚያመሠግንበት ነው፡፡ ይኼ ክብረ በዓል በቢሸፍቱ አርሰዴ ሐይቅ በየዓመቱ ይከበራል፡፡

ባለፈው ዓመት የኢሬቻ በዓል እየተከበረ ሳለ ከሃምሳ በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን እንዳጡና በመቶ የሚቆጠሩ ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ክብረ በዓል ላይ የሞቱ ዜጎችን ለማሰብ ሲባልም መታሰቢያ መቆሙ አይዘነጋም፡፡ በዘንድሮው በዓል በመገፋፋትና በሌሎች ምክንያቶች በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ፣ በዓሉ የሚከበርበትን አካባቢ መሬት የማስተካከል ሥራ እንደተሠራ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ባለፈው ዓመት በዚህ በዓል ላይ በርካቶች ሕይወታቸውን ያጡ ቢሆንም በዓሉ ዘንድሮም እንደሚከበር መንግሥት አስታውቋል፡፡ ዶ/ር ነገሪ እሑድ መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢሬቻ በዓል እንደሚከበር አስታውቀዋል፡፡

የመስቀል፣ የዘመን መለወጫና የኢሬቻ በዓሎች የሚከበሩት ፈጣሪን በማስታወስ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ እነዚህ በዓሎች የሰላም ምልክቶች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሕዝቦች በሰላምና በአንድነት የሚያከብሯቸው የሰላምና የአንድነት እሴቶቻቸው መገለጫዎቻቸው ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ፈጣሪን በማስታወስና በማመስገን ላይ ትኩረት አድርገው በሚከበሩ በዓላት ላይ የፖለቲካ ዓላማ ማራመድ የሕዝቦች አጀንዳ እንዳልሆነ ሊታወቅ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ‹‹አምና በኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት የተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት መቼም ቢሆን መደገም የለበትም፤›› ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ ከተፈለገ በሰላማዊ መንገድ ለእሱ ተብለው በተዘጋጁ መድረኮች መጠቀም እንደሚቻልና ይኼን መሰሉን በዓል ሕዝብና አገርን ለማወክ እንዳይውል አሳስበዋል፡፡

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል የኦሮሞን ሕዝብ ወግና ባህል በጠቀበ መንገድ ይከበር ዘንድ አባገዳዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረጉ፣ ሥነ ሥርዓቱ በሚካሄድበት ሥፍራ የነበረውን የአደጋ ተጋላጭነት ሥጋት ለማስወገድ ሥራዎች ማከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡ በመንግሥት በኩልም አስፈላጊው ዝግጅት እንደተደረገና ሕዝቡም ከመቼውም ጊዜ በተለየ የኦሮሞን ሕዝብ ባህልና እሴቶች ጠብቆ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ በቅርቡ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ተቀስቅሶ ስለነበረው ግጭትም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ግጭቱ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ቆሟል ተብሎ መናገር እንደማይቻል፣ በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎች በሚቋቋሙበት ሁኔታ ላይ መንግሥት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ከወሰን ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ግጭቶች እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል፣ እንዲሁም በአፋርና በአዋሳኝ ክልሎች መካከል፣ በኦሮሚያና በምዕራቡ ያሉ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግሥትና ከጋምቤላ ጋር፣ እንዲሁም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት መካከል ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች ለብዙ ወራት ያስቆጠረ ግጭት እንደነበር፣ በቅርቡ ደግሞ እነዚህ ችግሮች እየተፈቱ ነው ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ከፋ ግጭት ያደገበትና የዜጎች ሕይወት የቀጠፈ ክስተት ማጋጠሙን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደዚህ ያሉ ግጭቶች በዜጎች መካከል እንዲፈጠሩ የሚጋብዝ እንዳልሆነ ሞግተዋል፡፡ አገሪቱ የምትታወቀው ልዩነትን በማቻቻል እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በልዩነት ውስጥ ደግሞ የአገሪቱን አንድነት ተጠብቆና ሉዓላዊነቷን አስከብራ ለዘመናት የቆየች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ከደርግና ከደርግ በፊት በነበሩት ሥርዓቶች ልዩነቶች በኃይል ሲጨፈለቁ እንደነበርና ዜጎች መብቶቻቸውን ለማስከበር ሲሉ ትግል ወስጥ የገቡበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  ብሔር ብሔረሰቦች በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ ላይ በመሆን ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ በቋንቋቸው እየተማሩና እየተዳኙ፣ ባህላቸውን እያሳደጉ፣ ማንነታቸውን ምንም ሳይሸማቀቁበት በነፃነት እየገለጹ እንዲኖሩ አዲሱ ፌዴራላዊ ሥርዓት ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡

ዴሞክራሲ በሚፈለገው ደረጃ እንዲያድግ መሠረት መጣሉንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አንዳንዶች እንደሚሉት የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የግጭቶች መንስዔ የሚሆን አይደለም፡፡ ይኼ ሥርዓት የሕዝቦችን ፍላጎትና ነፃነት መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው አገራችን ባለፉት 25 ዓመታት ያየናቸውን ሁለንተናዊ ልማቶች ማስመዝገብ የቻለችው፤›› ብለዋል፡፡ የምንከተለው ሥርዓት ትክክል ስለሆነ ለውጦች ዓይተናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጣና የሰላም ቀጣና እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ በዚህ ባልተረጋጋ ቀጣና ውስጥ እንደ አገር ሰላምን ጠብቆ መቆየት ታላቅ ስኬት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የፖለቲካ መረጋጋትም ይሁን በሕዝቦች መካከል ያለው አንድነትና ሰላም ከሌሎች ጋር በሚነፃፀርበት ጊዜ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከተፈጠረው ግጭት ጋር በማያያዝ ዜጎች የፌዴራል መንግሥትን ሲወቅሱ ነበር፡፡ አገራችን ከራሷም ተርፋ ሌሎች በግጭት ሲታመሱ የቆዩትን የጎረቤት አገሮች ጭምር በማረጋጋት ውስጥ ተሳታፊ ነች፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ዕውቅናም ለማትረፍ የቻለች አገር ነች፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በሁሉም አካባቢዎች በተደጋጋሚ ግጭት እያየን ነው፡፡ ይኼ ግጭት ሥርዓቱ የሚፈቅደውና ሥርዓቱ የቆመለት እንዳልሆነ ሁላችንም ልንረዳው ያስፈልጋል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

‹‹አሁን ያለው ሁኔታ በሚገመገምበት ጊዜ ከውጭ የመጣ ችግር ሳይሆን፣ ውስጣችንን እንድናይ የሚያደርገን እንደሆነ ነው የተገነዘብነው፤›› ብለዋል፡፡ የዜጎችን ጥቅም የሚጎዱት ከሌላ አገር የመጡ ሳይሆኑ፣ ከዚሁ ያውም ደግሞ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሥርዓቱ ለዜጎች ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ ሳለ በአመራር ደረጃም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች አሁን የሚታዩ ችግሮች ምክንያት ከመሠረቱ ተጠንቶ የሚታወቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ በምናይበት ጊዜ ኪራይ ሰብሳቢነት ከየትም ዓለም የመጣ አይደለም፡፡ ይኼ ሥርዓት የቆመለትን ዓላማና የተፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ ለማድረግ ለግላቸው ጥቅም የሚያስቡ አካላት የፈጸሙት ነው፡፡ የዜጎች ጥቅም ግድ የማይላቸው ጉዳት እያደረሱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ መንግሥትም በዚህ ላይ ዕርምጃ እየወሰደ ነው የሚገኘው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ተፈናቅለው የመጡ ዜጎችን እያስተናገደች ባለችበት በአሁኑ ጊዜ፣ ኢትዮጵያዊያን የሞቀ ቀዬአቸውን ጥለው ለመሰደድ መብቃታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይኼ ኢትዮጵያን የማይወክልና የሚያሳዝን፣ እንዲሁም የሚያሳፍር ድርጊት መሆኑንም ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመሩ ዕድል ተሰጥቷቸው ሳለ፣ ይኼ ዓይነት ችግር መከሰቱ መሪዎች ራሳቸውን እንዲያዩ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም ይኼ የውስጥ ችግር እንደሆነ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ችግር መላቀቅ የሚቻለው ደግሞ ራስን በትክክል ማየት ሲቻል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ዋናው መትፍሔም የተፈናቀሉ ዜጎችን ማቋቋም እንደሆነ፣ ከዚህ በፊት አብረው ይኖሩ የነበሩ ዜጎች የሁለቱን ክልሎች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ዜጎች ከዚህ በሚወጡበት ጉዳይ ላይ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በድንበር አካባቢ ያሉ ዜጎች አሁንም ቢሆን በሥጋት ውስጥ እንዳሉ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በአራቱም አቅጣጫዎች ያሉ ዜጎች ነገ ደግሞ ምን ሊያመጣ ይችላል ብለው እንደሚሠጉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው እንደተፈናቀሉና ይኼንን ችግር ለመፍታት የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት የየራሳቸውን ክልል ሕዝቦች እያረጋጉ፣ አንዱ አካባቢ ሲፈናቀል ሌላው ደግሞ ተመሳሳይ ችግር እንዳይደርስበትና ከበቀል ነፃ የሆነ አያያዝ እንዲቀጥል ሲሠሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ ለወደፊት ይኼን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን እየተወያዩበት እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኞች አካባቢ የአገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሰፍር በማድረግ መረጋጋት እንዲፈጠር መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡ መጪው ጊዜ ምን ይሆናል በሚል ስሜት ሥጋት ውስጥ ቢኖሩም፣ አጠቃላይ ግጭቱ ግን በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ‹›ይኼን በምንልበት ጊዜ ግን ምንም ግጭት የለም ብለን መደምደም አንችልም፡፡ በጣም ሰፊ ድንበር ነው ያለው፡፡ ባለን መረጃ መሠረት አልፎ አልፎ መከላከያ ሠራዊት የማይደርስባቸው ኪስ አካባቢዎች ችግሮች እንዳሉና እናውቃለን፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ሲደርስበትም አስላፈጊውን ዕርምጃ እየወሰደ እያስቆማቸው እንደሆነ መረጃዎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሲባልም ትራንስፖርት በሁሉም ክልሎች መንቀሳቀስ እንዳይችል መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ይኼን ውሳኔ የሚቃረኑ እንቅስቃሴዎች እንዲታዩም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ይኼን ችግር ለመፍታት የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በጋራ የጀመሩት ሥራ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን ባለው ግን በየክልላቸው ችግሩን ለመቆጣጠር እየሠሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በዚህ ግጭት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም ከሁኔታው እንረዳለን ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይኼን በተመለከተም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በግጭት ቀጣናዎች ሠራተኞችን በማሰማራት መረጃ ሲሰበስብና አስፈላጊውን ጥናት ሲያካሄድ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ አካባቢዎች ሥራውን ጨርሶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሠራተኞችን አሰማርቶ እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ እንደሚጠናቀቅና እንደተጠናቀቀም ፓርላማ ሥራ በሚጀመርበት ጊዜ  ግልጽ ሪፖርት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

የሟቾች ብዛትን በተመለከተ በሁለቱም ክልሎች የተለያዩ ቁጥሮች እንደሚቀርቡ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ጉዳዩ ይፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የአገር ሽማግሌዎች የጀመሩት ሥራ እንዳለና በጋራ በመሥራት የሁለቱ ክልሎች የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጧቸው ኃላፊነት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ፣ ይኼንንም በቅርብ ከመንግሥት ጋር በመሆን የሰላም ኮንፈረንስ እንዲደረግና በሁሉም ሕዝቦች መካከል የነበረው መተማመን እንዲቀጥል የሚከናወኑ ሥራዎች እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

ይኼን ለመደገፍ በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የሚመራ ግብረ ኃይል እንደተቋቋመና ይኼ ኮሚቴ የተለያዩ ተቋማትን ያካተተ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች መካከል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤትና የብሔራዊ አደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡ ይኼ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ከመሆኑ ባሻገር፣ ለወደፊት በዘላቂነት ወደ ቀዬአቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

አንደኛውና ዋነኛው እየተሠራ ያለው ከቀዬአቸው የተፈናቀቁ ዜጎች ንብረት ያፈሩና የተሻለ ሕይወት የሚመሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህ ግለሰቦች ንብረታቸው ያለበት ሁኔታ በትክክል ተጠንቶና ጥበቃ ተደርጎላቸው ወደ አካባቢዎቻቸው እንዲመለሱ የተጀመረ ሥራ እንዳለ፣ አሁን ግን መመለስ ጀምረዋል ተብሎ መናገር የሚቻልበት ደረጃ ላይ እንዳልተደረሰ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ትልልቅ ድርጅቶች ያላቸው ናቸው የተፈናቀሉት፡፡ ስለዚህ ይኼ ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በማለት ግጭት እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል፡፡ ‹‹በቀን ሰላማዊ ንግግር እያደረጉ በሌሊት ደግሞ ሰላማዊ ዜጋ ላይ የሚተኩሱና ግጭት የሚቀሰቅሱ በዚሁ ሁኔታ መቀጠል እንደማይችሉ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊትም ይኼን መሠረት በማድረግ አስፈላጊውን ዕምርጃ እየወሰደ ስለሆነ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥንቃቄ በማድረግ፣ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ ወደ ሰላማዊ ግንኙነቱ እንዲመለስ ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ውስጣዊ ሰላማችንን የማናጋት አቅም ያላቸው የሕዝባችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሁሉ ሕገ መንግሥታዊ ምላሽ ባገኙበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ እየኖርን ባለንበት በዚህ ዘመን፣ ይኼንን መሰሉን የሕዝቦች ሰላምና ዘላቂ ጥቅም የሚፃረር ተግባራትን መካላከልና ማስቆም ከአመራሩ የሚጠበቅ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የማኀበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ሙያና ሥነ ምግባርን አክብረው የሚሠሩ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ፣ ሆን ብለው አደናጋሪ መረጃዎችን በመልቀቅና ግጭቶችን በማባባስ አልመው የሚሠሩ አካላት እንዳሉና እንደተደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም እነዚህ አካላት ከዚህ መሰሉ አፍራሽ ተግባራት እንዲታቀቡ መንግሥት እየጠየቀ፣ ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ ግን የትም ቦታ ቢሆኑ አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ተቀስቀሶ በነበረው ሕዝባዊ ተቋውሞ የበርካታ ዜጎች ሕይወትና ንብረት ወድሟል፡፡ መንግሥት ይኼን ችግር ለመፍታት እያደረገ ካለው ጥረት መካከልም ወጣቶችን የሥራ ዕድል ባለቤት ለማድረግ ያደረገው እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመበጀት ለወጣቶች ብድር በመስጠት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ፣ ለራሳቸው ብሎም ለአገር አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ እንቅስቃሴ ማድረጉን በተደጋጋሚ ጊዜ ገልጿል፡፡ ይኼን በተመለከተም ሚኒስትሩ ሲናገሩ እስካሁን ድረስ አራት ቢሊዮን ብር ተለቋል ብለዋል፡፡

የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶችን በመለየት ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ፣ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገና ትልቅ ድል የተመዘገበበት ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አፈጻጸሙ ግን ከክልል ክልል፣ ከዞን ዞን እንዲሁም ከወረዳ ወረዳ የተለያየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የተለቀቀላቸውን ተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ተጠቅመው ወደ ሥራ የገቡ እንዳሉ ሁሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ወጣቶች መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

የ2009 ዓ.ም. አፈጻጸም ሲታይ መንግሥት ከመደበው የአሥር ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ አራት ቢሊዮን ብር በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አማካይነት ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተላልፎ፣ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የብድሩ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የ2009 ዓ.ም. አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ የሚለቀቅላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...