የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር) በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የተመለከተ ወቅታዊ መግለጫ ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ሰጥተው ነበር፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የገቡት 20 ኩባንያዎች ምርት ጀምረዋል፡፡ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የነበሩት አሥር ኩባንያዎች ላይ አንድ የኮሪያ ኩባንያ ተጨምሮ 11 ደርሰዋል፡፡
ከሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለየ የሚታየው በኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ደግሞ 67 ኩባንያዎች የገቡ ሲሆን፣ 33 የሚሆኑት ምርት ጀምረዋል፡፡ ዱከም የሚገኘው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን እንደሌሎች ፓርኮች አንድ ዓይነት ምርት የሚያመርቱ ኩባንያዎች ያሉት ሳይሆን እንደ ጨርቃ ጨርቅ፣ ሲሚንቶ፣ ወረቀት፣ ብረት፣ መድኃኒትና የመሳሰሉት ምርቶችን የሚያመርቱ በመሆናቸው የተለየ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ በቅርቡ የተመረቁት የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የገቡ ኩባንያዎች ሥራ ለመጀመር የሚያስችላቸው እንቅስቃሴ መጀመራቸውና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተገነቡት ዘጠኝ ሼዶች ውስጥ ሰባቱ መያዛቸው ታውቋል፡፡ የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ካሉት 35 ሼዶች ውስጥ 31ዱ መያዛቸውን የምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ ያስረዳል፡፡ ሞጆ የሚገኘው የጆርጅ ሹ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን የሚጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ የቻይናና የጣሊያን ኩባንያዎች ደግሞ የየራሳቸውን ኢንዱስትሪ ፓርክ በአረንቲ ምንጃና በኮምቦልቻ እየገነቡ መሆኑንም በቅዳሜው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚቀጥለው ወር ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ መግለጫ ባሻገር ግን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ከሠራተኞች አያያዝና ደመወዝ ጉዳይ ጋር በተደጋጋሚ ትችት እየተሰነዘረበት ከመሆኑ አንፃር ምን እየተደረገ ነው? የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ ማብራሪያዎች እንደሚከተለው ተሰናድተዋል፡፡
የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና የውጭ ምንዛሪ ግኝት
ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በይፋ ሥራ መጀመሩ ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ እንዲሁም ፓርኩ ለወጪ ንግድ ሊኖው የሚችለውን አስተዋጽኦ በተመለከተ ሲሰጡ የነበሩ መረጃዎች በዓመት አንድ በሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ ነው፡፡ በቅዳሜው የምክትል ኮሚሽነሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመርተው ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች ይገኛል የተባለው አንድ ቢሊዮን ዶላር በእርግጥስ ይገኛል ወይ? እስካሁንስ ምን ያህል አስገኘ? የሚለውን ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምክትል ኮሚሽነሩ ‹‹ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመርያ ምርት ለውጭ ገበያ የቀረበው መጋቢት 2009 ዓ.ም. ነው፤›› በማለት ይጀምራሉ፡፡ ከዚህ ፓርክ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ያለው ምርት ያለማቋረጥ እየጨመረ ስለመምጣቱ አክለው፣ ነገር ግን የተቀመጠለትን ግብ ለመምታት ግን ጊዜ ይወስዳል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹እርግጥ ነው በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስገኛል የሚል ራዕይ አለን፤›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ይህ ማለት ግን ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ እንደ ጀመረ በአንድ ወር ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ማለት እንዳልሆነ ወይም በመጀመርያውም ዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በፓርኩ ውስጥ ያሉት ሁሉም ሼዶች ምርት ውስጥ ገብተው፤ 30 ሺሕ ሠራተኞች ይዘው በሁለት ፈረቃ ሠርተው ማየት አለብን ብለዋል፡፡ በአሁን ወቅት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለው ሠራተኛ 10,026 ነው፡፡ በተለይ የሠራተኞች ምርታማነት ታሳቢ መደረግ እንደሚኖርበት የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በአንድ ዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ላያመጣ እንደሚችል ቢያመለክቱም ግን ሒደቱ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዘውም በፓርኩ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ለአገሪቱ አዲስ መሆናቸው እንዲሁም የሠራተኞች የማምረት አቅምም ለወጪ ንግድ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዳለው ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ ‹‹አንዳንድ ሠራተኞች በዚህ ገንዘብ ከምሠራ ኮንስትራክሽን ላይ ብገባና ባሬላ ብሸከም አይሻለኝም ወይ?›› የሚለው አመለካከታቸውም መለወጥ ይኖርበታል ይላሉ፡፡
ሠራተኞች ራዕይ ያላቸው እንዲሆኑና እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖራቸው ለማድረግ ብዙ መሠራት እንዳለበት ያመለከቱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ይህ ጉዳይ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑንም በመግለጽ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ከሠራተኞች አመለካከት ጋር የተሳሰረ ጭምር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የሠራተኞች ደመወዝና ምርታማነት
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሠራተኞች ደመወዝ አነስተኛ ስለመሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በቂ ደመወዝ ስለማይቆረጥላቸው ለኑሯቸው በቂ እንዳልሆነ በመጥቀስ ሊሻሻል ይገባል የሚል ጥያቄ አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽንም ለሠራተኞች የሚታሰበው ደመወዝ በቂ እንዳልሆነ እስከመግለጽ ደርሷል፡፡ በቅዳሜው መግለጫ ላይ ይህም ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡
የሠራተኞች ደመወዝ አነስተኛ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ጉዳይ መሆኑን ያመላከቱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ሁሉም ሠራተኞች ቢጠየቁ ደመወዜ ትንሽ ነው ብለው እንደሚመልሱ እርግጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ምርታማነትና ብቃት በሌለበት የደመወዝ መጠን ያድጋል ተብሎ ማሰብ ከባድ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ደመወዜ አነስተኛ ነው ከሚለው ጥያቄ ጎን ለጎን መታየት ያለበት ምርታመማነቱ እንደሆነም በመግለጽ፣ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ያለው የሠራተኞች ምርታማነት ከሌሎች አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አንድን ምርት አምርቶ ለማውጣት ብዙ ነገሮች ቢኖሩም የሠራተኛ ጉልበት አንድ ግብዓት እንደሆነ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ያሉ ኩባንያዎች የደመወዝን ጉዳይ በተለየ የሚመለከቱት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ‹‹በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ምርት ለማምረት የሚወጣው የሠራተኛ ጉልበት ወጪና ተመሳሳይ ምርት ለማምረት ባንግላዴሽ ወይም ሌላ አገር የሚወጣውን ወጪ ነው የሚያመዛዝኑት፤›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ከዚህ አንፃር እዚህ ያለው የሠራተኛ ጉልበት ወጪ ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ አሁን በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለው የሠራተኛ ጉልበት ወጪ ከባንግላዴሽ በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ 20 ሸሚዝ ለማምረት የሚወስደው የሰው ብዛትና ጊዜ፣ ባንግላዴሽ ከ40 እስከ 60 ሸሚዝ የሚመረትበት በመሆኑ ምርታማነቱ ዝቅተኛ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ ደመወዝ አነሰ የሚለውን ነገር ከምርታማነት ጋር አያይዘው መልሰዋል፡፡ ሆኖም ሠራተኞች መብታቸው የሚጠበቅበት አሠራር ተዘርግቶ እየተሠራበት ነው ይላሉ፡፡
የአገር ውስጥ ገበያና የኢንዱስትሪ ፓርኮች
ወደ ሥራ የገቡትና የሚገቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለየ ከሚታዩበት አሠራራቸው ውስጥ አንዱ የሚያመርቱትን ምርት ለውጭ ገበያ ብቻ ማቅረብ ያለባቸው መሆኑ ነው፡፡ በእነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች በምንም ዓይነት መንገድ በአገር ውስጥ በገበያ መሸጥ አይችሉም፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ እንደገለጹትም፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች አንድም ሸሚዝ ለአገር ውስጥ ገበያ እንዳያቀርቡ ክልከላ አለባቸው፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ማናቸውም ቢሆኑ አገር ውስጥ እንዳይሸጡ መከልከላቸው የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ፓርኮቹን ለግንባታም ሆነ ለአስተዳደራቸው በጣም ብዙ ወጪ ወጥቶባቸዋል፡፡ ለአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ወይም በአብዛኛው ለአገር ውስጥ ገበያ አምርቱ ቢባሉ የተፈለገውን ጥቅም ሊያስገኙ ስለማይችሉ፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገቡ ኩባንያዎች የአገር ውስጥ ገበያን ታሳቢ እንዳያደርጉ መከልከሉን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ ለምርት የሚሆኑ ግብዓቶች በአብዛኛው ከውጭ የሚመጡ በመሆኑም አንድ አምራች ለግብዓት ወይም ለጥሬ ዕቃ መግዣ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ካላስገኘ፣ ትርጉም ስለማይኖረው እንዲከለከሉ ተደርጓል፡፡
እንዲህ ዓይነት ድንጋጌ ኩባንያዎች በመርህ ወደ ውጭ እንዲልኩ ያደርጋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ አንዳንዴ ግን ገፍተው የሚመጡ ነገሮች እንዳሉ ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ እንደ ምሳሌ ያቀረቡትም አንድ በቦሌ ለሚ የሚገኝ ኩባንያ የተበላሸና ምንም ላደርገው የማልችለው 200 ሺሕ ነጠላ (ፒስ) ጂንስ ስላለኝ እባካችሁ ፍቀዱልኝና አገር ውስጥ ልሽጥ ቢልም፣ እንዲህ ማድረግ አይቻልምና አይፈቀድልህም እንደተባለ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹አገር ውስጥ መሸጥ እንደማይቻል የተገለጸለት ይህ ኩባንያ፣ ወደ ሩዋንዳ ቢልከው ዋጋ ይቀንስበታ እንጂ መሸጡ አይቀርም፡፡ ያደረግነውም ይህንኑ ነው፤›› በማለት ኩባንያዎቹ ለአገር ውስጥ ገበያ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዱከም የሚገኘው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ያሉት ኩባንያዎች አብዛኛዎቹ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡት ለአገር ውስጥ ገበያ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን እንደ ሌሎቹ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የወጪ ንግድ ላይ እዲያተኩሩ አዲስ አሠራር መዘርጋቱን የምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ ያስረዳል፡፡
‹‹ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ ኩባንያዎች ለአገር ውስጥ ገበያ ነበር የሚያቀርቡት፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ለወጪ ንግድ አስበው እንዲሠሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ወደ ፓርኩ የሚገባ እያንዳንዱ ኢንተርፕረነር ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት የሦስትዮሽ ስምምነት መፈራረም እንደሚኖርበት የሚያስገድድ አሠራር ይተገበራል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ድርጅቱና አልሚው የሚፈርሙት የሦስትዮሽ ስምምነት ውስጥ ከተካተቱት ነጥቦች መካከል ወደ ፓርኩ የሚገቡት ኩባንያዎች መቶ በመቶ ምርታቸው ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚኖርባቸው መሆን የሚገልጽ ነው፤›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ይህንን ካልፈረሙ ፈቃድ እንደማይሰጣቸው አመልክተዋል፡፡
የአገር ውስጥ ባለሀብትና ኢንዱስትሪ ፓርክ
መንግሥት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የገነባቸውና እየገነባቸው ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጉዳይ ሲነሳ፣ ፓርኮቹ በሙሉ ከኮንስትራክሽን ግንባታቸው ጀምሮ ወደ ፓርኩ የሚገቡ ኩባንያዎች በሙሉ የውጭ ኩባንያዎችን ታሳቢ ያደረገና የአገር ውስጥ ባለሀብትን ያላማከለ ነው የሚለው አስተያየት በተደጋጋሚ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከንግድ ኅብረተሰብ ጋር በመከሩበት መድረክ፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአገር ውሰጥ ባለሀብቶችን ያላካተተ ሆኖ መገኘቱ ለምን? የሚል ጥያቄ እስከ መቅረብ የደረሰበት ነው፡፡
ይህ ጥያቄ አሁንም ከተለያየ አቅጣጫ ይቀርባል፡፡ በቅዳሜው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ምን ደረጃ ላይ ይሆን? ተሳትፎዋቸው ምን ያህል ነው? ምንስ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው? ቢያንስ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንዲቀላቀሉ የሚደረግበት አሠራር እንዲኖር ለምን አይደረግም? የሚሉና ተያዥ ጥያቄዎች ቀርበው ነበር፡፡
ምክትል ኮሚሽነሩ እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች የሰጡት መልስ፣ መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን የሚገልጽ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማስገባት ከፍተኛ የሆነ ሥራ እየተሠራም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዋነኛነት የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ቦርድ የተለየ ማበረታቻ በማድረግም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ጥረት ቢደረግም፣ የታሰበውን ያህል አለመሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በተደጋጋሚ ማስታወቂያ (አራት ጊዜ) ወጥቶ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ የሆኑ የተወሰኑ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተገኝተዋል፡፡
ነገር ግን ብዙዎቹ ከማምረቻ ኢንዱስትሪ ውጭ የሆኑ ግን ፍላጎት ያላቸው ናቸው እንጂ ችሎታና ልምዱ የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ የሚፈልጉ መሆኑን ነው ይላሉ፡፡ እንደተባለው ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ ሁኔታዎች ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ከመድኃኒት ማምረቻ ፓርኩ ውጭ በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ለውጭ ገበያ ነውና የውጭ ገበያን ሊያለማምዷቸው ፈቃደኛ የሆኑ አጋሮች ሊያገኙ እንደሚገባ በማመን የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተው ነበር ብለዋል፡፡ ይህንን የማፈላለጉ ጉዳይ ደግሞ ሰፊ ጊዜና ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በተለይ ማሳያ እንዲሆን ሐዋሳ ላይ በተደጋጋሚ ብዙ ዕርምጃዎች ስለመወሰዳቸው አስረድተዋል፡፡
በተለይ ማሳያ እንዲሆን ሐዋሳ ላይ በተደጋጋሚ ዕርምጃዎች ተወስደው ሞዴሎችን ለመቅረፅ ተሞክሯል፡፡ ‹‹በመሆኑም ካሉት አምራቾች ጋር በምን መልክ ነው የሚቀናጁት? በሚል ሦስት ዓይነት አማራጮች ነበር ያቀረብነው፡፡ አንደኛ ሰብ ኮንትራት እንዲሰጣቸው ነው፡፡ ካላቸው ምርት የተወሰነውን እነዚህ ኩባንያዎች በሰብ ኮንትራት ስምምነት እንዲገቡ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን ይህ አመራጭ አልተራመደም፡፡ በዚህ አማራጭ ላይ የገጠመው ችግር የታሰቡት የውጭ ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው ውስጥ አለመግባታቸው ነው፡፡ ያነጋገርናቸውም ኩባንያዎች አሁን በሙሉ አቅማቸው ሥራ ስላልጀመሩ ተጣጥሞ ለመሥራት ይቸግራቸዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ከዓመት ሁለት ዓመት ያላነሰ ጊዜ በመፈለጋቸው ያለመሳካቱን ጠቁመዋል፡፡
የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ ሁለተኛ አማራጭ ተደርጎ የተወሰደው ‹‹ኢኖቬቴቭ›› የሆነ ሞዴል ነው፡፡ ይህም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የገቡ የውጭ ኩባንያዎች እያመረቱ ካሉት ምርት ጋር ተያያዥ የሆነ ምርት ካለ፣ ምርቱ ምንድነው ብለው ፕሮፖዛል እንዲያቀርቡ በማድረግ ያንን ምርት እንዲያመርቱ ማድረግ ነበር፡፡ ለምሳሌ የልብስ ቁልፍና የፓኬጂንግ ሥራዎችን የአገር ውስጥ ኩባንያዎች መሥራት ይቻላሉ ተብሎ እንደ አማራጭ ተይዟል፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር፣ በዚህ ረገድ አንድ ድርጅት የተሻለ ሆኖ ስለተገኘ ጥሩ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡ ማሸጊያዎችን በመማምረት ለኩባንያዎቹ በማቅረብ ይሠራል ተብሎ የሚጠበቀው አንድ የአገር ውስጥ ኩባንያ፣ በቅርቡ ወደ ፓርኩ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ስለዚሀ በሐዋሳ ፓርክ ሊገባ የሚችል የአገር ውስጥ በለሀብት የተገኘው አንድ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የአገር ውስጥ ባለሀብትን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማስገባት ኮምሽኑ እንደ ሦስተኛ አማራጭ አድርጎ የወሰደው ደግሞ ውጤት የሚያመጣ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ እንደተናገሩት፣ ሦስተኛውና አስቸጋሪ ሆኖ የተገኘው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በራሳቸው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው አመርተው ወደ ውጭ እንዲልኩ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
እንዲህ ለማድረግ ያለው አማራጭ በጆንት ቬንቸር እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ሙከራ የተገኘው አንድ ድርጅት ብቻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ውጤታማ ነው ብለን የምንጠቅሰው እሱን ቢሆንም፣ ይህም ጊዜ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚገባ ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውጭ ግን በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክ የሚገጥማቸውን ችግር በመቅረፍ እየተሠራ ነው ይላሉ፡፡ በተለይ አንዳንድ የወጪ ንግድ አሠራር ላይ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ መመርያዎች እንዲሻሻሉላቸው በማድረግ ጭምር ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡