[ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲሉ ከልጃቸው ጋር እያወሩ ነው]
- አንተ ትምህርት ቤት አትሄድም እንዴ?
- ሙድ የለኝም ባክህ ዳዲ፡፡
- ምንድነው ያልከው?
- ሙዴ ተከንቷል አልኩህ እኮ ዳዲ፡፡
- ምንድነው የምታወራው?
- ምነው ዳዲ?
- ሙድ መከነት ምንድነው?
- የአራዳ ቋንቋ አታርፍም አይደል ዳዲ?
- ስማ አንተ ልጅ ከፀረ ልማት ኃይሎች ጋር መዋልህን አልተውክም ማለት ነው?
- ጀመረህ ደግሞ ዳዲ?
- ትምህርት ተጀምሯል አይደል እንዴ?
- በቃ ደብሮኛል ዳዲ፡፡
- ምን ሆነህ ነው የደበረህ?
- ሁሉም ነገር ነዋ ዳዲ፡፡
- ለትምህርትህ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ተደርጎልሃል አይደል እንዴ?
- አልተደረገልኝም ዳዲ፡፡
- ምን ጎደለህ ደግሞ?
- ብዙ ነገር ዳዲ፡፡
- እስቲ አንዱን ንገረኝ?
- በጣም የሚያሳፍር ነገር ነው የተደረገብኝ፡፡
- እኮ ምን?
- ክረምቱን እንዴት እንዳሳለፍኩት ረሳኸው?
- ክረምቱ ምን ሆነ?
- ያለፈውን ክረምት አስታውሰው እስኪ?
- ያለፈው ክረምት ምን ሆነ?
- ቫኬሽን የት ነበር የላከኝ?
- አውሮፓ ነበር አይደል የሄድከው?
- ምን ቫኬሽን ብቻ ሾፒንግ የት ነበር የላከኝ?
- ዱባይ ነዋ፡፡
- እሺ በዚህ ዓመት ቫኬሽን የት ነበረ?
- ገጠር ነዋ፣ አገርህንም ማወቅ አለብህ?
- ሾፒንግስ የት ነበር?
- ቦሌ ነዋ ያደረከው፣ ምን ችግር አለው?
- እኔ ይኼ መመርያ ምናምን የተባለው ነገር ከወጣ በኋላ ተቀያይረህብኛል፡፡
- ምን ሆኜ ነው የተቀያየርኩት?
- ባለፈው ዓመት ትምህርት ቤት በምንድን ነበር የምሄደው?
- በምንድን ነበር የምትሄደው?
- ሰኞ በነጭ ቪ8 ከሄድኩ፣ ማክሰኞ በጥቁሩ ነበር የምሄደው፡፡
- እሺ፡፡
- ረቡዕ በሲልቨር ቪ8 ከሄድኩ፣ ሐሙስ በመርሴዲስ ነበር፡፡
- እሺ…
- ዓርብ ደግሞ በሀመሩ ነበር፡፡
- አሁንስ?
- አሁንማ ከሰኞ እስከ ዓርብ በስኩል ባስ ነው የምመላለሰው፡፡
- ለመሆኑ አንተ ተማሪ ነህ የመኪና ነጋዴ?
- አንተው እኮ ነው ያስለመድከኝ?
- ምን ላድርግህ ታዲያ?
- እኔ እኮ ሳይኮሎጂካሊም ተጎዳሁ፤ እንዴት ብዬ ነው ከሌሎቹ ተማሪዎች ጋር አብሬ የምሄደው?
- ከሌሎቹ ተማሪዎች ጋር አብረህ ብትሄድ ምን ችግር አለው?
- እኔ የሚኒስትር ልጅ አይደለሁም እንዴ?
- እኔ እኮ ሚኒስትር የሆንኩት ሕዝብ ለማገልገል ነው፡፡
- ሕዝብ አገልግለህ ነው ፎቅ የሠራኸው?
- እ…
- ይኼን ሁሉ ቤት የሠራኸው ሕዝብ በማገልገል ነው?
- ምን አልክ አንተ?
- ለነገሩ አንተ ሕዝብ ማገልገል ሳይሆን የምትወደው…
- እ…
- በሕዝብ መገልገል ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር በስልክ እያወሩ ነው]
- በቃ እኔ እኮ ታገትኩ?
- ቤት ውስጥ አሸባሪዎች ገቡ እንዴ?
- ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እኮ አልቻልኩም?
- የምን እንቅስቃሴ ነው?
- ስማ በዓል በመጣ ቁጥር የምሠራውን ሥራ ረሳኸው እንዴ?
- ሴትዮ አሁን ጊዜው ጥሩ አይደለም፡፡
- እና እጅና እግሬን አጣምሬ ቁጭ ልበል?
- እንደዚያማ መሆን የለበትም፡፡
- ለምንድን ነው ግራ የምታጋባኝ?
- ግራ መጋባትን ምን አመጣው?
- ልንቀሳቀስ ስልህ ጊዜው ጥሩ አይደለም ትለኛለህ፤ ልቀመጥ ስልህ ደግሞ እንደዛ መሆን የለበትም ትለኛለህ፡፡
- እንደዚያ ያልኩሽ እኮ ዓይኖች ሁሉ እኛ ላይ ስለሆኑ ነው፡፡
- ምን ተሻለ ታዲያ?
- መጠንቀቅ አለብን፡፡
- ታዲያ ተጠንቅቀን መሥራት አንችልም?
- ተጠንቅቀን መሥራት ማለት ምን ማለት ነው?
- የማያስታውቅ ሥራ መሥራት ነዋ፡፡
- ስሚ እንደ እኔ እንደ እኔ አንቺ ዝም ብለሽ ብትሄጂ ይሻላል፡፡
- የት?
- ዱባይም ምናምን ቢሆን ነዋ፡፡
- ስማ ሰውዬ እኔ ልጆቼን ጥዬ የትም መሄድ አልፈልግም፡፡
- እሱን እንኳ ተይው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ቂሊንጦ ስትገቢ ልጆችሽን ጥለሽ አይደል እንዴ?
- እውነቱን እናውራ ከተባለማ ከእኔ ይልቅ አንተ ነህ ለቂሊንጦ ቅርብ፡፡
- አብዛኛው ነገር በአንቺ ስም መሆኑን ረሳሽው እንዴ?
- ታዲያ እኔ ባለሥልጣን አይደለሁ፤ ግፋ ቢል ንብረቴን ያግዳሉ እንጂ አያስሩኝም፡፡ ባለሥልጣን ስላልሆንኩ፣ ቢዝነስ መሥራት መብቴ መስሎኝ?
- ሙስና የግል ሴክተሩም እንደሚነካ መቼም ታውቂያለሽ፡፡
- እኔን አይመለከተኝም አልኩህ፡፡
- አሁን ደግሞ ዋና ትኩረትቸው በባለሥልጣናት ዙሪያ ያሉ ሰዎች ላይ ነው፡፡
- እያስፈራራኸኝ ነው?
- ለማንኛውም ወደ ዱባይ ብትሄጂ ጥሩ ነው፡፡
- ስማ እኔ የመጣብኝን እቀበላለሁ፡፡
- እስርም ቢሆን?
- ለምን እታሰራለሁ?
- ያልተገባ ሀብት አካብተሻል ተብለሽ ነዋ፡፡
- በቃ እንደሌሎቹ በስሜ ያለን ሀብት ሸጣችሁ ውሰዱት ብሎ መገላገል ነዋ፡፡
- አሁን አንቺን በዛ ይምሩሻል ብለሽ ነው፡፡
- እኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሳውቀው ምስኪንና መሃሪ ሕዝብ ነው፡፡
- ለዚያ ነው እንደዚህ ያለ ይሉንታ የምትበይው?
- አንተም ከመቼ ጀምሮ ነው ለሕዝቡ ተሟጋች የሆንከው?
- ሕዝብ ከተነሳብሽ ጥሩ አይደለም ብዬ ነው፡፡
- ምን አድርጊ እያልከኝ ነው?
- በቃ ለጊዜው ከአገር ውጪ፡፡
- ከዱባይ ግን ለምን ወደ ቻይና አልሄድም?
- ለምን?
- በዛው ዕቃ አስጭናለኋ፡፡
- ምን ዓይነት ዕቃ?
- በቃ ብዙ ዓይን ውስጥ የማይከት ዕቃ፡፡
- እኮ ምንድነው?
- ለምሳሌ ርችት፡፡
- ርችት ምን ያደርግልሻል?
- በቃ ሰው በየልደቱም፣ በየበዓሉም ይተኩሰዋላ፡፡
- ጥሩ ዕቃ አይመስለኝም፡፡
- ለምን?
- ሰው እንደድሮው ለርችት ቦታ መስጠት አቁሟል፡፡
- ለምን ተብሎ?
- መንግሥት በየቦታው እንደ ርችት የሚያፈነዳው ነገር ስላለ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ትራንስፎርመር!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማን ልበል?
- ወዳጅዎት ነኝ ከአሜሪካ፡፡
- ዛሬ ከየት ተገኘህ?
- ሁሌም ሲናፍቁኝ እኮ እደውላለሁ፡፡
- ለመስቀል በግ መግዣ ልከህልኝ ነው?
- ባለሥልጣን ስጦታ መቀበል ይችላል እንዴ?
- ምን ችግር አለው?
- ያው እዚህ አሜሪካ ባለሥልጣናት ስጦታ መቀበል ስለማይችሉ ነው፡፡
- አሁን በግ ስጦታ መሆኗ ነው?
- ለነገሩ እርስዎ ፎቅ ለምደው በግ ምንም ናት፡፡
- ስማ እርሱ ድሮ ቀረ፡፡
- እንዴት?
- አሁን እንኳን ፎቅ በግ የሚሰጥ የለም፡፡
- ዛሬ እንኳን የደወልኩት የዚህች አገር ጉድ ማለቂያው መቼ ይሆን ለማለት ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ክቡር ሚኒስትር የሰማሁትን ነገር ከእርስዎ ለማጣራት ነው የደወልኩት፡፡
- እኮ ምን ሰምተህ ነው?
- ሚዲያ ላይ የሚወራው እውነት ነው?
- ስለግጭቱ ነው?
- እሱማ እውነት መሆኑን እናንተም ተናግራችኋል፡፡
- ታዲያ ምን ሰምተህ ነው?
- ስለስኳር የሚወራው ወሬ፡፡
- ምን አወሩ ደግሞ?
- ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገር ስኳር ኤክስፖርት አድርጋ ነበር አሉ፡፡
- ታዲያ ኤክስፖርት ማድረግ ምን ችግር አለው?
- የራሷ አሮባት የጎረቤቷን ታማስላለች አሉ፡፡
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- አገሪቷ ውስጥ ስኳር የሚባል ነገር ጠፍቶ በብቸኝነት የሚገኘው ስኳር በሽታ ነው ይባላል፡፡
- ስማ አሁንም ከእነዚያ ፀረ ልማት ኃይሎች ጋር ነው አይደል የምትውለው?
- እኔ የምለው ክቡር ሚኒስትር፣ ኢምፖርት የተደረገውን ነው መልሳችሁ ኤክስፖርት የምታደርጉት?
- ኢምፖርት ኤክስፖርት ሲባል አልሰማህም?
- ኪኪኪ…
- ምን ያስቅሃል?
- ለነገሩ አገሪቷን በግምት እንደምትመሯት ይታወቃል፡፡
- ምን?
- አገሪቷ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆና እናንተ ለጎረቤት አገሮች ኃይል ትልካላችሁ፡፡
- ሰውዬ ከአገሪቷ የኤክስፖርት ፖሊሲ ጋር ችግር አለብህ?
- እውነት አንዳንዴ ሳስባችሁ እንኳን አገር ቤተሰብም በቅጡ መምራት የምትችሉ አይመስለኝም፡፡
- ለመሳደብ ነው እንዴ የደወልከው?
- ለነገሩ የደወልኩት ስኳሩ ጠረፍ ላይ መያዙ አስገርሞኝ ነው፡፡
- ምኑ ነው የሚያስገርመው?
- ስኳሩን አስይዛችሁ…
- እ…
- የላሱትን ማስመለጣችሁ!
- Advertisement -
[ክቡር ሚኒስትሩ ማታ ቤታቸው ደመራ እየተበራ አማካሪያቸው መጣ]
- እንዴት መጣህ አንተ?
- ክቡር ሚኒስትር ደመራ እኮ ከዓመት ዓመት እርስዎ ቤት ነው የማበራው?
- ዘንድሮ መቼ ጠራሁህ ታዲያ?
- ልማዴን ለማድረስ ነበር፣ ግን አንድ ነገር ግር ብሎኛል፡፡
- ምንድነው እሱ?
- በር ላይ ብዙ መኪናም የለም፤ በዛ ላይ እንደ ድሮው ሰውም የለም፤ እርስዎ ፈቃድ ያስፈልግዎታል እንዴ?
- የምን ፈቃድ?
- አይ አሁን አሁን ለአልበም ምርቃት፣ ለሠልፍ ምናምን ፈቃድ ስለሚያስፈልግ፣ እርስዎ ቤት ያነሰው ስላላስፈቀዱ ነው ብዬ ነው፡፡
- ስማ እንደ ድሮው ድግስ መደገስ እንደማልችል ታውቃለህ?
- ለነገሩ ሰው እኮ ክቡር ሚኒስትሩ ደመራ የሚያበሩት እስር ቤት ነው እያለ ነው የሚያወራው፡፡
- ታዲያ አንተ እዚህ ምን ልታደርግ መጣህ?
- ልተነብይ ነዋ፡፡
- ምንድነው የምትተነብየው?
- ወደ ምሥራቅ ከወደቀ ቂሊንጦ፣ ወደ ምዕራብ ከሆነ ደዴሳ፣ ወደ ሰሜን ከሆነ ደግሞ ሸዋሮቢት፣ ወደ ደቡብ ከሆነ ደግሞ ዝዋይ ነው የሚገቡት የሚለውን ነዋ፡፡
- እኔ ጠፋሁ?
- የሚሻለው መፀለይ ነው፡፡
- ለምኑ?
- ቅርቡ እንዲደርስዎት!
[ደመራው ወደ ምሥራቅ ወደቀ]
- በእውነት ክቡር ሚኒስትር ፀሎትዎ ተሰምቷል፡፡
- እንዴት?
- የወደቀው ወዴት እንደሆነ አዩት?
- ወዴት ነው?
- ወደ ቂሊንጦ!