Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው አራት የፌዴራል ዳኞችን ለማሰናበት የቀረቡለትን ሰነዶች ከድምፀ ተአቅቦ ጋር አፀደቀ

ፓርላማው አራት የፌዴራል ዳኞችን ለማሰናበት የቀረቡለትን ሰነዶች ከድምፀ ተአቅቦ ጋር አፀደቀ

ቀን:

ኃላፊነታቸውን በሚገባ ለመወጣት ባለመቻልና ከፍተኛ የዲሲፕሊን ግድፈት ፈጽመዋል የተባሉ አራት የፌዴራል ከፍተኛና የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችን ስንብት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. አፀደቀ፡፡ ከተለመደው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በተለየ አጨቃጫቂ መሆኑ በተስተዋለበት የስንብት ውሳኔ ሐሳብ ብዙ ጥያቄዎች የተስተናገዱ ሲሆን፣ የውሳኔ ሐሳቡን አሥር አባላት በድምፀ ተአቅቦና አንድ አባል የተቃውሞ ድምፅ ሰጥተውበታል፡፡

የስንብት ውሳኔ ከተላለፈባቸው ዳኞች አንዱ አቶ ውሂብ ማሞ ገብረ መድኅን ናቸው፡፡ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት ተሹመው ሲሠሩ መቆየታቸውን፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ለፓርላማው ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ያስረዳል፡፡

የውሳኔ ሐሳቦችን በንባብ ያቀረቡት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ተስፋዬ ዳባ ነበሩ፡፡

      የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ያደረገውን ስብሰባና የደረሰበት ውሳኔ በመጥቀስ፣ አቶ ውሂብ በከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት በሠሩባቸው ጊዜያት ፈጽመውታል የተባለውን ዝርዝር የዲሲፕሊን ጉድለት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በዚህም መሠረት የዲሲፕሊን ክስና ማስረጃ ቀርቦባቸዋል ከተባሉ ጥሰቶች ውስጥ፣ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ዓቃቤ ሕግና የግል ተበዳይ በፍርድ ቤት በይግባኝ ችሎት ላይ ባልተገኙበት ውሳኔ አስተላልፈዋል የሚል ክስ በቅድሚያ ተጠቅሶባቸዋል፡፡ ክሱ፣ ‹‹የሥር ፍርድ ቤት ስምንት ዓመት የተወሰነበት እስረኛ ባቀረበው ይግባኝ ላይ ተበዳይ ቀርባ ቃሏን ቀይራለች በማለት፣ የተበዳይዋን የምስክርነት ቃል በመቅረፀ ድምፅ ሳይኖር፣ በመዝገብ ሳይሰፍርና ዓቃቤ ሕግ ሳይቀርብ በመዝገብ ላይ ሆን ብለው ተበዳይዋ ቃሏን እንደቀየረች በማስመሰል፣ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ግራና ቀኝ ተከራካሪዎች ባልቀረቡበት ሁኔታ እስረኛው በነፃ እንዲለቀቅ አድርገዋል፤›› ይላል፡፡

እንዲሁም በልደታና በአቃቂ ምድብ ችሎቶች ተመድበው ሲሠሩ ከ62 መዝገቦች በላይ ‹‹በአየር ላይ በመቅጠርና በእንጥልጥል ለረዥም ጊዜ በቀጠሮ ሳይወስኑ በመቅረት›› የሚልም ይገኝበታል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተጠቀሰባቸው ክስ የመንግሥትን ሥራን ካለማክበራቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ያለምክንያት በሥራ ገበታቸው እንደማይገኙ፣ በተለይም ከሰዓት በኋላ ሥራ ላይ እንደማይኖሩ ተጠቅሷል፡፡

አቶ ተስፋዬ የውሳኔ ሐሳቡን በንባብ ካቀረቡ በኋላ ለተነሱላቸው ተጨማሪ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ከአስገድዶ መድፈር ጋር የተጠቀሰውን ክስ በተመለከተ ተደፋሪዋ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች የ13 ዓመት ታዳጊ እንደነበረች ገልጸዋል፡፡

በሌሎች ሦስት የውሳኔ ሐሳቦች ስንብታቸው እንዲፀድቅ ለምክር ቤቱ ጉዳያቸው የቀረቡት የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው የተሾሙ ሦስት ዳኞች፣ ተመሳሳይ የዲሲፕሊንና የሥነ ምግባር ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡

እነዚህም ዳኞች ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር በዚሁ ምክር ቤት ሹመታቸው ፀድቆ ቃለ መሐላ ፈጽመው የነበሩት በድሬዳዋ ምድብ ችሎት ያስችሉ የነበሩት አቶ ዳግም መርጊያ፣ በየካ ምድብ ችሎት ያስችሉ የነበሩት ወ/ሪት ግሩም አጎናፍርና በአራዳ ምድብ ችሎት ያስችሉ የነበሩት ወ/ሪት ምሕረት ብርሃኔ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ ተመሳሳይ ክስ የቀረበባቸው እነዚሁ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች በሥራ ገበታ ባለመገኘት፣ በእጃቸው የነበሩ የመንግሥት ንብረቶች ሳያስረክቡና በፍርድ ቤቶች በቀጠሮ ላይ የሚገኙ መዛግብትን ጥለው በመሄዳቸውና ሕዝብን ለማገልገል የገቡትን ቃለ መሐላ ወደ ጎን በመተው፣ ‹‹የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም›› የሚሉ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡

ነገር ግን ‹‹የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም›› በሚለው ላይ ሦስቱም ዳኞች አንድ ዓመት እንኳ ማገልገል ባለመቻላቸው በርካታ ጥያቄዎች ከምክር ቤት አባላት ቀርበዋል፡፡ ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት አቶ ተስፋዬ፣ ዳኞቹ በምርመራ ወቅት ሊገኙ አለመቻላቸውንና ከአገር መውጣታቸውን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የዕለቱን የምክር ቤቱን ስብሳባ የመሩት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታየ ምናለ ጉዳዩ ግልጽ በመሆኑ ያንን ያህል ሊያከራክር ስለማይገባው፣ ወደ ድምፅ መስጠቱ መግባት ይሻላል የሚል ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን በተሰጡት ማብራሪያዎች ላይ ደስተኛ ያልመለሱት የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

ወ/ሮ ሽታዬ ብዛት ያላቸው ጠያቂዎች እጅ ሲያወጡ በቀረበው ውሳኔ ላይ ብቻ ተንተርሶ ወደ ማፅደቁ እንዲገባ ግፊት ያደረጉ ቢሆንም፣ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በመፈልፈል የምርመራ ሥራ ማከናወን የምክር ቤቱ ሥራ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ እዚህ ያለነው ነገሮችን እንዴት? ለምን? እያልን በጥልቀት ለመመርመር የሚያስችለን ሥልጣን ያለን አይመስለኝም፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ እኛ የወከልነው አካል ነው፡፡ መጣራት የሚገባውን የቤት ሥራም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን እሱ ይከታተላል፣ ያጣራል፡፡ እዚህ እናንተ የምታነሱዋቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ጉባዔው እየተከታተለ ያጣራል፡፡ እኛም በሪፖርት እንከታተላለን፤›› በማለት ወደ ውሳኔ እንደሚሄዱ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን አባላቱ ወደ ማጉረምረም ሲገቡ የአካሄድ ጥያቄ ያነሱት በምክር ቤቱ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ  አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ ‹‹በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ብቻ ውሳኔ ሰጥተን ብንቀጥል፣ ሌሎች መነሳት በሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔም ሆነ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመሆን በዝርዝር እንዲታይ፣ በአቶ ተስፋዬ በኩል በሪፖርት ቀርቦላቸው ቢያዩት ይሻላል፤›› በማለት ወደ ማፅደቁ ቢገባ እንደሚሻል ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

የእሳቸውንም ሐሳብ ተከትሎ የውሳኔ ሐሳቡን ወደ ማፅደቁ ተገብቷል፡፡ በዕለቱ 320 የሚሆኑ የምክር ቤት አባላት መገኘታቸው የተመዘገበ ሲሆን፣ በድምፅ መስጠቱ ሒደት ግን በአብላጫ ድምፅ የውሳኔ ሐሳቦቹ ፀድቀዋል፡፡ አሥር አባላት ድምፀ ተአቅቦ ሲያደርጉ፣ አንድ አባል የተቃውሞ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

የተሻሻለው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 684/2002 ከጉባዔው ሥልጣንና ተግባራት መካከል፣ በአንቀጽ 6(ሸ) ላይ ‹‹ውሳኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከሚፀድቅ ድረስ ዳኞችን ከሥራ ማገድ ይችላል፤›› ይላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...