Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ የኤክስፖርት ምርቶችን አገር ውስጥ አሽጎ መላክ ጀመረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን አገር ውስጥ አሽጎ መላክ ጀመረ፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለየብቻ እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ በማጓጓዝ፣ ወደቡ ላይ ምርቶችን በኮንቴይነር በማሸግ ኤክስፖርት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ይኼን አሠራር  በማስቀረት በቃሊቲ ጉምሩክ (ኮሜት) ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የኤክስፖርት ቡና በማሸግ መላክ ጀምሯል፡፡

ለዓመታት ይህ አሠራር በነበረበት በመቆየቱ የሎጂስቲክስ ባለሙያዎች የኤክስፖርት ምርቶችንና ኮንቴይነሮችን ለያይቶ ማጓጓዝን በተመለከተ መንግሥትን ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ አዲስ አበባ በሚገኘው ቃሊቲ ጉምሩክ ግቢ ውስጥ ቡናና የተለያዩ የግብርና ምርቶችን አሽጎ መላክ ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ የደረቅ ወደብና የተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት፣ ‹‹ከዚህ በኋላም በሐዋሳና በሌሎች ከተሞች እየተገነቡ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ፣ እንዲሁም በሞጆ ደረቅ ወደብ የኤክስፖርት ምርቶችን አሽጎ ለመላክ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ በ2001 ዓ.ም. ሥራውን በይፋ የጀመረውን የሞጆ ደረቅ ወደብ የኢትዮጵያ ዋነኛ የገቢና የወጪ ዕቃዎች ማዕከል (ሎጂስቲክስ ሀብ) ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አቶ ደሳለኝ የሞጆ ደረቅ ወደብን የኢትዮጵያ የሎጂስቲክ ማዕከል ለማድረግ ለተያዘው ግዙፍ ዕቅድ የዓለም ባንክ ቦርድ 150 ሚሊዮን ዶላር ብድር መፍቀዱን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ሰሞኑን 50 ሚሊዮን ዶላር በኢንተርፕራይዙ አካውንት ገብቷል፤›› ሲሉ አቶ ደሳለኝ አረጋግጠዋል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ አሁን ካለበት 60 ሔክታር መሬት ወደ 140 ሔክታር የሚያሳድጉ ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ አበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና የሥጋ ውጤቶችን ለማጓጓዝ አስፈላጊ የሆኑ የማቆያ ማቀዝቀዣዎች፣ ተርሚናሎችና መጋዘኖች፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውታሮች ይገነባሉ ተብሏል፡፡

እነዚህ ግንባታዎች የሞጆ ደረቅ ወደብ ትኩረት አድርጎ ከቆየው ገቢ ንግድ ወደ ወጪ ንግድም እንዲያሰፋ እንደሚያደርጉት አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች