ዶሮ በምድር ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወፍ ዘር ሳይሆን አይቀርም። በአጠቃላይ ከ13 ቢልዮን የሚበልጡ ዶሮዎች እንዳሉ ይገመታል:: እንዲሁም ሥጋው በጣም ተወዳጅ በመሆኑ በየዓመቱ ከ33 ቢልዮን ኪሎ ግራም በላይ ለምግብነት ይውላል። ከዚህም በተጨማሪ ዶሮዎች በዓለም ዙሪያ በአንድ ዓመት ውስጥ 600 ቢልዮን ገደማ እንቁላሎችን ይጥላሉ።
ዶሮ በምዕራባውያን አገሮች በብዛት የሚገኝ ሲሆን ዋጋውም ርካሽ ነው። ከአሠርታት በፊት በአሜሪካ እጩ ተወዳዳሪዎች ለምርጫ በሚፎካከሩበት ጊዜ በምርጫው ካሸነፉ ዶሮ በገፍ ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ለመራጮቻቸው ቃል ይገቡ ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ ዶሮ እንደ ቅንጦት ምግብ መታየቱ ወይም የጥቂቶች ምግብ ብቻ መሆኑ ቀርቷል። በዓይነቱ ልዩ የሆነው ይህ የወፍ ዘር እንዲህ በብዛት እንዲገኝ እንዲሁም በጣም ተወዳጅ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው?
ሰው ዶሮን በቀላሉ ማልመድ እንደሚችል ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም። እንዲያውም ከ2, 000 ዓመታት ገደማ በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ዶሮ ጫጩቶቿን እንዴት ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስባቸው ተናግሯል። ይህን ምሳሌ መጠቀሙ ሰዎች ባጠቃላይ ስለ ዶሮ በደንብ ያውቁ እንደነበር ያሳያል። ሆኖም ዶሮና እንቁላል ለገበያ ለማቅረብ ሲባል በሰፊው የዶሮ እርባታ የተጀመረው ከ19ኛው መቶ ዘመን በኋላ ነው።
የዶሮ ሥጋ ዛሬ በብዙዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ምግብ ነው። የከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ በሚልዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ለራሳቸውም ሆነ ለገበያ ለማቅረብ ዶሮ ያረባሉ። እንዲያውም የዶሮን ያህል በተለያዩ የአየር ጠባዮች መርባት የሚችል የግብርና እንስሳ የለም ማለት ይቻላል። ብዙ አገሮች ለራሳቸው አገር የአየር ጠባይ የሚስማሙና ጥሩ ምርት የሚሰጡ የዶሮ ዝርያዎችን አራብተዋል። ከእነዚህ መካከል የአውስትራሊያው አውስትራሎፕ፣ መጀመሪያ በሜድትራኒያን የተገኘውና አሁን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በብዛት ያለው ሌግሆርን፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚረቡት ኒው ሃምፕሻየር፣ ፕላይማውዝ ሮክ፣ ሮሜ አይላንድ ሬድ እንዲሁም ውያንዶቴ፤ የእንግሊዞቹ ኮርኒሽ፣ ኦርፒንግቶን እና ሱሴክስ የሚባሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
(ንቁ!—2001)