Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እሰየው አገር በቀል ተቋራጮች አብረው መሥራትን አመጡ – በሽርክና አመለጡ!

ከአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ውስጥ ለመሠረተ ልማት የሚውለው ገንዘብ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ለመንገድ፣ ለግድብ፣ ለመስኖ፣ ለፋብሪካ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ፣ ለሕንፃ፣ ለቤቶች ግንባታ ለባቡርና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች የሚወፈሰው ገንዘብ ከአገሪቱ የፋይናንስ አቅም አንፃር እጅግ በርካታ ከመሆኑ አንፃር፣ በዚህ ዘርፍ የሚሽከረከሩ ተዋንናዎችም በርካቶች መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ግንባታዎቹን የሚያከናውኑት የውጭና የአገር ውስጥ ተቋራጮች ይጠቀሳሉ፡፡

የመንግሥትን ያህል አይሁን እንጂ በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ ግንባታዎችም ቢሆኑ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተዋንያኖችን በብዛት ያሳትፋሉ፡፡ በርካታ ገንዘብም ወጭ ይደረጋል፡፡ የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የሚያጣቅሱ የመንግሥት መረጃዎች ይፋ ተደርገዋል፡፡

እንዲህ እየጨመረና እየፈረጠመ በመጣው የግንባታ ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ አገር በቀል ተቋራጮችን በሚፈለገው ብዛትና ጥራት ማፍራት ግን አልተቻለም፡፡ የአብዛኛዎቹ የአገሪቱ ኩባንያዎች አቅምና ብቃት ገና አልጎለበተም፡፡ እርግጥ አብዛኞቹ ከተመሠረቱ ከ20 ዓመታት ያነሰ ዕድሜ ያስቆጠሩ መሆናቸው አንዱ መንስዔ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ስለሆነም ከእነርሱ የተሻለ ልምድ ያላቸው የውጭ ተቋራጮች ከሰፊው የአገሪቱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥ በርካቶቹ በተለይም ትላልቅ የሚባሉ ፕሮጀክቶችን እንዲረከቡ ዕድሉን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ቀስ በቀስ ግን ጥቂት የማይባሉ አገር በቀል ተቋራጮች የግንባታ ሥራዎችን ማግኘታቸው አይካድም፡፡ መንግሥትም በእነሱ አቅም የሚሠሩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን እንዲያገኙ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ እስከችግሮቻቸውም ቢሆን የጨረታ መሥፈርቶችን እየከለሰ ሥራዎችን እንዲወስዱ ያደርግባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ይህም ተደርጎ ከውጮቹ ጋር ለመወዳደር ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚጠቀሰው በፋይናንስ፣ በሠለጠነ የሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት ግብዓቶች አቅማቸውን ገንብተው ትልልቅ ሥራዎችን እንዲረከቡ ለማስቻል ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ብዙም የተሳካ ባይሆን ጥቂት የማይባሉት የአቅማቸውን ሞክረዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ባይባልም አሠራራቸውን ያሻሻሉ ጥቂት አይደሉም፡፡

ለብቻቸው መሥራት የማይችሏቸውን ሥራዎች በጋራ መሥራት የሚችሉባቸው ዕድሎች ስላሉ በዚህ ለመጠቀም መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ በትልልቅ የግንባታ ሥራዎች ውስጥ የሚጠየቀውን ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት (ተርንኦቨር) መጠን አሟልተው በመገኘት የውጮቹ ይቀራመቷቸው የነበሩ ፕሮጀክቶችን ለመረከብ በቅርቡ በጥምረት ተጫርተው የሁለት መንገድ ሥራዎችን ያሸነፉት የአገር ውስጥ ተቋራጮች ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡

የውጭ ተቋራጮች በትሪሊዮን ብሮች የሚገመቱ ግንባታዎች ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የያዙበት ምክንያትም መተባበራቸው ነው፡፡ የትብብር መንፈሱ ብዙ የሚባልለት ቢሆንም በአጋጣሚው ተጠቅመዋል፡፡ አገር በቀል ተቋራጮችም ይህ እንደሚጠቅማቸው ተጣምረው በመሥራት ውጤት ማሳየት አለባቸው፡፡

በሽርክና የተጣመሩት አፍሮ ጽዮንና ራማ ኮንስትራክሽን የተባሉት ሁለቱ አገር በቀል ተቋራጮች የቻይኖቹን አሸንፈው ሥራ መረከብ የቻሉት በጋራ በመቅረባቸው ነው፡፡ በግል ያቃታቸውን በጋራ በመሥራት ውጤት እንደሚገኝ አሳይተዋል፡፡ ይህ ለዘርፉ ትልቅ መነቃቃት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በቀላሉ የሚሠሩ ግንባታዎችን ተረክቦ ለመሥራት አስገንቢዎች የሚያወጡትን መሥፈርት ማሟላት እየተሳናቸው በርካታ ያጧቸው ሥራዎች መኖራቸው አሌ አይባልም፡፡

ለማንኛውም በጥምረት የቀረቡት ድርጅቶች አሸናፊ የመሆናቸው ፋይዳው ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶችን ያሸነፉት ሁለቱ ተቋራጮች በጥምረት ባይቀርቡ ኑሮ፣ ከእነሱ ይልቅ ከፍተኛ ዋጋ የጠየቁበትን ጨረታ የቻይና ተቋራጮች መውሰዳቸው አይቀሬ ነበር፡፡

በቻይኖቹና በአገር በቀሎቹ መካከል የታየው የዋጋ ልዩነት ሰፊ ነው፡፡ ለሁለት መንገዶች በአሸናፊዎቹና በተወዳዳሪዎቻቸው መካከል ከ300 ሚሊዮን እስከ አንድ ቢሊዮን የሚደርስ የዋጋ ልዩነት ታይቷል፡፡ ይህ ማለት በአሸናፊዎችና በተወዳዳሪዎቹ መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት ሌላ መንገድ ሊያሠራ የሚችል ነው፡፡ ይህንን ያህል ለውጭ ኩባንያዎች ሥራና ማስኬጃና ክፍያ ሊውል የነበረን ገንዘብ ማዳን ተችሏል፡፡

በትንሳኤ በዓል ዋዜማ ሰሞን የሰማነው ዜና ለዘርፉ ትንሳዔ ሊባል የሚችል ነው፡፡ የሁለቱ አገር በቀል ኩባንያዎች ጥምረት የበለጠ ትርጉም የሚኖረው ግን ተጣማሪዎቹ በጋራ የሚሠሩት ሥራ በአግባቡ ሲከናወን ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የዘርፉ ባለቤቶች በዚህ መልኩ በመሥራት የሚገኘውን ውጤት ከሥር ከሥር በመከታተልና በማጥናት ተጣምሮ መሥራትን ለማበረታታት ይህንኑ የሚደግፉ አሠራሮችን በማስፋፋት አገራዊ ጠቀሜታን ማስፋፋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ብቻም ሳይሆን በሌሎችም ቢዝነሶች ውስጥ ምሳሌ በመሆን አገልግሎታቸው ከአገር ውጭ እንዲወጣ ለማድረግ መንገድ ይከፍታልና ተባብሮ መሥራት ለተሻለ አገልግሎትና ጥቅም እንነሳ ያሰኛል፡፡

ይህንን መልካም ጅምር ለማጎልበት ደግሞ የግንባታ ሥራዎችን የሚያወጡ ተቋማት የጨረታ መሥፈርቶቻቸውን በጥምረት ቀርበው ለመሥራት የሚጠይቁትን አገር በቀል ተቋማት ሊያበረታታ በሚችል መልክ መቃኘቱ የጎላ ጠቀሜታ አለው፡፡ ተቋራጮችም የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ሳይሉ አጋጣሚውን ለመጠቀም ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ከልማዳዊ አሠራር ተላቀው ዘመናዊ አሠራር በመከተል ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪ ለመሆን ይተባበሩ፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት