Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜና ቤሊ ዳንስ

የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜና ቤሊ ዳንስ

ቀን:

በመስታወት ግርግዳ በተሸፈነው ክፍል ዓረብኛ ሙዚቃ ይንቆረቆራል፡፡ ከመስታወቱ ፊት ለፊት የቆሙት ሴቶች የሙዚቃውን ምት እየተከተሉ ሰውነታቸውን ያንቀሳቅሳሉ፡፡ እጆቻቸውን ዘርግተው ከወገባቸው ወደ ግራና ቀኝ ይወዛወዛሉ፡፡ የሴቶቹን ውዝዋዜ የምትመራው ካናዳዊቷ የቤሊ ዳንስ መምህርት ናይላ የደረት፣ የወገብና የዳሌ እንቅስቃሴ ምን መምሰል እንዳለበት ታስረዳለች፡፡ ሴቶቹም መመሪያዋን እየተከተሉ ይተገብራሉ፡፡ ሌሎችም ዓረብኛ ሙዚቃዎች ተከታትለው ሲደመጡ ሴቶቹ እጃቸውን ከትከሻቸው ከፍ በማድረግ፣ በእግራቸው ጣት በመቆም ወገባቸውን በየአቅጣጫው በስልት ያንቀሳቅሳሉ፡፡ ሙዚቃውን ለማድመጥ ሲደንሱ ፊታቸው ላይ ተመስጦ ይስተዋላል፡፡ ሴቶቹን ያገኘናቸው ጁቬንቱስ ክለብ ውስጥ ቤሊ ዳንስ ሲማሩ ነበር፡፡ ናይላ ከሃያ ዓመት በፊት ዳንሱን ከተማረች ጀምሮ በካናዳና ፈረንሣይ በማስተማር ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ ስልቱ ወደማይዘወተርበት ኢትዮጵያ የመጣችው ከቀድሞ ተማሪዎቿ አንዷ ክሪስቴል ባደረገችላት ግብዣ ነበር፡፡ ክሪስቴል ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ፈርመንቴሽን ለምግብ የኒውትረንት ይዘት ላይ ያለውን አስተዋጽኦ ለማጥናት ሲሆን፣ ምርምሯ በዋነኛነት በእንጀራ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከፉድ ሳይንስ ተመራማሪነት ጎን ለጎን ቤሊ ዳንሰኛ የሆነችው ክሪስቴል፣ ከአምስት ዓመቷ ጀምሮ ባሌ ዳንስ ትማር ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ ቤሊ ዳንስ ተምራ ለምርምር በምትሄድባቸው አገሮች ታስተምር ጀመር፡፡ የተለያዩ የቤሊ ዳንስ ስልቶችን ካስተሟራት መምህራን መካከል ከናይላ ጋር ትሩፕ ኬሊያፕ ቤሊትራይብ የተባለ የዳንስ ቡድን መሥርተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ዳንሰኞቹ ቤሊ ዳንስ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲዘወተር በማሰብ ነበር ከወራት በፊት ሥልጠና መስጠት የጀመሩት፡፡ ሁለቱ ቤሊ ዳንስ ሲያስተምሩ የኢትዮጵያን ባህላዊ ውዝዋዜ እንዲያስተምሯቸው ኢትዮከለርን እንደጋበዙም ክሪስቴል ትናገራለች፡፡ ጉራግኛ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ኦሮምኛና ሌሎችም ውዝዋዜዎችን ተምረው ከቤሊ ዳንስ ጋር ለማዋሃድ መሞከራቸውንም ትገልጻለች፡፡ ‹‹ቤሊ ዳንስን የምወደው ለዳንሱ በሚመረጠው ሙዚቃ፣ ልብስና ሙዚቃው ተደምጦ ሰውነት በሚታዘዝበት መንገድም ነው፤›› የምትለው ዳንሰኛዋ፤ የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜና ቤሊ ዳንስ የተራራቁ እንቅስቃሴዎች ቢሆኑም በሙከራዊ መንገድ ጎን ለጎን ለማስኬድ ሞክረዋል፡፡ ናይላ እንደምትናገረው፣ ከኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜዎች መካከል እንደ ጉራግኛ ያሉ ፈጣን የሰውነት እንቅስቃሴና ጉልበት የሚጠይቁ ውዝዋዜዎችን ለሰስ ካለው ቤሊ ዳንስ ጋር ማስኬድ ከባድ ነው፡፡ ‹‹ከፕሮፌሽናልና ጀማሪ ኢትዮጵያውያን ተወዛዋዦች ጋር በጥምረት ስንሠራ በሁለት ዳንሶች መካከል ያለውን ልዩነት አስተውለናል፡፡ ዳንሶቹ ቢለያዩም በጥምረት ለማስኬድ ያደረግነው ጥረት አስደሳች ነው፤›› ትላለች፡፡ ዳንሱን መማር ለሚፈልጉ ግለሰቦች ስለ ሥልጠናው በማኅበረሰብ ድረ ገጽ በማስተዋወቅ ባስተማሩባቸው ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ከተማሪዎቻቸው ተስፋ ሰጪ ምላሽ እንዳገኙም ትገልጻለች፡፡ በአንድ አገር ወይም ማኅበረሰብ የሚዘወተር ዳንስ ከአካባቢው ባህል ጋር ተሳስሮ ከኅብረተሰቡ መገለጫዎች አንዱ ይሆናል፡፡ እንደየማኅበረሰቡ አኗኗር አንዳች መልዕክት ለማስተላለፍ ወይም ከተለያዩ ክንውኖች ጋር ተያይዞም ይካሄዳል፡፡ ዛሬ ዛሬ መነሻቸው አንድ አካባቢ የሆነ ስልቶች በሌሎችም መዘውተራቸው እየተለመደ ነው፡፡ በዋነኛነት በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚዘወተረው ቤሊ ዳንስም በሙሉም ይሁን በከፊል ከሌሎች ዳንስ ስልቶች ጋር ይዋሃዳል፡፡ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያው ባህላዊ ውዝዋዜ አንፃር እየታየ ነው፡፡ ክሪስቴል ‹‹ቤሊ ዳንስ ማራኪ ነው፡፡ ማንኛዋም ሴት ውስጧ ያለውን ስሜት በማውጣት ራሷን ልትገልጽበት ትችላለች፤›› ትላለች፡፡ ዳንሱ በሰከነ ግላዊ መንገድ የሚከናወን መሆኑ በዓለም ላይ በስፋት እየተሰራጨ ለመምጣቱና ለመወደዱም ምክንያት መሆኑን ታምናለች፡፡ ናይላ በበኩሏ የዓለም ሕዝቦች እንደ አንድ መንደር ነዋሪዎች በተቀራረቡበት በዚህ ዘመን አንድ ባህል የሚገለጽበት የዳንስ ስልት ከሌላው ጋር መዋሃዱ አይቀሬ ነው ትላለች፡፡ ቤሊ ዳንስን በፕሮፌሽናል ደረጃ ለመደነስ ጊዜ ቢወስድም በአጭር ጊዜ መሠረታዊ የዳንሱን እንቅስቃሴ መማር ይቻላል፡፡ ዳንሱ ደረት፣ እጅና ዳሌን አንድ ላይ በማንቀሳቀስ የሚከናወን ሲሆን፣ በግብፅ፣ በቱርክና በሌሎችም አገሮች ልዩ ልዩ የቤሊ ዳንሶች አሉ፡፡ ክሪስቴልም በእንጀራ ዙሪያ እየሠራች ያለው ጥናት ሲጠናቀቅ ወደ ግብፅ በማቅናት የአገሪቱን ቤሊ ዳንስ በቅርበት የማጥናት ዕቅድ እንዳላት ትናገራለች፡፡ ዳንሰኞቹ በኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ የሚንፀባረቁ ባህላዊ እሴቶች እንዳሉ ሁሉ በቤሊ ዳንስ የሚስተዋሉ እንቅስቃሴዎችም የሚያስተላልፉት መልዕክት እንዳለ ይናገራሉ፡፡ የዳንሱ ጽንሰ ሐሳብ በኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ በቀጥታ ባይታይም፣ በሁለቱ እንቅስቃሴዎች መካከል ድልድይ መፍጠር እንደሚቻልም ያክላሉ፡፡ በተያያዥ የሚያነሱት ቤሊ ዳንስ በማንኛውም ሴት የሚደነስ እንጂ በሰውነት ቅርፅ ወይም በዳንስ ችሎታ የማይገደብ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ዳንሱ በተለምዶ ውበት የሚገለጽበትን መንገድ የሚለውጥ ሁሉንም የሚያሳትፍ ነው፤›› ትላለች ናይላ፡፡ ዳንሰኞቹ ከቤሊ ዳንስ በተጨማሪ የባሌና ሌሎችም ስልቶች ተሞክሮ ቢኖራቸውም፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ውዝዋዜ በሙዚቃ ክሊፖች ከመመልከት ያለፈ ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጧቸው ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ፈረንሣውያንም ከተለያየ ባህል እንደመምጣታቸው አንዳቸው የሚያውቁት ለሌላው እንግዳ ነበር፡፡ በጊዜ ሒደት ግን የጋራቸው በሆነው የዳንስ ቋንቋ እየተግባቡ የተለያዩ ስልቶችን እያጣመሩ እንደሆነ ናይላ ትናገራለች፡፡ ከኢትዮ ከለር ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ ስለ ኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ሙሉ በሙሉ ባያውቁም ያገኙትን ትምህርት ተመርኩዘው ውዝዋዜውን ከቤሊ ዳንስ ጋር አጣምሮ በመሥራቱ እንደሚገፉበት የሚናገሩት ዳንሰኞቹ፣ ባሳለፍነው ቅዳሜ በጁቬንቱስ ክለብ ቤሊ ዳንስና የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ትርዒት አቅርበው ነበር፡፡ የቤሊ ዳንስ ትርዒት የሚቀርብባቸው መድረኮች ባለመኖራቸው ትርዒቱን ብዙዎች ተከታትለውታል፡፡ ክሪስቴል እንደምትለው፣ ትርዒቱን ሲያቀርቡ የተመለከቷቸው ባህላዊ ተወዛዋዦች ሁለቱን ስልቶች በማዳቀል መሥራት እንደሚፈልጉ ገልጸውላቸዋል፡፡ ‹‹በተለይ አፋር አካባቢ ያለውን ባህላዊ ውዝዋዜ ከቤሊ ዳንስ ጋር ለማጣመር ይቀላል፡፡ ለወደፊት በስፋት የምንሠራበትም ይሆናል፤›› ትላለች፡፡ ከሁለት አሠርታት በላይ በዳንሰኝነት የዘለቁት ሁለቱ ዳንሰኞች ስልቱ ሴቶችን ግርማ ሞገሥ የሚያላብስ፣ ውስጣዊ ስሜትን በእንቅስቃሴ የሚገልጽና አዝናኝ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሁለቱም ከዳንሰኝነት በተጨማሪ በሌሎች ሙያዎችም ቢሰማሩም ለዳንሱ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ ይናገራሉ፡፡ ክሪስቴል ከኒውትሪሽን ጋር የተያያዙ ምርምሮችን በተለያዩ አገሮች እየተዘዋወረች ስትሠራ፣ ናይላ በባህላዊ ሕክምና ዘርፍ ተሰማርታለች፡፡ ‹‹ስሜታችንን በጥልቀት እንገልጽበታለን፤›› የሚሉት ቤሊ ዳንስ ደግሞ ያጣምራቸዋል፡፡ ዳንሱ ከሚታይባቸው መንገዶች መካከል በአዕምሮና በሰውነት ያለ ትስስር ስሜት በነፃነት የሚገለጽበት ይገኝበታል፡፡ በእርግጥ የዳንሱን ጥበብ ባለመገንዘብ ዳንሱን ሴቶች ወንዶችን የሚያዝናኑበት መንገድ የማድረግ ነገር መኖሩን የምትገልጸው በሥልጠናው ወቅት ያገኘናት ፈረንሣዊ ጋዜጠኛ ኤዛቤል ናት፡፡ ‹‹ሴቶች በተናጠልም ይሁን በቡድን ቤሊ ሲደንሱ ራሳቸውን በጥልቅ ይገልጻሉ፡፡ ባለማወቅ ዳንሱን በአሉታዊ መንገድ የሚመለከቱት አሉ፤›› ትላለች፡፡ የቤሊ ዳንስ እንቅስቃሴ ሴቶች ከስሜታቸውና ከሰውነታቸው ጋር የሚነጋገሩበት ከመሆኑ ባሻገር፣ ማንኛውም ሴት የሚደንሰው ስልት መሆኑ ያስደስታል ትላለች፡፡ ዳንሱን በአወንታዊ ጎኑ የማንነት መገለጫ አድርገው የሚወስዱ እንዳሉ ሁሉ የሚቃወሙትም አሉ፡፡ ዳንሱ እንደ መንፈሳዊ ክንዋኔ ተመስጦ የሚጠይቅ መሆኑ የሚያስደስታቸው አካሎች ከዳንስ ጥበብነት ወጥቶ በአሉታዊ መንገድ የታየው ከዐውዱ ውጭ ጥቅም ላይ የሚያውሉት በመኖራቸው እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ጥንታዊውን ቤሊ ዳንስ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ቢደመጡም ኤልዛቤል እንደምትለው፣ ጥልቅ ስሜት የሚገለጽበት ዳንስ መሆኑ ጎልቶ ከታየ የተዛቡ አመለካከቶች ይስተካከላሉ፡፡ ጋዜጠኛዋ ኢትዮጵያ የመጣችው አገሪቱን ለመጎብኘትና የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜንም ለመማር መሆኑን ትናገራለች፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜን በአጭር ጊዜ መማር ቢከብድም መሠረታዊ ዕውቀት ጨብጫለሁ ትላለች፡፡ ዳንስ የተለያየ ባህል ያላቸው ሰዎች የጋራ ቋንቋ ፈጥረው የሚግባቡበት መንገድ እንደሆነ የምታምን ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ በተጨማሪ ሂፕ ሃፕና ቦሊውድ ተምራለች፡፡ የተለያዩ የዳንስ ስልቶችን የማዋሃድ ሒደት እየተስፋፋ እንደመጣ ገልጻ፣ እሷም ቤሊ ዳንስን ከኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜና ሌሎችም ስልቶች ጋር እየቀላቀለች የመሥራት ፍላጎቷን ገልጻለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...