Thursday, March 20, 2025
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዱባና ቅልን ማን አንድ አደረጋቸው?

ሰላም! ሰላም! ሲናገሩት ተረት በሚመስል መራር እውነታ ተከበን፣ ስቃይን አፍነን በምን ተደረገና ተሰማ ሀተታ መቀባበል መቼም ሥራችን ሆኗል። ዕድሜ ለ‘ቴክኖሎጂ’ እንዳትሉ ብቻ! ባሻዬ ‹‹እኔ እኮ የማይገባኝ የሞት፣ የሁከትና የጦርነት መረጃ በደቂቃ ዕድሜ ማከፋፈል ነው አሁን ‘ቴክኖሎጂን’ ዕድሜ የሚያስመኝለት? የመሠረታዊ ፍላጎቶች ዕጦትና ጉስቁልና እየተጫወተብን ለራሳችን ዕድሜ መመኘት ትተን ‘ለኢንፎርሜሽን’ እንመኝ? እውነት የምንመኘውንማ አናውቅም። ጉድ እኮ ነው!›› ሲሉኝ ነበር። ታዲያ አንድ ትልቅ ሰው መቼ ዕለት ደወሉልኝና ገና ላስቲኩ ያልተላጠ ሰላሳ አራት ‘ኢንቺ፣ ኤልሲዲ’ ቴሌቪዥናቸውን ‹‹ወዲያ ሽጥልኝ!›› አሉኝ። እኔ ደግሞ አንዱን ሳናጣጥም በላይ በላዩ የሚጎርፍብንን የ‘ቴክኖሎጂ’ ትሩፋት እያሰብኩ ‘ከዚህ የተለየ ደግሞ ምን ዓይነት አስማተኛ ቴሌቪዥን ገዝተው ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። ስጠይቃቸው፣ ‹‹እኔማ ቴሌቪዥን የገዛሁ መስሎኝ ነበር። ደም መግዛቴን፣ ሽብር ቤቴ ማስገባቴን ካደረ አወቅኩ እንጂ፤›› አሉኝ። ‹‹አንበርብር መደንገጥ አማረኝ። ይኼ ቴሌቪዥንና ዲሽ ቤቴ ከመግባቱ በፊት የሞት ዜና እንዴት ያስደነግጠኝ እንደነበር ላስረዳህ አልችልም። እንኳን የሰው ለዓመት በዓል የማፈሰው የበግ ደም እንዴት እንደሚነዝረኝ እኔ ብቻ ነበር የማውቀው። ይኼው አሁን ግን ሞት አያስደነግጠኝ፣ ደም አያስበረግገኝ፣ መከስከስ አይኮሰኩሰኝ። ኧረ ወዲያ ውሰድልኝ…›› አሉኝ ፈርጠም ብለው። የገባውና ያወቀበት በጎ ፍርኃትና ድንጋጤን የሰውነቱ መጠለያው ሊያደርጋቸው ሲቆርጥ ሳይ፣ መላመድ የሠራለት ይኼን ሰምቶ የብልጥ ሰው ሳቅ ሊስቅ እንጥሉን ሲቧጥጥ አሰብኩ። የዚህ ዓለም ነገር ደንቆኝ ‘ለካ በቁም ሞትም ይለመዳል’ ብዬ ተከዝኩ። ያልባሰበት ሽብር የለማ! እናላችሁ ይኼን አነጋጋሪ የ‘አልሰማም አላይም’ አሻፈረኝ ባይነት ለአንድ ደላላ ወዳጄ ነገርኩት። መንገሬም ከእኔ ይልቅ እሱ እንዲህ ዓይነት ዕቃዎችን ፈጥኖ የማሻሻጥ ዕድል ስላለው ነበር። በከፊል እያዳመጠኝ ስልኩን ይነካካል። ደግሞ ሳምንቱ ታላቁን የፋሲካ በዓል ይዞ ከተፍ ይላልና ተቀምጦ አይሆንም። እንዳማረበት እያሽካካ መኖር ለአውራ ዶሮ ወይም ለይሁዳም አልጠቀመም። አንዷ ቆንጆ ሳያስበው ‹‹በፍቅር ያልሞተ ይሁዳ ብቻ ነው›› ብሎ የጻፈውን ‘ላይክ’ አድርጋለት ተወዳጅነቱን ሊጨምር ተጨማሪ አባባል ፍለጋ የደላላ አዕምሮውን እንደ ባለቅኔ ያስጨንቃል። አናዶኝ፣ ‹‹ደላላነቴን ትቼ ‘ብሎገር’ ሆኛለሁ በለንና እንረፈው። ሥራ እኮ ነው የምሰጥህ፤›› ስለው፣ ‹‹ብራቮ አንበርብር፤›› ብሎ፣ ‹‹ኮሚሽን የማይመጥነው ሥራ ፍቅር ብቻ ነው፤›› ሲል እያየሁት ጻፈ። መስመር ላይ የነበረችው ከፊል እርቃኗን የሚያሳይ ፎቶ የለጠፈችው ልጅ ‘ላይክ’ በማድረግ ፈንታ ‘ሎግ አውት’ አደረገች። ፊቱ አመድ መስሎ ‹‹ምን አደረግኳት?›› አለኝ። እኔም አጠገቡ ቆሜ እንደሌለሁ ቆጥሮኝ ስለነበር ብድሬን ልመልስ፣ ‹‹‘ኮሚሽን’ ብለህ ደላላነትህን አስፎግረህ ነዋ፤›› ብዬ በቆመበት ጥየው ሄድኩ። ቢወደድ ቢወደድ በጥሬው የሚቆጥር ደላላ እንጂ ላይክ የሚቆጥር ሊወደድ ያስባል እንዴ? ቀልደኛ! ብዙ ሥራዎች ስለነበሩብኝ ቴሌቪዥኑን ቶሎ ብዬ ማሻሻጥ ነበረብኝ። ስልኬን ጥቂት ነካካሁና ስደውል ሞባይሌ ባዶ ኪስ እንደሆነች በትህትና ተነገረኝ። ድህነትዎ በትህትና ሲነገርዎ ግን እንዴት ደስ ይላል? ደስ አይልም? ወዲያው የ50 ብር ካርድ ገዝቼ ሞላሁ። ‹‹ለምን እንደሆነ አላውቅም ካርድ ስሞላ ደስ እንደሚለኝ ሆዴን ስሞላ ደስ ብሎኝ አያውቅም፤›› የሚል ወዳጅ አለኝ። ሲተርቡት፣ ‹‹ሆድህ መቼም ሞልቶ ስለማያውቅ ይሆናል፤›› ይሉታል። የትረባ ተርቦች ፊት ከመናገራችሁ በፊት እስኪ ሁለቴ ሦስቴ እያሰባችሁ። ለጥላቻ ቅርብ ስለሆነ እንደሆነ እንጃ ጥሎብን ‘መንግሥት፣ መንግሥት’ እንላለን እንጂ እኮ የመናገርና የመጻፍ መብታችንን መጫኑ በእነሱ ይብሳል። ምን እያልኩ ነበር? አዎ — ካርድ ሞላሁና ወዲያው ያወጣሁትን ቁጥር ደወልኩ። የደወልኩለት ወዳጄ ሌላ ቁጥር ሰጠኝ። ስደውል፣ ‹‹ይቅርታ ሒሳብዎ አልቋል፤›› አለችኝ። ድምጿ የእምዬን ባይመስል? . . . ማርያምን ቴሌ አልቆለት ነበር። ምናለበት ደግሞ በይቅርታው ምትክ፣ ‹‹ጥሩ ተዘራፊ ሆነው በመገኘትዎ ዕድሜዎን ያርዝምልዎ እናመሰግናለን፤››፣ ወዘተ ብባል መጮህ አማረኝ። ዙሪያ ገባዬን ለእንድ አፍታ ሳጤን ቆይቼ . . . ከአንዱ ሱቅ በደረቴ ሌላ ካርድ ገዛሁ። ጠላቴ ሰፍ ብሎ ይቅርና! መቼስ የውሾን ነገር ያነሳ ሆኖ የቴሌን ነገር ብዙ ጊዜ እያነሳሁ ባላየ ሳልፍ ሳትታዘቡኝ አልቀራችሁም። ሆድ ይፍጀው ሆኖብኝ እኮ ነው። ምነው ግን እንዲህ ነውር የሚያውቅ ጠፋ። መልካም ነገርስ አስሶ አለማወቅ፣ አጥንቶ አለመግለጥ አልፈጠረብንም ይባል። ደርሰን ለክፋትና ለነቀፋ አንደኛ ነን። ምነው ታዲያ ይኼ ታለንታችን ቴሌ ላይ ከሸፈ? እውነቴን እኮ ነው። ለመሆኑ በጽሑፍ የሚደርሱንን መልዕክቶች ልብ ብላችሁ አንብባችኋችኋል? ከሞራል የሞራል መሠረት፣ ከቋንቋ ከሰዋሰው የተጣሉ። አንዴ ‹‹መተቸት ሰለቸን!›› ብሎ መጽሐፍ ጻፈ ብዬ ያጫወትኳችሁ ወዳጄ ትዝ ይላችኋል? ስለመጽሐፉ እያጫወተኝ እኔ የቴሌን ነገር አነሳሁለት። ትችት ነውና ለዚህ ለዚህማ እንተባበራለን አልኩና የድርሻዬን ጣል አደረግኩለታ። ምን አትሉም? የቴሌን ቴክስቶች። ከሰለቸን ነገር በላይ መተቸት ባይሰለቸን ኖሮማ ሳወራ፣ ስተች ዓመት ባልበቃኝ ነበር። እስኪ ልብ በሉት። እርስ በርሳችን እንደ በርበሬ በየጥጋጥጉ፣ በረባ ባረባው ስንሸካሸክ እኮ ነው የምንውለው። (አማርኛዬን አጣሞ መረዳት ፍፁም የተከለከለ ነው! ምነው? መከልከል ብርቅ ነው እንዴ? ሃሃሃ) ብቻ ‘መተቸት ለምን ሰለቸን?’ ብላችሁ ጠይቁኝ። መልሱ የማይተች ነገር ስለጠፋ! ምነው መብራትና ውኃ ብቻ መሰላችሁ እየጠፋብን ያስቸገረን? እኛ ደግሞ ሲፈጥረን መርቆን ይሁን ረግሞን (ኧረ ያጣሪ ኮሚቴ ያለህ? ምነው ለዚህ ለዚህ ጊዜ ኮሚቴ ማቋቋም አቃተን ጎበዝ?) ዕውቀታችን ትንሽ ናት። ስለዚህ እኔና እናንተ መሀል ውሸት አይገባም፡፡ ይኼው ያገኘነውን ሁሉ እየተቸን አለን። ‹‹ምናልባት መረጃ በአግባቡ ስለማይዳረስልንም ይሆናል፤›› አለኝ የባሻዬን ልጅ እንናንተን እንደማጫውታችሁ ሳጫውተው። ‹‹ዘመኑ የመረጃ ነው እየተባለ እንዴት ያለ ነገር ነው?›› ስለው፣ ‹‹የለም! እሱ ለእንደኛ ዓይነቶቹ የሚነገርና የማይነገር ለሚመረጥላቸው አይሠራም!›› ብሎ ዘጋብኝ። እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል ሲባል ሰምቼ እኔም ጥዬው ሄድኩ። ከራሳችን አልወርድ ያለ ስንት ነገር እያለ እንዲያው በየትም በኩል አድርገን ከመንግሥት ራስ ላለመውረድ ትግላችን መቼም አይጣል ነው። አውቀንበት ቶሎ ልብ ብንገዛ እንዴት ጥሩ ነበር? ከማይገዛ ገንዘብ ጋር አባሮሽ ከመጫወት አንዳንዴ የኢኮኖሚ ውጣ ውረድ የማያዋዥቀው ማስተዋል አያዋጣም ትላላችሁ? እንክት አድርጎ! በሉ እንሰነባበት። እንዳያልቅ የለም ሁዳዴም ይኼው ተሸኘ። የፆመም ያልፆመም ገበያውን ያደበላልቀዋል ይኼው። ውዷ ማንጠግቦሽ ደግሞ፣ ‹‹የዘንድሮ ፋሲካዬ ሸመታ ሞል ውስጥ መሆን አለበት፤›› ብላ ታንከራትተኛለች። እሷን አሉ የተባሉ የከተማችን ሕንፃዎችን ሳስጎበኛት ሰነበትኩ። በዚያውም ከሠፈር እሮሮና እይታ ወጣ ብላ የሰውን ሳይሆን የከተማውን ለውጥ ታያለች ብዬ ነበር። አንከራታኝ ስታበቃ፣ ‹‹አንበርብር ለምን ግን አንድ ሞል አንሠራም?›› አትለኝ መሰላችሁ በድንገት። ‹‹ደፋር!›› ብዬ ጓዳዬ እንደለመድኩት ሕዝብ ፊት ስጮህ ለራሴ ደነገጥኩ። አንዳንዱ ‘ሙሰኛ የሚያስደነግጥ ጩኸት አትጩህና እህቶቻችን ላይ ደንፋ’ በሚል አስተያየት አፈር ድሜ ያስግጠኛል። እንዳወጣጥዋ ቤቷ አስገብቼ ወደምሄድበት ስሄድ ይኼን ጉድ ባሻዬ ይስሙት ብዬ ቤታቸው ጎራ አልኩ። ባሻዬ ማንጠግቦሽ ያማራትን ሲሰሙ ከት ብለው ስቀው፣ ‹‹አንተም እንደ ፀረ ዴሞክራቶች ምኞት ልትከለክል አማረህ?›› አሉኝ። በደካማ ጎናቸው ልግባ ብዬ፣ ‹‹ባሻዬ መጽሐፉስ የሚለው ‘አትመኝ’ መስሎኝ፤›› ስላቸው፣ ‹‹እንደ ተጻፈው ቢሆን ኖሮማ በምድራዊውም በሰማዩም ሕግና ሕገ መንግሥት እንነታረክ ነበር?›› ብለው አመለጡኝ። ባሻዬ አጉል ‘ሙድ’ እንደያዙብኝ ገብቶኝ ለልጃቸው ብነግረው የእሱ ባሰ። ምን ይለኛል፣ ‹‹ኳስ ተጫዋች ሆነህ ጠረቡኝ እያልክ ካኮረፍክ መጀመሪያም አርፈህ ገበጣ መጫወት ነበረብህ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ስለዚህ በእሱ አባባል ዕድልና ‘ቻፓ’ የሌለን ሰዎች በምኞት ጠረባ ስናልቅ ዝም ነው ማለት ነው ያለብን ማለት ነው? እ? እስኪ ንገሩኝ በፈጠራችሁ። መቼ ወደን ሆነ ሕንፃ ሠርተን የከተማ ውበት ልንጨምር (ሰው መቼም ካልበላና ነገር የማታውቅ ሌሊት ካላሰለፈ አያምርበትም) ቀርቶ የጓሮ አትክልት ማልማት ያቃተን? እኔ ልሙት! ታዲያ ነገሩን ምንም ሳላንዛዛ በአጭሩ ቀጨሁና የሆዴን በሆዴ ይዤ ሳብላላ ሰነበትኩ። የማንጠግቦሽ ልበ ተራራ መሆን ምንጩ ምን ይሆን እያልኩ በልቶ እንዳልበላ ሆንኩ። ‹‹ምግብማ ሞልቷል አምላክ መች ነሳኝ፣ የምኞት ጣጣ ነው እኔን ያከሳኝ፤›› እያልኩ መሆኑ ነው። ግን ከሁሉ የገረመኝ የመንፈስና የሥጋው ምኞት እንዲህ ድብልቅልቅ ማለቱ ነው። አሁን እስኪ በዚህ ድህነት ሰው ሞል መሥራት ይመኛል? ታዲያ በዚህ ዓይነት የግልና የሕዝብ ጥቅም እሳቤ ቢደባለቅ፣ ጠላትና ወዳጅ ቢደበላለቅ፣ አልሚና አጥፊ ቢተራመስ፣ ወሬና ተግባር አልገናኝ ቢል ምን ይገርማል? ድሮስ ዱባና ቅልን ማን አንድ አደረጋቸው ብለን ብንለያይስ? መልካም ሰንበት! መልካም ዓውደ ዓመት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት

error: