Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም በውናንያ-ኰሶዬ

ማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም በውናንያ-ኰሶዬ

ቀን:

የዓለም ቱሪዝም ቀን ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 27) የተከበረው ‹‹ዘላቂነት ያለው ቱሪዝም የዕድገት መሣሪያ›› (ሰስቴነብል ቱሪዝም ኤ ቱል ፎር ዴቨሎፕመንት) በሚል መሪ ቃል ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀኑን ምክንያት በማድረግ ይፋ ያደረገው መግለጫ፣ የያዝነው ዓመት ዘላቂነት ያለው ቱሪዝም ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራበት መሆኑን ያመለክታል፡፡

‹‹ዘላቂነት ያለው ቱሪዝም ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ተፈጥሯዊ ዕድገት መሠረት ነው፤›› በማለት ነበር ድርጅቱ የቱሪዝም ቀን መሪ ቃልን ያብራራው፡፡ ዘላቂነት ያለው ቱሪዝም የማኅበረሰቡን ሕይወት የተሻለ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚጫወተው ሚናም ቀላል አይደለም፡፡ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅና በዓለም ሰላም እንዲሰፍን ለማስቻልም እንደሚያግዝ ተጠቁሟል፡፡

የዓለም ቱሪዝም ቀን ሲከበር ከግለሰቦች አንስቶ መንግሥታዊ የሆኑና ያልሆኑም ተቋሞች ዘላቂነት ያለው ቱሪዝምን ዕውን ለማድረግ ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የተባበሩት መንግሥታት አሳስቧል፡፡ ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ የለውጥ መሣሪያ እንዲሆን የሁሉም አካላት ተሳትፎ ያሻልም ተብሏል፡፡

- Advertisement -

የቱሪዝም ቀን በተከበረባቸው አገሮች የተላለፉ መልዕክቶች የአንድ ማኅበረሰብ አባላት በአካባቢያቸው ባለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ መሳተፍ እንዳለባቸው የሚያስገነዝቡ ነበሩ፡፡ የኅብረተሰቡን ተሳታፊነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በቱሪዝም ዙሪያ የሚሠሩ ተቋሞች የየድርሻቸውን ሲወጡ ዘላቂ ቱሪዝም መፍጠር እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡

የአንድ ማኅበረሰብ አባላት ሊሳተፉባቸው ከሚችሉ የቱሪዝም ዘርፎች መካከል ተፈጥሯዊ አካባቢዎችን ያማከለ ቱሪዝምን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ማኅበረሰቡ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በምን መንገድ መጠበቅ አለበት? ከሚለው ጥያቄ ባሻገር፣ ጥበቃ ከሚያደርግለት የተፈጥሮ ሀብት ምን ያህል ተጠቃሚ ይሆናል? የሚለውም ይነሳል፡፡ በተመሳሳይ ተፈጥሮን ካማከለ ቱሪዝም በተጨማሪ ግዙፍነት ያላቸውና የሌላቸው ቅርሶችን ያማከለ ቱሪዝምን ዘላቂ ለማድረግም የማኅበረሰቡ ተሳትፎ የግድ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ዋና ጸሐፊ ታሊብ ሪፋይ፣ ቱሪዝም የዘላቂ ዕድገት መሠረት እንዲሆን አስፈላጊ ናቸው ካሏቸው አምስት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል፣ ማኅበረሰብን ማሳተፍ ይገኝበታል፡፡ ተፈጥሯዊ ሀብትን እንዲሁም ግዙፍነት ያላቸውና የሌላቸውም ባህላዊ ቅርሶችን መጠበቅ ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል ሲሆኑ፣ ለቅርሶች ጥበቃ ከማድረግ በተጨማሪ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎችን ማሳተፍም በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል ይላሉ፡፡

ቱሪዝም በዓለም ኢኮኖሚ ገቢ በማመንጨት ሦስተኛውን ደረጃ የያዘ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 1.2 ቢሊዮን ቱሪስቶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2030 የቱሪስቶች ቁጥር ከ1.2 ቢሊዮን ወደ 1.8 ቢሊዮን ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዋና ጸሐፊው፣ ‹‹ለጉብኝት በምትጓዙበት ቦታ ሁሉ ተፈጥሮን አክብሩ፣ ባህልን አክብሩ፣ ጋባዦቻችሁን አክብሩ፤›› ብለው ቱሪዝም ከጎብኝዎች ጎን ለጎን ማኅበረሰብን አሳታፊ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በቱሪዝም ማኅበረሰብን በማሳተፍ ረገድ በአገራችን በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአካባቢያቸው የቱሪዝም ሀብት ጥብቃ ተሳትፈው ከቱሪዝም በሚገኘው ገቢም የሚጠቀሙ ማኅበረሰቦች ብዙ ባይሆኑም ጅማሮዎች አሉ፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ከቱሪዝም ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም ተገንዝቦ፣ ቱሪስት ሳቢ ሀብቶችን ጠብቆ፣ ከቱሪዝም ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ማስቻል የቱሪዝም ዘላቂነት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ጎንደር በቱሪዝም እንቅስቃሴ ጉልህ ድርሻ ካላቸው ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አስበው ስለ አገሪቱ ሰዎችን ሲጠይቁ፣ ድረ ገጽ ሲመለከቱ ወይም መጻሕፍት ሲያገላብጡ ከተማዋ በአገሪቱ ታሪክ ያላትን ቦታ ይገነዘባሉ፡፡ በታሪካዊ ቅርሶች፣ ባህላዊ እሴቶችና ተፈጥሯዊ ሀብቶችም የታደለች ከተማ ናት፡፡ ሆኖም እንደሌሎቹ የአገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ማኅበረሰቡን በቱሪዝም በማሳተፍ ረገድ ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡

አንድ ማኅበረሰብ ከቱሪዝም ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም ካልተረዳ ተፈጥሯዊም ይሁን ሰው ሠራሽ ሀብቶችን የመጠበቅ ተነሳሽነት አይኖረውም፡፡ ለነዚህ ሀብቶች ጥበቃ ቢያደርግም ተገቢውን ጥቅም ሳያገኝ የሚቀርባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ የማኅበረሰብ ተሳትፎን ከተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህብ ጥበቃ አንፃር የሚመለከቱት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ትምህርት ክፍል የኢኮቱሪዝምና ዋይልድ ላይፍ ማኔጅመንት መምህር እንዳልካቸው ተሾመ (ዶ/ር/) ናቸው፡፡

‹‹ኮምዩኒቲ ቤዝድ ኢኮቱሪዝም አስ ኤ ቱል ፎር ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን ኢን ውናንያ-ኰሶዮ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ የጥናት ጽሑፍ አዘጋጅተዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትና የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የውይይት መድረክም ጥናቱን ለውይይት አቅርበዋል፡፡

የውናንያ-ኰሶዬ ጥብቅ ቦታን እንደ ማሳያ በመውሰድ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ቱሪዝም ለተፈጥሯዊ ሀብት ጥብቃ ያለውን አበርክቶ በጥናታቸው ዳሰዋል፡፡ ጥብቅ ቦታው ከጎንደር ከተማ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት የሚገኝ ነው፡፡ ቦታው እንደ ፓርክ ተከልሎ ጥበቃ ይደረግለት የጀመረው በቅርቡ ቢሆንም፣ ጎብኚዎች ቦታውን ለማየት ወደ ሥፍራው ማቅናታቸው አልቀረም፡፡

ከጎንደር ከተማ ዋናው የአስፋልት መንገድ የሚገነጠለውን ኮረኮንች ይዘን ወደ 20 ደቂቃ ከተጓዝን በኋላ ነበር ጥብቅ ቦታውን ያገኘነው፡፡ በመንገዳችን ያስተዋልናቸው አንድና ሁለት ዛፎች ፓርኩ ውስጥ በብዛት ይታያሉ፡፡ ፓርኩ ተራራማ ሲሆን፣ ከአንዱ ኮረብታ ወደ ሌላው በሩቁ ከመመልከት ባለፈ ውስጥ ለውስጥ ለመጓጓዝ ያስቸግራል፡፡

በውናንያ-ኰሶዬ ውስጥ ባሉ ተራሮች መካከል ያለው ሸለቆ በተለይ በክረምት  በውኃ ይሞላል፡፡ ከመስከረም በኋላ የወራጅ ውኃው መጠን ቀንሶ ተራሮቹ በአደይ አበባ ይሞላሉ፡፡ ፓርኩን ለመጎብኘት በሄድንበት ወቅት መግቢያ ክፍያ ከተቀበለን ሰው ጀምሮ ፓርኩን ያስጎበኙንም የዚያው አካባቢ ተወላጆች ናቸው፡፡ ጥብቅ ቦታውን የሚጎበኙ ሰዎች ለሌሎች ቱሪስቶች ስለአካባቢው እየነገሩ የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸውልናል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች ስለ አካባቢው የሚሠሯቸው ጥናቶችም ለቦታው ዕውቅና የድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡ ወደ ፓርኩ የሚሄዱ ሰዎች ተፈጥሮ የሚማርካቸው በመሆናቸው በአካባቢው ለጥቂት ቀናት ቆይተው ማጣጣም ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ እንዲረዳ በሚልም ጥቂት ማረፊያ ክፍሎች በፓርኩ ውስጥ ተገንብተዋል፡፡ ክፍሎቹ በተለይም ፀሐይ ስትወጣና ስትጠልቅ ለመመልከት ምቹ ቦታ ላይ ስለተሠሩ ጎብኝዎችን ያስድስታሉ፡፡

ጥብቅ ቦታውን ከማኅበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም አንፃር የቃኙት መምህሩ፣ ቱሪዝም ተፈጥሯዊ ሀብትን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይናገራሉ፡፡ ማኅበረሰቡን በቱሪዝም ማሳተፍ ተፈጥሯዊ ሀብትን ከመንከባከብ ጎን ለጎን ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገርም ያግዛል ይላሉ፡፡

በአሁን ወቅት የውናንያ-ኰሶዬ አካባቢ ተራራማ መሆኑ ለግብርና አስቸጋሪ ሆኗል፡፡   በሚታረስባቸው ቦታዎች እንደ አፈር መሸርሸር ያሉ ችግሮች ስለተጋረጡ ማኅበረሰቡ ተቸግሯል፡፡ ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ ደን መጨፍጨፉ በአካባቢው የአየር ንብረት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ‹‹የአካባቢው ተፈጥሯዊ ይዘት እያሽቆለቆለ በመምጣቱ የግብርና ምርት እየቀነሰ ነው፡፡ ስለዚህ በአካባቢው ከዚህ በኋላ ግብርናን ብቻ የኑሮ መሠረት ማድረግ አይቻልም፤›› ይላሉ፡፡ መምህሩ እንደሚያስረዱት፣ ኅብረተሰቡን በቱሪዝም ማሳተፍ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር የማኅበረሰቡ አባላት የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡

የአካባቢው ማኅበረሰብ ለዘመናት ይተዳደርበት በነበረው ግብርና ብቻ ኑሮን መግፋት አዳጋች መሆኑ አማራጭ የገቢ ምንጭ እንዲፈልጉ ግድ ይላል፡፡ ከባህር ጠለል በላይ ከ1,500 ሜትር እስከ 3,200 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው ውናንያ-ኮሶዬ ጥብቅ ቦታ የቱሪስትር መዳረሻ ማድረግም እንደ ጥሩ አማራጭ ተቀምጧል፡፡

የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎችንም የመሳብ ጉልበት አለው፡፡ በእርግጥ አካባቢውን በተመለከትንበት ወቅት አስጎብኚዎቻችን ቦታው በስፋት ባለመተዋወቁ እንደሌሎች የተፈጥሮ መስህቦች በብዛት እንደማይጎበኝ ገልጸውልናል፡፡ እንዳልካቸው (ዶ/ር) አካባቢው ለማኅበረሰቡ ሊሰጥ የሚችልውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ተፈጥሯዊ ሀብቱ ስለሚጠበቅበት መንገድ የሠሩት ጥናት በፓርኩ ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎችን ያሳተፈ ነበር፡፡

ፓርኩን በጎበኘንበት ወቅት መንገድ ላይና በዙሪያውም የሚኖሩ ሰዎች አስተውለናል፡፡ ከነዚህ ምን ያህል ከቱሪዝም የሚገኘውን ጥቅም ይጋራሉ? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ምን ያህሉ የማኅበረሰቡ አባላት በተፈጥሯዊ ሀብቱ ጥበቃ ይሳተፋሉ የሚለው ጥያቄም ተያይዞ ይነሳል፡፡

አጥኚው እንደሚገልጹት፣ ማኅበረሰቡ ተፈጥሯዊ ሀብቱን በመንከባከብ ከቱሪዝሙ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ በመጠኑ ቢረዱም በቂ የሚባል ግንዛቤ የላቸውም፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም እንዲስፋፋ ፕሮጀክቶች ቢጀመሩም፣ ተጠቃሚ የሆኑት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ የደን ጭፍጨፋና ያልተገባ የከብት ግጦሽ መስፋፋታቸውም አልቀረም፡፡ ከግብርና ውጪ እንደ ቱሪዝም ያለ የገቢ ማግኛን እንደ አማራጭ ለመጠቀም ከባድ የሚሆነውም ለአካባቢው በቂ ጥበቃ ባለመደረጉ ነው፡፡

ውናንያ-ኮሶዬን በጎበኘንበት ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎችን ለማሳተፍ የተደረጉ ሙከራዎችን አስጎብኚዎቻችን ቢያስረዱንም፣ በሥፍራው ካለው ሕዝብ ቁጥር አንፃር በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በጥብቅ ቦታው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት የተመለከተ ሰው ማኅበረሰቡ ከቱሪዝም ምን ያህል መጠቀም እንደሚችልም ይገነዘባል፡፡

መምህሩ እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት፣ ተፈጥሯዊ ሀብቱ በአግባቡ የሚጠበቅባቸው ሕግጋትን መተግበር ነው፡፡ የከብቶች ግጦሽና ሌሎችም ለተፈጥሯዊ ሀብቱ አደጋ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መግታት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ተፈጥሯዊ ሀብቱ ተጠብቆ ሲቆይ ወደ አካባቢው ከሚሄዱ የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኝዎች የላቀ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚገኝም ያክላሉ፡፡

‹‹ማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም አማራጭ የገቢ ምንጭ ለማግኘት ተመራጭ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ሀብቱን በመጠበቅ ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ይቻላል፤›› ሲሉም በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡ ለዚህም በቱሪዝም ዘርፍ የሚሳተፈውን ማኅበረሰብ ቁጥር መጨመርና ግንዛቤያቸውን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡

መምህሩ፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝምን ለማሳደግ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳስባሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ተፈጥሯዊ ሀብትና የዱር እንስሳትን በዘለቄታዊ መንገድ መጠበቅና የተጨፈጨፈውን ደን ለመተካት  አገር በቀል ዛፎች መትከልን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የውናንያ-ኮሶዬን ጥብቅ ቦታ ቱሪዝም ዘላቂ ለማድረግ ከማኅበረሰቡ ጎን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ  የቱሪዝም ተቋሞች ያላቸው ሚናም ተመልክቷል፡፡

የጎብኚን ልብ በቀላሉ የሚገዛውና መንፈስ የሚያድሰውን ፓርክ በጎበኘንበት ወቅት ተመሳሳይ ስሜት አድሮብናል፡፡ ጋራው፣ ሸንተረሩ፣ ጅረቱና ዕፅዋቱ ጎብኚዎችን ከማስደስት በዘለለ ማኅበረሰቡን መጥቀም አለባቸው፡፡ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እስከሆነ ድረስ የተፈጥሮውን ደኅንነት ከመጠበቅ ወደ ኋላ አይልም፡፡

ዶሃ፣ ኳታር ላይ የተከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን፣ ዘላቂነት ያለው ቱሪዝም ቀዳሚ ትኩረቱ ያደረገው ለማኅበረሰቡ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንፃር ነው፡፡ የኳታር ቱሪዝም ባለሥልጣን ተጠባባቂ ኃላፊ ሀሰን አል ኢብራሒም፣ የአገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከዓመት ወደ ዓመት እየጎለበተ መምጣቱን መነሻ አድርገው፣ ዘላቂነት ያለው ቱሪዝም ለማኅበረሰብና በአጠቃላይ ለአገር ዕድገት የጀርባ አጥንት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ከኳታር በተጨማሪ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ መልክዕት ተስተጋብቶ ቀኑ ተከብሯል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...