Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ለሴቶች መኪና መንዳት ፈቀደ

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ለሴቶች መኪና መንዳት ፈቀደ

ቀን:

  • የባል ወይም የአባት ፈቃድ ማግኘት አለባቸው

ለሴቶች መኪና መንዳትን በመከልከል የዓለም ብቸኛ በሆነችው ሳዑዲ ዓረቢያ፣  ሴቶች ከመጪው ሰኔ ጀምሮ መኪና እንዲነዱ መንግሥት ፈቀደ፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ሴቶች መኪና እንዲነዱ ቢፈቀድላቸውም ሌሎች ተጨማሪ ገደቦች አሉባቸው፡፡ የሳዑዲ ሴቶች የፓስፖርት ጥያቄ ማቅረብ፣ ከአገር ውጭ መጓዝ፣ በፍቃዳቸው ማግባትም ሆነ መፍታት፣ የባንክ ደብተር መክፈት፣ ንግድ መጀመር፣ ለውበት የሚሆኑ ቀዶ ሕክምናዎችን ማድረግ አይፈቀድላቸውም፡፡

ከእስልምና አስተምርሆ ጋር በተያያዘ ነው ተብለው በሳዑዲ ዓረቢያ ሴቶች ላይ የተጣሉ ገደቦች በአብዛኞቹ የእስልምና እምነት ተከታይ አገሮች የማይተገበሩ ሲሆን፣ የ2016ቱ ‹‹የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ግሎባል ጀንደር ጋፕ ኢንዴክስም››፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ አገሮች በጦርነት ውስጥ ከሚዋዥቁት የመንና ሶሪያ ቀጥሎ ከፍተኛው እኩልነት የሌለበት አገር ሲል አስፍሯል፡፡

- Advertisement -

ሂዩማን ራይትስ ዎችም የሳዑዲ ዓረቢያን ሴቶች ‹‹በሕጋዊ መንገድ ውሳኔ እንዳይሰጡ የተገደቡ›› ሲል ይገልጻቸዋል፡፡

የሳዑዲ ሴቶች መኪና መንዳት እንደሚችሉ የመፈቀዱን ዜና ሲሰሙ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶችም መኪና ውስጥ ሆነው ደስታቸውን ሲገልጹ በዓለም አቀፍ ቴሌቪዥኖች መስኮቶች ታይተዋል፡፡ ሆኖም ይህ ደስታ በአንዳንዶች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ሴቶች መኪና መንዳት የለባቸውም፣ ከሸሪሃ ሕግ ይጣረሳል ያሉም አሉ፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ለሴቶች መኪና መንዳትን ቢፈቅድም፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳዑዲ ዓረቢያ ቋሚ ተወካይ ጉዳዩን ቢያረጋግጡም፣ የሳዑዲ ሴቶቸ መኪና ለመንዳት የባሎቻቸው ወይም የአባት ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንዳንድ ባሎችና አባቶችም ሴት ልጆች መኪና መንዳት እንደሌለባቸው የማሳመን ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ሮይተረስ በድረገጹም ‹‹እባካችሁ አታሽከርክሩ›› የሚል ወረቀት የያዘ የሴት እጅ ፎቶ አስፍሯል፡፡

በሳዑዲ የሴት መብት ተሟጋቾች ጥረት ለሴቶቸ መኪና ማሽከርከር ቢፈቀድም፣ ለማሽከርከር ከዚህ በኋላ ዘጠኝ ወራት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

በአገሪቱ በሴቶች ላይ ይህና ሌሎች ገደቦች  የተጣሉት ‹‹የማኅበረሰቡ ፍላጎት ነው›› በሚል ቢሆንም፣ በተለይ የሳዑዲ መንግሥት ለሁሉም ሴቶች የመማር ግዴታን ካስቀመጠ ወዲህ አመለካከቶች እየተቀየሩ፣ ሴቶችም መብታቸውን እየጠየቁ መምጣታቸውን ዘገባው ያሳያል፡፡

በአገሪቱ 16 በመቶ ያህሉ ሠራተኞች ሴቶች ሲሆኑ፣ ለዚህም መንግሥት ሴት ልጅ ከ15 ዓመት ወዲህ ትምህርት እንድታቋርጥ አለመፍቀዱና ከወንዶች ይልቅ በርካታ ሴቶች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው መውጣታቸው አስተዋጽኦ አድረጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሴቶች በስኮላርሺፕ ውጭ ሄደው የሚማሩበት መንገድ መከፈቱም ሴቶች መብታቸውን እንዲጠይቁ ረድቷል፡፡

ሴቶች ለእያንዳንዷ እንቅስቃሴያቸው መኪና ለመንዳትም ሆነ ፓሰፖርት ለማውጣት፣ ለማግባትም ሆነ የባንክ ደብተር ለመክፈትና ሌሎችንም ድርጊቶች ለማከናወን የአባት ወይም የባል ፈቃድ የሚጠይቁበት ሥርዓት እንዲነሳላቸው፣ በመስከረም 2016፤ 14 ሺሕ ያህል የሳዑዲ ሴቶች ፊርማ በማሰባሰብ መንግሥታቸውን መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ የከረረና የሴቶችን መብት ለማገድ ተብሎ ባይሆንም በተወሰኑ አገሮችም ሴቶች ላይ የተጣሉ የሥራ ገደቦች አሉ፡፡ ገደቡን የሚያያይዙትም ሴቶች ለአደጋ ይጋለጣሉ ከሚል ነው፡፡

በቻይና ሴቶች በማዕድን ቁፋሮ፣ በመርከብ መንዳትና በተነል (ዋሻ) ኢንጂነሪንግ መማር አይችሉም፡፡ የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴርም ይህን ያደረገው ለሴቶች ካለው ክብርና ከአደጋ ለመታደግ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በሱዳን ሴቶች ሱሪ እንዳይለብሱ የሚከለከሉ ሲሆን፣ በሩሲያ ደግሞ የእሳት አደጋ ሠራተኛ፣ አናጢ፣ የባቡር ሾፌርም ሆነ የመርከብ ካፒቴን መሆን አይችሉም፡፡ ሆኖም አደጋውን እንጋፈጣለን የሚሉና ፈተናውን የሚያልፉ ከሆነ ሥራውን መሥራት ይችላሉ፡፡ ቢቢሲ እንዳሰፈረው ግን፣ አብዛኞቹ ሴቶች ወደ እነዚህ ሥራ መገባት አይፈልጉም፡፡

በእስራኤል ጋብቻ በአብዛኛው በእምነት ሥፍራ የሚፈጸም በመሆኑ ሴት ፍቺ ብትጠይቅ የወንዱ ፈቃደኝነት ካልታከለበት አይፈቀድላትም፡፡ በኢንዶኔዢያ ደግሞ ሴቶች ወንድ ከሚነዳው ሞተር ሳይክል ኋላ ተፈናጠው መሄድ አይፈቀድላቸውም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...